Saturday, 01 May 2021 14:03

በፖለቲካዊ የሃሳብ ልዩነቶች ምክንያት እርስበርስ የመናቆርና የመጠፋፋት አባዜ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 "-ስለዚህ የሃሳቦችን ትክክለኛነትና ጠቃሚነትን ለይተን ማወቅ የምንፈልግ ከሆነ፤ የሰዎች ግንኙነት ከጥቃት ትንኮሳ የፀዳ መሆን ይኖርበታል። አሁንም፤ የሰዎችን ሃሳብና የሰዎችን ግንኙነት ለብቻ ነጣጥሎ፤ አንደኛውን ብቻ በቁንፅል ማየት የለብንም። አንዱ ከሌላው ውጭ ሊኖር አይችልም።--"
          ሰው “ሁሉም ሃሳቦችና ስርዓቶች እኩል ናቸው” ብሏል በግድ የለሽነት። ነገር ግን፤ ነፃነትን የሚያከብር ስርዓትና እንዳሰኘው እያሰረ የሚገድል ስርዓት በጭራሽ እኩል አይደሉም። እኩል እንዳልሆኑ በራሱ ህይወት ላይ ካየ በኋላ ደግሞ፤ “እኔ ከምደግፈው ሃሳብና ስርዓት ውጭ ሌሎቹ መጥፋት አለባቸው” ብሎ በስሜት ጦዞ ያስፈራራል። ግን ይህም መፍትሄ አያመጣም። አንዱ የሌላውን ሃሳብ ለማጥፋት በጭፍን ስሜት ሲናቆሩ ከፍተኛ ጥፋት ይደርሳል። ያኔ፤ “ሁሉም ሃሳቦችና ስርዓቶች እኩል ናቸው” ወደ ማለት እየዞረ ዥዋዡዌው ወይም አዙሪቱ ይቀጥላል። እና ምን ይሻላል?
እንዲህ፤ አንዴ ወዲህ አንዴ ወዲያ እየወላወልን፤ በአላስፈላጊ አጣብቂኝ አዙሪት ውስጥ እንድንሰቃይ የሚያደርጉ ክስተቶች በርካታ ናቸው። ግን መፍትሄ አለው። አዙሪቱን በጥሰን መውጣት የምንችለውም፤ ስረ-መንስኤውን በአግባቡ በማጤን ነው። በፖለቲካዊ የሃሳብ ልዩነቶች ምክንያት እርስበርስ የመናቆርና የመጠፋፋት አባዜ ሲያስጨንቀው፤ “ሁሉም የፖለቲካ ሃሳቦች እኩል ናቸው” ይላል-መፍትሄ1
ነገር ግን ሁሉም ሃሳቦች (ተቃራኒ ሃሳቦችም ጭምር) በእኩል ደረጃ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም። በተግባርም ሲታዩ በውጤታቸው እኩል አይሆኑም፤ እንደ ትክክለኛነታቸው ወይም እንደ ስህተትነታቸው መጠንም ስኬትን ወይም ውድቀትን፤ ጥቅምን ወይም ጉዳትን ያስከትላሉ።
ጠቃሚና ጎጂ ሃሳቦችን እንደ እኩል መቁጠር፤ ህይወትን ውጥንቅጡ በወጣ ቀውስ ውስጥ በማስገባት ወደ ውድቀት ያወርዳል- ምግብንና መርዝን እንደመቀላቀል ነውና። ህይወቱ በዚህ ሲጨነቅ፤ “እኔ ጠቃሚ ነው ብዬ ከምደግፈው ሃሳብ ውጭ ሌሎች መጥፋት አለባቸው፤ ሌሎች ሰዎችም የግድ የኔን ሃሳብ መከተል ይኖርባቸዋል” ይላል- መፍትሄ2። እንዱ የሌላውን ሃሳብ ለማጥፋትና ለማደን ሲጣጣር፤ እንደገና በሃሳብ ልዩነት ሳቢያ እርስበርስ የመጠፋፋት አዙሪት ይጀምራል።
ሁለቱም መፍትሄዎች አልሰሩም፤ ስህተቱ የቱ ጋ ነው? ሁለት ተያያዥ ስህተቶች አሉ።
ሀ. አንድን ነገር ለብቻ ነጥሎ የመመልከት ቁንፅልነት
ለ. ነገሮችን በደፈናው አደባልቆ የማየት ብዥታ
ለምሳሌ በሃሳቦች ዙሪያ ያነሳነው ጉዳይ፤ ቢያንስ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካትታል።
1.  የሃሳቦችን ትክክለኛነትና ጠቃሚነት እንዴት ለይቶ ማወቅ ይቻላል?
2. የተለያዩ ሃሳቦችን በያዙ ሰዎች መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ምን አይነት ነው?
ከድፍን ብዥታ በራቀ ሁኔታ ፤ የሁለቱን ጥያቄዎች ልዩነትና ድንበር ለይቶ መረዳት፤ እንዲሁም ከግንጥል ቁንፅልነት በራቀ ሁኔታ የሁለቱን ጥያቄዎች ትስስርና መስተጋብር አቀናጅቶ መገንዘብ ያስፈልጋል። በአንድ በኩል ፤ የሃሳቦች ትክክለኛነትና ጠቃሚነት ተለይቶ ሊታወቅ የሚችለው በሪዝን ወይም በአእምሮ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የሰዎች ግንኙነት የጥቃት ስንዘራን የማይፈቀድ፣ የመከባበር ግንኙነት መሆን ይኖርበታል። እነዚህን ሁለት ጉዳዮች፤ በድፍን ብዥታ ሳይሆን በግልጽ ድንበራቸውን ለይቶ መረዳት ያስፈልጋል። ግን ተነጣጥለው በቁንጽል መታየት የለባቸውም። እንዴት?
