Monday, 07 June 2021 00:00

አዲስ አበባ፤ የመጪው ሀገራዊ ምርጫ ወሳኝ ኩርባ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

    የፖለቲካ ፓርቲዎች አሰላለፍ ምን ይመስላል?
                           

               ንድፈ ሐሳባዊ ማብራሪያ
ታዋቂው የሥነ ማኅበረሰብ ፈላስፋ ቱርካዊው ዱርካይም፣ ከተሜነት የዘውጌ ማንነት ማቅለጫ ጋን (melting pot) እንደሆነ ያብራራል፡፡ እንደ ልሂቁ አባባል፣ የከተማ መስፋፋት ከኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳት ለጥቆ የሚመጣ ኹነት ነው። ይኽ ነባራዊ ኹኔታ ደግሞ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካውና በኢኮኖሚ ረገድ የፋፋ ዘመናዊ ማኅበረሰብን ለዐይነ ሥጋ በማብቃቱ ረገድ ድርሻው የላቀ ነው፡፡ በዚህ አውድ ውስጥ የተፈጠረ የዳበረ ማኅበረሰብ፣ ለዘውጌ ማንነት ፊት አይሰጥም፡፡ አጠቃላይ የግለሰቦች የእርስ በርስ ግንኙነት፣ በላቀ ኅላዌ (ኦርጋኒክ ሶሊዳተሪ) የሚገለጽ እንደሆነ ከፈላስፋው ሐተቲ እንረዳለን፡፡
በአንጻሩ፤ የዘመናዊነት መዳፍ ያልዳበሰው ኋላ ቀር ማኅበረሰብን ያስተሳሰረው የግንኙነት መረብ፤ ከአመክንዮ በተራቆተ የደቦዋዊ ቅኝት፣ ማለትም በወንዝ ልጅነት፣ በእምነት፣ በባህል ወይም በትውፊት የሚገለጽ ይሆናል፡፡ እሴቶቹ፣ በመወለድ ብቻ የምንላበሳቸው ቆሞ ቀር የማንነታችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ የእኛን ማውጣት ማውረድ /Rational endeavor/ ወይም የአእምሮ ፍሬ የሚጠይቁ አይደለም። እነዚህ ኋላ ቀር የትስስር ዘረ-መሎች፣ ዘመናዊነት በሚፈነጥቃቸው ዕድገቶች ምክንያት፤ በሌላ ውስብስብ መስተጋብር ደብዛቸው ይጠፋል።
በሌላ አነጋገር፣ የዘውጌ ፖለቲካ በጽኑ የሚሻው ባህላዊ ንጣፍ፣ ከተሜነት በሚያመጣው እድገት የተነሳ ጠፍ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ባህላዊውን ማኅበረሰብ እንደ ወጋግራ ያቆመው ከምክንያት ይልቅ፤ ለስሜት ቅርብ የሆነው የጋራ ማንነት፣ ዝመና የሚፈጥረውን ልህቀት መቋቋም ተስኖት ሥፍራውን ለሌላ ገዢ መስተጋብር መልቀቁ ግዴታ ይሆናል፡፡ ከተሜው በሐሳብ የበላይነት እንጂ፤ በቋንቋ ማንነት ወይም በወንዜ ልጅነት ልቡ ሊሸፍት አይችልም፡፡ የአዲስ አበባ ነባራዊ ሁኔታም በዚህ ማእቀፍ ነው መገምገም ያለበት፡፡
 
