Tuesday, 01 June 2021 00:00

ኮሮና 9 አዳዲስ ቢሊየነሮችን ፈጥሯል፤ 115 ሺህ የጤና ባለሙያዎችን ገድሏል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ  የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ከ115 ሺህ ማለፉ የተነገረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ወረርሽኙ ለ9 አዳዲስ ቢሊየነሮች መፈጠር ምክንያት መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ፒፕልስ ቫክሲን አሊያንስ የተባለው ጥምረት በበኩሉ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በክትባት ምርት ዘርፍ ለተሰማሩ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መልካም አጋጣሚ መሆኑንና፣ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በዘርፉ የተሰማሩ 9 ሰዎች ወደ ቢሊየነርነት መቀየራቸውን አስታውቋል፡፡
ግለሰቦቹ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት የቻሉት የኮሮና ክትባቶችን በብቸኝነት የማምረት መብት ባለቤት የሆኑ ኩባንያዎቻቸው በስፋት ምርታቸውን መሸጥ በመቻላቸው ነው ያለው ጥምረቱ፣ ዘጠኙ ቢሊየነሮች በድምሩ 19.3 ቢሊዮን ዶላር ያህል ሃብት ማፍራታቸውንና ይህ ገንዘብ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አገራትን ዜጎች ሙሉ ለሙሉ ለመከተብ የሚያስችል መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡
ከዘጠኙ ቢሊየነሮች አመካከል ከፍተኛ ገቢ በማግኘት በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሞዴርና የተባለው ክትባት አምራች ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑትና የተጣራ ሃብታቸው 4.3 ቢሊዮን ዶላር የደረሰው ስቴፋኒ ባንሴል ሲሆኑ፣ የባዮንቴክ ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ኡጉር ሳሂን በ4 ቢሊዮን ዶላር፣ ተመራማሪውና ከሞዴርና መስራቾች አንዱ የሆኑት ቲሞቲ ሰፕሪንገር በ2.2 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
የሞዴርና ሊቀ መንበር ኑባር አፊያን በ1.9 ቢሊዮን ዶላር፣ የሮቪ ኩባንያ ሊቀ መንበር ጁኣን ሎፔዝ ቤልሞንቴ በ1.8 ቢሊዮን ዶላር፣ ሳይንቲስትና የሞዴርና መስራች የሆኑት ሮበርት ላንገር በ1.6 ቢሊዮን ዶላር፣ የካንሲኖ ባዮሎጂክስ ኩባንያ መስራች የሆኑት ዙ ታኦ በ1.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የካንሲኖ መስራችና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ዢኡ ዶንግዡ በ1.2 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የኩባንያው የቀድሞ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ማኦ ሁኢሁኣ በ1 ቢሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ ዘጠነኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውም ተነግሯል፡፡
በሌላ ተያያዥ ዜና ደግሞ፣ ቫይረሱ ወረርሽኙን ለመከላከልና የወገኖችን ህይወት ለመታደግ ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ ከ115 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችን ለሞት መዳረጉን ከሰሞኑ ያስታወቀው የአለም የጤና ድርጅት፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎችም በቫይረሱ ተይዘው እንደሚገኙ መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

Read 7265 times