Saturday, 05 June 2021 13:05

"ኢምፔሪያሊዝምን ማስጠንቀቅ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

   "እግረ መንገድ... አንዳንድ  በጉዳዩ ላይ ይሰጡ የነበሩ ‘ትንታኔዎች’፤ ከምርጥ ስታንድ አፕ ኮሜዲ በላይ እንዳዝናኑን መዝገብ ላይ ይከተብልንማ! ተንታኞቹስ እሺ... ኸረ የቲቪና የሬድዮ ጣቢያዎች፤ ወንፊት ቢጤ አዘጋጁ፡፡ አሀ...ሰዉ እንደፈለገው ሀሳቡን መናገር ይችላል ተባለ እንጂ... እንደፈለገ ሰው ማሳቀቅ ይችላል ተባለ እንዴ! --"
       
               እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስንትና ስንት ‘በሰው’ የተፈጠሩ ‘ክረምቶች’ ውስጥ የከረመች ሀገር፣ ከእነሱ በቅጡ ሳትወጣ የተፈጥሮው ክረምት ሊመጣባት ነው አይደል! ከመቼው መስከረም ሆኖ ከመቼው ሰኔ እንደሚሆን ግርም አይላችሁም! መለስ ብላችሁ ስታዩት እኮ እንደ የካቲት፣ ጥር ምናምን የመሳሰሉ ወራት ለዘንድሮ የታለፉ ነው የሚመስለው። ብቻ ክረምቱን ተከትሎ የሚመጣው ‘ፈሳሽ የወንዝ ውሀ፣” ከፉውን በሽታ ሁሉ፣ ክፉውን ሀሳብ ሁሉ፣ የውስጡንም፣ የውጪውንም፣ ክፉውን እቅድ በሙሉ፣ ጠራርጎልን ይሂድማ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የአማሪካን ነገር አስቸገረን አይደል! በበቀደሞቹ ሰልፎች ላይ፣ በሰልፈኞች የተያዙት መፈክሮች አብዛኞቹ ታስቦባቸው የተጻፉ መልእክቶቻቸው ግልጽ የሆኑ መሆናቸው አሪፍ ነው፡፡ የምንማር ካለን ከዚህ እንማር፡፡ አሀ… ልክ ነዋ! እዚህ ሀገር የሚታዩ ቀይ መስመር ያለፉ መፈክሮች በሰልፎች ላይ ስናይ ነው የከረምነው፡፡ በእርግጥ ለአንዳንዶቻችን የ‘ፈረንጅ አፎቹ’ መፈክሮች አልተዋጡልንም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ በፈረንጅ አፍ ‘ተጽፈው’ በእጅ የተያዙና መኪኖች ላይ የነበሩ መፈክሮች ‘የአቅም እጥረት’ ነበረባቸው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ... በስተኋላ “የፎቶሾፕ ቅንብር ሳትሆን አትቀርም...” ምናምን ተባለች እንጂ ሆነችም፣ አልሆነችም አንዲት በስፋት የተሰራጨች መፈክር ቢጤ ገራሚ ነበረች፡፡ “እንከባበር ብለን ነው እንጂ አሜሪካ ያሉትን ኢትየጵያውያን ማስታጠቅ ይቻላል…” አሪፍ አይደለች! (በዚህ ሰበብ ደግሞ ሌላ አይነት ማእቀብ እንጥላለን ቢሉ... አለ አይደል... "እኛ እናስታጥቃለን ስንል በጦር መሳሪያ ሳይሆን በሀሳብ ማለታችን ነው፣” ማለት ይቻላል፡፡)  እናላችሁ... ምናልባት “አሜሪካ፣ ቀጥነን ብታየን ጅማት እየለመነችን ስለሆነ ልክ ልኳን መንገር ያስፈልጋል፣” ተብሎ ሊሆንም ይችላል፡፡ ‘ሀሎ ሁዋይት ሀውስ፣ ይሰማል!”
