Print this page
Tuesday, 15 June 2021 18:15

የአገር የስልጣኔ ታሪክ፣ “የነዳጅና የኤሌክትሪክ” ታሪክ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

ያለ ኢንዱስትሪ፣ ያለ ኤሌክትሪክና ያለ ነዳጅ፣ “ብልፅግና” ብሎ ነገር የለም። ያለ ብልፅግና ደግሞ፣ ሰላም አይገኝም - በየዓመቱ ከሚሊዮን በላይ ስራ አጥ ወጣቶችን እያከማቸ፣ እንዴት አገር ሰላም ይሆናል?
በሌላ አነጋገር፣ መበልፀግ የፈለገ፣ ሰላምን የወደደ አገር፣ ከአሜሪካና ከአውሮፓ፣ ከዚያም ከጃፓን፣ ከታይዋንና ከደቡብ ኮሪያ የብልጽግና ታሪክ ይማራል፡፡ ፋብሪካዎችን ያበረክታል። እንደ አገራችን ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች፣ በከንቱ፣ “የካርቦን ልቀት”፣ “አረንጓዴ ልማት”፣ “ታዳሽ ኃይል” እያለ፣ አይጃጃልም። ሃብት አያባክንም። በኢንዱስትሪና በነዳጅ ላይ ጦርነት አያውጅም። በኤሌክትሪክና በሲሚንቶ ላይ አይቀልድም።
ሲሚንቶ ላይ የቀለደ፣ ግንባታ
ላይ የቀለደ።
አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ግን፣ በጣም እየተቀለደ ነው። በሲሚንቶ ላይ የተፈጠረውን ግርግር ተመልከቱ። “ሲሚንቶ ጠፋ፤ ተወደደ፣ ዋጋው እጥፍ ጨመረ” ከሚል የዜጎች ምሬት ጎን ለጎን፣ ምን የሚል የባለስልጣናት ቀልድና ቧልት እንሰማለን? የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ የከሰል የድንጋይ እንደዳይጠቀሙ የሚከለክል እቅድ አዘጋጅተናል - ብለዋል የአገራችን ባለስልጣናት።
“የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ለጊዜው፣ ለጊዜው ብቻ፣ በአገር ውስጥ፣ የከሰል ድንጋይ አፈላልገው መጠቀም ይችላሉ። ወደፊት ግን፣ ቁጥቋጦና አረም እያቃጠሉ መስራት አለባቸው” ተብሏል። ለምን ብላችሁ ጠይቁ። “የከሰል ድንጋይ ሲቃጠል፣ ብዙ ካርቦንዳ ኦሳይድ ይወጣል” የሚል መልስ ታገኛላችሁ - ከባለስልጣናት።
“በካርቦን ልቀት የአለም ሙቀት እንዳይጨምር፤ የሰሜን ዋልታ በረዶ እንዳይቀልጥ በማሰብ ነው” እቅዱ የወጣው። አሁን፣ የአገሪቱን እንጭጭ የሲሚንቶ  ኢንዱስትሪ የሚቀነጭር ይሄ እቅድ፣ምን የሚሉት ቀልድ ነው?
