Saturday, 29 May 2021 12:15

በታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስመር

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ግብፆች ኢትዮጵያ በዓመት 935 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የዝናብ ውሃ ስለምታገኝ ፊቷን ወደ ወንዞች ማዞር እንደሌለባት በድፍረት ይናገራሉ፡፡ የዝናብ ውሃ በየቦታው ባሊ ደቅና እንደምታጠራቅመው አድርገው ለዓለም ህዝብ ለማሳየት ይጥራሉ፡፡ ጥቂቱ ወደ መሬት ሊሰርግ ቢችልም እጅግ የሚበዛው የዝናብ ውሃ ጎርፍ ሆኖ አፈራችንን እየጠረገ ወደ ወንዞች እንደሚገባ፣ ከዚያም ወደ ሱዳንና ግብጽ ድረስ እንደሚወርድ ግን አይገልፁም፡፡
የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ 3%  ወርዶ እንደነበር ይታወቃል። በተከታታይ በተደረገው የችግኝ ተከላ ሽፋኑ ወደ 15%  ከፍ እንዳለም እየተገለፀ ነው፡፡ ግብፆች ይህን እውነት መቀበል አይሹም፡፡ 94% የሚሆነው የኢትዮጵያ መሬት አረንጓዴ የለበሰ ነው እያሉ ነው የሚደሰኩሩት። በሌላ አነጋገር 96% በረሃማ ለሆነችው ግብጽ የውሃ ፍላጎት ሊታሰብላት ይገባል ማለታቸው ነው፡፡
“አንድ መቶ ሚሊዮን የሚሆን የእንስሳት ሃብት ኢትዮጵያ አላት፡፡ እነዚህ እንስሳቶቿ በዓመት 84 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይጠጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ግብጽና ሱዳን ከሚፈልጉት የውሃ መጠን ጋር እኩል ነው፡፡” በማለት የሚገልፁት ግብፆች፤ በዚህ መንገድ  ማስጠበቅ የሚፈልጉት የተለመደውን “የውሃ ድርሻችን” የሚሉትን ነው፡፡
ለግብፆች የሱዳንም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት እየጨመረ እንደሚሔድ  አይታያቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከእነሱ አንድ መቶ ሚሊዮን በአስር ሚሊዮን እንደሚበልጥ ማስታወስ አይፈልጉም፡፡ እየጨመረ ለሚሄደው የሕዝብ ብዛታቸው በዓመት 114 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ይህን ማሟላት ግን እንዳልቻሉ የሚናገሩት እንጥላቸው እስኪታይ  እየጮሁ ነው፡፡
ሙስጠፋ ሀሰን አልዞቢር በሕዳሴው ግድብ የሱዳን ዋና ተደራዳሪ ናቸው፡፡ “ኢትዮጵያ አንድም አይነት አስገዳጅ ውል ሳትፈርም ሁለተኛውን የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ጀምራለች የሚል መግለጫ ሰሞኑን ሰጥተዋል፡፡ በሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሆነ በሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ያልተደገፈውን የዋና ተደራዳሪው መግለጫ፣ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በየነ “እያንዳንዱን ሰው ለማደናገር ሲባል የተሰራጨ መረጃ ነው” ሲሉ ውድቅ ቢያደርጉትም፣ ለአጭር ጊዜም ቢሆን አቧራ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡
የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪ፤ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት የሚገኙበት ድርድር፣ በአሜሪካ መንግስት ጋባዥነት በዋሽንግተን እንዲካሄድ ለማድረግ እያግባቡ ሲሆን ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውድቅ ያደረገችውና ሱዳንም አልፈርምም ያለችው በአሜሪካ የተዘጋጀው ስምምነት ነፍስ እንዲዘራ ግብፆች እየተሯሯጡ ነው። በሌላ በኩል፤ “የናይል ዘቦች” በሚል ግብጽና ሱዳን በጀመሩት የጦር ልምምድ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ እየተጉ ነው። የጦር ልምምዱ “ኢትዮጵያ አንድ አይነት አሳሪ ስምምነት ሳትፈርም ግድቡን ብትሞላ  የሚጠብቃት ወታደራዊ እርምጃ ነው”፡፡ የሚል መልዕክት ለኢትዮጵያ ለማድረስ ያለመ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
እዚህ ላይ “ዘቅዝቄ ልስቀላችሁ ወይስ አጋድሜ ልረዳችሁ” የሚለው የሰሞኑ የአሜሪካ አቋም ሲጨመርበት ኢትዮጵያ የገባችበትን ፈታኝ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ድርድሩን ወደ አሜሪካ ለመውሰድ በማቀድ፣ የአፍሪካ ህብረትን ሚና  ለማንኳሰስ የሚደረገውን ተደጋጋሚ ሙከራ በእንጭጩ መቅጨት  ያስፈልጋል፡፡
ለአሜሪካም ሆነ ለሌላው “ቆሞም ሆነ ተጋድሞ” የሚታረድ  ህዝብ በዚህች አገር አለመኖሩን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀመረውን የህዳሴ ግድብ ከዳር ለማድረስ መከፈል ያለበትን መስዋእትነት እየከፈለ ለፍፃሜ እንደሚያደርስ ማሳወቅ ግድ ይላል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሕጎችን አክብራ፣ የማንንም ፈቃድ ሳትጠብቅ የውኃ ሃብቷን  እንደምታለማ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ አስተዳደር ማንም እጁን እንዲያስገባ እንደማትፈቅድም፣  እንደ ውዳሴ ማርያም ደጋግማ እየነገረች፣ አለም እንዲረዳት ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡
ግብፆች በየጊዜው እየተነሱ “ቀይ መስመር ነው” እንደሚሉት ሁሉ፣ ኢትዮጵያም የራሷን ቀይ መስመር አስምራ፣ “ከዚህ ማለፍ አይቻልም” ማለት ይገባታል፡፡ የሕዳሴው ግድብ አስተዳደርም አንደኛው ቀይ መስመር መሆን ይኖርበታል፡፡
ማስታወሻ፡- የኢትዮጵያ መንግስት እያሣየ ላለው የአቋም ፅናት፣ አክብሮቴን የምገልፀው ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ ነው!!

Read 1714 times