Monday, 24 May 2021 00:00

እጣ እና ምርጫ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  •  የፖለቲካ ምርጫ፣ በውድድርና “በድምጽ ብልጫ”? ወይስ በማያከራክር “ገለልተኛ እጣ”? የምርጫ ክርክርና ውድድር፣ አልቻልንበትም።
   • ይሄኛውና ያኛው ጎራ፣ እንደየአቅሙ ጦርና ጥፍር ወድሮ፣ እርስ በርስ የሚናቆሩበት የሚጠፋፉበት ውድድር ሆኖብናል።
   • የምርጫ ፉክክር ማለት፣ አንዱ ሌላውን ከርክሮ፣ በእንጭጩ ቆርጦ ለመጣል ወይም ገንድሶ ለማስወገድ የሚዝትበት ፉከራ መስሎብናል።
   • ታዲያ፣ “ሁሉንም እኩል የሚያሳትፍ”፣ የማይጭበረበር፣ የማያጭበረብር፣ የውዝግብ ሰበብ የሌለው፣ እንከን የማይነካው፣ ንፁህ የእጣ ምርጫ  አይሻልም? ሁሉም “እጣ ክፍሉን” ያገኛል እንዲሉ።
   • የማላገጥ ወይም የመቀለድ ሙከራ አይደለም። በእርግጥ፣ “ካርድ የመረጠው መንግስት” ከማለት ይልቅ፣ “እጣ የመረጠው መንግስት” ሲባል፣ ትንሽ ግር ይላል። “ባለ እጣ መንግስት”... ብለን ብንሰይመውስ?
   • የእጣ ምርጫ፣ ድሮ ያልነበረ ነገር፣ ዛሬም የሌለ ነገር፣ መቼም የማይሆን ነገር ይመስላል። ይመስላል እንጂ፣ “ምርጫና እጣ”፣ በፍጹም አይዛመዱም ማለት አይደለም። “ምርጫ በእጣ”፣ በታሪክ ያልተከሰተ፣ በዓለምም ያልታየ ነገር አይደለም።
   • የአገራችን የምርጫ ህግ ይመስክር። የአገራችን የፖለቲካ ምርጫ፣... “የህዝብ ምርጫ”...ማለትም በሰዎች ምርጫ፣ በድምጽ ብልጫ ነው። እጣ ቦታ   አለው - በአገራችን የምርጫ ህግ። ግን፣ የአቴንስ፣ የሮምና የፍሎረንስ ታሪክንም እናጣቅሳለን።
   • የእጣ ገለልተኛነትን፣ ከፖሊስና ከፍርድ ቤት “ገለልተኛነት” ጋር እናወዳድራለን። ገለልተኛ በመሆንማ፣ የእጣ ዳኝነት፣ ይበልጣል። ሕግና ስርዓትን  ሊያስከብርልን ግን አይችልም - ገለልተኛነት።
             ዮሃንስ ሰ

              “ምርጫና እጣ”፣ ምንም ልናቀራርባቸው ብንለፋ፣ በጭራሽ የማይገናኙ ይመስላሉ። እንዲያውም፣ የእጣ ተቃራኒ ይመስላል - ምርጫ። ግን፣ ለእጣ፣ ጨረታን የሚያክል ተቃራኒ አለው? የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤትነት፣ በእጣ እና በጨረታ ሲሆን አስቡት። ልዩነቱ፣ የትና የት?
የአሜሪካ የመኖሪያ ቪዛም፣ በእጣ ሲሆን እና በጨረታ ሲሆን፣ ልዩነቱ ሰፊ ነው። አንዳንድ የአውሮፓ አገራት፣ የመኖሪያ ቪዛ፣ ከዚያም የዜግነት ፓስፖርት በክፍያ እየሰጡ፣ ደህና ገቢ ለማግኘት መጣራቸው፣ የሚገርም ነገር አለው። ለነገሩ፣ የበጀት ጉድለት ማሟያ ቢሆንላቸው ምን ጨነቀን? ደግሞስ ዜግነትን በክፍያ መስጠት አስገራሚ ከሆነ፣ ዜግነትን በእጣ መስጠትስ አይገርምም? የጨረታና የእጣ ነገር!
