Saturday, 22 May 2021 12:54

የዓለማችን ምርጥ የማራቶን አሰልጣኝ ሃጂ አዴሎ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)


- በአትሌቲክስ ስፖርት በሯጭነት፤ በአሰልጣኝነት እና በአትሌቶች ተወካይነት እየሰራ ከ30 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡
- በኢሊቴ ስፖርት ማኔጅመንት ኢንተርናሽናል (ESMI) ውስጥ በአስልጣኝነት እና ተወካይነት ሲያገለግል 15 ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፤ ከ110 በላይ
      አትሌቶች አብረውት ይሰራሉ፡፡
- ማሬ ዲባባ ፣ ፈይሳ ሌሊሳ ፣ ሌሊሳ ዲሳሳ ፣ ሩቲ አጋ ፣ ሹራ ቂጢሳ ፣ ሮዛ ደረጄ ፣ ማሚቱ ዳስካ ፣ ድሬ ቱኔ ፣ ታይባ ኤርኪሶ ፣ አማኔ ጎበና እና ታደሰ
      ቶላ ውጤታማ ካደረጋቸው አትሌቶች ይጠቀሳሉ፡፡
- ኢትዮጵያ ውስጥ የኦሎምፒክ ማራቶን ሚኒማ የሚያሟሉ አትሌቶች ከ50 በላይ ይሆናሉ፡፡
- ‹‹የኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን ምርጫ አልቋል ብዬ ነው የማምነው፡፡››
- ቀነኒሳ እንደማንኛውም የማራቶን አትሌት 4 እና 5 ወራት ትኩረት አድርጎ ልምምድ ቢሰራ በየትኛውም የማራቶን ውድድር ላይ 2 ሰዓት እና ከ2
     ሰዓት በታች ለመሮጥ ይችላል፡፡
- ቶኪዮ 2020 ላይ በማራቶን ኢትዮጵያውያውያን ከሜዳልያ ውጭ ይሆናሉ የሚል ግምት የለኝም፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ሁለት ሁለት ሜዳልያዎችን….


          የ46 ዓመቱ  እውቅ የማራቶን አሰልጣኝ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች ተወካይ ሃጂ አዴሎ ትውልዱ አርሲ ውስጥ ጭላሎ ተራራ አቅራቢያ ነው፡፡ 13 ወንድሞችና እህቶችን ባፈራው ሰፊ የገበሬ ቤተሰቡ ተወልዶ ያደገ ሲሆን ከአትሌቲክስ ስፖርት ጋር የተዋወቀው ገና በ14 ዓመቱ በትምህርት ቤት ውድድር ለመሳተፍ ከቻለ በኋላ ነው፡፡  በአገር አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከታላቁ ኃይሌ ገብረስላሴ ጋር አርሲን እንዲወክል  ተመርጦ አዲስ አበባ ላይ በተሳተፈበት የማራቶን ውድድር 12ኛ ደረጃ ነበረው፡፡ ከዚህ ውጤቱ በኋላም የማረሚያ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብን ለመቀላቀል ችሏል፡፡ በተለይ በማራቶን ሯጭነት ላይ አተኩሮ በመስራት በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ጥሩ ውጤቶችንም አስመዝግቧል፡፡ በ1996 እኤአ ላይ  በአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ ስድስተኛ ደረጃ ያገኘ ሲሆን ከፍተኛ ውጤቱን ያስመዘገበው ደግሞ በ1997 እና 1999 እኤአ ላይ  የግራዝ ማራቶን ሁለት ጊዜ በማሸነፉ ነው፡፡ በግራዝ ማራቶን ላይ የግሉን ምርጥ ሰዓት  2 ፡12፡ 25 በሆነ ጊዜ አስመዝግቧል። ከሯጭነቱ የተገለለው  ከ 2001 እስከ 2003 እኤአ  በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሶስት ማራቶኖችን ከሮጠ በኋላ ነው፡፡
ሯጭነቱን ቢያቆምም ከአትሌቲክስ ስፖርት ግን ሙሉሙሉ አልራቀም፡፡  ከ2006  እኤአ ጀምሮ ታዋቂው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተቋም ኢሊቴ ስፖርት ማኔጅመንት ኢንተርናሽናል (ESMI) የሚሰራበት እድል ተፈጥሮለታል፡፡ በዓለም አቀፉ ተቋም ከታዋቂው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማናጀር ሑሴን ማኬ ከተገናኘ በኋላ የአትሌቲክስ ህይወቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል፡፡ በESMI ውስጥ የኢትዮጵያ አትሌቶች ተወካይ እና  አሰልጣኝ ሆኖ መስራት ከጀመረ በኋላ ባለፉት 15 ዓመታት በመስራት በማራቶን፤ የጎዳና ላይ ሩጫዎችና በረጅምና በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ምርጥ የኢትዮጵያ ሯጮችን በማፍራት ስኬታማ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በማራቶን አሰልጣኝነቱና በኢትዮጵያ አትሌቶች ተወካይነቱ ከቤተሰቦቹ ጋር መስራቱም ልዩ ያደርገዋል፡፡ በስልጠናዎቹ ላይ ረዳቶቹ ወንድሞቹ ቃሲሜ አዲሎ እና ሞገስ አዲሎ  ናቸው፡፡