አንደኛ፤ እርስበርስ ከመጠፋፋት ለመዳንና  በፈቃደኝነት ተባብሮ ለመበልጸግ ከፈለግን፤ የሰዎች ግንኙነት ቢያንስ ቢያንስ፤ ከጥቃት ትንኮሳ ነፃ መሆን ይገባዋል፤ የጡንቻ፤ የስድብ፤ የጠመንጃና የአሉባልታ ጥቃት ከማነሳሳት የፀዳ። ይሄው ነው፤ ነጻነት ወይም መብት የሚባለው። ግን፤ ሰዎች በየጊዜው የተለያየ ሃሳብ ይይዛሉ፤ በሃሳቦች ልዩነት ምክንያትም በሰዎች መካከል አለመግባባት ይፈጠራል። በቁንጽልነት ከተመራን፤ የሰዎችን ግንኙነት የሚያሳምር መስሎን በሃሳቦች ልዩነት ሳቢያ አለመግባባት እንዳይፈጠር በመመኘት ፤ “ሁሉም ሃሳቦች እኩል ናቸው” እንላለን። ይሄም በጣም ቀሽም የማምለጫ አባባል ነው-የማያዛልቅ ከሻፊ ጥገና። እንዴት? የሰዎች ግንኙነት ከጡንቻና ከአሉባልታ ጥቃት የጸዳ መሆን አለበት” የሚለው ሃሳብ፤ “በጡንቻም ሆነ በአሉባልታ፤ ሳይቀድምህ ቅደመው” ከሚለው ሃሳብ ጋር እኩል ነው ወደማለት እናመራለን። “ሳይቀድምህ ቅደመው” በሚል ሃሳብ፤ የሰዎችን ግንኙነት ማሳመር እንችላለን? አንደኛው ሃሳብ እውነት ነው- ወደ ሰላም የሚወስድ። ሌላኛው ሐሰት ነው- ወደ ጥፋት የሚያወርድ። ልዩነታቸው የብርሃንና የጨለማ፣ የክብርና የውርደት ያህል ነው። እና፣ የሰዎችን ሃሳብና የሰዎችን ግንኙነት ለብቻ ነጣጥሎ፤ አንደኛውን ብቻ በቁንጽል ማየት አያዋጣም።
ሁለተኛ፤ የሃሳቦችን ትክክለኛነት ማወቅ የሚቻለው፤ ሃሳቦቹን ከተፈጥሮ ጋር (ከእውኑ አለም ጋር) በማመሳከር ብቻ ነው (በሪዝን)። ጠቃሚነታቸው የሚፈተሸው፤ ለህይወት ከሚያስገኙት ውጤት አንፃር በማመዛዘን ብቻ ነው (በሪዝን)። ከሪዝን ውጭ ሌላ የማወቂያ መንገድ የለም። በጡንቻ ወይ በስድብ፤ በጠመንጃ ወይ በአሉባልታ አማካኝነት፤ አንድን ሃሳብ እንድንቀበል የሚያስገድደን ሃይል መኖር የለበትም ማለት ነው- ሪዝንን እንዳንጠቀም ማለትም እንዳናገናዘብና እንዳናመዛዝን ፤ በአጠቃላይ እንዳናውቅ የሚያግደን ስለሆነ።
ስለዚህ የሃሳቦችን ትክክለኛነትና ጠቃሚነትን ለይተን ማወቅ የምንፈልግ ከሆነ፤ የሰዎች ግንኙነት ከጥቃት ትንኮሳ የፀዳ መሆን ይኖርበታል። አሁንም፤ የሰዎችን ሃሳብና የሰዎችን ግንኙነት ለብቻ ነጣጥሎ፤ አንደኛውን ብቻ በቁንፅል ማየት የለብንም። አንዱ ከሌላው ውጭ ሊኖር አይችልም። ለዚህም ነው አንዱን ብቻ ነጥለን በቁንጽል በማየት የምንፈጥራቸውና የምንተገብራቸው መፍትሄዎች ከስኬት ይልቅ የውድቀት ምህዋር ውስጥ እንድንዳክር የሚያደርጉን።
እውነታ ላይ በመመስረት እውቀትን መገንባት እንዲሁም፤ ያማረ የሰዎች ግንኙነትን ማስፈን እንፈልጋለን? እንግዲያውስ፤ የሃሳቦችን ትክክለኛነትና ጠቃሚነት የምንመረምርበት ሪዝን እንዲሁም የሰዎችን ግንኙነት የምንመራበት የነፃነትና የመብት መርሆዎችን አቀናጅተን የምንገነዘብበት ቅንብራዊ አስተሳሰብ ያስፈልጋል።
ነገሮችን በግልፅ ምንነታቸውንና ድንበራቸውን ለይቶ በመገንዘብ፤ እንዲሁም ትስስርና መስተጋብራቸውንም በማጤን አዙሪቱን በቀላሉ መፍታት እንድንችል ብቃት ያጎናጽፈናል- በእውነታ ላይ የተመሰረተ ቅንብራዊ አስተሳሰብ።
(“ኑሮ MAP” ከሚለው መፅሐፍ የተቀነጨበ)

Read 2376 times