Saturday, 05 June 2021 12:37

ፕ/ር መረራ ጉዲና - በአሜሪካ ማዕቀብ፣ በትግራይ ቀውስ፣ በሽብርተኝነት ፍረጃ፣ በዲፕሎማሲ ተግዳሮቶች--- ዙሪያ ምን ይላሉ?.

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

     *"የብሔራዊ አንድነት መንግስት" እንዲቋቋም ጠይቀን ነበር
           *ከረጂዎች ጋር የማይሆን ጠብ ውስጥ መግባት ጥቅሙ አይገባኝም
           *ድርድር የሚደረገው ከወዳጅ ጋር ሳይሆን ከጠላት ጋር ነው
           *የምዕራባውያን "የተደራደሩ ጥያቄ" ትክከልና ተገቢ ነው

          የህወኃት ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ጥቃት ተከትሎ፣ ከተወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ፣ በትግራይ ክልል የተከሰተው  ሰብአዊ ቀውስ አገራችንን  ለምዕራባውያን የዲፕሎማሲ ጫናዎች ዳርጓታል፡፡ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ መጣሉን ይፋ አድርጓል፡፡ በትግራይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ ወደ ድርድር ካልተገባ፣ ተጨማሪ ማዕቀቦች ሊጥል እንደሚችልም አስጠንቅቋል፡፡ እነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በአንጋፋው ፖለቲከኛና የኦህዴድ ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና ግምገማ እንዴት ይታያሉ? የችግሮቹ መንስኤና መፍትሄ ምንድን ነው ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማሁ አንበሴ በሳምንቱ መጨረሻ ፕሮፌሰር መረራን አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

                   ወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካን  እንዴት ይገልጹታል?
አሁን ያለንበት ሁኔታ ፖለቲካዊ ችግሮች የጎሉበት ነው፤ መፍትሔውም ፖለቲካዊ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለ50 ዓመታት ንጉሱም የሄዱበት መንገድ አላዋጣም፤ ደርግም ለ17 ዓመታት የሄደበት መንገድ አላዋጣም፤ ኢህአዴግም ለ27 ዓመታት የሄደበት መንገድ አላዋጣም፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ችግሮችን በጠመንጃ የመፍታት አማራጭ ነበር የተወሰደው፡፡ ይሄ የሃገሪቱን ፖለቲካ ይበልጥ ከማወሳሰብ ባለፈ መፍትሄ አልመጣም፡፡ አሁንም ቢሆን ልዩነቶችን በጠመንጃ ለመፍታት የመሞከር አካሄድ ነው የታየው፡፡ ይሄ የማታ ማታ ግን ነገሮችን በድርድር ወደ መፍታት ነው የሚሄደው። አሁን ይመስለናል እንጂ ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኋላ በመጨረሻ የሚቀርበው ብቸኛ አማራጭ ድርድር ነው፡፡ ሌላ ሰላም የሚመጣበት አማራጭ በአለም ላይ የለም። ወታደራዊ ፍጥጫዎች  ሁሉ መቋጫቸው ድርድር ነው፡፡ አሜሪካኖች ያንን ሁሉ መሳሪያ ይዘው ከ30 ምናምን ዓመት በኋላ በአፍጋኒስታን ወደ ድርድርና ትብብር ነው የመጡት፡፡
ዓለማቀፍ ጫናዎችን ያስከተለውን የትግራይ  ሁኔታ እንዴት ይረዱታል?
