Saturday, 15 May 2021 00:00

ዘሚ የኑስ፤ የሥነ-ውበት ባለሙያና የኦቲዝም ማዕከል መስራች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 "--በርካታ አርአያ የሆኑኝ ሰዎች ቢኖሩም፣ ከሁሉም የላቀችው አርዓያዬ ግን እናቴ ናት። ዛሬም ድረስ የምመራባቸውን የሕይወት መርሆዎች የቀሰምኩት ከሷ ነው። ከዋና ዋናዎቹ መካከልም፤ ሁሉንም ሰው እኩል ማክበር የሚለው መርህ ትልቁ ነው።--"
        ባለፈው ሰኞ ለሊት በኮሮና ሳቢያ ህይወታቸውን ባጡት  ወ/ሮ ዘሚ የኑስ የተሰማንን ሀዘን እየገለፅን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡
      ዝግጅት ክፍሉ

             የተወለድኩት ጥር 9 ቀን 1951 ዓ.ም አዲስ አበባ ነው። አባቴ ትጉህ ሠራተኛ ነበር። ልጅነቱን በእረኝነት ያሳለፈው አባቴ፤ እውቅ የወንዶች ሙሉ ልብስ ሰፊ ነበር። ገጠር የተወለደችው እናቴ፤ የ9 ዓመት ልጅ ሳለች ነው የተዳረችው። ሁለቱም ወላጆቼ የትምህርት ቤትን ደጃፍ አልረገጡም። ነገር ግን እጅግ አስተዋዮች ነበሩ።
በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ለወጣቶች አስጊ የነበረውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በመፍራት፣ በ17 ዓመቴ ወደ ጣልያን ተሰደድኩ። በጣልያን ትምህርት እየተማርኩ ጎን ለጎንም፣ በአገሪቱ ማዕከላዊ የስደተኞች ፅሕፈት ቤት ውስጥ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ። ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በጥምረት በሚንቀሳቀሰው ፅሕፈት ቤት ውስጥ ሥሰራ፣ በጣልያን በኩል ወደ ሌሎች አገራት የሚሻገሩ ብዙ ሺ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞችን አስተናግጃለሁ።
በ1973 ዓ.ም ለአጭር ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ  በመጣሁ ጊዜ፣ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት፣ “ፀረ-አብዮተኞች ከአገር እንዲኮበልሉ እረድተሻል" በሚል በመወንጀል፣ ጥቁር መዝገብ ውስጥ አሰፈረኝ። እንደመታደል ሆኖ ግን ለሁለተኛ ጊዜ  በማምለጥ፣ አሜሪካ ገባሁኝ፡፡ እስከ 1987 ዓ.ም ድረስም ለ14 ዓመታት ያህል በስደት ኖርኩኝ።
እዛም እያለሁ በመዋቢያ ንጥረ ነገሮችና በአጠቃቀማቸው ዙሪያ ሥልጠና ከወሰድኩ በኋላ፣ በፊልም ማዕከልነቷ በምትታወቀው ሆሊውድና በቤቨርሊ ሂልስ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ቦታዎች፣ በቆዳና ፀጉር እንክብካቤ ላይ በማተኮር በሙያዬ እሰራ ነበር። ስራው በዘርና በባህል፣ በአስተዳደግና በኑሮ ደረጃ እጅጉን ከሚለያዩ ብዙ አይነት ሰዎች ጋር በማገናኘት፣ የሕይወት ትምህርት እንድቀስም እድል ሰጥቶኛል።
