Monday, 31 May 2021 00:00

በምርጫው ማን ማንን ያሸንፋል? ማንስ ቢያሸንፍ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)


            “ማን ያሸነፋል?” የሚለውን ጥያቄ ሳነሳ፣ “ማን በለጠ?”፣ “ማን ቀናው?” በሚል ትርጉሙ ማለቴ ነው። ማን ማንን ድባቅ መታ? ማን በማን ኪሳራ አተረፈ? በሚል ትርጉሙ ባናስበው ጥሩ ነው።
የአትሌቲክስና የእግርኳስ፣ የስራና የጨረታ  ውድድርን ማሰብ ትችላላችሁ።  እነዚህ ውድድሮቹ ውስጥ፣ አሸናፊና ተሸናፊ ማለት፣ መቺ እና ተመቺ፣ ጀግንነትና ቅሌት፣ ጎበዝና ሰነፍ ማለት አይደለም። ብቃት ያላቸው ጎበዝ ተፎካካሪዎች ናቸው ተወዳዳሪዎቹ - ስፖርተኞችና ባለሙያዎች። ምርጥ አትሌቶች ያልተሰለፉበት ውድድር፤ አይመስጥም። በኦሎምፒክ፣ አሸናፊውና ተሸናፊው፣ የዓለም ምርጦች ናቸው።
 በሌላ በኩል፣ የፖለቲካ ምርጫ፣ እንደ ጦርነት ካየነው ግን፣ አሸናፊና ተሸናፊ ማለት፣ መቺና ተመቺ፣ አጥፊና ጠፊ፣ አትራፊና ከሳሪ የሚል ትርጉም ይይዛል። አንዱ የሚከብረው፣ በሌላኛው ውርደት ብቻ ይሆናል።
በሌላ አነጋገር አሸናፊ እና ተሸናፊ የሚሉ ቃላት፣ ለእንዲህ ዓይነት የተሳሳተ ትርጉም የተጋለጡ ናቸው።
የደስታ ተክለወለድ መዝገበ ቃላት፣ አሸነፈ ለሚለው ቃል፣ “አሰነፈ” የሚል ትርጉም በማስቀደም፣ ፍቺውን ይዘረዝራል። አሸነፈ ማለት፡
አሰነፈ፣ አቃተ፣ አባተ፣ ሠለጠነ፣ ዐየለ፣ በረታ፣ ድል ነሣ፣ ድል አደረገ፣ ረታ፣ መታ፣ ሻረ፣ አዋረደ፣ አታከተ፣ አደከመ... ማለት እንደሆነ ይገልፃሉ ደስታ ተክለወልድ።
በአንድ በኩል፣ በረታ ወይም ሰለጠነ የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል- መሻሻልን ማደግን የሚያጎላ። በረታ ስንል፣ የተቀናቃኝ ድክመትን የሚያጎላ መንፈስ የለውም። ከብርቱም ብርቱ ሊሆን ይችላል ውድድሩ እንደ ኦሎምፒክ፡፡ ከቆንጆም ቆንጆ ሊሆን ይችላል ትርኢቱ እንደ “ወይዘሪት ኢትዮጵያ”፣ እንደ “ሚስ ወርልድ”።
በሌላ በኩል ግን፣ አሸነፈ ከአሰነፈ፣ ተሸነፈ ደግሞ ከሰነፈ ጋር ተያይዟል።
የአንዱ ዝቅታ ነው፤ የሌላው ከፍታ። የአንዱ ውርደትና ቅሌት ነው፣ የሌላው ክብር እና ማዕረግ። የአንዱ ውድቀት የሌላው ትንሳኤ። አንዱ በአጭሩ ከተቀጨ ሌላው ይፀናል።  አንዱ ከተሻረ ለሌላው ሹመት “ይሽራል” እንደ ማለት ይሆናል።የፖለቲካ ምርጫ እንዲህ ከሆነ፣ ከሞት ሽረት ፍልሚያ በምን ይለያል? ይሄ አሳዛኝ የኋላቀር ፖለቲካ ትረካ ነው።
የፖለቲካ ምርጫ፣ውስጥ የአንዱ ፓርቲ ድል፣ ለሌላው ፓርቲ ኩነኔ፣ የአንዱ መመረጥ፣ ለሌላው ውግዘት መሆን አልነበረበትም። ሌላውን ፓርቲ የማስነፍ፣ የመሻር፣ የመርታት፣ የማዋረድ ትርጉም ባይኖረው ይሻል ነበር። በአንዱ ኪሳራ ሌላው የሚያተርፍበት ውድድር ባይሆን በጎ ነበር።
ለማንኛውም፣ በምርጫው ማን ያሸንፋል ለሚለው ጥያቄ፣ ሁለት ፖርቲዎች፣ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ምላሽ ሲሰጡ ሰምተናል። ማን ያሸንፋል?