ብዙ ሰው  በትግራይ ያለውን ሁኔታ በስሜት ብቻ ነው የሚረዳው፡፡ ትልቁ ችግርም በስሜት ብቻ መነዳቱ ነው፡፡ ለዚህ ነው ፖለቲካችን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እየሆነ የቀጠለው፡፡ ፈረንጆች “የተቀባባ ለውጥ” የሚሉት አይነት ነገር ነው የገጠመን፡፡ በንጉሱም ዘመን ተቃውሞ ሲበዛባቸው “ህገ መንግስት” የሚል መቀባባት ነው ያመጡት። ደርግም “ከወንበዴዎች ጋር ድርድር የለም” ብሎ ከስምምነት ጫፍ የደረሱ ድርድሮችንና መልካም አጋጣሚዎችን በሙሉ ወደ ኋላ ነው የመለሰው፡፡ ኢህአዴግም ለ27 ዓመታት፣ “ማን ከማን ጋር ተጣልቶ ነው ብሔራዊ እርቅ የምትሉት” እያለ በሃገሪቱ እውነተኛ ለውጥ ማምጣት የሚችልበትን ዕድል አበላሽቷል፡፡ አሁንም በዚያው መስመር ላይ ነው ያለነው፡፡ ከስሜት ወጥቶ የጋራ ሃገራችንን እንዴት እናስተካክል ካልተባለ፣ ባለ ጊዜው ወይም ጉልበት ያለው እየመጣ ይፈራረቅብናል ማለት ነው፡፡ ከዚሁ አዙሪት መውጣቱ ነበር የሚጠቅመው፡፡
አሁን ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ለእርቅ አስቸጋሪ ወደ ሆነ  ደረጃ እየተሸጋገረ ያለ ይመስላል፡፡ እኛ “ጦርነቱ አያዋጣም ይቁም” ስንል ካድሬዎችና  እነ ግፋ በለው፣ ብዙ ነው የተንጫጩብን፡፡ ጭራሽ እኛ ለህወኃት የተለየ ፍቅር ያለን አድርገው ፖለቲካ ሊሰሩብንም ሞክረው ነበር፡፡ ችግሩም እንደፈራነው ከሃገር ሽማግሌና ምሁር አልፎ፣ ይኸው ወደ ፈረንጆች ሄዷል። ፈረንጆቹም እያቃታቸው ይመስላል፡፡ ግፋ በለውም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይሄ እንዴት የጋራ ራዕይ ያላት ሃገር  ለማቆም ያስችላል የሚለውን እያደር የምናየው ይሆናል። ወደ መነጋገርና ሰጥቶ መቀብል ፖለቲካ  ካልገባን፣ አሁንም ጉዳዩ የጉልበተኞችና ጊዜ ያገኙ ሃይሎች መፈንጫ ነው የሚሆነው። ፖለቲካውን የሁላችንም ካላደረግነውና ህዝብ የራሱን ምርጫ በነፃነት እንዲመርጥ ዕድሉን ካላመቻቸን፣ እዚያው አዙሪት ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡  የትግራይ ምርጫም ሆነ አሁን ያለው የብልጽግና ምርጫ ምኑም ባይጥመኝም፣ የህዝቡን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ምርጫ ማድረጉ የተሻለ ነው። አሁን ትግራይ ላይ ፖለቲካው ተለውጦ ወጣቱ ነው ታጥቆ ወደ ጫካ እየገባ ያለው፡፡ ይህ እንግዲህ ጉዳዩ ከህወኃት ውጪ እየሰፋ መሆኑ ነው የሚያመላክተው፡፡
በእርስዎ አመለካከት፤የዚህ ሁሉ ቀውስ መነሻ ምንድን ነው? ዋነኛ ተጠያቂውስ ማን ነው?
ለኔ ትልቁ ችግር የሚመስለኝ ለመንግስት ያቀረብነው ጥሪ ተቀባይነት ማጣቱ ነው። እኛ  “የብሔራዊ አንድነት መንግስት ይቋቋም” ጥሪ እና “የመንግስት ተቋማት በተቻለ መጠን ሪፎርም ይደረጉ”፣ “በጋራ ፍኖተ ካርታ ሃገሪቷንና ህዝቦቿን ለነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እናዘጋጅ” የሚል ሃሳብ ለመንግስት አቅርበን ነበር፡፡ ነገር ግን ይሔ ያልተዋጠላቸው ሃይሎች፣ ከጠ/ሚኒስትሩ አቋሞች ጋር  ነው  የገፉበት። ገዢው ፓርቲ ያሻግረናል ብለው አመኑ። ይሄ ነው የመጀመሪያው የስህተት መነሻ፡፡ ቀጥሎ እኔም የተሳተፍኩበት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ምርጫ ጉዳይ ነው። ጠ/ሚኒስትሩ የስምንት ሰዎችን ዝርዝር ሰጥተውን “ማን የተሻለ ነው ምረጡ?" አሉን፡፡ "ወ/ት ብርቱካን የምናውቃት ጠንካራ ታጋይ ናት" በማለት ነው፣ ማንም ሳይቃወም የተለያየነው፡፡ እኔ በወቅቱ “አድረን ሃሳብ ይዘን እንምጣ” ብዬ ነበር፤ ግን ጠ/ሚኒስትሩ ፍቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ወዲያው ለፀሃፊዋ “በዚሁ የቦርድ ሰብሳቢ ምርጫ ላይ እኔ ቅሬታና ተአቅቦ እንዳለኝ ፃፊልኝ” ብዬ ነበር፡፡ ያው የፈራሁት  ሆኖ አሁን "ምርጫ ቦርድ ለቅርጫ እንኳ የማይበቃ ምርጫ ነው" ለማዘጋጀት እየሰራ ያለው፡፡ ስለዚህ ነገሩ የተበላሸው በእነዚህ ሁኔታዎች ነው፡፡ በወቅቱ እኔ፣ አሁን ወዳለንበት ሁኔታ ልንመጣ እንደምንችል ገምቻለሁ። በሂደቱ ለውጡን አምጥቻለሁ የሚለው እና ተገቢውን እውቅና የሚፈልገው ቡድን እንዳለ ነው የተገፋው፡፡ ለጠ/ሚኒስትሩ በአንድ ስብሰባ ላይ በቀጥታ ያነሳሁላቸው ጉዳይ የእነዚህ አካላት መገፋት ሊያመጣ የሚችለውን ችግር  ነበር፡፡ ነገሩ ያው እዚህ ሃገር ብዙ አማካሪ ይበዛል፤ እነዚህ አጉል መካሪዎች ደግሞ በአብዛኛው የግፋ በለው እሳቤ ያላቸው ናቸው፡፡ በእነዚህ አጉል መካሪዎች ብዙ ነገር የተበላሸ ይመስለኛል።  ዋናው ጉዳይ ግን የጋራ ፍኖተ ካርታ  ሳንይዝ፣ የአንድ ፓርቲ ወይም ቡድን ሃሳብ፣ ኢትዮጵያን ያሻግራል ተብሎ የተገፋበት መንገድ ስህተት ነበር፡፡ ለዚህ ሁሉ ጣጣ ያበቃን እሱ ነው፡፡
የ”ህወኃት” እና “ኦነግ ሸኔ” በሽብርተኛነት መፈረጅ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ምን እንደምታ ይኖረዋል ይላሉ?
