Saturday, 08 May 2021 13:50

ሳልሳዊው እማኝ.....

Written by  ህላዊ ተስፋዬ
Rate this item
(1 Vote)

   የማዕዱ ወለል ፩
አዎ ይህንንም ቦታው ላይ ተገኝቻለሁና እመሰክራለሁ።
በጊዜያት ውስጥ ቀናቶች ላይ ተመላልሻለሁ፡፡ ሌት በጨረቃ፣ ቀን በብርሃን፣ በእነዛ ደካማ የኑሮ ጠል ባጠላባቸው ምስኪን ፍጡሮች እጅ ሰርክ እየተገፋሁ እጓዛለሁ፡፡
ከመሰሎቼ ጋር ተስፋ፣ ምኞት፣ ደስታ፣ ሃዘንም በሌለበት ምዕራፍ ላይ ደጋግመን እንሄዳለን፡፡ ከሚጋረፍ የነጎድጓድ ባህር አንስቶ ፀጥታው ከነገሰበት የተነጠፈ የውሃ ምንጣፍ ላይ እንንሳፈፋለን፡፡
ይህም እንዲሆን ተፈቅዷልና፣ አንዱ ለመኖር አንዱን አጥምዶ በሚያድርባት ምድር፣ የሰው ልጅ ከባህር የሚያጠምደውን ምግቡንና እሱንም ጭምር ተሸክመን በባህር እየተንሳፈፍን፣ ከባህሩ ወደ የብስ እናጓጉዛለን። የኛ ህይወትም እውነታ ይህ ምልልስ ነው፡፡
ከመሃል ውሃ ውስጥ የተሰገረው የሰው  ልጅ መና፣ እኛ ወለል ላይ ተጥሎ፣ አለሁ ለማለት ወለላችን ላይ ሲንፈራገጥ የመጀመሪያ ወዙን የሚቀባው እኛኑ ነው፡፡ አዲስ ነገር በሌለበት በዚህ ምልልስ ዑደት ላይ ያቺ የተለየች የመጀመሪያዋ ቀንን እንዴት አላስታውስ?......
በገሊላ ባህር ላይ ከወንድማማቾቹ ስምዖንና እንድርያስ ጋር ሰርካችንን ወጥተን ባዶ እጃችንን ሳይቀናን የተመለስን ቀን ነው፣ ይህ ራሱን “የሰው ልጅ” እያለ የሚጠራው ሰው፣ በባህሩ ዳርቻ ሲጓዝ እነዚህን የቆዘሙ ወንድማማቾች የተመለከተው። ይቀርባቸውና በአንድ እግሩ እኔን ተጭኖ  እንዲህ ይላቸዋል።
“ከኋላዬ ተከተሉኝና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ”
ለመጀመሪያ ጊዜ እግሩ ወለሌን ሲረግጥ ከጫማው ተርፋ የወጣች ጣቱ ስትነካኝ፣ በአንዳች ክብደት ግርማ ያለው ምድርን የሚበልጥ የመልዕኮት ስሜት ነበረው። እልፍ አእላፍ ሰዎች ሳመላልስ ለኖርኩት እኔ፤ ተመላላሾቹ እነዚህ ተሰብስበው እንደ  ቅንጣቱ ዳና አይሆኑም ነበር፡፡
ለኔ ይህ ሰው በዛች ከፊል ንኪያ ብቻ ሃያልነቱ ቢገባኝም፣ በባህሩ ላይ ስንበታዬ ያስተማረኝ፣ የሰው ልጆች ግን በተደጋጋሚ ይዘነጉና ይጠራጠሩ ስለነበር በተደጋጋሚ ዳርቻው ላይ ቆሞ በቃል አፋቸውን ከፍተው እስከሚያዩት ድረስ ሲያስተምር፤ በግብሩ ደግሞ ከፍ ያለ ማእበል በእጁ ሲያቆም፣ ውሃ ላይ ሲራመድ፣ በሰባት እንጀራና በጥቂት አሳ እልፉን ሲመግብ፣.. ብዙ ብዙ ተአምራቶች ለነሱ ሲያደርግ በቦታው ነበርኩና ይህንን እመሰክራለሁ፡፡
የማዕዱ ወለል ፪
አዎ ይህንንም ቦታው ላይ ተገኝቻለሁና እመሰክራለሁ።
በጠፈር መስፈሪያ እሽክርክሪት ውስጥ የሰው ልጅ ማዕድ ማንበሪያ ሆኜ እያገለገልኩኝ፣ ጌቶቼ እያለፉ በሌሎች ጌቶች እየተተኩ፣ እስከ ልጅ ልጅ ልጆቻቸው ድረስ ቆይቻለሁ፡፡
አንዱ ከሌላው በማይለይበት፣ አዲስ ነገር በሌላት ምድር ላይ ያቺ ቀን ተከሰተች፡፡
በአምስተኛው ቀን ላይ በዕለተ ሃሙስ፣ በጌታዬ ኤልያቄም ቤት እንግዳ ይመጣል ተብሎ ሽርጉዱ በዝቶ ነበር፡፡ አመሻሹ ላይ እንደተባለው ከደቀመዛሙርቱ ጋር ይህ ሰው ሲደርስ፣ በእንደዚህ ሁኔታ እናየዋለን ብሎ ማንም አልጠበቀም ነበር፡፡