ወታደራዊው መንግስት መውደቁን ተከትሎ፣ ለራሴ በገባሁት ቃል መሰረት፣ በ1983 ዓ.ም ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ። በስራ አጥነት ተስፋ የቆረጡ ብዙ ወጣቶችን ስመለከት፣ ልቤ በሃዘን ተሰበረ። ይሄኔ ነው ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልዬ በመምጣት፣ ወጣቶችና ህፃናት ላይ በማተኮር፣ ለምወዳት ሀገሬ የድርሻዬን ለማበርከት የወሰንኩት። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ በኋላ፣ የስራ እድል ለመፍጠርና የሙያ ክህሎቴን ለወገኖቼ ለማካፈል በማሰብ፣ በሀገሪቱ ፈቃድ የተሰጠው የመጀመሪያውን የውበት ማሰልጠኛ ት/ቤት ከፈትኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ በኒያና የውበትና ሞዴሊንግ ት/ቤት፣ ከ6 ሺ በላይ ወጣት ሴቶችና ወንዶችን አሰልጥኜ አስመርቄያለሁ።
የውበት ት/ቤቱ፣ የማስተምርበት ብቻ ሳይሆን የምማርበትም ቦታ ነው ማለት እችላለሁ። እንዴት? ቢባል፣ የተለያየ ህይወትን አልፈው ከሚመጡ ብዙ ተማሪዎች ጋር ስለምገናኝ፤ ስለ ወጣቶች ኑሮ፣ ስለ ፍላጎቶቻቸውና ስለሚገጥሟቸው ፈተናዎች ጥልቅ እውቀት አግኝቼበታለሁና፡፡ በውበት ሙያ ሰልጥነው ለመስራት የሚፈልጉ በርካታ ወጣቶች ቢኖሩም፣ ብዙዎቹ ገንዘብ ከፍለው ለመሰልጠን አቅም አልነበራቸውም። ይሄን በማስተዋል መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነጻ የትምህርት እድል አመቻቸሁ። ነፃ የትምህርት እድሉ፤ በአብዛኛው ተገድደው በወሲብ ስራ፣ በቤት ሰራተኝነትና በቀን ስራ ተሰማርተው ለነበሩ ወጣት ሴቶች በእጅጉ ጠቅሟል። ከስራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን፤ ሰብእናቸውን የሚያበለጽግና ተደብቆ የቆየ የግል ዝንባሌያቸውን የሚያዳብር፤ እንዲሁም አኗኗራቸውን የሚቀይርና በራስ የመተማመን መንፈሳቸውን የሚያሳድግ የሕይወት ክህሎት ስልጠና ለመስጠት በትጋት ሰርቻለሁ። ዛሬ አብዛኛዎቹ ወጣቶች በውበት ሳሎኖች ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ ሆኑ የተወሰኑት ደግሞ የራሳቸውን የውበት ሳሎኖችና ስፓዎች ከፍተዋል።
በዚህ መሃል ግን፣ ትንሹ ልጄ የኦቲዝም ችግር እንዳለበት በባለሙያ ተነግሮኝ፣ ከባድ ፈተና ውስጥ ገባሁ።። ያልወሰድኩት ት/ቤት የለም። ሁሉም ግን “የተለየ ባህሪ አለው” እያሉ በየተራ አሰናበቱብኝ፡፡ ይሄኔ ነው የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ህፃናት ያሏቸው ወላጆች፣ የሚጋፈጧቸውን ፈተናዎች በቅጡ የተገነዘብኩት። ኦቲዝም እንደ ጤና ችግር ሳይሆን እንደ እርግማን እየተቆጠረ፤ በርካታ ህፃናት “አንዳች ነገር ተጠናውቷቸዋል” በሚል በሰንሰለት ታስረው፣ ጨለማ ውስጥ እንደሚወረወሩ አስተዋልኩ። አንዳንዶቹማ በቤተሰባቸውም ጭምር  ይገለላሉ።