ዋና አሰልጣኝ ሃጂ አዲሎ  በተለይ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ከበሬታ ባለው የማራቶን ሩጫ ላይ መስራቱ ያስደስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶችን  በዓለም የማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች   ከፍተኛ ስኬት እንዲያገኙ ወሳኝ ሚናውን እየተጫወተም ይገኛል፡፡  የስልጠና ዘይቤው፤ ከአትሌቶች ጋር ያለው ቤተሰባዊ ግንኙነት እና የልምምድ መርሃ ግብሮቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱ ምርጥ የማራቶን  አሰልጣኞች ተርታ አሰልፎታል፡፡ በታላላቅ የዓለማችን ከተሞች በሚዘጋጁ የማራቶን ውድድሮች ላይ በሁለቱም ፆታዎች ተደራራቢ ድሎችን፤ የቦታ ሪከርዶችንና ፈጣን ሰዓቶችን የሚያስመዘግቡ አትሌቶችን የያዘ ነው፡፡ በዓለም የማራቶን ሪከርድ የመሻሻል ሂደት ላይ ብቁ አትሌቶችን በየጊዜው በማውጣት  ግንባር ቀደሙ ተጠቃሽ ነው፡፡
ሃጂ እና ወንድሞቹ ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው በሚገኙ ኮረብታማ ስፍራዎች ፤በባህር ዛፍ ጫካ በተዋጡ መንገዶች ላይ የማራቶን አትሌቶቹ በተናጠል እና በቡድን በሚያሰሩበት ፍልስፍናቸው እየተከበሩ መጥተዋል፡፡ የአዴሎ ቤተሰብ በስራቸው ከሚገኙ አትሌቶች ጋር በሚሰሩት ስልጠና  ላይ አብረው ይሮጣሉ፡፡  ይህም የአትሌቶቻቸውን ወቅታዊ ቁመና እና  ቅርፅ ለመመልከት አስችሏቸዋል። የስልጠና ስትራቴጂያቸው ከአትሌቶች ጋር  የቀረበ ግንኙነት በመፍጠር መስራት ነው፡፡ ባለፉት  አስርት ዓመታት በእነሱ ስልጠና ውስጥ  ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አትሌቶች ተሰባስበዋል፡፡ በስልጠና ፍልስፍናቸው የሚይዟቸው አትሌቶች ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ በፍላጎት እና በደስታ የሚሰሩ እንዲሆኑ አድረገዋል፡፡ በእያንዳንዱ የሥልጠና መርሃ ግብሮች አሰልጣኞቹ ግልፅ ውይይት ከአትሌቶቹ ከደጋፊዎች  ሌሎች አጋሮች ያደርጋሉ፡፡ እያንዳንዱ አትሌት በየስልጠናው የሚያሳየው እድገት፣ የአእምሮ፣ የአካልና የስሜት ጤንነትን ከግምት ውስጥ በሚያስገባ አሰራራቸውም ለመታወቅ በቅተዋል። ከ90 በላይ ምርጥና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን አትሌቶች በጋራ ሊያከናውኗቸው የሚችሏቸውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሥልጠናዎችን መፍጠር መቻላቸውም ያስደንቃል፡፡ ከአትሌቶቻቸው ጋር ያላቸው ቤተሰባዊ ግንኙነት በስልጠናው ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ብዙዎቹን አትሌቶች ከስፖርቱ በሚያገኙት ገቢ እና ሌሎች የገንዘብ ሽልማቶች  ምክር በመስጠት፤ ስለ ኢንቨስትመንት በማማከርና የግል ልምዶችን በማካፈልም ይሰራሉ፡፡
ዋና አሰልጣኝ ሃጂ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያለው ሚና በማራቶን ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡   በረጅምና መካከለኛ ርቀት የትራክ ውድድሮች ላይም አትሌቶችን በማሰልጠንና በወኪልነት በማገዝም ይሰራል፡፡ በዚህ አቅጣጫም የዓለም አትሌቲክስ ፈጣን ሯጮችና ሻምፒዮኖችን እያፈሩ ናቸው። ለቶኪዮ 2020 በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት ላይ የኢትዮያ ተስፋ ሊሆኑ ከሚችሉ አትሌቶችም ጋር በመስራት ላይ ናቸው፡፡  በ800 ሜትር ሴቶች ሃብታም አለሙ ፣ በ 1,500 ሜትር  