በሌላ በኩል ግን፣ የእጣ ተቃራኒ፣ በዘፈቀደ የማይገለባበጥ “እውነታ” ነው... ማለት ይቻላል። ወዲህ ወዲያ የማይከረባበት የተፈጥሮ ህግ፤ የእጣ ተቃራኒ ካልሆነ፣ የምን ተቃራኒ ይሆናል? እውነታና የተፈጥሮ ህግ፣ ከዛሬ ነገ፣ እንደ እጣ አይቀያየሩም። Nature doesn’t play dice የሚል ሃሳብ ተናግሯል - አንስታይን። “ተፈጥሮ” ሳይሆን “ፈጣሪ” ነው ያለው? የሆነ ሆኖ፣ ዳኝነትና ፍትህስ? ብለን እንጠይቅ።
የተቃናውን እና ጠማማውን፣ ንፁሁንና ክፉውን፣ በዳይና ተበዳይን የማያምታታ ትክክለኛ ዳኝነት፣ ማለትም ፍትህ፣ የእጣ ተቃራኒ ነው። አይደለም? አዋቂና አላዋቂ፣ ጎበዝና ሰነፍ፣ ወንጀለኛና ንጹህ ብለን ሰዎችን የምንዳኘው፣ በስነ ምግባርና በህግ ሚዛን ሳይሆን፣ አይናችንን ጨፍነን በእጣ ቢሆን አስቡት።
ፀሀይ በእጣ የምትመጣ ወይም የምትቀር፣ በምስራቅ ወይም በደቡብ በእጣ እያፈራረቀች የምትወጣ፣ በሰሜን ወይም በምዕራብ እጣ እየወሰነላት የምትጠልቅ ቢሆን፣.... ኧረ አያድርገው። የተፈጥሮ ዑደት የእጣ ጉዳይ ቢሆን፣... “ከሆረር” በምን ይሻላል?
ከዚህ አንጻር፣ እጣ መጣጣል፣ “የእውነታና የተፈጥሮ ሥርዓት ጠላት”፣ “የስነምግባርና የፍትህ ተቃራኒ” ይሆናል። ቢሆንም ግን፣ እጣ ማለት፣... “የክፋት ሌላ ስም” ነው ማለት አይደለም።
በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ፣ የዘወትር የውድድር መነሻ፣ እጣ መጣል አይደል? የትኛው ቡድን በየትኛው የጎል አቅጣጫ እንደሚጫወት፣ የትኛው ቡድን ጨዋታውን እንደሚጀምር፣ በእጣ ይወሰናል። ወይም “እጣ ይወስናል”። ከእጣ ውጪ፣ ሌላ የተሻለ ዘዴ አለ? ሌላ “ፍትሀዊ” መንገድ አለ? Fairplay ይባል የለ? እጣ፣ የፌርፕለይ ወይም የጨዋ ጨዋታ አንድ ገፅታ ነው - ቅንጣት ገፅታ ቢሆንም። አዎ፣ እጣ፣ ዋናው የእግር ኳስ ገፅታ አይደለም። እጣው አይደለም ጨዋታው።
የእቁብ እጣም እንደዚያው ነው። ያለ እጣ፣ እቁብ የለም። ነገር ግን፣ እጣው አይደለም እቁቡ። የመቆጠብና በየተራ ቁጠባውን የመጠቀም ጉዳይ ነው - እቁብ። ተርታውን ለመወሰን፣ አንቺ ቅደሚ፣ አንተ ተከተል ብሎ ለመለየት ነው - የእጣው ፋይዳ።
በእርግጥ፣ የእጣ ድርሻ፣ ከዚያም የሚያልፍበት ጊዜ አለ።
እጣ አያዳለም። ቂምና ውለታ አይቆጥርም።
እጣ፣ የዳኝነት መሳሪያ ሆኗል - በተለያየ አገር፤ በተለያየ ዘመን። የጥንት ታሪክን መጥቀሴ አይቀርም። የነብዩ ዮናስ ትረካንም አስታውሳችኋለሁ። እስከዚያው ግን፣ በጥቅሉ የእጣ ዳኝነትን ልግለፀው። እጣ የወጣበት፣ ሞት ይፈረድበታል። ይገድሉታል። እጣ የወጣለት ካሳ ይከፈለዋል። ሽልማት ይሰጡታል።