“ኢትዮጵያ ታሸንፋለች” ይላሉ - ብልፅግና ፓርቲ፣ ኢዜማ ፓርቲ። ምን ማለታቸው ነው? የትኛውም ፓርቲ ቢያሸንፍ ችግር የለውም። ምርጫው ከተቃና፣ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች... ይላሉ ፓርቲዎቹ።
ወገኛ አባባል ይመስላል። “በአዲስ አድማስ ጋዜጣም፤ ተመሳሳይ ሃሳብ ተፅፎ ነበር- ነገርዮው፣ ምርጫ እንጂ፣ የሞት ሽረት ፍልሚያ አይደለም በሚል ርዕስ። ይሄኛው አባባል፣ “የሞት ሽረት ፍልሚያ መሆን አይገባውም” ብለን ካልተገነዘብነው በቀር፤ ወደ ፓርቲዎቹ አባባል የተጠጋ ወገኛ ዝንባሌ ይጫነዋል። በእርግጥ፣ በፓርቲዎች አፍ ሲሆን፣ ወገንተኛነቱ ይገንናል። ለብዙ ሰዎች ጆሮም፣ የምር ወገኛ አባባል ነው።
 ቢሆንም ግን፣ የፓርቲዎቹ አባባል፣ አንዳች እውነት ይዟል። አዎ፣ የፓርቲዎቹ አባባል፣ ከዛሬው የአገራችን ፖለቲካ ጋር የማይመጣጠንና የማይሰራ አባባል መሆኑ አያጠራጥርም።
እንዲያም ሆኖ፣ በሆነ ገፅታው ስናገናዝበው፤ ተገቢና ትክክለኛ አባባል ነው። ምክንያቱም፣ በስልጡን ፖለቲካ ውስጥ፣ የትኛውም ፓርቲ ቢያሸንፍ፣ ችግር የለውም።
በስልጡን ፖለቲካ ውስጥ፤ ይሄኛ ፓርቲ ቢያሸንፍ፣አንዳች የሚያመጣው ተዓምረኛ ሲሳይ አይኖርም። ያኛው ፓርቲ ቢያሸንፍም፣አንዳች የሚፈጥረው መዓተኛ መከራ አይኖርም።
የመንግስት አስተዳደርን መምረጥ፣ የጥበቃ ሰራተኛን አወዳድሮ እንደመቅጠር ነው - አበበ አልያም ከበደ ቢያሸንፍ ለውጥ የለውም - በስልጡን ፖለቲካ ውስጥ።
የአገራችን ፖለቲካ ግን፣ ከስልጣኔ እጅግ ርቋል።  አንዱ ችግር፣ መንግስት፣ “ሁለገብ” መሆኑ ነው። “ሃላፊነቱ የተወሰነ፣ ስልጣኑ የተገደበ” መሆን ይገባው ነበር። ኋላቀር የፖለቲካ ባህል ውስጥ ግን፣ መንግስት ባሻው ጊዜ ያሰኘው ነገር ውስጥ መግባት ይችላል። መንግስት በራሱ ፈቃድ እጁን ሰብሰብ ካላደረገ በቀር፤ሁለገብና ሁሉን አቀፍ እንዳይሆን የሚገታ ልጓም የለም- በኋላቀርነት ውስጥ። የመንግስት ስልጣን፣ በጣም ብዙ ነው- ከባድ፣ ሃያል፣ አስፈሪ፣ አደገኛ፣ ዝርክርክ፣ ባለ ብዙ ኮተት ነው- የመንግስት ስልጣን። አንዱ ፓርቲ በምርጫም ሆነ በእርግጫ፣ ስልጣን ላይ ሲወጣ ፣ ሌሎችን ፓርቲዎች ማጥፋትና ማሰቃየት፣ ለዘብ ካለም፣ ተቀናቃኞችን ማሳደድና ማዋከብ ይችላል። ማን ከልክሎት?
ታዲያ፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ፣ “ማንም ቢያሸንፍ አያሳስብም። ኢትዮጵያ ታሸንፋለች “ ብሎ መነጋገር ያዋጣል? ያሳምናል? ለወጉ ያህል ካልሆነ በቀር፣ ምን ፋይዳ አለው?
በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ የጦዘ አገር  ውስጥ፣ “ያኛውን ከተማ እነጥቃለሁ። ያኛውን ዞን ወደ ክልል እቀይራለሁ። ያኛውን ክልል ገንጥዬ አገር እፈጥራለሁ” የሚሉ ፓርቲዎች የበዙበት ዘመን ውስጥ መሆናችንን አትርሱ። እና የትኛውም ፓርቲ ቢያሸንፍ፣ ለውጥ አያመጣም? ምን ይ ብቻ። አሁን አሁንም ደግሞ፣ የሃይማኖት ፖለቲካም እየተጨመረበት ነው።
በዚያ ላይ፣ ከግማሽ በላይ የአገሪቱ ተንቀሳቃሽ ኢኮኖሚ፣ በመንግስት ስልጣን ስር ነው። አብዛኛው ተቀጣሪ ሰራተኛ፣ መንግስት ሰራተኛ ሆኗል።
ምናለፋችሁ፣ ብሔር ብሔረሰብ፣ ሃይማኖትና ኢኮኖሚ፣... ከመንግስት የፖለቲካ ስልጣን ጋር ሲወሳሰቡ፣... ሁሉም ነገሮች አሳሳቢ አደጋዎች ይሆናሉ።
እንኳን የፖለቲካ ምርጫ ቀርቶ፣ የሁለት መንገደኞች ንትርክም፣ አገርን የሚያናውጥ ሰበብ ይሆናል። በሁለት ሰዎች አምባጓሮ ሰበብ ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፣ ብዙ ሺ ሰዎች ቤትና ንብረታቸውን ሲዘረፉ ፣ ሲሰደዱ፣ ከተሞች ሲቃጠሉ ፣ ስንቴ አይተናል?
እና፤ “ማንም ቢያሸንፍ አያሳስብም፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች” ብሎ መናገር፣ ትርጉሙ ምንድነው? እውነት ይወጣዋል? አንዳች ፋይዳ ይኖረዋል? ከላይ እንደገለፅኩት፣ በአንድ በኩል፣ ለዛሬ የሚሰራ አባባል አይደለም። በሌላ በኩል ግን፣ ፋይዳ ቢስ ነው ማለት አይደለም። ምናልባት፣ የወደፊት የስልጣኔ ምኞትን ለመግለፅ ይጠቅም ይሆናል። ቀላል ምኞት እንዳይመስላችሁ ካወቅንበት።
“ማንም ቢያሸንፍ አያሳስብም” የምንልበት፣ በጎ፣ የስልጡን ፖለቲካ ዘመን እንዲመጣ መመኘት፣ ትልቅ ቁም ነገር ነው። በቅርብ የሚገኝ ምኞት አይደለም። የሩቅ ዘመን  ምኞት ነው። ነገር ግን፣ ዛሬ ከወዲሁ በጎ ካልተመኙ፣ ስልጡን ፖለቲካ፣ ሁሌም ፣ ከብዙ ዓመታት በኋላም፣ መቼም የማይደርስበት እጅግ ሩቅ ሆንብናል።
የሩቁን በጎ ነገር መመኘት ዛሬ ነው። በጎ እንመኝ። እንዲህ እንበል። “ማንም ቢያሸንፍ ፣ አያሳስብም” ለማለት ያብቃን እንበል። ወይም፣ ለማለት እንብቃ።
በእርግጥ፣ በደፈናው፣ በጎ ነገር መመኘት፣ እንደመነሻ ይጠቅም ይሆናል እንጂ፣ በቂ አይደለም። ምኞታችን፣ በትክክል በጎ ምኞት መሆኑን አጥርተን ካላረጋገጥን፣ የኋላ ኋላ ጉድ ይፈላል- ተመኘነው ነገር ሲደርስ። ደግሞም አትጠራጠሩ። አነሰም በዛ፣ ቢከፋ ቢለማም፣... ብዙዎች የተመኙት ነገር፣ በእውን ይደርሳል።
ብዙዎች የተመኙት ነገር፣ ቢያንስ ቢያንስ ጥቂት ሰዎች፣ ስራዬ ብለው ይዘምቱለታል። ብዙ ሰዎች የዘመሩለት ነገር፣ ብዙ ተቃዋሚ አይገጥመውም። ለዚህም ነው፣ በጥቂት ሰዎች ዘመቻ ወደ ተግባር የሚለወጠው።
ታሪክን ተመልከቱ። የድሮዎቹ የሶሻሊዝም አብተኞች ምን እንደተመኙ አስታውሱ። ከሌሎች ሶሻሊስቶች የተለየ ምኞት አልነበራቸውም።
አንደኛ ነገር፣ የሰዎችን ንብረት የሚወርስ፣ ኢኮኖሚን የሚቆጣጠር መንግስት እንዲመጣ ተመኝተዋል።