ወንዶች የዓለም ሪከርድ ባለቤት ሳሙኤል ተፈራ ፣ በ5ሺ ሜትር በዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ የተጎናፀፈው  ሰለሞን ባረጋ እና በ10,000 ሜትር የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮኗ ሰንበሬ ተፈሪ ይገኙበታል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ሃጂ በሙያ ልምዱ የነበረው ፅኑ ምኞት  በዓለም አትሌቲክስ ላይ ከምርጦች ተርታ መሰለፍ ሲሆን ይህንም ከሞላ ጎደል አሳክቶታል ማለት ይቻላል፡፡ በማራቶን ስልጠናው ብቁ አትሌቶችን ለይቶ በማውጣት ያለው ብቃት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የንስር ዐይን ያለው አሰልጣኝ አስብሎታል፡፡ ከአትሌቶች ጋር ባለው ቅርበት የቡድን ስራዎችን ሊያሳምር የሚችል ፍልስፍና የሚያሰርፅ ባለሙያ ነው፡፡ በስሩ ያሉ አትሌቶች የጊዜው መሻሻል በማሳየት ከፍተኛ ውጤት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ በሚተጋበት ዲስፕሉንም ብዙዎች አክብረውታል። ለማራቶን ያለው መሰጠት፣ ሙያዊነት እና የአባትነት አቀራረብ በምርጥ የማራቶን አትሌቶቹ ላይ ጥሩ ውጤት በማስገኘት ተረጋግጧል። ማሬ ዲባባ፣ ፈይሳ ሌሊሳ፣ ሌሊሳ ዲሳሳ፣ ሩቲ አጋ፣ ሹራ ቂጢሳ፣ ሮዛ ደረጄ፣ ማሚቱ ዳስካ፣ ድሬ ቱኔ፣ ታይባ ኤርኪሶ፣ አማኔ ጎበና እና ታደሰ ቶላ ሌሎችም ታላላቅ አትሌቶች  በዋና አሰልጣኝ ሃጂ ስለጠና አስተዳደር ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡
የሃጂ  አዴሎ ምርጥ አሰልጣኝነት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብቻ አልተወሰነም፡፡ የቻይና አትሌቲክስን በትልቅ ለውጥ ባነቃቀበት ሃላፊነቱም ማሳየት ይቻላል፡፡  የቻይና አትሌቲክስ ፌደሬሽን ሙያዊ ችሎታውን በመፈለግ ዋና ቡድናቸውን እንዲያሰለጥንላቸው በሩን አንኳኩተዋል፡፡ ቻይናውያን አትሌቶችም ከኮቪድ  በፊት ከኢትዮጵያ አትሌቶች ጋር ተቧድነው በመስራት በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ለውጥና እድገት አሳይተዋል። አንዳንዶቹ በማራቶን ከነበራቸው የግላቸው ምርጥ ሰዓት 11 ደቂቃዎች በላይ አሻሽለዋል፡፡
አሰልጣኝ ሃጂ ሯጭ በነበረበት  ዘመን  በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር የሚያስፈልገውን ሁሉ ችሎታ ቢኖረውም፣ ያንን ለማድረግ እድሉ በጣም አናሳ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ምክንያቱ ለአትሌቶች ውድድሮችን ማመቻቸት የሚችሉ በቂ የስፖርት ማኔጅመንት ኩባንያዎች ባለመኖራቸው እንጅ ሌላ አልነበረም፡፡ ይህኑ ተገንዝቦ ከስልጠናው ባሻገር በአሁኑ ትውልድ አትሌቶች  ለይ  ተመሳሳይ ችግሮች እንዳያጋጥሙ በማሰብም ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ በትልልቆቹ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ላይ በተደጋጋሚ የሚያሸነፉ አትሌቶችን በመምራት በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ክብርና ዝናውን መጎናፀፍ ቀጥሏል፡፡  ይህም ለአትሌቶች አጠቃላይ ደህንነት ትኩረት የሚሰጥ ልዩ ባለሙያ አድርጎታል፡፡ ስለዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ከቅርብ ጊዜ በፊት በተፃፈ ዘገባ ላይ የኤሊት ስፖርት ማነጅመንት መስራች ሁሴን ማኬ “ሀጂን ጥሩ አሰልጣኝ የሚያደርገው እያንዳንዱን አትሌት በተናጠል የማንበብ ችሎታ ስላለው ነው፤ በጣም አስተዋይ እና እውነተኛ  ሰው ነው።" ብሏል፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት በሯጭነት፤ በአሰልጣኝነት እና በአትሌቶች ተወካይነት  ከ35 ዓመታት በላይ ከሰራው ሃጂ  አዴሎ ጋር ስፖርት አድማስ ይህን ልዩና ወቅታዊ ቃለምልልስ አድርጓል
***

Read 1137 times