በኢትዮጵያ የኦቲዝም ችግር ያለባቸውን ህፃናት የማስተናገድ አቅም ያለው ት/ቤት ፈልጌ ሳጣ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ነበረብኝ። ልጄን ይዤ ወደ አሜሪካ ብሄድ፣ መሰል ት/ቤቶችን እንደ ልቤ እንደማገኝ አውቃለሁ። ሆኖም በመሄድና እዚህ በመቅረት መሃል ብዙ ዋለልኩኝ። ከሁሉም በፊት ከገባሁበት ከባድ ውዥንብርና ተስፋ መቁረጥ ወጥቼ፣ ከእውነታው ጋር ለመጋፈጥ ቆርጬ መነሳት ነበረብኝ። ከዚያም ወደ አሜሪካ የመሄዱን ነገር እርግፍ አድርጌ ተውኩት። ምንም እንኳን ለልጄ የሚሻለው አሜሪካ ቢሆንም፣ እሱን ይዤ ስሄድ፣ እዚህ ያሉ ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ህጻናት፣ የህሊና እረፍት እንደማይሰጡኝ አሰብኩኝ። እናም እዚሁ ሀገሬ ላይ ሆኜ፣ ህብረተሰቡን ስለ ኦቲዝም ማስተማርን፣ የሕይወት ዓላማዬ አድርጌ ተነሳሁ። ልጄንና ተመሳሳይ የጤና እክል ያለባቸውን ህፃናት ለመርዳትና የወላጆችን በተለይም የእናቶችን ሸክም ለመጋራት በቁርጠኝነት ወሰንኩ።
በኢትዮጵያ ስለ ኦቲዝም ግንዛቤ የመፍጠር ጉዞዬን የጀመርኩት፣ ከውበትና ፋሽን ሙያ ጋር በተያያዘ ለጋዜጠኞች በምሰጣቸው ቃለ ምልልሶች ላይ፣ እግረ መንገዴን ስለ ኦቲዝም በመናገር ነበር። ኦቲዝምን የተመለከቱ መረጃዎችን (ምልክቶቹን፣ ተፈጥሮአዊ ሁኔታውን፣ ስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖዎቹን) ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት ፣ የተለያዩ ሚዲዎችን እጠቀም ነበር። በዚህ መንገድ ጉዳዩ በስፋት እየታወቀ መጣ። ነገር ግን ግንዛቤ መፍጠር ብቻውን በቂ አልነበረም። በ1994 ዓ.ም ጆይ የኦቲዝም ማዕከልን ከፈትኩ። ጆይ የኦቲዝም ማዕከል፣ በኢትዮጵያ የኦቲዝም ችግር ያለባቸውን ህፃናት ተቀብሎ የሚያስተናግድ የመጀመሪያው የኦቲዝም ማዕከል ነው። ማዕከሉ ስራ ሲጀምር ከተጋፈጥናቸው ትላልቅ ፈተናዎች መካከል፣ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረትና የገንዘብ አቅም ውስንነት በዋናነት ይጠቀሳሉ። ስለ ኦቲዝም ያለኝን እውቀትና ግንዛቤ ለማስፋት ጥረት ማድረግ ነበረብኝ። በምርምርና ከወላጆች የድጋፍ ሰጪ ቡድን ጋር በሚደረግ የተሞክሮ ልውውጥ ብዙ ግንዛቤ አግኝቻለሁ። ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሃገር ባለሙያዎች፣ ኦቲዝም ተኮር መረጃዎችን ለማግኘት ብዙ ተግቻለሁ። በበርካታ ሀገራት በኦቲዝም ዙሪያ የሚሰጡ ወርክ-ሾፖችንና ስልጠናዎችን እያሰስኩ ተሳትፌያለሁ። እነዚህም ስልጠናዎች፣ ስለ ኦቲዝም ያለኝን እውቀትና ግንዛቤ በቅጡ አጎልብተውልኛል። እኔም ያገኘሁትን እውቀት ለማዕከሉ ሰራተኞች በማጋራት፣ አንድ ፕሮግራም ለመቅረጽ በቃን። ፕሮግራሙ የልጆቹን የየግል ፍላጎት በማወቅና በመለየት፣ ለእያንዳንዳቸው ተስማሚ የሆነ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ነው።
በተለይ “አቡጊዳ ፎነቲክስ” በሚል የፈጠርኩት አዲስ የቋንቋ ስርዓተ ትምህርት፣ ውጤታማ በመሆኑ በእጅጉ አስደስቶኛል። በግዕዝ ፊደላት ላይ ተመርኩዞ የተቀረፀው ስርዓተ ትምህርቱ፤ ሀገር በቀል እውቀትና መሳሪያዎችን ከድምፅ ልሳኖች (ፎነቲክስ) ጋር በማቀላቀል የሚያቀርብ ነው። ፕሮግራሙ ተማሪዎች የመንጋጋ ጡንቻዎቻቸውን እንዲያንቀሳቅሱ፣ ድምጾችንና ቃላትን እንዲፈጥሩና እንዲያወጡ እንዲሁም ቃላትን በመገጣጠም ዓረፍተ ነገሮችን መስራት እንዲችሉ የሚያግዛቸው ሲሆን ትኩረታቸውን ለመሰብሰብ፣ አቅማቸውንና የማሰብ ክህሎቶቻቸውን ለማዳበርም ይረዳቸዋል።