እኔ የምለው… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ግራ ግብት ያለችን ነገር አለች፡፡ ሀገር ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ በውጭ ሀገራት ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ  እነ አሜሪካንን «እጃችሁን ከሀገራችን ላይ አንሱ” እያሉ ሲቃወሙ፣ ያ ሁሉ ትንፋሻችንን ሲያሳጥር የከረመ ፖለቲከኛ፣ ያ ሁሉ ደም ብዛትም፣ ደም ማነስም በአንድ ላይ ሲሰጠን የከረመ አክቲቪስት፣ ያ ሁሉ በየቴሌቪዥኑ ሆነ ተብሎ (ቂ…ቂ…ቂ…) በእራት ሰዓት እየመጣ የምንመገበውን ማኘክ እስኪያቅትን ድረስ ሲያሳቅቀን የከረመ ተንታኝ፤ ምነው ጭጭ፣ ምጭጭ አሉሳ! ልክ ነዋ... ስንት ነገር ላይ በእሽቅድድም መግለጫ ያወጡ የለም እንዴ! እንደው ሰው እንዳይታዘበን እንኳን ብለው ፓርቲዎቹ፤ ብጣሽ ወረቀት ላይ የሆነ ነገር ጻፍ አድርጎ ለሚዲያ ለመላክ ምን አቃተቸው! መቶ ምናምን በቃ ቁጥር ብቻ ነው! እንደውም አንዳንዶቹ በመግለጫ ብዛት ሀገራችን በሆነ የዓለም መድረክ ሊያስጠሩ ይችሉ ነበር፡፡ እና ይህን በመሰለ ከበድ ያለ ጉዳይ ላይ የሆነ ነገር ማለት አልነበረባቸውም እንዴ! ይህ እኮ እንትናን የመደገፍ እንትናን የመቃወም ጉዳይ አይደለም፡፡ የሀገር ጉዳይ አይደለም እንዴ?! ነው ወይስ አሜሪካ ‘አንተቸብል ነች!’ (ድሮኖችን ፈራችሁ እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…) … ለነገሩ በእኛ ‘አሸር በአሸር’ በሆነ ፖለቲካ፣ ምንስ ነገር ምን ይገርማል!
እግረ መንገድ... አንዳንድ  በጉዳዩ ላይ ይሰጡ የነበሩ ‘ትንታኔዎች’፤ ከምርጥ ስታንድ አፕ ኮሜዲ በላይ እንዳዝናኑን መዝገብ ላይ ይከተብልንማ! ተንታኞቹስ እሺ... ኸረ የቲቪና የሬድዮ ጣቢያዎች፤ ወንፊት ቢጤ አዘጋጁ፡፡ አሀ... ሰዉ እንደፈለገው ሀሳቡን መናገር ይችላል ተባለ እንጂ... እንደፈለገ ሰው ማሳቀቅ ይችላል ተባለ እንዴ! ተሳቀን፣ ተሳቀን ጭብጦ ልናክል እኮ ነው! አንዳዶቻችንማ፣ ይቺ አማሪካን የሚሏትን ሀገር...አለ አይደል... ልክ የቀበና ወንዝን ጎርፍ የሚያህል ውሀ ቢያገኛት ይዟት ጥርግ የሚል፣ የሆነች ሚጢጢዬ ደሴት አስመሰልናትሳ!
እናላችሁ... ‘የትንታግ ቦተሊከኞቻችን፣ ‘ተናግረው የማይደክማቸው’ አክቲቪስቶቻችን፣ ‘አንዲት እንኳን ቃላቸው መሬት ጠብ የማትል’ ተንታኞቻችን ዝምታ፣ በራሱ ቀሺም የ‘ቦተሊካ’ ምን አለሽ ተራ ነገር አይነት ነው፡፡ (ቂ...ቂ...ቂ...) ነገርዬው ኤምባሲ ለቪዛ ሲኬድ፣ ‘እስኪጣራ ማን ይጉላላል፣” ነገር ነው እንዴ!
“ቀጠሮ ተሰጥቶህ ነው የመጣኸው?”
“አዎ፣ ይኸው ቀጠሮ የተሰጠበት ኢሜል...”
“ዋናው ነገር ቀጠሮ የተሰጠህ ማእቀቡ ከመጣሉ በፊት ነው ወይስ ከተጣለ በኋላ?”
“ኸረ... በፊት ነው፡፡;
“እንግዲያው የአንተ ጉዳይ ገና ነው…”
“አቅርብ ያላችሁኝን ሁሉንም ማስረጃዎች አያይዣለሁ እኮ!”
“ስለ እነሱ አይነት ማስረጃዎች አይደለም…ስለ ማእቀቡ ምን አስተያየት እንደሰጠህ በሚገባ መጣራት አለበት፡፡”
“ኸረ እኔ ምንም አስተያየት ሰጥቼ አላውቅም…”
“እሱን ገና አጣርተን የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የዛሬ አስራ አምስት ቀን ተመለስ፡፡”
ከአስራ አምስት ቀን በኋላ፡-
“ይኸው ባላችሁኝ መሰረት መጥቻለሁ፡፡”
“ያንተ ጉዳይ አስቸጋሪ ነው፡፡”
“ምን ጥፋት አገኛችሁብኝ?”
