Print this page
Sunday, 30 May 2021 00:00

“ግብፅን የፈጠሯትና ያሰለጠኗት ኢትዮጵያውያን ናቸው”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   የስነ ፅሁፍና ቋንቋዎች ፕሮፌሰር የሆኑትና በታሪክ ምርምሮችና ጥናቶች ላይም የሚሳተፉት ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ ከዚህ ቀደም "የኦሮሞና አማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ" እንዲሁም "ስውሩና ያልተነገረው የአይሁዳውያንና የኢትዮጵያውያን ታሪክ" የተሰኙ ታሪክ ላይ ያተኮረ መፃህፍትን በአማርኛ ቋንቋ ለአንባቢያን ያቀረቡ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ “ኢትዮጵያ ግብፅን እንደፈጠረቻት እና እንዳሰለጠነቻት” የተሰኘ የታሪክ መጽሐፍ ለአንባቢያን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ናቸው። ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ይህን የታሪክ መፅሐፍ ለማዘጋጀት የታሪክ አባት ተብሎ -ከሚታወቀው ግሪካዊው ሄሮዱተስ እስከ አውሮፓ ታሪክ አጥኚዎች ከትበው ያቆዩዋቸውን የታሪክ ሰነዶች መመርመራቸውንና ማመሳከራቸውን  ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን ጊዜያቸውን በኢትዮጵያ በማሳለፍ በታሪክ ላይ ምርምርና ጥናት እያደረጉ የሚገኙት ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ ከቀናት በኋላ ለአንባቢያን በሚቀርበው መፅሐፋቸው ጭብጥ ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-


           በቅርቡ የሚወጣው መፅሐፍዎ በምን ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው?
ርዕሱ “ኢትዮጵያ ግብፅን እንደፈጠረቻትና እንዳሰለጠነቻት” የሚል ነው። እንግዲህ  እንዲህ ብሎ ደፍሮ ለመፃፍ ማስረጃ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ በቂ ማስረጃ አለኝ። ኢትዮጵያ እንዴት ግብፅን ፈጠረቻት? እንዴት አሰለጠነቻት? ለሚለው ሁሉ ከእነ ማስረጃው የቀረበበት ሰፊ ጥናት የተደረገበት መፅሐፍ ነው።
እስኪ የመጽሐፉን ጭብጥ በጥቂቱ ያብራሩልን?
