Thursday, 17 June 2021 00:00

“ፖለቲከኞች የሥነ-ልቦና ህክምና ያስፈልጋቸዋል”

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(0 votes)

 ጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ በቅርቡ ለንባብ ካበቃቸው መፃህፍት አንዱ “ፍልስምና ፭”  የተሰኘው ሲሆን በስነ-ልቦና፣ በጋብቻና በአእምሮ ህክምና ላይ ያጠነጥናል፡፡ በመፅሐፉ ከተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር የተደረጉ ጥልቅና ጥብቅ ቃለ-መጠይቆች የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከስነ-ልቦና ባለሙያዋ ወ/ሮ ትዕግስት ዋልተንጉስ ጋር የተደረገው ይገኝበታል። የቃለ-መጠይቁ ርዕሰ ጉዳይ በአእምሮ ቁስለት ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ስለ አዕምሮ ቁስለት ምንነት በዝርዝር ዕውቀትና መረጃ ያስታጥቃል፡፡ የጥላቻ ትርክት የሚያቀነቅኑ ፖለቲከኞች የአዕምሮ ቁስለት እንዳለባቸውና የስነ-ልቦና ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ባለሙያዋ ታስረዳለች፡፡ ከቃለ-መጠይቁ የተወሰኑትን መርጠን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል- እንድታነቡት፡፡
ቴዎድሮስ፡- በዓለም ላይ የአዕምሮ ቁስለት እንደ ጉዳትና ህመም ከታወቀ ምን ያህል ጊዜ ይሆነዋል?
ትዕግሥት፡- ብዙ ጊዜው ነው፡፡ በተለይም በቬትናም ጦርነት ጊዜ የአእምሮ ቁስለት ትልቅ እውቅና አግኝቷል፡፡ ከጦርነት ተመላሾቹ ወታደሮች በአሜሪካ መንግስት ገንዘብ፣ ቤትና የመሳሰሉት ይሰጣቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሲታዩ ሁሉም ኖሯቸውም ከቤተሰባቸውና ከዙሪያቸው ሰዎች ጋር መግባባት አልቻሉም፡፡ እንኳን ከባዱ የጦር መሳሪያ ጎማ ሲፈነዳም መደንገጥ ይታይባቸው ነበር፡፡ ራሳቸውን የሚያጠፉ ወታደሮችም ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲያጋጥም “ለምንድነው ይህ የሚሆነው?” የሚል ጥያቄ ተነሳ፡፡ የአዕምሮ ቁስለት እንዳለባቸው ነው የተደረሰበት፡፡ ዓለም አሁን የአዕምሮ ችግሮችን ለመፍታት ፊቱን እየመለሰ ነው፡፡ ይሁንና በሌላው መልኩ ዓለም ራሳቸውን የሚያመልኩ መሪዎች እየበዙባት ስለመጡ “እኛ ምንም ችግር የለብንም፡፡ ልክ ነን፡፡ ንጹህ ነን” ባዮች በበዙባት ዓለም ላይ ስለ አዕምሮ ጤና ማውራት ከባድ ነው፡፡ መሪዎች “ችግር የለም” ብለው ያምናሉ፡፡ የሚያሳዝነው ግን መሪዎቹ ራሳቸውም የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው መሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ የአዕምሮ ጤናን አስፈላጊነትን ተቀበሉት ማለት “እኔ ችግር አለብኝ” ብለው እንደማመን ይቆጠራል ብለው ያምናሉ፡፡
አሁን ተስተካክሎ እንደሆነ አላውቅም እንጂ ከዓመት በፊት የጤና ሚኒስቴር ዌብ ሳይት ብትገባና “የአዕምሮ ጤና” ብለህ ብትፈልግ ባዶ ነው የምታገኘው። ምንም የለም፡፡ ይህ ራሱ ያስደነግጥሀል፡፡ መንግሥትን ትተህ ዋናው ጤና ሚኒስቴር  ዌብ ሳይቱ ላይ የአዕምሮ ጤና መረጃ ምንም ከሌለው እስከ 27 በመቶ የሀገሪቱ ሕዝብ ይጠቃበታል ለሚባለው የአዕምሮ ህመም ምን ትኩረት እንዳልተሰጠው ከዚህ በላይ ምንም ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም፡፡
ቴዎድሮስ፡- በሀገራችን በተለይም ከአፄ ምኒልክ ጋር ተያይዞ ሕዝቦች ላይ ቁጭት በሚፈጥር መልኩ የሚተረኩ ታሪኮች አሉ። ትርክቶቹ ተደርገውም ይሁን ተፈጥረው ከመቶ ዓመት በላይ አልፏቸዋል፡፡ ይሁንና አንቺ እንዳልሽው የትርክቶቹ መደጋገም ታሪካዊ የአዕምሮ ቁስለት ያመጡና የአዕምሮ ቁስለቱ የወለደውን ቀውስ ደግሞ እያየን ነው፡፡ ያለፈን ቁስል ማከክ ከዚህ የተሻለ ምን መልካም ነገር ሊያመጣ ይችላል? የባሰስ የአዕምሮ ቁስለትን ከማስተላለፍ ያለፈ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?