ከአዲስ አበባ ሥነልቦና ጋር የተጣሉት ብሔረተኞች
በአዲስ አበባ ዜጎች በደቦ በሚቧደኑበት ዝግ ማንነት (ቋንቋ እና ዘረመል) ምትክ ከተሜነት በወለደው ሁሉን አቃፊ በሆነ፣ ሥልጡን መስተጋብር እርስ በርሳቸው ሳይነጣጠሉ የተቆራኙ ናቸው፡፡ አዲሱ የለውጥ አስተዳደር የሥልጣን መንበሩን በተቆናጠጠባቸው ጥቂት ወራት ውስጥ፣ ዋነኛ የክረት ማእከል ሆኖ ብቅ ያለው፤ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ጉዳይ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ዋልታ ረገጥ የዘውጌ ብሔርተኞች፤ አዲስ አበባን ያለ ተፈጥሮዋ አዲስ ማንነትን ሊያላብሷት ቢውተረተሩም፣ ብዙም ርቀት ሳይሄዱ ተሰነካክለዋል፡፡
እነዚህ ኃይሎች፤ ሥርዓት አልበኝነት በሰፈነበት የፖለቲካ ድባብ ላይ፣ ለጊዜውም ቢሆን ወሳኝ ኃይል  መስለው ይታያሉ፤ ማእበሉ ሲረግብ ግን፤ የሐሳብ ጠኔ ምን ያህል እንዳጠናገራቸው ገሀድ ይሆንልናል። በአሁኑ የምርጫ ክርክር እንኳን የዘውጌ ድርጅቶች፣ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ አማራጭ ሐሳብ ይዘው በመቅረብ፣ መራጩን ያሳመኑበትን መድረክ በትክክል ያስተዋልንበት አጋጣሚ የለም ቢባል፤ ከእውነታው ጋር መጋጨት አይሆንም፡፡
ማእበሉ ሲረግብ አዋጪ ሐሳብ እንጂ ሚዛን ላይ የሚቀመጠው ብሶትና በደልን መደርደሩ አንዲት ጋት ፈቀቅ አያደርግም። የዘውጌ ብሔርተኞች፣ ለአዲስ አበባ ውስብስብ ሥነልቦና የሚመጥን አመራጭ ሐሳብን ለማቅረብ ሥሪታቸውም አይፈቅድላቸውም፡፡ በክርክር መድረኮች ላይ፣ ለመራጩ ሕዝብ ዐይን የሚሞላ ፖሊሲንና ስትራቴጂን ለአውደ ርዕይ አለማቅረባቸው ሊደንቀን አይገባም፡፡ ለመሆኑ፤ የመጪው ምርጫ ፉክክር ዋንኛ ማእከል በሆነችው አዲስ አበባ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሰላለፍ ምን ይመስላል?

ግራ የተጋባው ገዢው ብልጽግና
በኢህአዴጋዊ ባህል ላይ የበቀለው ብልጽግናን፣ “በአሮጌ አቁማዳ ላይ የተቀዳ አዲስ ወይን” በማለት አንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ሽግግሩን ያጣጥሉታል፡፡ ድርጅቱ ከላይ ቀናኢ መሪዎች ቢኖሩቱም፤ ዋንኛው የካድራዊ መዋቅሩ በኢህአዴጋዊ ባህል የሚዳክር ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ ሬኒ ልፍሮህ፣ የቀድሞውን ኦህዴድን “Head Without Body”  ብሎ የገለጸው፤ ለአሁኑ ብልጽግና በትክክል ይሰራል፡፡ የብልጽግና ጭንቅላቱ ምንም እንኳን ለለውጥ ሒደት ተባባሪ ቢመስልም፣ አካሉ ወይም የታችኛው መዋቅር በኢሕዴግ ቅኝት የሚደንስ ነው፡፡ በነቢብ የተለወጠ፣ በግብር ከኢህአዴግ ብዙም ፈቀቅ ያላለ ድርጅት ይሉታል፤ ተቺዎች፡፡
ሀገሪቱን ሁለንተናዊ ቅርቃር ውስጥ የጨመረውን ሕገ መንግሥትም ሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለማሻሻል ብልጽግና ጨከን ባለ ቋንቋ ሲገልጽ አይስተዋልም፡፡ እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች፣ የድርጅቱ ተወካዮች በምርጫ ክርክር መድረኮች ላይ "ብሔራዊ መግባባት" በሚል ጭምብል፣ አድበስብሰው ነው የሚያልፉት፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት፣ እንደ አዲስ አበባ ሕዝብ ያጎደለው የለም። የከተማዋ ነዋሪ ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት፣ የፖለቲካ ውክልና ተነፍጎት፤ የፓርቲ ሹመኞች እንዳሻቸው ሲቀልዱበት ነው የኖሩት፡፡ የኢሕአዴግ ግንባርን የመሠረቱት አራቱ የዘውጌ ድርጅቶች፣ በመዋጮ ከተማዋን ሲያስተዳድሯት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከከተማ ሥነልቦና ጋር ፍጹም የማይተዋወቁት የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ተወካዮች፤ ዐይናቸውን በጨው አጥበው፣ ነዋሪው እንዲመርጣቸው በምርጫ ሰሞን ግርግር ይፈጥሩ ነበር ፡፡    
ሕገ መንግሥቱ አዲስ አበባን  “ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ” አይደለሽም ብሎ፤ ፖለቲካዊ ውክልና ነፍጓታል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተማዋ መቀመጫ የላትም፡፡ ምክር ቤቱ ወደ 12 የሚጠጉ ሀገራዊ አጀንዳዎችን መወሰን እንዲችል፤ ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን ለግሶታል። በእነዚህ ሁሉ ትልልቅ ርዕሰ ጉዳዮች፣ የአዲስ ሕዝብ የበይ ተመልካች እንዲሆን ተፈርዶበታል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ አበሳ በዚህ አያበቃም፡፡ ሕወሓት ያጠመደው ልዩ ጥቅም የሚል ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ አለ፡፡ በአንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5  መሠረት፤ አሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም ይኖረዋል ተብሎ ተደንግጓል፡፡ እስካሁን ይህን ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ ማስፈጸሚያ አዋጅ ባይወጣም፣ ወደፊት ከድንጋጌው ጋር ተያይዞ የሚመጣ ፖለቲካዊ ሸክም እንደሚኖር ከጥያቄ ላይ የሚወድቅ አይደለም፡፡
ይህን በአዲስ አበባ ላይ ድርብ ድርብርብ ሸክም ያጎናጸፈን ሕገ መንግሥት ለማስቀጠል ቁርጠኛ ሆኖ፣ ብልጽግና የከተማዋን ነዋሪ እንዲመርጠው በጽኑ መዳዳቱ ግርምትን ያጭራል፤ ይላሉ ታዛቢዎች፡፡
ሌላው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በብልጽግና ላይ የሚሰነዘረው ትችት፣ ድርጅቱ የከተማዋ ነዋሪ ያልመረጣቸውን ሹመኛ እጩዎችን አቅርቧል የሚል ነው፡፡ ሹመኛ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ታማኝነቱ ለሾመው ፓርቲ እንጂ፤ ለመራጩ ሕዝብ እንዳልሆነ የእስካሁን የፖለቲካ ባህላችን ዋቢ ምስክር መሆን ይችላል፡፡