ግብፅ መጀመሪያ ዝም ብሎ የአባይ ወንዝ የሚፈስበት ረግረግ ቦይ መሬት ነበር። ከ7 ሺህ አመት በፊት ማለት ነው። ያኔ ኢትዮጵያኖች፣ ከኢትዮጵያ ወደ ቦታው ሄደው፣ ቦታውን ሰልለው አይተው ቆረቆሯት። በወቅቱ የኢትዮጵያ ነገስታት ሁለት ሃላፊነትና ማዕረግ ነበራቸው። አንድም ንጉስ ናቸው፤ በሌላ በኩል ካህናት ናቸው። ካህንም ንጉስም ሆነው መለኮታዊና ዓለማዊ ማዕረግ ነበር፣ የኢትዮጵያ ነገስታት የነበራቸው። ህዝቡን በንግስናቸው ያስተዳድራሉ፤ ለህዝቡና ለሃገራቸው በፀሎት ፈጣሪን ይማለዳሉ። ከእግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ነበራቸው፤ የወቅቱ ነገስታት። እነዚህ ነገስታት ወደ ረግረጋማው ምድር ግብፅ ወረዱ፤ ቦታውን አለሙት፣ ፒራሚድ ገነቡ፤ መድሃኒት አገኙ፤ ፍልስፍናውን ፈለሰፉ፤ ከግሪክና ከጣሊያን እየመጡ የእነሱን ፍልስፍና ይማሩ ነበር። እነ አርስቶትል ፕሌቶ የሚባሉት ፈላስፎች በሙሉ ግብፅ ውስጥ ነው የተማሩት። በመፅሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ፣ እነዚህ ከማስረጃዎች ጋር ይብራሩበታል።
ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ምዕራባውያን አሁን ድረስ የሚከራከሩበት የፍልስፍና ምንጭ ግሪክ ነች የሚለውን በማስረጃ የሚሞግት ነው። የኛ ፈላስፎች ለግሪኮችና ለጣሊያኖች እንዳስተማሯቸው የሚተነትን ነው። ራሳቸው ፈላስፎቹ #ግብፅ ሄደን ተማርን; ያሉትን ማስረጃ ጭምር ነው የማቀርበው። የአውሮፓውያን መሰረታዊ ስልጣኔ ከግሪክና ከጣሊያን ሳይሆን ግብፅን ከፈጠሯት ኢትዮጵያውያን እንደተቀዳ መጽሐፉ ያብራራል። ማስረጃም በሰፊው ያቀርባል። እስከ ዛሬ ግሪክና ጣሊያን የሚጠቀሱት ውሸት እንደሆነ የሚያስረዳ ነው። የታሪክ አባት የሚባለው ሄሮዱተስ የዛሬ 2450 አመት ግብፅ ሄዶ ማናችሁ? ከየት ናችሁ? ሲል "ኢትዮጵያውያን ነን እኛ፤ ማስረጃ ከፈለግህ ፒራሚዱም የኛ ነው። ተጨማሪ ከፈለክ የ330 ንጉሶች ስም ዝርዝር ይሄውልህ" ብለው ሰጥተውታል። እሱም ያንን መሰረት አድርጎ ስለ ኢትዮጵያውያ ግብፅን መፍጠርና ማስተዳደር ጽፏል። እኔም እሱን ነው ያጣቀስኩት። የፈጠራ ስራ አይደለም። አሁን ላይ እነሱ ዝቅ ብለው ስላሉ የትናንት አባቶቻችንም ዝቅ ያሉ የሚመስላቸው አሉ። ለእነሱ አስተማማኝ ማስረጃ ጭምር አቅርቤያለሁ።
ከሄሮዱተስ በኋላ የመጣው ዲዮዶሮስ የሚባለው የግሪኩ የታሪክ ፀሐፊ፣ "ፒራሚዱንም ሄሮግራፊውንም ኢትዮጵያውያን ናቸው የሰሩት" ብሎ የመሰከረው አለ። እሱንም አጣቅሻለሁ። ከዚያ በኋላም የአውሮፓ የታሪክ ተመራማሪዎችም ጭምር ግብፅን የፈጠርነው ኢትዮጵያውያን መሆናችንን፣ እንደውም ከግብፅ አልፈን እስከ ሳይቤሪያ ድረስ ከተማ እንደገነባን፣ እስከ ማያ ስልጣኔ ድረስ የኢትዮጵያ ስልጣኔ መሆኑን የሚመሰክሩ የታሪክ ማስረጃዎችን በሙሉ አግኝቼ በመፅሐፉ ውስጥ አካትቻለሁ።
