Saturday, 08 May 2021 12:57

6ኛው አገራዊ ምርጫ 2013 "መንግስት ድርጅቶቹን በአሸባሪነት ለመሰየም ዘግይቷል"

Written by 
Rate this item
(0 votes)

           •   የተሻሻለው የሽብርተኛ አዋጅ አጥፊዎችን ለይቶ ለህግ የሚያቀርብ ነው
            • ማንኛውም ህግ ቅንነትን ይፈልጋል፤ በቅንነት መተርጎም አለበት

             “ህወሓት” እና “ሸኔ” በአዲሱ የፀረ ሽብር አዋጅ መሰረት፤ በሽብርተኛነት ተፈርጀዋል፡፡ ድርጅቶቹ በሽብርተኝነት መፈረጃቸውን በተመለከተ ብዙዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የህግ ባለሙያዎች ሲደግፉት፣ የተቃወሙትም አልጠፉም፡፡ ለመሆኑ የአሁኑ የጸረ ሽብር አዋጅ ከቀድሞው በምን ይለያል? የድርጅቶቹ ሽብርተኛ ተብሎ መሰየምስ ምን ያህል የአዋጁን መስፈርቶች ያሟላል? አዲሱ አዋጅ ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከጥቃት እንዴት ይከላከላል? በሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የህግ ባለሙያና ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን  ቆይታ አድርገዋል፡፡