የኢዜማ ፈተና
ኢዜማ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ፣ ከገዢው ፓርቲ በመለጠቅ በርካታ እጩዎችን ያቀረበ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የድርጅቱ አመራሮች፣ በከተማዋ በሁሉም የምርጫ ክልል ከብልጽግና በላይ እጩ ማቅረባቸውንና ወደ 42 የሚጠጉ ፖሊሲዎችን መቅረጻቸውን፤ ለጠንካራ ተፎካካሪነታቸው በዋቢነት ያነሳሉ፡፡ ትልቁ ጥያቄ፣ ኢዜማ በምርጫ አሽንፎ ሥልጣን ቢረከብ፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ትቶት የሄደውን የቤት ሥራ እንዴት ይፈተዋል የሚለው ይሆናል?   
ሕወሓት/ኢሕአዴግ በምርጫ 97 በቅንጅት የደረሰበትን አሸማቃቂ ሽንፈት ተከትሎ፣ በጊዜው ደንገጡር ፓርቲ የነበረው ኦህዴድ በተላለፈለት ቀጭን ትዕዛዝ መሠረት፣ የክልሉን መቀመጫ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ሊያሸጋግር ችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ፤ ከተማዋ ድርብ ድርብርብ ችግሮችን ለመሸከም ተገዳለች፡፡ ለአብነት ያህል፣ አዲስ አበባ ለኦሮሚያ ክልል ተቋሟት መገንቢያ የሚሆን መሬት የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የኦሮሚያ ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ የማቋቋም ጉዳይ፣ ሌላ የራስምታት አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሏል። በዚህም ምክንያት፣ የክልሉ ሠራተኞች በአዲስ አበባ ውስጥ በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ሲፈጽሙ፣ የሚዳኙበት መንገድ መወሳሰቡ አይቀርም፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አሸናፊ ሆኖ፣ ከተማዋን ለመረከብ ቢችል፣ ሕወሓት በልዩ ጥቅም ሽፋን ቀብሮት የሄደውን የሴራ ፖለቲካ፣ በምን መልኩ እንደሚያከሽፈው ግልጽ አይደለም። በኦሮሚያ ብልጽግና ውስጥ ያሉ ጽንፈኛ አጀንዳን የሚያቀነቅኑ ኃይሎች፣ አሁን አሁን የልዩ ጥቅምን ጉዳይ ትተው የባለቤትነት ጥያቄን ማንሳት ጀምረዋል፡፡
138 ቁልፍ ግቦችን የያዘ ማኒፌስቶን ለመዲናዋ አዘጋጅቻለሁ የሚለው ኢዜማ፤ አሸንፎ የከተማዋን ምክር ቤት ቢረከብ፤ ከዋልታ ረገጥ ብሔረተኞች ጋር የሚኖረው ግብግብ በዋዛ የሚታይ አይሆንም፡፡ የከተማዋን ምክር ቤት ተቆጣጥሮ ብቻ፣ ከገዢው ፓርቲ አርጩሜ መራቅ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም፣ በ1995 በአሊ አብዶ የሚመራው የአዲስ አበባ ምክር ቤት የተበተነው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንድ ደብዳቤ ነበር፡፡
ኢዜማ የአዲስ አበባ ምክር ቤትን ቢያሸንፍ እንኳን፤ ገዢው ብልጽግና መንግሥት መመሥረት የሚያስችል መቀመጫ ካገኘ፣ ከተጽእኖ የሚላቀቅበት ቀዳዳ ጠባብ ነው፡፡ “የተወካዮች ምክር ቤትን መቀመጫ መቆጣጠር የሚያስችል በቂ እጩ ስላቀረብን የሚያሳስበን ጉዳይ አይሆንም፡፡ ይህ ስጋት በቂ እጩ ማቅረብ ያልቻሉት የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንጂ፤ የእኛ ሊሆን በፍጹም አይችልም፤” በማለት ኢዜማዎች  መልስ ይሰጣሉ፡፡
 