በሌላኛው የመፅሐፉ ምዕራፍ ደግሞ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ተዋግታ ሁሌም እንደተሸነፈች መሆኑን በማስረጃ የሚብራራበት ነው። ኢትዮጵያውያን የማሸነፋቸውን ሚስጥር አውጥቻለሁ። ግብፅንና ሱዳንን የመሩ ኢትዮጵያውያን ሴት ነገስታትን ስም ዝርዝር አስቀምጫለሁ። ከእነዚህ ነገስታት ውስጥ አራቱ አማልክት ተብለው ይመለኩ እንደነበር፣ በሌላ በኩል አምላክ ተብለው የተመለኩ ወንድ ኢትዮጵያውያን ፈርኦኖችንም ጠቅሻለሁ። እነዚህ ነገስታት በግብፅ፣ ፐርሽያ፣ ኢራቅ፣ ሱዳን የተመለኩ ናቸው። በሌላኛው ምዕራፍ ደግሞ ግብፅን የገዙ የኢትዮጵያ ስርወ መንግስታትንም ከነማስረጃው አቅርቤያለሁ። የአፋር ስርወ መንግስት ግብፅን ከመቼ እስከ መቼ እንደገዛ ተዘርዝሯል። ለምሳሌ ነፈርቲቲ የተባለች የአፋር ንግስት ነበረች፡፡ ከዚያ ደግሞ የኦሮሞ ስርወ መንግስት ግብፅን የገዛበት ታሪክ አለ። 18ኛው ስርወ መንግስት የኦሮሞ ነበር። ለዚህ ስዕላዊ ማስረጃዎች ሁሉ አሉ። ከዚያ ደግሞ የአማራ ስርወ መንግስት የገዛበት ዘመን አለ። የአማራ ስርወ መንግስት አማርና የምትባል ከተማን በስሙ ቀይሮ ሰይሟል። ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜ የአማራ ንጉስ ነበር። ይሄ ንጉስ የጎጃም ሰው ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ 1800 ዓመት ቀደም ብለው አማርና የሚባል ከተማ በአማሮች ተከትሞ ነበር። ለማሪያም፣ ዮሴፍና ኢየሱስ ጥገኝነት የሰጧቸው ኢትዮጵያውያ ነገስታት ነበሩ። መፅሐፍ ቅዱስ ወደ ግብፅ ሄዱ ይላል እንጂ እነማን ተቀበላቸው የሚለውን አያብራራም፡፡ ነገር ግን ሌሎች የታሪክ ማስረጃዎች ኢትዮጵያዊው ንጉስ እንደተቀበላቸው ነው የሚጠቁሙት። በወቅቱ ጥበቃ ያደርግላቸው  የነበረውም የጎጃሙ ሰው የሆነው አማናቱ ተትናይ የሚባል ንጉስ ነበር። ሌላው በመፅሐፉ የሚገለፀው ልክ እንደ ግብፅ ሁሉ ኑባ የሚባል የኢትዮጵያ አራተኛ የልጅ ልጅ፣ ወደ አሁኗ ሱዳን ወርዶ፣ ኑቢያ እንዳሰኛትና ከተማዋንም መረዌ እንዳሰኛት በማስረጃ ቀርቧል። መረዌ የሚለው መርሃዊ ከሚል የግዕዝ ቃል የመጣ ነው። ሙሽራ ማለት ነው። መርዌ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነበር። በቅርብ ጊዜ እንኳ አፄ ቴዎድሮስም በሱዳን ካሉ ሃያላን ጋር በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ግንኙነት ነበራቸው። ምን ዓይነት ግንኙነት የሚለው በመፅሐፉ ተዘርዝሯል።
ኢየሱስ በህፃንነቱ የተቀበሉትና የሚያውቃቸው በመሆኑ በ22 ዓመት ተኩል እድሜው፣ ወደ መርዌ መጥቶ ለአንድ ሳምንት ክርስትናን አስተምሮ፣ ሱዳንን በሞላ የክርስቲያን ሃገር አድርጎ ነበር። ሱዳን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የክርስቲያን ሃገር ነበረች። ቱርኮች ናቸው ሙስሊም ያደረጓቸው። ነገር ግን በአፄ ፋሲልም በአፄ ቴዎድሮስም ዘመን፣ የሱዳን ገዥዎች በኢትዮጵያ ነገስታት ስር ነበሩ። ካርቱም የተባለችው ከተማም በአፄ ላሊበላ ዘመን፣ ክርስቲያኖች በግብፅ እየተጠቁ መሆኑን ሲያውቅ፣ የዛሬዋ ካርቱም ድረስ ወርዶ ነጭና ጥቁር አባይ የሚገናኙበት ላይ ውሃውን በከፍተኛ የድንጋይ ቴክኖሎጂ ጥበብ ወደ ሰሃራ በረሃ እንዲፈስ አደረገው። በወቅቱ ከግብፅ #እባክህ ማረን; ብለው ለምነው፣ ስጦታ ሰጥተው፣ ውሃው ተከፈተላቸው። በወቅቱ ውሃው “ተከረተመ” ስለተባለ ቦታው ካርቱም ተባለ- በሂደት። አሁን ቦታው ካርቱም ይባላል። በአጠቃላይ ዛሬ  የኢትዮጵያ ግዛት ይገባኛል የምትለው ሱዳን ምንም ያልነበረች ናት። እንግሊዞች መጥተው እስከያዟት ድረስ በኢትዮጵያ ስር የነበረች፣ የሰፊዋ ኢትዮጵያ ግዛት አካል ነች። በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ማለትም አፄ ቴዎድሮስ ከእነ ኢድሪስ መሃዲ ጋር በመተባበር ነፃ ለማውጣት ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። አሁን ሱዳን ቤንሻንጉል የኔ ነው የሚል ነገር ታነሳለች። በዚህ ሎጂክ ከተሄደ ሙሉ ሱዳንን የቆረቆርነው እኛ ስለሆንን፣ እኛም ሙሉ ሱዳንን የኛ ነች ማለት እንችላለን  ማለት ነው።
ቀጥሎ ባለው የመፅሐፉ ክፍል ደግሞ ከግብፅ የሚላኩ ጳጳሳት እንዴት ኢትዮጵያን እንዳቆረቆዟትና ለማጥፋት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር በማስረጃ ይተነትናል። በመፅሐፉ ሌላኛው ምዕራፍም፣ ለግብጻውያን የተፃፈ የደብዳቤ መልዕክት አለ። ደብዳቤው ምንድን ነው የሚለውን አንባቢያን መፅሐፉን ሲያገኙት ይረዱታል።
መፅሐፉን ያዘጋጁት በምን ዓላማና ግብ  ነው?
መፅሐፉን  ለመፃፍ ያነሳሳኝ ለኢትዮጵያ ያለኝ ቅንአት ነው። ለኢትዮጵያ በመቅናትና ግብፃውያን የሚያደርጉት ነገር የፈጠረብኝ ስሜት ነው ታሪኩን የበለጠ እንድመረምር የገፋፋኝ። ምክንያቱም እኛ ግብፅን መስርተን ገንብተን እዚህ አድርሰን ከኋላ የመጡ አረቦች፣ አውሮፓውያን፣ ቱርካውያን፣ ፈረንሳውያን፣ እንግሊዞች ተቀላቅለው የፈጠሩት ማህበረሰብ በዚህ መጠን በግብፅ ቆርቋሪዎች ላይ መነሳታቸው የፈጠረብኝ ስሜት ነው። እነዚህ ሰዎች የመጡት እኮ እኛ ግብፅን መስርተን አሰልጥነን ከጨረስን ከ4 ሺህ 5 መቶ ዓመት በኋላ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከኋላ የመጣ አይን አውጣ ሆነው፣ አባይን ለብቻቸው መጠቀማቸው አንሶ ፒራሚዱንም፣ ነገስታቱንም አስከሬናቸውንም፣ ቀለሙ የኢትዮጵያውያን መሆኑን እያሳያቸው፣ አረብ ለማድረግ መሞከራቸው አስቆጭቶኝ ነው። ፒራሚዱም ነገስታቱም የኛው መሆናቸው እውቅና መነፈጉ የፈጠረብኝ ቁጭት ነው መፅሐፉን ለማዘጋጀትና ታሪኩን ለመግለጥ የፈለግሁት። ፒራሚዱም ሁሉም የኛ ሆኖ ሳለ፣ ዛሬ በታሪክ እንኳ እውቅና ለመስጠት አለመፈለጋቸው ያሳዝናል። እንደውም እኛ በሰራነው ሃብታም