               የቀድሞ የፀረ ሽብር አዋጅና አዲሱ አዋጅ ምንና ምን ናቸው? ልዩነታቸውን በንጽጽር ቢያስቀምጡልን….?
የመጀመሪያው የሽብር አዋጅና አዲሱ አዋጅ ልዩነታቸው ከአላማ ይነሳል፡፡ ሁለተኛው ልዩነታቸው ሃገሪቷን ከገጠመው ወቅታዊ ችግር ይነሳል፡፡ የመጀመሪያው አዋጅ ቀድሞውኑ በሃገር ላይ የደረሠ አደጋ ኖሮ የወጣ አይደለም፡፡ በሃገሪቷ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ላይ የደረሰን አደጋ ለመግታት ሳይሆን በወቅቱ የነበረውን የህወኃት/ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲን ህዝቡ አልቀበልም ማለቱን ተከትሎ፣ ተቃዋሚዎችን  ለማጥፋት ያለመ አዋጅ ነበር፡፡ አዲሱ አዋጅ ግን በለውጡ ማግስት የወጣ ነው፡፡ ይሄ ለውጥ ደግሞ ባለፉት 30 እና 50 ዓመታት ጭምር የመጣንበትን መንገድ በመገምገም የጀመረ ነው፡፡ በዚሁ ሂደት ከዚህ ቀደም የነበረው አካሄድ ስህተት መሆኑን አምኖ፣ “ሽብርተኛ የነበርኩት እኔ መንግስት ራሴ ነኝ” ብሎ ገምግሞ፣ ሽብርተኛ ተብለው የነበሩትን “አይደላችሁም” በማለት፣ እገዳቸውን አንስቶላቸው፣ ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ አድርጓል፡፡ አዲሱ አዋጅ ወደ 12 የቀድሞ መንግስት የማፈኛ አዋጆችን አሻሽሎ ተሃድሶ አድርጓል፡፡ በዚህ የተሃድሶ መንፈስ ነው  አዲሱ አዋጅ ሊወጣ  የቻለው፡፡ አዋጁ በተሃድሶ መንፈስ የወጣ መሆኑ በራሱ ከቀድሞ በተለየ መልኩ የህግ ጥበቃ ማድረግ ያስችለዋል፡፡ የአንድን ተጠርጣሪ መብትና ግዴታ ተረድቶ የወጣ አዋጅ ነውና፡፡ ሌላው ከቀድሞ ለየት የሚያደርገው በመንግስት ላይ ሳይሆን በህዝብ ላይ የተነሱ አማፂያንን - ያ ማለት ህፃናትን፣ ሽማግሌዎችን፣ንፁሃንን ከፖለቲካ የራቁ ሰዎችን ለፖለቲካ አላማ ሲል መንግስትን አስገድዶ ወደ ድርድር ለማምጣት ወይም ዳግም ስልጣን ለመያዝ ሲሉ የፈጠሩት ግብግብ ስላለ ይሄን አሸባሪ ድርጊት ለመቋቋም የወጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን አዋጅ የወጣበት ጊዜውም አስተሳሰቡም ከቀድሞ ጋር አንድ አይነት አይደለም፤ ይሆናል ተብሎም አይገመትም፡፡
እንዴት?
እንደሚታወቀው አሁን ላይ ሽብርተኛ የተባሉት ድርጅቶች በመከላከያ ሰራዊት ላይ የሽብር ጥቃት የፈፀሙ ሲሆኑ፤ ያ አላማቸው  ሲከሽፍባቸው ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለ27 ዓመታት በሁሉም ክልሎች ያዋቀሯቸው የተንኮል ፈንጂዎች እየፈነዱ፣ እዚያም እዚያም የሚፈጠሩት ችግሮች፣ በዋናነት በመንግስት ላይ ሳይሆን  በህዝብ  በሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ነበሩ፡፡ ይሄን ለመቋቋም የወጣ አዋጅ ነው፡፡ ልዩነቱ በጣም ግልጽ ነው፡፡
እነዚህን ድርጅቶች ሽብርተኛ ብሎ ለመፈረጅ መንግስት አጥጋቢ ማስረጃ አለው ማለት ይቻላል?
በአዲሱ አዋጅ አንድ አካልን በሽብርተኛነት ለመፈረጅ መኖር ስለሚገባቸው መስፈርቶች በአንቀጽ 19 ላይ ተቀምጧል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሰረት አንድ ድርጅት በአሸባሪነት ሊፈረጅ የሚችለው ድርጅቱ የሽብር ድርጊትን አላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ከሆነ፤ የሽብር ድርጊት የሚያሰኘው የድርጅት የፖለቲካ አላማውን ለማስፈፀም በማሰብ ከፖለቲካ አላማው ውጪ የሆኑ ንፁሃንን ሲገድል፣ ሲያጠቃ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ደግሞ ባለፉት 3 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከበቂ በላይ ተፈፅመዋል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የሚታወቁና የማይታወቁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ህወኃትን ብንወስድ ህጋዊ  የነበረ ድርጅት ነው፡፡ “ሸኔ” ደግሞ በስሙ ህጋዊ ፓርቲ የለም፣ ነገር ግን ድርጊት ፈፃሚዎች አሉ፡፡ እነዚህን መንግስት “ሸኔ” ብሎ ይገልጻቸዋል፡፡ ስለዚህ ይሄን ድርጊት የሚፈፅሙ ከሆነ “ሸኔ” ሆነው ይያዛሉ፤ ለህግ ይቀርባሉ ማለት ነው፡፡ ድርጊቱን መፈፀም ብቻ ሳይሆን ዛቻ መሰንዘርም የወንጀሉ አካል ነው፡፡ ለምሳሌ ህወኃት ምስራቅ አፍሪካን እናተራምሳለን ብለው በግልጽ ይዝታሉ፡፡ ስለዚህ ይሄ ድርጊታቸው በራሱ ሽብርተኛ ብሎ ለመሰየም ያበቃቸዋል። እንደውም መንግስት ለመሰየም ዘገየ ነው የሚባለው እንጂ ባለፉት 3 ዓመታት በኢትዮጵያ ያልተፈፀመ የሽብር አይነት  የለም፡፡ ስለዚህ የአሁኑ በግልፅ  ወንጀለኛን ዒላማ ያደረገ ፍረጃ ሲሆን የበፊቱ ግን በግልፅ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት ነበር። የአሁኑ አዋጅ ህዝቡ ላይ የሚፈፀመውን ወንጀል ለማቆምና  ለመግታት የወጣ ነው፡፡