 ባልደራስ እና ተቃርኖው
ባልደራስ ለእውነተኛ  ዲሞክራሲ ፓርቲን ከአደረጃጀት ጥንካሬ ይልቅ፣ የእስክንድር ገናና ስም ተጭኖታል፤ የሚሉ ተቺዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ለዚህም በማስረጃነት የሚያነሱት ነጥብ፣ ድርጅቱ ማኒፌስቶ ከማስተዋወቅ በዘለለ፣ የከተማዋ ሕዝብ ከተደራረበበት ውስብስብ ችግር ሊያላቅቁ የሚችሉ ማኅበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ነክ ፖሊሲዎችን ቀርጾ ለውይይት ማቅረብ አለመቻሉን ነው፡፡
የአንድ የፖለቲካ ፓርቲን ጥንካሬ ለመመዘን፣ ሕዝብን ማእከል አድርጎ ከታች ወደ ላይ ምን ያህል ተደራጅቷል? የሚታገልለትን ሕዝብ ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ምን ያህል ፖሊሲዎችን ቀርጿል? የሚሉት ወሳኝ መለኪያዎች ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው የፓርቲ ፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ባልደራስ፣ በሁለቱ መለኪያዎች ሲመዘን፣ አመርቂ ሥራን እንዳልሠራ ተቺዎች ይሞግታሉ፡፡
ሌላው ግራ አጋቢ እውነታ፤ ለአዲስ አበባ ሕዝብ መብት እታገላለሁ የሚል ድርጅት፣ በዘውግ ማንነት ዙሪያ ከተሰባሰበ ድርጅት ጋር ጥምረት የመፍጠሩ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጥምረት፣ የፓርቲውን የሲቪክ ፖለቲካ ውቅር ከሚመስሉ ከሌሎች ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር ለምን መፈጸም አልፈለገም? የሚል ለትችት የሚዳርግ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ፓርቲው ሙሉ እጩ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ በጎደለው ቦታ የአብንን እጩዎች በመሙላት በምርጫው ላይ ለመወዳደር ወስኗል፡፡ ከሀገራዊ ማንነት ጋር ጥብቅ ትስስር ባለው ማኅበረሰብ ፊት፣ በዘውግ ድርጅት መቅረብ፤ በምንም መመዘኛ አዋጪ የትግል መስመር ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ የአዲስ አበባን ሕዝብ በአዋጪ ሐሳብ መማረክ ይቻላል። ከዚህ በተረፈ የእናት አባቱን ዘር ቆጥሮ ልቡን ለማሸፈት መሞከር፣ በፖለቲካ ፊት የዋህ የሚያስብል ተግባር ነው፡፡

ማሰሪያ ነጥብ
የ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የልብ ምት አዲስ አበባ እንደሆነች ቢታወቅም፣ ተገቢው ትኩረት አልተሰጣትም፡፡ የአዲስ  አበባ ጉዳይን የመገናኛ ብዙኃንም ሆኑ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈሩት ይመስላል። በተለይ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን፣ ገዢውና ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ አማራጭ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ለመፍጠር  አልቻሉም፡፡ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ፓርቲዎቹን ያከራከሩት አርትስ ቲቪ እና ኢሳት ብቻ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ፣ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚረከብ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የከተማዋን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የወሰን መብት እውን ለማድረግ፤ ሥርነቀላዊ የሆነ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ገቢራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በአንድ ጎን ሕገ መንግሥቱ በመቃብሬ ላይ ነው የሚነካው እያሉ፤ በሌላ ወገን ስለ አዲስ አበባ ሕዝብ መብት ተቆርቋሪ መሆን አይቻልም፡፡
ከአዘጋጁ፡ ከላይ የቀረበው ሃሳብ ወይም አመለካከት የሚወክለው የጸሃፊውን ብቻ እንደሆነ እየገለጽን፣በተነሳው ርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ ማናቸውንም ሃሳቦችና አስተያየቶች ለማስተናገድ መድረኩ ክፍት መሆኑን ልናረጋግጥ እንወዳለን፡፡ ሃ
ሳብ አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው!


Read 3113 times