ገዢው ፓርቲ ጠላቶቼ ናቸው የሚላቸውን አካላት ለመቆጣጠር ፍረጃው ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ሊመቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ  ችግር ፍረጃው ፈፅሞ አይፈታውም። እኔም እኮ ሽብርተኞችን ትደግፋለህ፤ አብረህ ታይተኻል ተብዬ ታስሬያለሁ፡፡ በኢህአዴግ ጊዜ የታሰርኩት  ከፕ/ር ብርሀኑ ነጋ ታይተሃል ተብዬ ነው፡፡ በወቅቱ እኔ ከኦኤም ኤን ጃዋር መሃመድና ፕ/ር ብርሃኑ  ጋር ተከስሼ ብቻዬን ነበር ፍ/ቤት ስመላለስ የነበረው፡፡ ያ ክስና ውንጀላ በፖለቲካ አቋሜ ላይ ያመጡት ነገር የለም፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ያሉ እርምጃዎች ተቃዋሚን ፀጥ ለማሰኘት የተሻለ መሳሪያ ይሆናል ተብሎ ከታሰበ ስህተት ነው፡፡ በኔ በኩል አሁን መሬት ላይ ያሉ ችግሮችን ይፈታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የአፄው ጊዜ “የሃገር ከሃዲ” እያለ ፖለቲከኞችን በአደባባይ ይቀጣ ነበር፡፡ ደርግም “ገንጣይ አስገንጣይ” እያለ ይቀጣ ነበር፡፡  ኢህአዴግም እንደዚያው “ሽብር አሸባሪ” እያለ ብዙ ነገር አድርጓል፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ገንጣይ አስገንጣይም ሲባሉ የነበሩት ብዙ ነገሮች አልፈው ለስልጣን በቅተዋል፣ ሽብተርተኛ የተባሉትም ዛሬ የፖለቲካዊ ዋና ተዋናይ እየሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለው ፍረጃ ለኔ ብዙም ለፖለቲካዊ ችግሮቹ መውጫ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ለትግራይ ጉዳይ እርስዎ የሚታይዎት መፍትሔ ምንድን ነው?