እየሆኑ፣ እኛ የተፈጥሮ ሃብታችንን እንኳ እንዳንጠቀም ሴራ ሲሸርቡብን  ያሳዝናል። ቢችሉ አሁንም ከሚያገኙት ማካፈል አለባቸው፤ ይሄንን መብታችንንም በአለማቀፍ ፍ/ቤት መጠየቅ እንችላለን። በሌላ በኩል፤ ለዚህ መፅሐፍ መዘጋጀት ገፊ ምክንያቱ እኛ ታሪካችንን በአግባቡ አውቀን ለምን ሞጋቾች አንሆንም የሚል ነው። ግብፅ ሱዳን፣ ሊቢያ የጥንት የኛ ግዛቶች ነበሩ። ህዝቡም መልኩም የኛ ህዝብ ነበር። አሁን ያሉት ከየትም የመጡና በዘመናት ሂደት የተሰባሰቡ ናቸው እንጂ የእነዚህ አካባቢዎች ጥንታዊ ህዝቦች ኢትዮጵያውያን ነን። ግብፆቹም ይህን ታሪክ ማሰብ አይፈልጉም። ስለዚህ እንዲያስታውሱ ማስታወስ ያስፈልጋል። አጋዚያንም፣ አፋሮችም፣ ኦሮሞዎችም፣ አማሮችም ግብፅን የገዙት በኢትዮጵያዊነት፣ ኢትዮጵያ ብለው ነው። ስለዚህ እኛም ይህን ገናና ታሪካችንን ማወቅ አለብን። ዛሬ ግብፅን የያዙት ግብፃውያንም፣ ይህን ስረ መሰረታዊ ታሪክ ማወቅ አለባቸው። የሚንቁን አረቦች ታሪካችንን አውቀው፣ እንዲያከብሩን ነው ፍላጎቴ። ይሄን ለማድረግ መፅሐፉ በአረብኛ ተተርጎሞ፣ በአረቡ ዓለም እንዲሰራጭ ይደረጋል። ግብፅም ልኳን እንድታውቅ ነው ፍላጎቴ።
እርስዎ ይሄን ታሪክ ለመግለፅ ምን ያህል ቅቡልነት ያላቸው ሁነኛ ማስረጃዎች ተጠቅመዋል?
የኢትዮጵያን ገናና ታሪክና ክብርን በዛሬው ውድቀት በመለካት እውነት የማይመስላቸው አሉ። በራሱ መጠን የሚገምት ትውልድ አለ። ይሄ  ባለማወቅ የሆነ ነው። ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያን ስለሚጠላ የኢትዮጵያ ገናና ታሪክ እንዲወሳ አይፈልግም። ኢትዮጵያ ትንሽ ሃገር መስላ፣ ትንሽ ታሪክ ያላት መስላ እንድትታይ ነው የሚፈለገው። የመቶ ዓመት ታሪክ ብቻ እንደሆነ እንዲታሰብ ነው የሚፈለገው። ግብጾች ወይም ሌላው ጋ ብትሄድ ደግሞ የራሳቸው ያልሆነውንም የኛ ነው ብለው ገናና ታሪክ ለመፍጠር ይጥራሉ። እኛ በዚህ መፅሐፍ የምናወሳው የ7 ሺህ እና 6 ሺህ ዓመታት ታሪክ ነው። ስለዚህ ይሄን የረዥም ዘመን ታሪክ የማያውቅና ሁኔታዎችን በሙሉ በዛሬ ውድቀት የሚለካ ሰው፣ ነገርየው ተረት ነው ሊል ስለሚችል፣ በቀጥታ የታሪክ አባት የሚባሉት እነ ሄሮዱተስ የመሰከሩትን ነው ያጣቀስኩት።
በሰፊው የሄሮዱተስና የወቅቱ ባለታሪኮችን ምስክርነት ነው የጠቀስኩት። ቀጥሎም የጀርመን፣ የአውሮፓ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ጥቁር ምሁራንና ፈላስፎች የተናገሯቸውን፤ ከኢትዮጵያውያንም ቀደም ብለው በጉዳዩ ላይ ምርምር የሰሩ ሰዎችን ምስክርነት አድርጌ ነው በሰፊው ያጣቀስኩት፡፡ ማጣቀሻውን በአማርኛም በእንግሊዝኛም ነው ያቀረብኩት። ዋቢ መፅሐፍትም 50 ያህል  አስቀምጫለሁ። ሰዎች እነሱንም አግኝተው መመልከት ይችላሉ።
መፅሐፉ መቼ ለአንባቢያን ይቀርባል?
