Sunday, 06 June 2021 00:00

“ኮሮና ቢራ” የአመቱ የአለማችን ባለከፍተኛ ዋጋ ቢራ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኮሮና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አጫሾች ሲጋራ እንዲያቆሙ አነሳስቷል

              ብራንድ ፋይናንስ የተባለው ኩባንያ የ2021 የፈረንጆች አመት ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ያላቸው 50 የአለማችን ቢራዎችን የንግድ ምልክቶች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ 5.8 ቢሊዮን ዶላር የተገመተው የሜክሲኮው “ኮሮና ቢራ” በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
“ኮሮና ቢራ” ምንም እንኳን ስሙ ከአደገኛው ቫይረስ ጋር መመሳሰሉ በተጠቃሚዎች ዘንድ በፈጠረው መጥፎ ስሜትና በሌሎች ምክንያቶች የንግድ ምልክት የገበያ ዋጋው ባለፈው የፈረንጆች አመት ከነበረበት የ28 በመቶ ቅናሽ ቢያሳይም፣ በአሜሪካ በብዛት በመሸጥ ቀዳሚነቱን የያዘውና ከ120 በላይ አገራት የሚጠጣው ይህ ቢራ በንግድ ምልክት ዋጋው የሚስተካከለው አለመገኘቱ ተነግሯል፡፡
5.64 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ የተነገረለት የሆላንዱ ሄኒከን ቢራ፤ በዘንድሮው የምርጥ 50 ቢራዎች ዝርዝር ውስጥ የ2ኛ ደረጃን ሲይዝ፣ የአሜሪካው ባድዋይዘር ቢራ በበኩሉ፣ በ4.79 ቢሊዮን ዶላር ሶስተኛ ሆኗል፡፡
የሜክሲኮው ቪክቶሪያ በ4 ቢሊዮን ዶላር፣ የአሜሪካው ቡድ ላይት በ3.9 ቢሊዮን ዶላር፣ የቻይናው ስኖው በ3.45 ቢሊዮን ዶላር፣ የሜክሲኮው ሞዴሎ ስፔሻል በ3.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የጃፓኑ ኪሪን በ2.853 ቢሊዮን ዶላር፣ የአሜሪካው ሚለር ሊቴ በ2.850 ቢሊዮን ዶላር፣ የጃፓኑ አሳሺ በ2.84 ቢሊዮን ዶላር የገበያ ዋጋ ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአለማችን ምርጥ 50 ቢራዎች በፈረንጆች አመት 2020 የነበራቸው የ94.9 ቢሊዮን ዶላር የገበያ ዋጋ፣ በ2021 አመት በ16 በመቶ ቅናሽ በማሳየት ወደ 80.2 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱን የጠቆመው ኩባንያው፤ ለዚህ ቅናሽ በምክንያትነት የጠቀሰው ደግሞ የኮቪድ 19 ክልከላዎችን ነው፡፡ በአመቱ ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ጭማሪ ያደረገው ቀዳሚው ቢራ የቤልጂየሙ ሚቼሎብ ሲሆን፣ ዋጋው በ39 በመቶ ጭማሬ በማድረግ፣ ወደ 1.2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ ተያያዥ ዜና ደግሞ፣ ወረርሽኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአለማችን ሲጋራ አጫሾችን ሲጋራ ለማቆም እንዳነሳሳቸው የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡ ከማያጨሱት ጋር ሲነጻጸር አጫሾች በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ ለከፍተኛ ህመምና ሞት የመጋለጥ ዕድላቸው በ50 በመቶ ያህል እንደሚጨምር ማረጋገጡንና ይህም በመላው አለም የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አጫሾችን ስጋት ውስጥ እንደከተታቸውና ሲጋራ ለማቆም እንዳነሳሳቸው የጠቆመው ድርጅቱ፤ ይህም ሆኖ ግን አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ካልተደረገላቸው ሲጋራ የማቆም እድላቸው እጅግ ጠባብ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በመላው አለም ከሚገኙት 1.3 ቢሊዮን ያህል የትምባሆ ተጠቃሚዎች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሲጋራ ለማቆም የሚያስችላቸው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው የጠቆመው ድርጅቱ፤ በአለማችን 39 በመቶ ያህል ወንዶችና 9 በመቶ ያህል ሴቶች ትምባሆ እንደሚጠቀሙ ማረጋገጡንም ገልጧል፡፡
በአለማችን በየአመቱ 8 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በሲጋራ ሳቢያ ለሞት እንደሚዳረጉ የጠቆመው ድርጅቱ፤ አጫሾች ለሲጋራና  ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተያያዘ ለህክምና የሚያወጡትን ገንዘብ ጨምሮ በየአመቱ 1.4 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጡም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 2661 times