ይህንን ፕሮግራም ከጀመርን ወዲህ የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ህፃናት፣ የማንበብና የመፃፍ ክህሎት ላይ አስደናቂ መሻሻል አይተናል። የ”አቡጊዳ ፎነቲክስ” ፕሮግራም መጀመሩን ተከትሎ፣ የልጆቻችን ችሎታ ተሻሽሏል። ለምሳሌ ሳሚያ የተባለችው ታዳጊ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ13 ዓመት እድሜዋ  ልሳኗ ተከፍቶ መናገር ጀምራለች። የኔም ልጅ ጆጆም ቢሆን ፣ ማንበብና ፍላጎቱን በአንደበቱ መግለጽ ጀምሯል። ልጄ እራሱን ችሎ ስልኬ ላይ መደወልና ማነጋገር በመቻሉ፣ የትም ብሆን እንኳን ድምጹን መስማት ችያለሁ። ለስራ ከቤት ስወጣ፣ እንደ ድሮው በሀዘንና በብቸኝነት ስሜት በመስኮት አሻግሮ መመልከቱን ትቷል። አሁን ነገሮች ተቀይረዋል። ልጄ ወደ ት/ቤት ሲሄድም ሆነ በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ለመሳተፍ ከአጠገቤ ሲለይ፣ ፊቱ በደስታና በፈገግታ ተሞልቶ እጁን እያወዛወዘ “ባይ! ባይ!” ይለኛል እንጂ፣ እንደ ወትሮው የሃዘንና የመከፋት ስሜት አይታይበትም።
በአሁኑ ጊዜ የኦቲዝም ችግር ያለባቸውን እንቁ የሆኑ 80 ታዳጊዎችን በተቋሙ ውስጥ ተቀብለን እያስተናገድን  ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል በምንሰጣቸው ጠንካራ ፕሮግራሞችና ህክምናዎች ከፍተኛ መሻሻል ማሳየታቸውን ስናገር ደስታ ይሰማኛል።
ከጎናችን ሆነው ያገዙንን ሁሉ አመሰግናቸዋለሁ። በተለይ ደግሞ ለግሎባል ፈንድ ፎር ችልድረን፣ ለዴቪድ ልዊስ ፓካርድ ፋውንዴሽን፣ ለፊንላንድ ኤምባሲ፣ ለኢትዮጵያ መንግስትና ድጋፋቸውን ሳይሰስቱ  በቸርነት ለለገሱን ግለሰቦችና ተቋማት ሁሉ ምስጋናዬ ወደር የለሽ ነው። በእርግጥ የባለቤቴ፣ የቤተሰቤና የጓደኞቼ አስተዋፅኦም እጅግ ከፍተኛ ነውና፣ እነሱም ምስጋና ሲያንሳቸው ነው።
የልህቀት ማዕከል በመክፈት ፕሮግራሙን የማስፋት እቅድ አለኝ። ለህንፃ መስሪያ የሚሆን ቦታ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ተረክበናል። ለግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የማሰባበስ ስራም ተጀምሯል። ፕሮጀክቱን እንድናጠናቅቅ ሊያግዙን የሚፈልጉ በርካታ በጎ ፈቃኞች እንደምናገኝ እርግጠኛ ነኝ።
በቅርቡ በፋና ኤፍኤም 98.1 ሬዲዮ፣ ዘወትር እሁድ ከምሽቱ 1፡00-2፡00 የሚተላለፍ “ያገባናል” የተሰኘ ፕሮግራም ጀምሬአለሁ። ይሄም ከበርካታ ሰዎች ጋር ለመገናኘትና ተሞክሮዬን ለማካፈል እንዲሁም ከሌሎች ለመማር ትልቅ እድል ይፈጥርልኛል ብዬ አምናለሁ።
