Saturday, 29 May 2021 14:17

“የረር ሆምስ” የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   “ሮሃ” አፓርትመንት በ170 ሚ. ብር ሲጠናቀቅ የረር ሆምስ በግማሽ ቢ. ብር እየተገነባ ነው
                       
             በሁለት ዓመታት ውስጥ 300 ያህል ቤት ፈላጊዎችን የቤት ባለቤት ያደርጋል የተባለውና በሆሴዕ ሪል እስቴት የሚገነባው “የረር ሆምስ” የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
ባለፈው አርብ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም  በሮሃ አፓርትመንት  በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤  “አዲስ ፕሮፐርቲ ማርኬቲንግ ግሩፕ” የተሰኘውና የሪል ስቴት አልሚዎችን አደራጅቶ የሚሰራው ድርጅት፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሚሊዮኖችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል። ማርኬቲንግ ግሩፑ በሪል እስቴት ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ ዘርፉን በማዘመንና በማሳደግ በኢትዮጵያ  በተለይም በአዲስ አበባ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ አልሞ እንደሚንቀሳቀስ የማርኬቲንግ ግሩፑ ማኔጅንግ ፓርትነር አቶ ሚካኤል ተካ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው አርብ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በሸራተን ሆቴል በተካሄደ ስነ-ስርዓት  ከአክሱም ሆቴል ጀርባ የተገነባውን ባለ ሰባት ፎቅ “ሮሃ አፓርትመንትን” አጠናቅቆ ለገዢዎቹ አስረክቧል።
በኩባንያው በዚሁ ዕለት ይፋ የተደረገውና በሆሴዕ ሪል ስቴት የተጀመረው “የረር ሆምስ” የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሃያት 49 ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ በ23 ሺህ ስኩየር ካ.ሜ ላይ የሚገነባና 300 ቤት ፈላጊዎችን የቤት ባለቤት የሚያደርግ  ሲሆን በ8 ወራት ብቻ 55 በመቶው የቤቱ ግንባታ መጠናቀቁም ተገልጿል። የነዋሪዎቹን የመክፈል አቅም ያገናዘበና ከመንግስት የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ ጋር ተቀራራቢ በሆነ ዋጋ ለቤት ፈላጊዎች የቀረቡት እነዚህ ቤቶች፤ ከ2.3 ሚሊዮን ብር ጀምሮ የሚሸጡ ሲሆን የአከፋፈል ሁኔታውም ቤት ፈላጊዎች የዋጋውን 15 በመቶ በቅድሚያ በመክፈል ቀሪውን እንደየቤቱ የግንባታ ሂደት ከአልሚው ከማርኬቲንግ ግሩፑና ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር በመግባባት አመቺ በሆነ መልኩ  መክፈል እንደሚቻል የኩባንያው ሃላፊዎች ገልጸዋል። እስካሁንም ለእነዚህ 300 ቤቶች ገዢዎች እየመጡ መሆኑን ገልፀው፤ በቀጣይ በከተማዋ ያለውን የቤት ችግር ለመቅረፍ በርካታ እቅዶችና እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩም ሃላፊዎቹ ጠቁመዋል።
ሆሴዕ ሪል እስቴት ሮሃ አፓርትመንትን ለመገንባት 170 ሚ. ብር በጀት እንደፈጀ የገለጹት ሃላፊዎቹ፣ የረር ሆምስ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታም በ500 ሚ. (ግማሽ ቢ.) ብር በጀት ግንባታው እየተፋጠነ ስለመሆኑ ተገልጿል። ቤቶቹ በአፓርትመንትና በቪላ መልኩ እየተገነቡ ሲሆን ቤት ፈላጊው እንደየምርጫውና አቅሙ የመረጠውን ቤት መግዛት ይችላል ያሉት ሀላፊዎቹ፣ በመኖሪያ መንደሩ የመናፈሻ ቦታ፣ የልጆች መጫዎቻ፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ሌሎችም መሰረት ልማቶች ተሟልተውለት ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡


Read 2380 times