ሲፈርዱበትም ሲፈርዱለትም፣ በአድልዎ አይደለም። በእጣ ነው። ዘመድና ባዕድ አይሉም። የዘር ሀረግ ቅርበቱና ርቀቱን ለክተው ገምተው፣ ቂምና ውለታውን አስልተው አይደለም። ፈራጁ እጣ ነው። መሃሪውም እጣ ነው። የፈረደብህም እጣ፣ የፈረደልህም እጣ።
እጣ አያዳለም። እጣ ለዘመድ ለባዕድ፣ ለመጤ ለነባር አይልም። እጣ፣ በውለታና በጉቦ አይሰራም። ክፉ ጥላቻ አይጠናወተውም፤ ቂም አይቆጥርም።
በአጭሩ፣ በዘመናችን አነጋገር፤ እጣ “ገለልተኛ” ነው።
የፍርድ ቤት ዳኝነትንና የእጣ ዳኝነትን ስናወዳድር።  
የዘመናችን አላዋቂ ምሁራን፤ የድናቆታቸው ጫፍ፣ “ገለልተኛ” የሚል ቃል ሆኗል። ፖሊስን፣ የምርጫ ቦርድን፣ ፍርድ ቤትንም ሳይቀር ሲያደንቁ፣ “ገለልተኛ ነው” ይላሉ። ሲያወግዙ “ገለልተኛ አይደለም” ይላሉ።
የፖሊስ ስራ፣ እንደ “እጣ”፣ ገለልተኛ መሆን ነው? ወይስ የሰዎችን ነፃነትና መብት ማስከበር? የሰው ህይወት፣ በነፍስ ገዳይ እንዳይጠፋ፣ ሰላምና ኑሮ በነውጠኛ እንዳይታወክ፣ ንብረት በዘራፊ እንዳይበዘበዝ፣ በሞገደኛ እንዳይወድም መጠበቅ አይደለም የፖሊስ ስራ? ማለትም፣... ወንጀልን መከላከል፣ ወንጀል ከተፈጸመም በህግ ማስቀጣት፣... የሰዎችን ነፃነትና መብት በሚያከብር መንገድ፣ በህግና ስርዓት መስራት አይደለም የፖሊስ ስራ? ነው። ነው እንጂ።
በእርግጥም፣ የፖሊስን ተግባር ለማስመስገንና ለመውቀስ፣ ለማጽናትም ሆነ ለማስተካከል፣ ዋናው መመዘኛ፣ “በህጋዊ ስርዓት፣ ህግን እያስከበረ ነው ወይ?” የሚለው ጥያቄ መሆን ይገባዋል። ዋናው ትኩረት፣ “ህግና ስርዓት” ላይ ማነጣጠር አለበት። ከተቋማት አወቃቀርና ከበጀት ጀምሮ፣ እስከ አሰራርና መመሪያ፣... ከፖሊሶች ትምህርትና ስልጠና፣ ከትጥቅ አይነትና ከስምሪት ምደባ፣ እስከ ልምድና ባህርይ፣ የጤንነትና የአካል ብቃት፣... ሊሟሉ የሚገባቸው በርካታ ቁምነገሮች ሊዘረዘሩ ይችላሉ። ለምንድ ነው የሚሟሉት? ለህግና ስርዓት ሲባል።
የተቋማት ዝርክርክነትን ወይም ቅጥ አልባነትን ማስተካከል ይገባል። ለብቃት ጉድለትና ለድክመት፣ ለሙስናና ለእድልዎ የሚያዳርጉ አልያም የሚያጋልጡ ስህተቶችን ማስወገድ ተገቢ ነው። ለጥፋትና ለወንጀል መንገድ የሚከፍቱ፣ የዘረኝነት፣ የሃይማኖት አከራካሪነት፣ ወይም የፖለቲካ ጎራ ዘማችነት.... እነዚህን የመሳሰሉ የጭፍንነት ቅኝቶችን ማስወገድ የግድ ያስፈልጋል። ለምን? ህግና ሥርዓትን ስለሚያስፈርሱ።
በአጭሩ፣ ፖሊስን በሚመለከት ዋናው መመዘኛ፣ የሌሎች እልፍ መመዘኛዎች ዋና ምንጭ፣ “የህግና የስርዓት ጉዳይ” ነው። ለህግና ስርዓት ሲባል ከሚዘረዘሩ ተገቢ እልፍ መመዘኛዎች መካከል አንዱ ቅንጣት ነው - “ገለልተኛነት”።
አሁን አሁን ግን፣ ዋናው ቁም ነገር ተረስቶ “ገለልተኛ” የሚለውን ቃል ለብቻው አንጠልጥለው የሚያራግቡ በዝተዋል።
“ገለልተኛ” በሚባለው መመዘኛማ፣ ከእጣ ጋር የሚወዳደር ከወዴት ይገኛል? ነገር ግን፣ የእጣ ጠጠር፣ ሕግና ስርዓትን ያስከብርልናል?