ትዕግሥት፡- የእኛ ሀገር ነገር ትንሽ ግራ ያጋባል፡፡ በብዙ ጉዳዮች ላይ ግልፅ የሆነ ነገር የለም፡፡ መረጃው ተባባሪ ነው፡፡ ስለተነገረና ስላልተነገረ ብቻ ሳይሆን የተነገረበት መንገድ በሚያሳምምና ለአመጽ በሚያነሳሳ መንገድ መሆኑ  ነው ችግሩ፡፡ ለምሳሌ አፄ ቴዎድሮስ እኮ እንግሊዞች ናቸው አይደል የገደሏቸው? ራሳቸውን ቢያጠፉም ለዚያ ያበቋቸው ግን እንግሊዞች ናቸው፡፡ ጣሊያኖችም ዜጎቻችንን ዓለም በሚያውቀው መልኩ ጨፍጭፈዋል። እኛ ግን ከእንግሊዞችም ከጣሊያኖችም ጋር ዛሬ ችግር የለብንም፡፡ እንሄዳለን፤ ይመጣሉ፡፡ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ደረጃም ግንኙነት አለን፡፡ ካየኸው ከእንግሊዝም ሆነ ከጣሊያን ጋር ያለን ቂምና ጥላቻ በአፄ ምኒልክ ላይ የሚነገረውን ያህል አይሆንም፡፡ ምንድነው ችግሩ? መረጃው የተነገረበት መንገድ እንደ ታሪክ፣ እንደ መማሪያ ሳይሆን እንደ ጠብ መጫሪያ ነው። ይህ ደግሞ historical trauma ይባላል፡፡ የተደረገና የሆነ ብቻ ሳይሆን ባይፈጸምም ተደጋግሞ የተነገረ ታሪክም በሂደት ለታሪካዊ የአዕምሮ ቁስለት ይዳርጋል፡፡ እናትና አባትህ ተለያይተው እናትህ ስለ አባትህ የምትነግርህ ጠጥቶ ይገባ እንደነበር፣ ይደበድባት እንደነበር፣ የቤት ወጪ አይሰጣት እንደነበር፣ በላይዋ ላይ ውሽማ ይይዝ እንደነበር ከሆነ… ከምትነግርህ ብቻ ተነስተህ ምንም ማጣሪያ ሳታደርግ፣ አባትህን አምርረህ ልትጠላው ትችላለህ - እንኳን አጼ ምኒልክን፡፡                   
ቴዎድሮስ፡- በቅርቡ በሀገራችን በተከሰተ ግጭት ንብረት ያወደሙና የሰው ሕይወት ያጠፉ ወጣቶች አሉ፡፡ ብዙዎቻችን በገንዘብና በሀሰተኛ ትርክት የገፏቸው ሀይሎችን እናስባለን፡፡ ልጆቹን ጨካኝ እናደርጋቸዋለን፡፡ እናንተስ እነዚህን ለጥፋት ዓላማ የዋሉ ወጣቶች እንዴት ነው የምታስቧቸው?                                 