“ለጊዜው ብቻ” ብሎ፣ የከሰል ድንጋይ ፍለጋና ምርት ውስጥ የሚገባ ባለሃብት፣ ምን አይነት ባለሃብት ነው? ነገ እንደሚከለከል እያወቀ፣ ዛሬ ሃብቱን በከንቱ እንደማባከን ይሆናላ።
እና ምን ይሻላል? ያው፣ የከሰል ድንጋይ እስኪከለከል ድረስ፣ ከውጭ ለማስመጣት፣ ከደቡብ አፍሪካ ለመግዛት ይሞከራል፡፡ ከመንግስት የዶላር ምንዛሬ እንዲፈቀድለት ይጠይቃል፤ ይወተውታል። የተፈቀደለት ያህል ብቻ ይሰራል። በዚህም ሳቢያ፣ የሲሚንቶ እጥረት ይባባሳል። ዋጋው ይንራል። ከዚያማ፣ እንደተለመደው፣ የመንግስት የቁጥጥር መመሪያዎች ይታወጃሉ።
መንግስት፣ የሲሚንቶ እጥረትንና የዋጋ  ንረትን “ለመቆጣጠር”፣ የተመንና የኮታ መመሪያ፣ የአከፋፋይና የቸርቻሪ “ልዩ ፈቃድ” ለማዘጋጀት ይዋከባል፡፡ ጊዜና ሃብት ያባክናል። አሳዛኙ ነገር፣ ቁጥጥሩ ሲጀመር፣ የሲሚንቶ እጥረትንና የዋጋ ንረትን ከማቃለል ይልቅ የሚያባብስ መዘዘኛ  ሆኖ ያርፈዋል። የዘንድሮው መዘዝም ያው ሆኗል መደበኛ የንግድ ስራ ተመሳቀለ፡፡ በልዩ ፈቃድና በሙስና፣የሲሚንቶ ገበያ፣አየር በአየር ወከባ ሆኖ ተጥለቀለቀ፡፡ ይሄውና፣ እንደካሁን በፊቱ፣ የቁጥጥር አሳዛኝ ውጤቶችን በድጋሚ ዘንድሮም በእውን አየን።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ፣ “የካርቦን ልቀት ለመቀነስ”፣ “ሞተር አልባ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት” እቅድ እንዳዘጋጀ ተናግሯል። እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ፣ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ መጀመሩንም አውጇል።
“ሞተር አልባ” ማለቱ፣ በብስክሌትና በእግር ተጓዙ ለማለት ነው። አንዳንዴ፣ “ባህላዊ ትራንስፖርት የሚል ስም ይጨመርበታል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ “አገር በቀል ትራንስፖርት” ይሉታል።
“በእግር የመጓዝ ባህል ለማዳበር”፣ ምን ጥረት ያስፈልገዋል? ለእግር ጉዞ፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማቋቋምና ዘመቻ ማካሄድ ያስፈልጋል? ለመሆኑ ምክንያቱስ ምንድን ነው? “ከነዳጅ የሚወጣ የካርቦን ልቀት ለመቀነስ፣ የሰሜን ዋልታ በረዶ እንዳይቀልጥ ለመጠበቅ”…. ምናምን ምናምን። አይ ወግ! ለዚያም ያላአዋቂ ወግ፣ የቸከ ወግ።
- ኢትዮጵያ፣ የመኪና ደሃ፣
የነዳጅ ደሃ አገር፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ከኬንያ ህዝብ በእጥፍ ይበልጣል። በመኪና ቁጥር ግን፣ የኬንያ ይበልጣል - በእጥፍ። ኬንያ ደሃ አገር ናት። ኢትዮጵያ ግን፣ የድሃ ድሃ አገር ሆናለች፡፡ አገራችን፣ የመኪና ደሃ ናት።
በመላው ዓለም፣ ከአንድ ቢሊዮን ሁለት መቶ ሚሊዮን በላይ መኪኖች አሉ። ከዚህ ጋር ሲነፃፀር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሚሊዮን መኪና፣ ከቁጥር አይገባም። ተቀነሰ ተጨመረ ለውጥ አያመጣም።
ታዲያ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ “ስለካርቦን ልቀት” ማውራትና፣ በመኪና ላይ የጥላቻ ጦርነት ማወጅ፣ አላዋቂነትና ከንቱነት አይደለም?
የኢትዮጵያ ጠቅላላ የቤንዚን ፍጆታ፣ በቀን ሁለት ሚሊዮን ኪሎ አይሞላም። አስተውሉ። ይሄ፣ የኢትዮጵያ፣ የሀገሬው ሁሉ፣ ጠቅላላ የቤንዚን ፍጆታ መሆኑን አስቡ። ከቦይንግ 747  ትልልቅ አውሮፕላኖች ጋር አነፃፅሩት። 10 አውሮፕላኖች በአንድ ቀን በረራ፣ ሁለት ሚሊዮን ኪሎ ነዳጅ ይፈጃሉ። ይሄ አይገርምም?