ፖሊስ ነው፤ ሕግና ስርዓትን ሊያስከብር የሚችለው። ለምን? የፖሊስ ፋይዳ፣ በገለልተኝነት ከእጣ ጋር መፎካከርና መብለጥ አይደለም። ሕግና ስርዓትን አክብሮ ማስከበሩ ላይ ነው - የፖሊስ ፋይዳው። ምስጋናና ወቀሳም፣ በዚሁ ልክ መሆን ይኖርበታል - ለህግና ለስርዓት ባበረከተው ፋይዳ ልክ። በዚህ መሃል፣ ከደርዘን ጉዳዮች መካከል የገለልተኛነት ጉዳይ ቢነሳ፣ ጥሩ። ገለልተኛ የሚለው ቃል፣ አልፋና ኦሜጋ ከሆነ ግን፣ ችግር አለ።
ፖሊስንና ፍርድ ቤቶችን፣ በእጣ ጠጠር እንተካቸው?
በህግና በስርዓት፣ ዳንነትን መስጠት፣ ፍርድን መወሰን ነው - የፍ/ቤቶች ፋይዳ። በቀጥታ የፍርድቤትን ስራ የሚያደናቅፍ ጉዳይ ካልተፈጠረ በቀር፤ ፍርድ ቤት፣... በተገቢው ስርዓት የቀረበለት ክስ ወይም አቤቱታ ላይ እንጂ፣ ባሰኘው ጉዳይ ላይ፣ ራሱ ከሳሽና ፈራጅ መሆን አይገባውም። ሥርዓትን ይጥሳል። ይሄኛው ህግ ስህተት፤ ያኛው ህግ ጎዶሎ፣ ያኛው ህግ ደግሞ አላስፈላጊ ሊሆን ቢችልም፣ ህግን ማስተካከል፣ አንቀፆችን ጨምሮ ወይም ቀንሶ ህግን ማወጅ፣ የፍርድ ቤት ስራ አይደለም።
ከእጣ ዳኝነት ጋር መፎካከርም፣ የፍርድ ቤቶች ምኞት መሆን አይገባውም።
አስቡት። ነብዩ ዮናስ፣ አስገራሚ ትረካ ላይ፣ በእጣ ነው የተፈረደበት።
አስገራሚውን ታሪክ ለሌላ ጊዜ እናቆየውና፣ የዳኝነት ዘዴውን ብቻ እናስታውስ። እንግዲህ፣ ዮናስ፣ ከፈጣሪ ለመሸሽ ነው፣ በመርከብ ለጉዞ የተሳፈረው። መርከቧ፣ በአውሎ ነፋስ በማዕበል ተናወጠች። ነገሩ የፈጣሪ ቁጣ እንደሆነ አምኗል - ዮናስ።
አንስታችሁ ወደ ባህር ጣሉኝ፤ የባህሩ ነውጥ ይረግባል ብሎ ለመርከበኞቹ ነገራቸው። መርከበኞቹ ግን በጣም “ፍትሀዊ” ናቸው፤ እሺ ብለው አልወረወሩትም። የማዕበሉ ሰበብ ምንነትን፣ ጥፋተኛው ሰው ማንነትን ለመለየት፣ እጣ እንጣል አሉ። እጣው ዮናስ ላይ ወደቀ። ተፈረደበት ማለት ነው። ወደ ባህር ተጣለ።
ፕሮፌሰር ሮበርት አልተር እንደሚሉት፣ እጣ መጣጣል ገለልተኛ የዳኝነት መንገድ እንደሆነ ይታመንበት ነበር። የጥንት ዘመን ተመራማሪ ናቸው። የኦሪት መፃህፍትን ከዋና ዋና የእብራይስጥ ፅሁፎች ወደ እንግሊዝኛ ለመተርጎም ለ30 ዓመታት ተመራምረዋል። ትርጉሙን ከነማብራራያው፣ እኤአ በ2018 አጠናቅቀው ሙሉውን ሲያሳትሙ፣ ከፍተኛ አድናቆት እንደተቸራቸው በወቅቱ ተዘግቦላቸዋል።