ትዕግሥት፡- እኔ በግሌ ወጣቶቹን ተዋቸውና ገንዘብ የሚሰጡት ወይም “አድርጉ” ብለው ገፊዎቹ ራሳቸው የአዕምሮ ቁስለት ያለባቸው እንደሆኑ ነው የማስበው፡፡ የአዕምሮ ቁስለት አለብን ማለት የምንወስነው ውሳኔ በሙሉ የተዛባ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ለአዕምሮ ቁስለት ስትዳረግ በምክንያታዊው የአንጎል ክፍል አይደለም የምትወስነው፡፡ በስሜታዊው ክፍል ነው የምትወስነው፡፡ ስሜታዊው የአዕምሮ ክፍል “ተጋፈጥ፤ ተዋጋ፤ ተደባደብ፤ አቃጥል፤ አውድም፤ አዋርድ” ነው የሚልህ። ይህን ትዕዛዝ የሚሰጠው ሰውዬ ራሱ በአዕምሮ ቁስለት  የተጠቃ ነው፡፡ መሪው የአዕምሮ ቁስለት ካለበት፣ ተከታዮቹ ይህን ቢያደርጉ አልገረምም፡፡ ምክንያቱም ታሪካዊ የአዕምሮ ቁስለት አለ ብለናል፡፡ በታሪክም፣ በትርክትም ለልጆቹ እየተነገራቸው ልጆቹ የበታችነት እንዲሰማቸው፣ በምክንያታዊው ሳይሆን በስሜታዊው የአዕምሮ ክፍል እንዲያስቡ ተደርገዋል፡፡ የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው ሆነዋል፡፡ መሪያቸው ማሰብ አልቻለም፡፡ ግን ደግሞ ለመሪያቸውም ማዘን አለብን፡፡ ምክንያቱም መሪው ራሱ የአዕምሮ ቁስለት ስላለበት ነው በስሜታዊው የአዕምሮ ክፍል የሚያስበው፤ ፈልጎት ብቻ አይደለም፡፡ ስላልዳነ ነው፡፡ አንተን “ይህን ያህል ብር እሰጥሀለሁና ይህን አካባቢ አቃጥል፤ እነ እገሌን ግደል ቢሉህ ታደርገዋለህ?; አታደርገውም እንበል፡፡ ደግና ሩህሩህ ስለሆንክ ነው የማታደርገው? ለእነዚህ ወጣቶች የተነገረው ሁሉ ተነግሮህ ብታድግስ? አሁን የሆንከውን ትሆን ነበር? በአመዛኙ እነሱን የመሆን እድልህ ነው የሚበዛው፡፡
…በእኛ ሙያ ምን እምነት አለ መሰለህ? የበታችነት መገለጫው የበላይነት ነው፡፡ ጥሩ፣ ለራሱ የተሻለ ግምት የሚሰጥ፣ በጣም ተናጋሪ፣ አሳማኝ ይሆናሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች አለባበሳቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ተናግሮ ማሳመንና ሰዎችን መገፋፋት ይችላሉ፡፡ “በራሱ ይተማመናል” ይባላሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ የበታችነት የሚሰማቸው ሰዎች፣ የበታች ስሜትን ለመደበቅ ሲሉ መስለው የሚታዩት ነው የበላይነት፡፡ ውስጣቸው ግን የሆነች የምታለቅስ ልጅ አለች፡፡ የሆነች የተጨነቀች፣ መወደድ የምትፈልግ፣ መደነቅ የምትፈልግ፣ ተሰሚነት የምትፈልግ የራባት ህጻን ልጅ አለች - ከውስጥ፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ሲናገሩ ሰምተህ እንደሆነ “እኔ ተሰሚ ነኝ፤ ተወዳጅ ነኝ፤ ተከታይ አለኝ፤ በአንድ ቃል ብቻ የፈለኩትን ማድረግ እችላለሁ” ይላሉ፡፡ ነገር ግን ውስጥ ገብተህ ስትፈትሽ የሚሰማቸው የበታችነት ስሜት ታገኛለህ፡፡ እሱን ለመደበቅ ነው ጩኸቱና ፊት ፊት ማለቱ፡፡
ቴዎድሮስ፡ በተለያዩ ሀገራት፣ በተለይ አፍሪካ (ለምሳሌ ብንወስድም በሀገራችን) የተለያዩ አማፂያን በረሀ ገብተው በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ይታገላሉ። ከዓመታት በኋላ በለስ ቀንቷቸው መንግሥትን ይገለብጡና ስልጣን ይይዛሉ። እነዚህ አማፂያን ከጫካ በቀጥታ ነው ወደ ቤተ-መንግስት የሚገቡት፡፡ ምንም ስነ-ልቦናዊ ተሀድሶ ሳያደርጉ በቀጥታ ሕዝብ ወደ ማስተዳደር ነው የገቡት፡፡ እንዲህ ያሉ ሽግግሮች በህዝብ አስተዳደር ላይ ምን ችግር ያመጣሉ?