የነዳጅና የኤሌክትሪክ ሃይል ጉዳዮች ዙሪያ፣ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ምሑራን መካከል አንዱ የሆኑት ቫክላቭ ስሚል፣ “የስልጣኔ ታሪክ፣ የነዳጅ የኤሌክትሪክ ሀይል ታሪክ ነው” ይላሉ። ከሁሉም ቀድመው የከሰል ድንጋይና ነዳጅ ዘይት ያመረቱ፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫና ሞተር የፈጠሩ፣ በገፍ የፈበረኩ አገራት፣ በተለይ እንግሊዝና አሜሪካ፣ ከሌሎች ቀድመው ወይም ልቀው በልፅገዋል፡፡ አምፑልና ምድጃ፣ ባቡርና መኪና፣ አውሮፕላንና ሮኬት፣ …..ከኤሌክትሪክና ከነዳጅ የተያያዙ ቴክኖሎጂዎችና ምርቶች ላይ ቀዳሚዋ ተጠቃሽ አገር አሜሪካ፣ የብልጽግና የላቀች አገር ናት፡፡ በብልጽግና ታሪክ፣ የነዳጅና የኤሌክትሪክ ታሪክ ነው እንዲሉ፡፡ ብልጽግና ከእግር ተጓዥ ወደ መኪና፣ ወደ ባቡር፣ አውሮፕላን ተጓዥ መሸጋገር ነው፡፡
 የሰው የጉልበት ስራ፣ ለአንድ አምፖል ከሚያስፈልገው ጉልበት ብዙ አይበልጥም። የሰው ጉልበት፣ ለሁለት አምፖል አይበቃም። ባለ 60 ሻማ አምፖል ይባል የለ? 60 watt (w) ለማለት ነው። የጎልማሳ አማካይ የጉልበት አቅም መቶ ዋት ነው። ለእርሻ የተጣመሩ ሁለት በሬዎች፣ ወደ አራት መቶ ዋት ገደማ ጉልበት ይኖራቸዋል። የጠንካራ ፈረስ ጉልበት፣ የ7 ሰዎች ጉልበት ያህል ነው የሚባለው አለምክንያት አይደለም። የአንድ ፈረስ ጉልበት፣ ከ700 ዋት በላይ ነው።” one horse power= 745 watt` እንዲሉ። መኪናና አውሮፕላንስ?

- በፈረስ ፋንድያ የጨቀየ የኒውዮርክ ጎዳናዎች
ከመቶ ሃያ ዓመት በፊት፣ የመኪና ቴክኖሎጂ ገና “እግር” ሳይተክል፣ የመኪና ፋብሪካና ቢዝነስ ገና ሳይወለድ፣ ገና ጨርሶ ሳይታሰብ በፊት፣ “ባህላዊ ሞተር አልባ ትራንስፖርት” ምን ይመስል እንደነበር አስቡት። የኢትዮጵያ ጦር፣ ከመሃል ሀገር ወደ አድዋ ለመድረስ፣ ከሶስት ወር በላይ ፈጅቶበታል።
በአውሮፓና አሜሪካ? ለትልቅ ባለ ሃብት የተዘጋጀ፣ እጅግ ውድ፣ ባለ አራት ፈረስ ጋሪ፣ በኑውዮርክና በለንደን ጎዳናዎች ሲመላለስ ይታያችሁ። ጋሪና ፈረስ የሚተራመስበት የኒው ዮርክ ጎዳና፣ በፋንድያ ሲጨቀይ፣ በማግስቱ የደረቀ ፋንድያ እየቦነነ፣ ጎዳናው በአቧራ ሲታፈን፣ አስቡት። ምን ይደረግ? “አገር ያፈራው፣ ዘመን የሰራው”፣ የያኔ ቴክኖሎጂ፣ የፈረስ ጋሪ ነው፡፡ ግን ቆሻሻው፣ የነዋሪዎች  የእለት ተእለት እሮሮ ነበር።