በእርግጥ፣ የእጣ ፍርድ፣ ሁልጊዜ ተመራጭ የዳኝነት ዘዴ ነበር ማለት አይደለም። በህግ መሰረት፣ በምስክር፣ በማስረጃ፣ በክርክር አማካኝነት ነው የዳኝነት ፍርድ የሚተላለፈው። “በህግና በስርዓት” መሆኑ ነው። አንዳንዴ ግን፣ ከሳሽ ምንም ማስረጃ ከሌለው፣ ተከሳሽም ውንጀላውን ማፍረስ ካልቻለ፣ ጉዳዩ በእጣ ይወሰናል።
እጣው በተከሳሽ ላይ ብቻ አይደለም። በከሳሽም ላይ ነው። እጣው የወደቀበት ሰው ላይ፣ ከሁለቱ አንዱ ላይ ይፈረድበታል። ከሳሽ ላይ እጣ ከወጣበት፣ የሀሰት ውንጀላ ይዞ ነበር የመጣው ማለት ነው። ገለልተኛው የእጣ ዳኝነት፣ ወስኖበታላ - ያለ አድልዎ።
እዚህ ላይ፣ የፍርድ ቤት ዳኝነትንና የእጣ ዳኝነትን እናወዳድር።
በህግና በስርዓት ትክክለኛ ዳኝነትን መስጠት ነው - የፍርድ ቤቶች ሥራ። ይህንን፣ ከእጣ ዳኝነት ማግኘት አይቻልም።
“ገለልተኛ” መሆን እንደ ዋና መመዘኛ የሚቆጠር ከሆነ ግን፣ ፍርድ ቤቶች ጉዳቸው ነው። እጣ ይበልጣቸዋል። እጣ፣ እንከን የለሽ ገለልተኛ ነውና። ፍርድ ቤቶች፣ በህግና ስርዓት ብቻ ዳኝነት የመስጠት ስራቸውን ባይዘነጉ ይሻላል። አለበለዚያ፣ የእጣ ጠጠር ይተካቸዋል።
የእጣ ጠጠር፣ የተፈጥሮ ህግ ወይም ፍትህ ማለት ነው?
እጣ እና የተፈጥሮ ህግን፣ እንዲሁም እጣ እና የፍትህ ዳንነትን እያዛመድን ለማየት ሞክረናል። እነዚህን ሁሉ የሚገልጽ አንድ ቃል አለ - Dice የሚል የግሪክ ቃል።
ትርጉሙ፣ የተፈጥሮ ህግ ወይም ፍትህ ማለት ነው ይላሉ - ሮበርት ግሬቭስ። Greek Myths በሚለውና ኦክስፎርድ ባሳተመው ግዙፍ መፅሐፋቸው፣ በምዕራፍ 17 ላይ አጣቅሰው ፅፈውታል - “Natural Law or Justice” በማለት።
ግን ደግሞ፣ dice፣ የእጣ ጠጠር ማለት ነው። እጣ ለማውጣትም፣ ቁማር ለመጫወትም ያገለግላል። በዚህ ላይ “እውነትን የሚገልጥ፣ የፍትህ ዳኝነትን የሚያወርድ” ነው ተብሎ ይታመንበት ስለነበር፣ የእጣ ጠጠር፣ እንደ ትልቅ የፈጠራ ውጤት ይከበር ነበር። የግርማዊቷ አምላክ፣ የአቴና ድንቅ የፈጠራ ውጤት ነው ተብሎም ተተርኮለታል ይላሉ - ሮበርት ግሬቭስ። ስለእውነታና ስለተፈጥሮ፣ ስለፍትህ እና ስለዳኝነነት፣ ከእጣ ጋር አዛምደንም አጣልተንም አየን።
እጣና ምርጫ - ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ከባህር ማዶ እስከ አገር ቤት።
በዓለም ደረጃ፣ በፖለቲካ ምርጫ በኩል፣ በቀዳሚነት የሚታወቁ አሉ። ከ2000 ዓመት በፊት፣ የግሪክ በተለይም የአቴንስ ከተማ አስተዳደር በቀዳሚነት ይነሳል። ስርኣት በያዘና ደልደል ባለ የምርጫ ታሪክ ይጠቀሳል።