“በማእቀቡ ላይ ያለህ አቋም የአሜሪካን ጥቅም የሚጸረር ነው፡፡ እንዲህ በአደባባይ  እየተቃወምከን ቪዛ እንድንሰጥህ ትፈልጋለህ?!”
“ተሳስታችኋል፣ እኔ አይደለም በአደባባይ መናገር ቀርቶ ለሚስቴ እንኳን አንዲት ነገር ትንፍሽ ብዬ አላውቅም!”
“እዚህ አዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ሲደረግ፣ የፌስቡክ ፕሮፋይል ፒክቸርህን ወደ ኢትዮጵያ ባንዲራ የለወጥከውን አናውቅ መሰለህ?”
“ታዲያ እሱ ከዚህ ጋር ምን ግንኙነት አለው?”
“ካልጠፋ ቀን ያን እለት ፕሮፋይል ፒክቸርህን፣ ያውም በድሮው ባንዲራ የለወጥከው ምን እንደሆነ የማይገባን መሰለህ? ይሄን ያህል ሞኝ አደረግኸን እንዴ?”
“ለምንድነው እያላችሁኝ ነው!”
“በተዘዋዋሪ ለተቃዋሚዎች ድጋፍህን እየገለጽክ ነዋ!”
“ኸረ እኔ ፕሮፋይል ፒክቸሬን በየወሩ ነው የምለዋውጠው!”
“በአንተ ቤት ብልጥ መሆንህ ነው። በየወሩ ከሆነ ይሄኛውን ለምንድነው በሀያ ዘጠነኛው ቀን የለወጥከው? እናንተ ኢትዮጵያውያን እኮ ቅኔያችሁን ትንሽ ትንሽ እናውቃታለን፡፡”
“ኸረ እኔ ተቃውሞ ለሚባል ነገር አለርጂክ ነኝ…ባለቤቴ  ሳምንቱን ሙሉ ቀንም፣ ማታም ሹሮ ስታበላኝ እንኳን ለአንዲት ደቂቃ ተቃውሜ አላውቅም፡፡”
“ጨርሰናል፤ ውሳኔው ለአሜሪካ ያለህ አመለካከት እየታየ ሊራዘምም፣ በዛው ሊበቃም የሚችል ሆኖ፣ እስከዛው ድረስ ግን ለአምስት ዓመት አሜሪካ እንዳትገባ ታግደሀል!”
እናማ... ይሄ ይመጣል ተብሎ ነው እንዴ ጭጭ፣ ምጭጩ! “ይፍለጣችሁ!” በሉ አልተባለ፣ “ይቁረጣችሁ!” በሉ አልተባለ... ለምንድነው ጮክ ብለው እንኳን  ’በውስጥ ጉዳያችን አትግቡብን!‘ ማለት የተሳናቸው!…ቢያንስ፣ ቢያንስ የፖለቲካ ሽመል በማያማዝዘን በግድቡ ጉዳይ “ግድቡ የእኔ ነው!” ማለት ለምነ ተሳናቸው! ቪዛ ነዋ! ልጄ ተነቃቅተናል፣ “ቪዛ እንከለከላለን” ነው። “ብላክ ሊስት ውስጥ እንገባለን፣” ነው፤ እናማ...ምን መሰላችሁ፣ የሀገራችን ቦተሊካ እንዲህ ነች.... “እሞትልሃለሁ! እፈለጥሀለሁ!” ሲባል ተከርሞ የቁርጡ ቀን ሲመጣ፣ ህዝቤን በአደባባይ  አስጥቶ ጭጭ፣ ምጭጭ!
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው  የለ.... እንዲህ አይነት ቀሺም ‘ቦተሊካ’ ሲገጥማችሁ፣ እነኛ ኢምፔሪያሊዝምን ያስጠነቀቁት አርሶ አደሮች አይናፍቋችሁም! ልክ ነዋ....ኢምፔሪያሊዝም ማንም ይሁን ምንም፣ ለእነሱ ዋናው ነገር፣ በሀገራቸው ላይ ለመጣ፣ ተገቢውን መልዕክት ማስተላለፍ ነው!
“እንከባበር ብለን ነው እንጂ አሜሪካ ያሉትን ኢትየጵያውያን ማስታጠቅ ይቻላል…” የምትለዋ እኮ ለየት ባለ መልኩ ከተሜዎች፣ ኢምፔሪያሊዝምን ማስጠነቀቅ እንደሚችሉ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
እና ምን ለማለት ነው? በተመቸን መንገድ ‘ኢምፔሪያሊዝምን ማስጠንቀቅ’ መብታችን ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2091 times