ለባለሃብት ጋሪ የተጠመዱ አራቱ ፈረሶች፣ ወደ ሶስት ሺ ዋት የሚጠጋ ጉልበት ሊኖራቸው ይችላል። የዛሬ 110 ዓመት ገደማ፣ የመኪና ቴክኖሎጂን የሚያሻሽሉ፣ አዳዲስ የአመራረት ዘዴዎችን የሚፈጥሩ እነ ሄነሪ ፎርድ መጡና፣ የትራንስፖርት ታሪክ ተቀየረ። T Model የተሰኘችው የፎርድ መኪና እየተፈበረከች ለገበያ ቀረበች። ለባለሃብት ብቻ አይደለም፡፡ ዋጋዋ 5 መቶ ዶላር ነው። ጉልበቷ የ20 ፈረስ ያህል ነው። በነዳጅ የምትሰራ ባለሞተር መኪና። በ20 ዓመት ውስጥ፣ ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኪናዋን ገዝተዋል። የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ መሆኑ ነው። ዛሬ የመኪኖች ዓይነት፣ ምቾት፣ አገልግሎት፣ ጉልበትና አስተማማኝነት የትናየት ሄዷል።
በአሜሪካ፣ ከ10 ቤተሰቦች መካከል ሰባት ያህሉ፣ የግል መኖሪያ ቤት ባለንብረት ናቸው። ከ10 ቤተሰቦች መካከል፣ ቢያንስ 9 ያህሉ ባለመኪና ናቸው።
ከ10 ቤተሰብ መካከል 6 ያህሉ፣ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የቤት መኪና አላቸው።
እንግዲህ እናስላው፡፡ አንድ የፈረስ ጉልበት፣ የሰባት ሰው ያህል፣ ወይም የ12 አምፑል ያህል ጉልበት ነው፡፡ ዛሬ፣
ከ60 እስከ 250 የፈረስ ጉልበት አላቸው አብዛኞቹ የቤት መኪኖች፡፡ ከ45 ሺዋት እስከ 200 ሺህ ዋት እንደ ማለት ነው። የውድድር መኪናዎችና ግዙፍ የጭነት መኪናዎች፣ ከ300 እስከ 1000 የሚደርስ የፈረስ ጉልበት የታጠቁ ናቸው። (ከ250 ሺህ እስከ 500 ሺህ ዋት)።
ከመኪኖች አቅም ጋር የሚመጣጠኑ፣ አነስተኛ የአውሮፕላንና የሄሊኮፕተር አይነቶች የመኖራቸው ያህል፤ ፈርጣማ ተዋጊ ጄት አውሮፕላኖች ደግሞ አሉ። ከአንድ ሺህ አምስት መቶ እስከ 10 ሺህ የፈረስ ጉልበት ይደርሳል- አቅማቸው። ከአንድ ሚሊዮን ዋት በላይ እስከ ስምንት ሚሊዮን ዋት መሆኑ ነው።
ሚሊዮን ዋት በሌላ ስሙ፣ ሜጋ ዋት ተብሎ ሲነገር ሳትሰሙ አልቀራችሁም። የዛሬ 30 ዓመት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎች ጠቅላላ አቅም፣ 330 ሜጋ ዋት እንደነበር አስታውሱ።
የበለስና የተከዜ ግድቦች፣ እንዲሁም ሶስት የጊቤ ሀይል ማመንጫ ተቋሞች ተጨምረውበት፣ የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሀይል፣ ወደ 14 እጥፍ ተጠግቷል። 4500 ሜጋ ዋት ደርሷል። የህዳሴ ስኬት ሲጨመርበት፣ የአስር ሺህ ሜጋ ዋት አቅም ይሆናል። 10ጊጋ ዋት ማለት ነው። አስር ቢሊዮን ዋት እንደ ማለት።