ሁለተኛ ነገር፣ አምባገነን መንግስት እንዲነግስ ተመኝተዋል። የያኔ ምኞታቸው፣ ዛሬ ግራ ሊያጋባን ይችላል። የአንድ ፓርቲ አምባገነንነትን ነው የተመኙት። አንድ ህዝባዊ ፓርቲ፣ አንድ ሶሻሊስት ፓርቲ፣ አንድ አብዮታዊ ፓርቲ፣ አንድ የጭቁኖች  የሰርቶ አደሮች ፓርቲ... ስያሜው ምንም ሆነ ምን፣ አንድ አምባገነን ፓርቲን መመኘት ብቻ  ሳይሆን ፣ በጉጉት በናፍቆት ጠብቀዋል። ጊዜው ቀርቧል ብለው ትንቢት ተናግረዋል፣ ሰብከዋል። አስተምረዋል።
በዩኒቨርሲቲ፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ሳይቀር፤  የአምባገነንነት  ስብከትና ጉጉት ፋሽን ወረት ሆነ። ሁሉም የአዲስ ስርዓተ ማህበር አዋላጅ፣ ነባሩን አፍርሶ አዲስ ነገር የሚያመጣ ተዓምረኛ ፈጣሪ የሆነ መሰለው።
የአብዛኞቹ አብዮተኞች ችግር፤ “ንፁህ” አላዋቂነት ነው። ነገር ግን ፣ ለአዋቂነት ተመርጠር፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ወደ ከፍተኛ ትምህርት የገቡ፣ ከዚያም የተመረቁና በምሁራን ዘንድ ገንነው ተሰሚነትን ያገኙ መሪዎችስ? የአላዋቂነት ክብር የተጎናጸፉት ቀንደኛ መሪዎችስ? የአብዛኛዎቹ ምኞት ተመሳሳይ ነበር።
የአንድ ፓርቲ ሶሻሊስት አምባገነንነትን ተመኙ። ምኞታቸውን ሰበኩ። ማህበራትንና ፓርዎችን አቋቋሙ፣ አባላትን መለመሉ፤ መፅሔቶችን አሳተሙ፣ ቀሰቀሱ፤ ለአመፅና ለአብዮት አነሳሱ። ምኞታቸው የማይሳካ መስሏቸቸው ነው?  ምኞታችን ቢሳካ ምን ይውጠናል ብለው ማሰብ ነበረባቸው። የተመኙት ተሳክቷል።
“የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት” የሚመኙ ደርዘን ፓርቲዎች፤ ምኞታቸው ሲሳካ ምን እንደሚሆኑ ገምቱት። አንድ ፓርቲ እስኪቀር ድረስ ይጨፋጨፋሉ። አመፅ፣ ሽብርና ሴራ፣ የጅምላ ግድያ፣ የጅምላ እስርና ግርፊያ፣ ስደት... ምኑ ይቆጠራል። ማለቂያ የለውም- የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት እንዲጸና። የተመኙት እንዲነግስ።
ምን ለማለት ነው? በጎ መመኘት ጥሩ መነሻ ነው። ነገር ግን፣ የእውነት በጎ መሆኑን በጥንቃቄ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ምኞት ይሳካና መከራ ይከፋል። Be ware what you wish for! እንዲሉ።
አዎ፣ “ማንም ቢያሸንፍ አያሳስብም” ለማለት እንድንበቃ፣ ስልጡን ፖለቲካን መመኘት፣ በጎ መመኘት ነው።
ምኞታችን፣ እንከን የማይወጣት ድንቅ በጎ ምኞት እንደሆነ እርግጠኛ መሆን አለብን። ግን በቂ አይደለም።
የምኞታችንን ምንነት፣ በዝርዝር ገፅታዎቹን ተንትነን፣ ሁለመናውንም በምልዓት አዋህደን መገንዘብ፣ በቅጡ የተቀናበረ እውቀትም መጨበጥ ይገባናል። ለምኞታችን ተገቢነት መነሻ የሆኑ ጠንካራ  ስረመሰረቶችንና እውነታዎችን አጥርቶ አንጥሮ ማወቅም ያስፈልጋል። መንገዱንም ጭምር። ጥረትንም ማከል።... ይሄ ሁሉ ለዘላቂው ነው፡፡
 እስከዚያው ግን፣ የዘንድሮው ምርጫ ማን ያሸንፋል?

Read 9531 times