በርካታ አርአያ የሆኑኝ ሰዎች ቢኖሩም፣ ከሁሉም የላቀችው አርዓያዬ ግን እናቴ ናት። ዛሬም ድረስ የምመራባቸውን የሕይወት መርሆዎች የቀሰምኩት ከሷ ነው። ከዋና ዋናዎቹ መካከልም፤ ሁሉንም ሰው እኩል ማክበር የሚለው መርህ ትልቁ ነው። የአንድ ወገን መረጃ በመስማት ብቻ ማንም ላይ አለመፍረድ፤ በማንኛውም ዓይነት ግንኙነት ውስጥ በጎ ሀሳብ መያዝ፤ እንዲሁም የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች በሙሉ በአሸናፊነት መወጣት እንደምችል ማመን እንዳለብኝ አስተምራኛለች። “አንቺ የምትፈልጊውን ነገር፣ ራስሽ ካልሰራሽው ማን ይሰራዋል?” እያለችም ታበረታታኝ ነበር። ዛሬም ድረስ፣ ማንኛውንም ነገር ከመወሰኔ በፊት እናቴን አስባታለሁ። ሌላ የህይወቴ ኃይል ልጄ ቢላል ነው። ውጥኔን ለብቻዬ እንደጀመርኩትና ወደፊት ብቻዬን ብሆን እንኳን ፈተናዎችን ማሸነፍ እንደምችል ያስታውሰኛል። የኦቲዝም ችግር ካለበት ልጄ ከጆጆ ጋር ፍቅር እየሰጠሁት አብሬ መኖሬ፣ ዓለምን በተለየ መነፅር እንድመለከት አስተምሮኛል።
በግል ህይወትና በስራ ላይ ፈተናዎችን መጋፈጥ የተለመደ ነው ብዬ ስለማምን፣ በየቀኑ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ቀድሜ ራሴን አዘጋጃለሁ። ለውሳኔ አለመጣደፍን ተምሬአለሁ። እንቅፋቶች አላማዬን እንዲያሰናክሉብኝ ወይም ብርታቴን እንዲሸረሽሩብኝ አልፈቅድም። በቀኝ ጣቴ ላይ ያጠለቅኩት ቀለበት ይህን ያስታውሰኛል።
በኦቲዝምና በሌላ በማንኛውም የጤና እክል የሚቸገሩ ሁሉም ህፃናት፣ በሰው ልጅነታቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ሲያገኙና በህብረተሰቡ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በነጻነት ሲሳተፉ ማየት እሻለሁ። በኢትዮጵያ የኦቲዝም ችግር ባለባቸው ልጆች ላይ የሚከሰተውን ስቃይ የሚያባብሱትን አጉል ፍረጃ፣ ማግለልና ባዶ ቤት ውስጥ መቆለፍን ለማስቆም እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት አለብን። የእናቶች እምባ ታብሶ ማየት ምኞቴ ነው። ሌላው ህልሜ ደግሞ፣ ወጣት ልጆቻችንና እህቶቻችን ገላቸውን በመሸጥ ሳይሆን፣ በክህሎታቸው ኑሮአቸውን ሲመሩ ማየት ነው። የቤት ሰራተኞችና የቀን ሰራተኞች፣ በተሰማሩበት የስራ ቦታ ሁሉ ተገቢውን አክብሮት እንዲያገኙ አልማለሁ።
ለወጣት ሴቶች የምለግሰው ምክር እንዲህ የሚል ነው። ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት። የምትሰሩትን እወቁ፤ ለማንኛውም ዓይነት ሱስ ተገዢ አትሁኑ። ማንም እንዲረግጣችሁና እንዲረማመድባችሁ አትፍቀዱ። በውስጣችሁ ምን ያህል እምቅ አቅም እንዳላችሁ ተገንዘቡ፤ እናም ማንንም ለመምሰል ሳይሆን ራሳችሁን ለመሆን ጣሩ። ከምታደንቁት ሰው በምንም አታንሱም፤ አላማችሁን እውን ለማድረግ በትጋት ሰርታችሁ ስኬትን ተቀዳጁ። ከሌሎች ሰዎች ጋር ፈጽሞ አትፎካከሩ። መፎካከር ያለባችሁ ከራሳችሁ ጋር ብቻ ነውና። በሙሉ አቅምና በላቀ ብርታት መስራታችሁን አረጋግጡ፤ ራሳችሁን ውደዱ።  
ምንጭ፡- (“ተምሳሌት፡ ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች” ፤2007)


Read 1898 times