Tuesday, 25 May 2021 00:00

አልኮል በስሱ ሲጎነጩትም ቢሆን አእምሮን እንደሚጎዳ በጥናት ተረጋገጠ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አልኮልን በመጠኑ መጎንጨትም ሆነ አብዝቶ መጠጣት በአእምሮ ጤንነት ላይ ጉዳት ማስከተሉ እንደማይቀር በጥናት ማረጋገጣቸውን የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
አልኮል በመጠኑ አልፎ አልፎ መጎንጨት ጉዳት አያስከትልም የሚለውን የብዙዎች አመለካከት አፈር ድሜ ያስገባው የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ አልኮል በመጠኑ መጎንጨትም ቢሆን በማዕከላዊ የነርቭ ስርዓት ላይ የጤና እክልን እንደሚያስከትል ማረጋገጡን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
ከዚህ በፊት በተደረገ አንድ ጥናት፣ በቀን አንድ ብርጭቆ ቀይ ወይን መጎንጨት የመርሳት በሽታንና ሁለተኛውን አይነት የስኳር በሽታ ጨምሮ የተወሰኑ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚረዳ መገለጹን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይሄኛው ጥናት ግን በመጠኑ መጎንጨትም አደጋ አለው ሲል ማስጠንቀቁን ገልጧል፡፡ #አልኮል ከዚህ መለስ አይጎዳም ከዚህ ባለፍ ይጎዳል የሚባል ነገር የለም፤ አልኮል ያው አልኮል ነውና ጤናን ይጎዳል; ሲሉ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉበትን ጥናት የመሩት የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲዋ ዶክተር አንያ ቶፒዋላ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2553 times