ትዕግሥት፡- የሀገራችን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ችግርም ይህ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ሁሌም የማስበው ነው፡፡ መንግስትን በግልበጣ ወይ በጦርነት ታስወግድና ስልጣን ትይዛለህ፡፡ በጦርነቱ ወቅት ደም ሲፈስ፣ ሰው ሲገደል፣ ቤት ሲነድ፣ ሰቆቃ፣ እምባ አይተሀል፡፡ ስልጣን ስትይዝ ስልጣን በመያዝ ብቻ ማስተዳደር እንደምትችል ታምናለህ፡፡ ስህተት እንደማይገኝብህ፣ አጠፋህ ማለት የጠላቶችህ ሴራና ተንኮል እንደሆነ ነው የምታስበው፡፡ በምን ውስጥ አልፈህ ወንበሩ ላይ ለመቀመጥ እንደበቃህ ትረሳዋለህ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን በራሱ ጤነኛነት አድርገህ ነው የምታስበው። ለመዳን የአርምሞ ጊዜ ያስፈልግሃል፡፡ ለዓመታት ወህኒ ቤት ቆይተው ወዲያው ስልጣን ተሰጥቷቸው ሌላ ፖለቲካዊ ቀውስ ሲፈጥሩ የምናያቸው አሉ፡፡ መጀመሪያ ለምን ታሰሩ? ማን አሰራቸው? እስሩን ተቀብለውታል ወይ? ከተቀበሉትስ በማን ላይ ቂም ይዘዋል? ወህኒ ቤት ምን ዓይነት የተሀድሶ ስልጠና ይሰጣቸው ነበር? ከእስር ሲለቀቁ ለወህኒ ባበቃቸው አካል ወይ ስልጣን ላይ ምን በቀል ሊፈጽሙ ያስቡ ነበር? ይህ ሁሉ ሳይጣራ ወስደህ (“ድሮም መታሰራቸው አግባብ አልነበረም” በማለት ወይም በሌላ ምክንያት) ሕዝብን እንዲያስተዳድሩ ሀላፊነት ትሰጣቸዋለህ፡፡
ከውጊያ እንደመጡ ስልጣን ላይ የወጡ አማፂያን ደግሞ ሞት ለእነሱ ምናቸውም አይሆንም፡፡ በመግደልና በመሞት ላይ ተረማምደው ነው ስልጣን ላይ የወጡት። ከዚያ  ከሕዝብም ጋር ያንኑ የመግደልና የማሰር ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በመፈንቀለ መንግስት ስልጣን የሚይዙ የአፍሪካ መሪዎች ለምንድነው እነሱ ከገለበጡት መንግሥት የተሻሉ ሆነው በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት የማያገኙት? እነዚህ ሰዎች ብዙ ቀውስ የሚያመጡት ማስተዳደሩ ከብዷቸው አይመስለኝም፡፡ የአርምሞ ጊዜ አልወሰዱም፡፡
ከባድ መሳሪያ በላይህ ሲተኮስና አንተም ስትተኩስ፣ ስትገድልና ስትሞት ለዓመታት ኖረህ እንዴት ሁሉም አስተሳስብህ በአንዴ የተረጋጋና ሰላማዊ ይሆንልሃል? የሰው ልጅ ነህ፡፡ የሰው ልጅ እንደ ማሽን ተሞልቶ በተፈለገው ጊዜ አድርግ የተባለውን የሚያደርግ ፍጡር አይደለም፡፡ መግደል፣ ማጥፋትና፣ መገልበጥ አልመህ እየሄድክ፣ ሲሳካም በዚያው ነው የምትቀጥለው። ቀደም ብለን እንደገለፅነው የአዕምሮ ቁስለት ሲኖርብህ ከምክንያታዊው