ሌላው ከዚህ ቀደም ሽብርተኛ ተብሎ ሲሰየም ቀጥታ ውሳኔ በማሳለፍ ነበር። አሁን ግን በግልፅ እንዳየነው፣ ይህ ድርጅት በሽብርተኛነት መሰየም የለበትም፤ በቂ ማስረጃ አምጡ እያለ ፓርላማው ሲጠይቅ ነበር፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ይሄ አይነት የክርክር አካሄድ አልነበረም፡፡ ይሄን ማድረግም በግልጽ በአዋጁ አንቀጽ 21 ላይ በግዴታነት ተቀምጧል፡፡ ይሄ አሰራር መኖሩ “የአይንህ ቀለም አላማረኝም” በሚል የሚደረግ ፍረጃን በእጅጉ ይከለክላል። መንግስት በእነዚህ ድርጅቶች ስም ሌላ ጥቃት በተቃዋሚዎች ላይ ይፈፅማል ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የአዋጁ መንፈስም ይሄን አይፈቅድም ወይም ዕድል አይሰጥም፡፡ ኦሮሞ የሆነ ሁሉ ሸኔ፣ ትግሬ የሆነ ሁሉ ህወኃት ይባላል ብሎ ለማመን የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ በቀጥታ የፖለቲካ ስልጣን ሳይሆን ህዝብን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አዋጅና ፍረጃ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አጥፊዎችን  ለይቶ በህግ የሚያቀርብ አዋጅ ነው  ብዬ ነው የማስበው።
ህወኃት የሚታወቅ ነው፤ ራሱን ህወኃት ብሎ የሚገልፅ አካል አለ፡፡ “ሸኔ” ግን የለም፤ ራሱን “ሸኔ” ብሎ የሚገልፅ በሌለበት እንዴት በአሸባሪነት ሊሰየም ይችላል? መንግስት ያላማረውን ሁሉ “ሸኔ” እያለ እየፈረጀ ለማጥቃት ክፍተት አይፈጥርለትም?
ይሄ አወዛጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 19 እንደተቀመጠው፤ አንድ ድርጅት ህጋዊ ሆኖ ሽብርተኛ ሊባል ይችላል። በሌላ በኩል አንድ ድርጅት ህልውና ሳይኖረው፣ የወንጀል አፈፃፀሙ ሽብርተኛ ከሆነ፣ መንግስት ያንን አካል በይኖ ድርጊቱን መከታተል ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሸኔ የሚባል ድርጅት የለም፤ ነገር ግን እጅግ ለጆሮ የሚከብዱ እዚህም እዚያም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን “ሸኔ” ፈፀመው ነው የሚባለው። ድርጊቱ ነው ሸኔ የሚያስብለው፡፡ ስለዚህ ድርጊት ብሎ ወደ ህግ ማቅረብ ይቻላል ማለት ነው፤ ተግባሩ ነው የሚተነተነው፡፡ “ሸኔ” የሚያስብለው ተግባሩ ነው፡፡ አቅመ ደካሞችን መግደል፣ገበሬ መግደል፣ ከተማ ሙሉ ማውደም-- እነዚህ ተግባራት ሁሉ ሽብር ናቸው፡፡ ስለዚህ ይሄን የፈፀመው አካል “ሸኔ” ነው ተብሎ ወደ ህግ ሊቀርብ ይችላል፡፡
በተፈረጁ ድርጅቶች ስም ተቃዋሚዎች እንዳይጠቁ አዋጁ ምን ያህል ከለላ ይሰጣል?
 አንቀጽ 19 ላይ ዝርዝር የሽብርተኛነት አሰያየም ተቀምጧል፡፡ በዚያ ዝርዝር ውስጥ ያለ ድርጊት ያልፈፀመ ግለሰብ ፍ/ቤት ሲቀርብ መከራከር ይችላል ማለት ነው። ህጉ እንደከዚህ ቀደሙ አሻሚ ድንጋጌዎች የሉትም፡፡ ግልጽ ናቸው ዝርዝር መስፈርቶቹ። በአሁኑ ጊዜ ነፃ ተቋማትን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ማንሳት እንችላለን፡፡ ግፍ ሲፈፀም ይሄ ተቋም በገለልተኛነት ስራውን ይሰራል፤ አሁንም እየሰራ ነው፡፡ እርግጥ ማንኛውም ህግ ቅንነትን ይፈልጋል፤ በቅንነት መተርጎም አለበት፡፡ ዋናው ኢትዮጵያን የማዳን ጉዳይ ነው፤ ከሽብር ትርምስ ሃገሪቱን የማዳን ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ መንግስት አሁን ህግጋትን እንከተል፤ ለሃገሪቱ ፈታኝ የሆነውን የዘውግ ፖለቲካ ስረ መሰረቶች እንናድ እያለ ነው፡፡
ኢትዮጵያን በኦሮሞ መልክ በአማራ መልክ፣ በትግሬ መልክ ብቻ እሰራለሁ የሚለውን በመቃወም፣ ተደማምረን በሁላችንም  አምሳል እንስራት የሚል ፍልስፍና ያለው መንግስት ነው፡፡ ይሄ ፍልስፍና ነው የዘውግ ፖለቲካ  ስረ መሰረትን  ሰርስሮ የሚበጣጥሰው፡፡


Read 1275 times