ሁለት መቶ ሺህ አነስተኛ የቤት መኪኖች ካላቸው ጠቅላላ አቅም ጋር ተመጣጣኝ ነው። ወደ 50 ሺዋት ወይም 67 የፈረስ ጉልበት የሚጠጋ አቅም ያላቸው  የቤት መኪኖችን ማለቴ ነው።
እንግዲህ፣ በሀገራችን ከተሰሩ ምርጥ የሌሌክትሪክ አመንጪ ግድቦች መካከል፣ ጊቤ አንድ በምሳሌነት የሚጠቀስ አይደል? 180 ሜጋ ዋት ነው አቅሙ። ሁሌ የግድቡ ውሃ ሙሉ ቢሆን፣ በሙሉ አቅሙ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ይችላል ማለት ነው። ነገር ግን፣ ግድቡ በክረምት ይሞላል፤ ከዚያ እየቀነሰ ይሄዳል። እናም ግድቡ በአማካይ በ90 ሜጋ ዋት አቅም ዓመቱን ሙሉ የኤሌክትሪክ ሀይል ያመነጫል ማለት ነው። የአቅሙን 50 %እንደማለት። ይህ ትልቅ ብቃት ነው።
የንፋስ ተርባይን በ20% አቅም፣ የፀሐይ ሀይል ማመንጫዎች ደግሞ በ10% አቅም፣ ነው ኤሌክትሪክ የሚያመነጩት። ለዚያውም፣ እንደአየሩ ሁኔታ ነው፡፡ “ንፋስን እንደመከተል ነው” ይባል የለ?
የሆነ ሆኖ፣ ከሰውና ከፈረስ ጉልበት ጀምረን፣ እስከ መኪና እስከ ግድብ፣ የነዳጅና የኤሌክትሪክ ሀይልን ለማስተያየት ሞክረናል።
 የሰው የጉልበት ስራ ውሎ፣ ወደ ሁለት አምፖል የተጠጋ ነው።
የፈረስ ጉልበት፣ ከ7 ሰው ጋር ይስተካከላል።
አነስተኛ የቤት መኪና፣ ከ60 የፈረስ ጉልበት ይበልጣል። ግቤ 1 የሀይል ማመንጫ፣ የ3500 መኪኖች ያህል አቅም አለው።
ወደ ትልልቅ አውሮፕላኖች ስንሻገር፣ ቦይንግ 737 አውሮፕላኖችን እናገኛለን። በጥቅሉ ስለ ትልቅ አውሮፕላን ስትሰሙ፣ ሁለት  ቁም ነገሮችን አስታውሱ። ነዳጅ ሞልቶ፣ ተሳፋሪና እቃ ጭኖ ለበረራ ሲነሳ፣ የአውሮፕላኑ ጠቅላላ ክብደት፣ ከገደብ ማለፍ የለበትም። በግርድፉ፣ ሩብ ያህሉ የአውሮፕላን ክብደት፣ የተሳፋሪና የጭነት ክብደት ነው። ቢያንስ ቢያንስ ሩብ ያህሉ ደግሞ የነዳጅ ክብደት ነው። ግማሹ ክብደት ደግሞ፣ የአውሮፕላኑ አካልና ቁሳቁስ ነው።
የቦይንግ 737 አውሮፕላኖች፣ max 7 የሚባለው ጣጠኛ አውሮፕላንን ጨምሮ፣ ክብደታቸው ከ80 ሺህ ኪሎ ማለፍ የለበትም። ከ5 ሺህ ኪሎ ሜትር ያላነሰ ርቀት የመብረር አቅም አላቸው። ለዚህም 20 ሺህ ኪሎ ነዳጅ መሙላት ይችላሉ። የሞተራቸው ከፍተኛ የጉልበት አቅም 30 ሜጋ ዋት ገደማ ነው።