አንደኛ የትግራይ ጉዳይ ከጅምሩ የተያዘበት አግባብ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ህወኃትና ህዝቡ አንድ አይደለም የሚለው አረዳድ ችግር ያለበት ይመስለኛል፡፡ እኛ ከአረና ጋር ስለምንሰራ ጉዳዩን በቅርበት እናውቀዋለን፡፡ አሁን በርካታ ወጣቶች ወደ ጫካ የሚሄዱበት ሁኔታ እየሰፋ  መምጣቱንና ጦርነቱም ወደ ህዝብ ደረጃ መለወጡን ነው እየሰማን ያለነው፡፡ መሪዎቹን እንፈልጋለን ቢባልም በጦርነቱ አጋጣሚ ተፈጽሟል የሚባሉ ነገሮች የሚሰጣቸው ምላሾች ወጣቱን ወዳልተገባ አቅጣጫ እንደወሰደው ነው መረጃው ያለን፡፡
ለኔ የተሻለው አማራጭ ፖለቲካዊ መፍትሔ ላይ ማተኮር ነው፡፡ የጦርነት አማራጭ አሁንም ውጤታማ አይሆንም፡፡ ሁሉም ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ሃይሎች መንግስትም ጭምር ቁጭ ብለው እንዴት ይሄን ችግር እንፍታው ብለው መነጋገሩ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አሁን ባለው የአንድ ወገን የሃይል መፍትሄ ውጤት የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡ መደራደርን መፍራት አያስፈልግም፡፡ ከጠላት ጋር ምንም ድርድር የለም ሲባል እሰማለሁ። ድርድር የሚደረገው ታዲያ ከማን ጋር ነው? ከወዳጅ ጋር መቼም አይሆንም፡፡ ከወዳጅ ጋር የሚሆነው መስማማት መተባበር ነው፡፡ ድርድር የሚደረገው  እኮ ከጠላት ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ጦርነቱን አቁሞ ምን እናድርግ የሚለውን የአካባቢውን የሃገር  ሽማግሌዎችና ምሁራን አቀራርቦ ማደራደር ነው፡፡ ወሳኙ የሚነደውን እሳት ማቆም ነው። ይሄ ለዓለም ፖለቲካ አዲስ አይደለም። ታሊባን እና አሜሪካ እኮ ብዙ ደረጃ ከተደራረሱ በኋላ አቁመዋል። ፍልስጤምና እስራኤል የተሻለው ተኩስ ማቆም ስለሆነ ያንን አድርገዋል፡፡ ታዲያ በእኛስ ሁኔታ የሚሻለውን መምረጥ ለምን ሃጢያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እንደውም እኮ የፅድቅ ስራ ነው የሚሆነው።
የአሜሪካ ማዕቀብን በተመለከተ እርስዎ ምን ይላሉ?
ይሄ ጉዳይ ለኔ በጣም ይገርመኛል። የአሜሪካ መንግስት ምን አድርጉ ነው ያለው? “ተኩስ አቁሙና ተመካከሩ፤ አትተላለቁ”  ነው ጥያቄው፡፡ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ፈልጉ ነው መልዕክቱ፡፡ አሜሪካ ይሄን ስትል “ቅኝ ግዛት ልታመጣብን ነው፤ ሉአላዊነት ተደፈረ” ሲባል  ስሰማ  በጣም ይገርመኛል፡፡ ነገሩ አስተያየት  ለመስጠትም  በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙዎች የሚጮሁት ደግሞ በአሜሪካ ክክ የሚኖሩ ናቸው፡፡ 20 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ በእርዳታ ይኖራል እየተባለ ይሄን ህዝብ ይዞ ከፍረጃዎች ጋር የማይሆን ፀብ ውስጥ መግባት ምን እንደሚጠቅም  አይገባኝም፡፡ ነገሩን አጣሞ ለመረዳት መሞከሩም ይገርመኛል፡፡
በአገራችን በኩል ያለው ዲፕሎማሲ በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት?
እንደምናውቀው ዲፕሎማሲ ትልቅ አቅም መፍጠሪያ ነው፡፡ በኛ ሃገር ደግሞ ዲፕሎማሲ ማለት በፖለቲካ ታማኝነት የተመረጡ ሰዎች እንዲዝናኑ ተብሎ የሚመደብላቸው የመዝናኛ ቦታቸው ነው። እውቀት ላይ የተመሰረተ በሃገር ፍቅር መመዘኛ ምደባ አይደረግም፡፡ እዚህ አዲስ አበባ የማይፈለጉ ሰዎች የሚደበቁበት ቦታ ነው፡፡ አሁንም እኮ ከኢህአዴግ ጋር የሚሰሩና ወዳጅ የሆኑ ግለሰቦች  በዲፕሎማትነት ተመድበዋል፤ ለማን እንደሚሰሩ አላውቅም። ዲፕሎማሲው በእውቀት ላይ የተመሰረተ አለመሆንና በፖለቲካ ታማኝነት ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑ በእጅጉ እየጎዳን እንደሆነ እያየነው ነው፡፡ በመንግስቱ ሃይለ ማሪያም ዘመን “የኢምፔሪያሊዝምን  ደም አፈሳለሁ” እያለ አብዮት አደባባይ በጠርሙስ የተሞላ ቀይ ነገር ያፈስ ነበር፡፡ አሜሪካኖቹ ያንን ቂም ይዘው በመጨረሻ ላይ የደርግን ውድቀት አፋጥነውታል፡፡ እነዚህ ነገሮችን ምንም ያህል ብንጠላ መጠንቀቅ አለብን፡፡  በአሜሪካን ሃገር አንደኛ ወንጀል ባንዲራቸውን ማቃጠል ነው፡፡ በእነዚህ በማይታገሷቸው ነገሮች ለመምጣት መሞከር ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ሁኔታውን በሰከነ አዕምሮ የተያዘ አይመስለኝም፡፡ ነገሩ እርጋታ ያስፈልገዋል፡፡  ሁኔታውን በትክክለኛው ትርጉሙ ተረድቶ ማድረግ የሚገባውን ማድረጉ ነው የሚሻለው፡፡




Read 4348 times