በቀጣይ ሳምንት ለአንባቢያን ይቀርባል። ዋጋው በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጌያለሁ። ምክንያቱም በብዛት ታትሞ አንባቢያን እጅ እንዲደርስ እፈልጋለሁ። ሁሉም ታሪኩን እንዲያውቅ ስለምፈልግ ከ350 ብር በላይ የተገመተውን መፅሐፍ ወደ 220 ብር ገደማ እንዲሆን ነው የወሰንነው።
ፕሮፌሰር ካገኘህዎት አይቀር ስለ አሜሪካ የሰሞኑ ማዕቀብ ምን አስተያየት አለዎት?
በእውነት በኢትዮጵያ ላይ የተደረገው አግባብ አይደለም። በትግራይም ቢሆን መንግስት በትልቅ ጥንቃቄ ነው እርምጃ የወሰደው። ህውኃት የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ነው። ወገኔ መሃል ነኝ ብሎ ተደላድሎ የተቀመጠን ሰራዊት አድፍጠው ያደረሱበት ግፍ ከሚታሰበው በላይ አሳዛኝ ነው። በማይካድራ ያደረጉት የጅምላ ጭፍጨፋ  አሰቃቂ ነው። ሆነ ብለው ህዝብ በሚሰበሰብበት ቤተ ክርስቲያንና አደባባይ እየገቡ የፈጸሙት የፈሪ ድርጊት በጣም ነውር ነው። ነገር ግን  የኢትዮጵያ ሰራዊት እነሱን ብቻ ለይቶ ለመምታት ያደረገው ጥረት የሚያስመሰግን ሆኖ ሳለ፣ ተቃራኒው መደረጉ በጣም አሳዛኝ ነው። ልክ እንደ ባዕድ ሃገር መሰረተ ልማት አፈራርሰው፣ ምግብ ለዜጎች እንዳይደርስ እንቅፋት አዘጋጅተው፣ መንግስት የምግብ እርዳታ ሲያደርስም እርዳታውን እየቀሙ እንዳይተላለፍ እያደረጉ፣ የጭካኔ ተግባር እየፈጸሙ ሳለ፣ ጩኸታቸው መበርታቱ በጣም የሚገርም ነው። የህውኃት ሰራዊት ላለፉት 27 ዓመታት መጠነ ሰፊ ግፍ ሲፈፅም በዝምታ ነበር የተመለከቱት፤ በሺህ የሚቆጠር የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ሲቀርብላቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው የነበሩ ምዕራባውያን፣ ዛሬ ምን ታይቷቸው ይሆን ይህን ለማድረግ የፈለጉት።
"ለናንተ አሻንጉሊት አንሆንም" መባሉ አስቆጭቷቸው ነው ማዕቀብ ያደረጉት። ለዚህ ዋና ተዋናይ ደግሞ ሱዛን  ራይስ የተባለችው የአቶ መለስ ዋና ወዳጅ የነበረች ሴት ነች። ይቺ ሴት ከአቶ መለስ ብዙ እጅ መንሻ ትቀበል የነበረች፣ የሰውየው አንደኛ ወዳጅ የነበረች ነች። አሁን ይቺ ሴት በባይደን አስተዳደር ተመልሳ መጥታለች።  የኢትዮጵያ መንግስት ለምዕራባውያን አልታዘዝም ማለት ነው የማዕቀቡ መንስኤ። አሁን የብልፅግና መንገድ ስለተጀመረና ግድቡም ፍሬያማ እየሆነ በመምጣቱ ኢትዮጵያ የበላይ ልትሆን ትችላለች፤ በዚህም ጥቁር ሁሉ አልታዘዝ ሊለን ይችላል ከሚል መነሻ ነው እቀባው። በነገራችን ላይ እቀባው ያን ያህል ጉዳት የለውም። ምናልባት የኢትዮጵያን ህዝብ በኢኮኖሚ ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ለማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ዝግጁ ሆኖ ራሱን ማጠናከር አለበት። መተባበርና በጋራ መቆም ያስፈልጋል።


Read 3513 times
Administrator

Latest from Administrator