ከዚያ በኋላ፣ የሮም አስተዳደር አለ - በግሪክ እግር የተተካ። ከዚያ በኋላ ያለው የአውሮፓ የሺ ዓመታት ታሪክ፣ የመፍረክረክና የመጨለም ታሪክ ነው።
እንደገና የመወለድ፣ ከጨለማ የመውጣት፣ ከቅዠት የመንቃት ምልክቶች፣ ጎላ ጎላ ብለው መታየት የጀመሩት “ሬነሰንስ” በተሰኘው ዘመን ነው - እንደገና መወለድ እንደማለት።
ቻርለስ ፍሪማን፣ Awakening በሚለው መፅሀፋቸው፣ ይህንን የአውሮፓ ዳግም ልደት በሰፊው ይተርካሉ - ወደ ሩብ ሚሊዮን በሚጠጉ ቃላት። በተለመደው መፅሐፍ ህትመት፣ 700 ገፅ አይበቃውም። “ዲጂታል መፅሐፍ” መምጣቱ በጀ።
ለማንኛውም፣ ፍሪማን፣ በገፅ 237-40 ስለ ፍሎረንስ ከተማ አስተዳደር ያብራራሉ። የዛሬ 650 ዓመት፣ የከተማዋ የነዋሪዎች ብዛት፣ ወደ 150 ሺ ገደማ ቢሆን ነው። ግማሾቹ ሴቶች ናቸው። የፖለቲካ ምርጫ ውስጥ አይገቡም። ህፃናትም የሉበትም። የፖለቲካ ምርጫ ውስጥ የመግባት እድል ያላቸው 50 ሺ ሰዎች ቢሆኑ ነው። ታዲያ፣ የብቃት መመዘኛዎችን ማሟላት ያስፈልጋል።
የመተዳደሪያ ሙያና ገቢ ያለው፣ አነሰም በዛ ንብረት ያፈራ፣ ወንጀል ያልፈፀመ ነው፣ ወደ ምርጫ የሚገባው። ይሄ ሁሉ ከተጣራ በኋላ፣ የምርጫ ተወዳዳሪዎች ቁጥር ይታወቃል። የከተማው የአስተዳደር ምክር ቤት አባላት 10 ብቻ ናቸው። ተወዳዳሪዎች ደግሞ ከ1 ሺህ ይበልጣሉ። አንዳንዴም ከ5 ሺህ በላይ ይሆናሉ።
ከዚያ ምርጫው ይካሄዳል - በእጣ።
እጣ የወጣላቸው 10 ተወዳዳሪዎች፣ ከተማዋን ያስተዳድራሉ።
ታዲያ፣ ስልጣናቸው፣ ለሁለት ወራት ብቻ ነው። እንደ እቁብ እጣ፣ ሌሎች ተረኛ ባለዕጣ ተወዳዳሪዎች ስልጣን ይረከባሉ። በየሁለት ወሩ፣ ነባሮቹ ተመራጮች ይወርዳሉ፣ አዳዲስ ተመራጮች ስልጣን ይረከባሉ - “እጣ የመረጣቸው አስተዳዳሪዎች”።
በፍሎረንስ፣ ከዚያ በፊትም፣ በሮምና በግሪክ ጥንታዊ የምርጫ ታሪክ ውስጥ፣ የእጣ ምርጫ፣ ተመራጭ የምርጫ ዘዴ ነበር - እድልዎ የሌለው ገለልተኛ ምርጫ። ማጣሪያው ላይ በብቃት መመዘኛና በሰዎች ድጋፍ ነው፤ የፍፃሜው ምርጫ ደግሞ በእጣ ይወሰናል።
የአገራችን የምርጫ ህግ፣ ከፍሎረንስ ይለያል - የተገላቢጦሽ ነው።
የፍፃሜው ምርጫ የሚወሰነው፣ በሰዎች የድጋፍ ድምጽ ነው። ማጣሪያውስ? የብቃት መመዘኛ አለ። ተወዳዳሪዎች ከብዙ ግን፣ ቁጥራቸውን ለመቀነስ እጣ ይወጣል። ስለዚህ፣ ማጣሪያው በእጣ ነው።


Read 9186 times