ከዚህ በፊት እራት ተጋብዘው  እንደሚመጡት ባለጠጋ እንግዶች፣ ይሄኛው በቆነጃጅት ሴቶች አልተከበበም፣ መአዛ ያለው ውድ ሽቶ አልተቀባም፣ ውድ የሀር ልብስ አለበሰም፣ በከበሩ ጌጦች አልተሸንቆጠቆጠም፣.. ታዲያ ይህንን ሁሉ ሳያሟላ እንዴት እነዛን ባለጠጎች በግርማው እንዴት እንደበለጣቸው የተረዳሁት፣ በዙሪያዬ ማዕዳቸውን ለመመገብ ተደርድረው፣ እሱ ከመሀል ተቀምጦ እጆቹን የጫነብኝ ጊዜ ነበር፡፡
እንደታዘብኩት፣ የሰው ልጆች ግን በተደጋጋሚ ይዘነጉና ይጠራጠሩ ስለነበር፣ በተደጋጋሚ በምሳሌም ጭምር ዶሮ ሳይጮህ እንደሚሸሹት፣ አንደኛው አሳልፎ እንደሚሰጠው ፣ቤተ መቅደሱን አፍርሶ በሶስተኛው ቀን ተመልሶ እንደሚሰራው፣ ደጋግሞ ሲናገር ነበርኩኝ፤ ዳሩ እነሱ በጊዜው ሳይገባቸው ልክ ሲፈፀም ነበር የተናገረው የሚገለጥላቸው፡፡
የማዕዱ ወለል ፫
አዎ ይህንንም ቦታው ላይ ተገኝቻለሁና እመሰክራለሁ።
ወደ ኋላም ወደ ፊትም ባለው፣ በሚኖረውና በማይኖረው፣ አንድ አይነት ግብር ውስጥ በፈዘዘ የሂደት ጊዜ ነጥብ ከቆምኩበት መሰሎቼ ጋር አዙሪቱ ላይ እየባተትን፣ መደድ ቀናችንን ስንኖር፣ ብልጭ ብሎ በሚጠፋ ጉዞ ላይ ብልጭታዋን ዘላለም አድርጎ የሚያቆም የተባለው ይፈፀም ዘንድ የኔም ቀን ቀናትን ቆጥሮ በቀኑ ደረሰ።
በስድስተኛው ቀን ከተቀመጥኩበት ቅጥር  ውስጥ አራት የወታደር ዘቦች መጡና አመሳቅለው ካበጁኝ በኋላ፣ በራሳቸው ትከሻ ተሳፍሬ፣ “የሰው ልጅ” ከነበረበት ጠል ደረስኩኝ::
ከልክ በላይ በእንግልት፤ ግርፋትና፣ እርዛት ተጎሳቁሏል፤ በድካም መታከት ውስጥ ሆኖ፣ ሁሉንም ነገር የሚያስተውለው ልክ እዛ ቦታ ውስጥ እንደሌለ ሆኖ፣ በባይተዋር ስሜት ነው።
ለአራት ያመጡኝን በዚህ ሰውነቱ በድካም ደምና ላብ ባወረዛው ሰው ጀርባ ላይ አስቀምጠውኝ፣ ተራራውን መውጣት ጀመርን። ነጭ ላቡ እያራሰኝ በቀይ ደሙ እየታጠብኩ፣ እስትንፋሱ እየገረፈኝ፣ እንደ ሰው ልጅ የሰውን ስቃይ ተሸክሞ፣ እንደ ምንም ጫፍ ደረስን።
ጲላጦስ ጋር ቀርቦ “ምንም ሀጢያት አላገኘሁበትም” የተባለው ይህ ንፁህ ሰው፣ የመላው የሰው ልጅ፣  የሰዳቢዎቹንም ሀጢያት ሰብስቦ በመጫኑ፣ ወንጀለኛ ተባለ እንጂ እሱማ ምን አድርጎ።
ሰው ሁሉ ራሱን እንዲመረምር እንደ መስታወት ሁሉን ሊያሳይ የመጣ እንደሆነ  ባለመረዳታቸው፣ የተሰባሰቡት ህዝቦች ሲጮሁበት፣ በገዛ ሀጢያታቸው ላይ እንደሚጮሁ ፣ ሲተፉበት በገዛ እኩይነታቸው ላይ እንደሚተፉ፣ አልተረዱትም እንጂ፣ ሁሉን የተቀበለው የገዛ መልክን በሚሳይ መስታወት ራሳቸውን ነበር።
በመጨረሻም እረጃጅም ሚስማሮች መዳፎቹንና እግሮቹን አልፈው ውስጤ ሲገቡ፣ በላብ የተለወሰ ትኩስ ደሙ ሚስማሩ የፈጠረውን ክፍተቴን ሲደፍነው፣ እላዬ ላይ ሆኖ ከጎኑ የተሰቀሉት እንኳን ሳይሰሙ፣ ከመጨረሻው ህቅታ በፊት በለሆሳስ ሲናገር እዚያው ነበርኩ።
ልዕለ ሀያሉን እላዬ ላይ አኑሬአለሁ፤ ውስጤንም በሱ ላብና ደም ተዋጅቷልና፣ ቤዛ ሆኜ ዘላለምም እኖራለሁ።
በቦታውም ነበርኩና እመሰክራለሁ!!

Read 1428 times