ይልቅ በስሜታዊው የአዕምሮህ ክፍል ነው ድርጊቶችን የምታከናውነው፡፡ መሪም ብትሆን ሰው ነህ፡፡ መሪም የስነልቦና ምክር ያስፈልገዋል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ግን ትልቁ ችግር፣ የሀገር መሪ ስትሆን፣ ሁሉም አይነት እውቀት ተሟልቶ ያለህ አድርገህ ትቆጥራለህ፡፡ የጎደለህ እንዳለ ካላሰብክ ደግሞ ለመሙላት አትሞክርም፡፡
ቴዎድሮስ፡- ያለፉት 50 ዓመታት ገደማ ታሪካችን “እገሌ በእገሌ ላይ በደል አድርሷል” በሚል ላይ የተመሰረተ ነው። እንዲህ ባዮቹም ራሳቸው ስልጣን ይዘው የተናገሩትን በማረም ፈንታ እነሱም ከሳሽ ሲሆኑ ነው ያየነው፡፡ “እገሌ ብሔር በእገሌ ብሔር ላይ በደል አድርሷል” ብለሽ  ለትግል ተነስተሸ አንቺስ ስልጣን ላይ ብትወጪ መልስ ታመጫለሽ ወይ?
ትዕግሥት፡- ሁኔታውን ስታየው ቂላቂል ነገር ነው፡፡ የሚያስቅ፣ ኮሚክ ነገር ነው የምታየው፡፡ በዚህ መንገድ መልስ ቢገኝ ኖሮ ሀገራችን ለምንድነው ለግማሽ ምዕተ ዓመት መልስ ያላገኘችው? የሆነው ብሔር ስልጣን ለቆ የሆነው ብሔር እየያዘ እኮ ነው የምናየው፡፡ ለምንድነው መልስ ያላገኘነው? የእኔን ዕይታ ብነግርህ፣ እነዚህ ወገኖች የሚያደርጉት ነገር ሁሉ በምክንያት የተደገፈ አይደለም፤ በስሜት የተደገፈ ነው። ሌላው እነዚህ “ተበደልን” ባይ ሰዎች የበታችነት ይሰማቸዋል፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ በሀይል ነው የሚያደርጉት። ማስተዳደር ሳይሆን ቁጭትን መወጣት ነው ያለው፡፡ እነዚህ ወገኖች ሌላውን በማጥቃትና፣ በማሰር፣ በመግደል የውስጥ የአዕምሮ ቁስለታቸውን ሽረው ጤነኛ የሚሆኑ እየመሰላቸው ነው የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያደርጉት፡፡ ግን ምንም ለውጥ የለም፡፡
ስልጣን  ይዘው እየገደሉ፣ እያፈናቀሉ፣ እያሰሩም “ገና ያለፈው በደል አልጠፋም” ሲሉ እኮ ነው የምትሰማው፡፡ ግን ያልተመለሰው ውጭ ያለው ሳይሆን ውስጥ ያለው ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚፈወስ ህመም እንደሌለ አያውቁትም፡፡ ወይም ደግሞ የአዕምሮ ቁስለቱ እንዳያውቁ አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህ በሰላማዊና በመነጋገር መንገድ የሚፈታውን ችግር፣ በማሰርና በሃይል ለመፍታት ሲሞክሩ ውሉ እንደጠፋ ልቃቂት ውትብትብ ይላል፡፡ ቀውስ ይሆናል፡፡ አመፅ ይነሳል፡፡ እነሱም በመጨረሻ በመጡበት መንገድ ይሄዳሉ፡፡ የሚያሳዝነው አዙሪቱ ይቀጥላል፡፡---


Read 5330 times