ትልልቆቹ አውሮፕላኖች ደግሞ አሉ። B777 እና B747። የአንዱ አውሮፕላን የጉልበት አቅም፣ ከ150 ሜጋ ዋት እስከ 250 ሜጋ ዋት ይደርሳል። ቦይንግ 747 አውሮፕላን፣ የ5 ሺህ መኪኖች አቅም አለው። በዚያ ላይ እንደመኪኖች አጭር ተጓዥ አይደለም። እንደ መኪኖች፣ ብዙ ስራ አይፈታም። ቀን ከሌት ለረዥም ሰዓታት ይጓዛል። በቀን፣ ከ18 ሰዓታት ላላነሰ ጊዜ ይበራል፡፡ የነዳጅ ፍጆታውም የዚያኑ ያህል ነው። 200 ሺህ ኪሎ የጄት ነዳጅ (ኬሮሲን) ተሞልቶ ሲነሳ አስቡት።
ይሄ፣ ከመኪናና ከቤንዚን ጋር ሲነፃፀር፣ አጃኢብ ያሰኛል። 200 ሺህ ኪሎ ቤንዚን ማለት፣ ማለትም 200 ቶን ቤንዚን ማለት…….
አስር ትላልቅ B747 አውሮፕላኖች፣ ነዳጅ ሞልተው ለበረራ ሲነሱ፣ 2000 ቶን ነዳጅ ይኖራቸዋል።
የኢትዮጵያ መኪኖች እለታዊ የቤንዚን ፍጆታስ በሉ። 2000 ሺህ ቶን አይደርስም። የአምና መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኢትዮጵያ  አማካይ እለታዊ የቤንዚን ፍጆታ፣ 1500 ቶን ነው። ስምንት ትላልቅ B747 አውሮፕላኖች ከሚሞሉት የጄት ነዳጅ ጋር ይቀራረባል ማለት ነው።  የአገሪቱ የነዳጅ ፍጆታ፣እንደዚህ ነው፡፡ ታዲያ፣ ኢትዮጵያን በመሰለ አገር፣ ከነዳጅ የሚወጣ ጭስ፣ የካርቦን ልቀት፣ የሰሜን ዋልታ  በረዶ፣ የሚል ጨዋታ ቅዠት አይደለም?
“ሲሉ ሰምታ” ነው ነገሩ፡፡ እስኪ ደግሞ፣ በዓለም የቤንዚን ፍጆታ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ድርሻ ስንት እንደሆነ እንመልከት።
የዓለም የቤንዚን ፍጆታ በዓመት 1170 ሚሊዮን ቶን  ነው። እንደ ህዝብ ብዛት ቢሆን ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ድርሻ ወደ 15 ሚሊዮን ቶን ገደማ በሆነ ነበር። ግን፣ ገና ግማሽ ሚሊዮን ነው። ኢትዮጵያ፣ “መኪና አልባ እና ሞተር አልባ እግረኛ” እንድትሆን ቢፈረድባት እንኳ፣ የዓለም የቤንዚን ፍጆታ ጠብታ አይጎድልበትም። ከ1170 ብር ውስጥ 50 ሳንቲም እንደመቀነስ ነው። የካርቦን ልቀት የሚባለው ወግም፣ የዚህን ያህል ነው- ወገኛነቱ።
የኢትዮጵያ የቤንዚን ፍጆታ፣ ከሌላው ዓለም  ጋር ሲነጻጸር፣ ከቁጥር የማይገባ ኢምንት ነው፡፡ “የካርቦን ልቀት” የሚሉት ነገርም በዚያው መጠን ከኢምንት አያልፍም።
ይልቅስ፣ ኢምንቷን የነዳጅ ፍጆታ ለማሟላት፤ የአገሪቱ እጅ ማጠሩ ነው ችግሩ። ዶላር እያጣች ያለች አገር መሆኗ ነው አሳሳቢ ነገር፡፡Read 987 times