Saturday, 01 September 2012 09:28

ለሁለት ሳምንት የሰነበተ የአገር ሃዘን

Written by  ዳዊት ንጉሡ ረታ
Rate this item
(0 votes)

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከጠ/ሚኒስትሩ ህመም ጋር በተያያዘ እኔና ጥቂት ጓደኞቼ ሰውየው በሞት ቢለዩን የዚህች አገር ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? እየተባባልን እንዳብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስንጨነቅ ነበር፡፡ ደግነቱ እነዚያ ትናንትና ስንወያይባቸው የነበሩትና ሊፈጠሩ ይችላሉ ብለን ያሰብናቸው ስጋቶቻችን ዕውን ባለመሆናቸው ተመስገን ብያለሁ፡፡ ዛሬ የጠቅላይ ሚ/ሩን ህልፈት ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሃዘን ቢዋጡም አገራችን ግን ሁሉን ነገር ፍፁም በሰላማዊና በተረጋጋ መንገድ እያስተናገደች በመሆኑ ህዝቡም እንደኔ ተመስገን ብሎ ሳያመሰግን የሚቀር አልመሰለኝም፡፡ መቼም መሪ ግልጽ/ኦፊሴላዊ በሆነ ሁናቴ በሞት ሲለየን የመጀመሪያችን እንደመሆኑ አገሪቱ በታሪክ ቀዳሚ ሊባል የሚችለውን ክስተት አስተናግዳለች፡፡ ሀዘኑ እንደተሰማ እንዴት ተብሎ እንደሚከረም ከዚህ ቀደም ልምዱ ስላልነበረን አንዳንድ መደናገሮች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ ለቅሶ የት ነው የሚደረሰው? የመገናኛ ብዙሃን የህዝቡን ስሜት እንዴት ያስተናግዱታል? የቀብሩ ሁናቴስ እንዴት ይሆናል? ማን ይተካል? ወዘተ የሚሉ ዓይነት ስጋቶች… ነበሩ፡፡

የሆነው ሆኖ ያን ያህል የከፋ ስህተት ሳይስተዋልና ጉልህ ችግር ሳይከሰት ይህቺ አገር በበርካታ ወሳኝ ጊዜያት ሰላምና አንድነትን አስጠብቃ እንዳለፈችው ሁሉ ዛሬም በኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ሁሉንም እንዳመጣጡ በሰላም እያስተናገደች መሆኑ ሊያስደንቃትና ሊያስከብራት የሚገባ ነው፡፡ እነሆ፤ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በአፀደ ስጋ ከተለዩን ሁለት ሳምንት ሊሆናቸው ነው፡፡ በነገው ዕለት ደግሞ እንደዚሁ የእርሳቸውን ክብር በጠበቀ ሁናቴ የቀብር ስነ - ስርዓታቸው በፍፁም ሰላማዊ ሁናቴ እንደሚፈፀም ተስፋ አለኝ፡፡ ባሳለፍናቸው ሁለት የሀዘን ሳምንታት ያስተዋልኳቸውን አንዳንድ ክንውኖች በመዳሰስ ላስታውሳችሁ ወደድኩ፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖን፤ መለስ ከዘመን መለወጫ በዓል በፊት ወደ ስራ ገበታቸው ይመለሳሉ ብለው ብዙም ሳይቆይ የጠቅላይ ሚ/ሩን ህልፈተ ህይወት የማርዳት ሃላፊነቱ ተጣለባቸው፡፡ የዛን ቀን ጠዋት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት፤ ጠቅላይ ሚ/ሩ እንዳለፉ የማኒስትሮች ም/ቤትን መግለጫ በማንበብ ካሳወቀን በኋላ ህዝቡ ዝም ጭጭ ባለበት ሰዓት በረከት ስምዖን እንደ መንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትርነታቸው በሂልተን ሆቴል ተገኝተው የረጅም ጊዜ የትግልና የስራ ጓደኛቸውን ሞት በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ፡፡ የዚያኑ ቀን ማታ ላይ ደግሞ አስከሬን የሚመጣበት ቀን በመሆኑ ከሌሎች የስራ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በከፍተኛ ሁኔታ ሲያለቅሱ በቲቪ መስኮት ተመልክተናቸዋል፡፡ እኚህ ሰው ምርጫ 97ን ጨምሮ በበርካታ ወሳኝ ጊዜያት ፓርቲያቸውን በመወከል ከፊት የቆሙ አመራር ሲሆኑ በህዝብ ዘንድ ግን በልዩ ልዩ ጉዳዮች ሲወቀሱ ይደመጣል፡፡ ለምሳሌ ስለመለስ ሚዲያዎች የት ገቡ እያሉ በጮሁ ቁጥር መንግስት መልስ ለመስጠት አይችልም ባሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመለስን ሞት እንዳረዱን ማለት ነው፡፡

ብሔር ብሔረሰቦች መዝሙር

የጠቅላይ ሚ/ሩን ሞት ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች የሚመጣውን የሀዘን መግለጫ በምን መልኩ ማስተናገድ እንደሚችል ልምድ ያጠረው ኢቴቪ፤ ማክሰኞ ጠዋት ከመርዶው በኋላ የጠቅላይ ሚ/ሩን ፎቶ እያሳየ ብሔር ብሔረሰቦች የሚለውን ዜማ ሲያሰማ ተስተውሏል፡፡

በኤፍ ኤም ራዲዮም የመለስን የቀደመ ንግግር ካሰሙ በኋላ “ትንፋሼ ተቀርፆ ይቀመጥ ማልቀሻ…ያስቀየምኩት ቢኖር የጠላኝ በቁሜ፤ ድምፄን ሰምቶ ያዝናል ለረገፈው አጽሜ” የሚለውን የክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰን ዘፈን አስደምጠውናል፡፡ ከዚያ ቀን በኋላ ግን እንዲህ ዓይነቱን አቀራረብ በመለወጥ በዋሽንትና በመሳሪያ ብቻ በተቀነባበሩ ሙዚቃዎች ተክተውታል፡፡

ይዘጋ የነበረው የቦሌ መንገድ

ጠቅላይ ሚ/ሩ ለውጪ አገር ስራ ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ለመጓዝ ሲፈልጉ ወይንም ደግሞ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የቦሌ መንገድ ለሰዓታት ተዘግቶ በንቁ ፌደራሎች በጥብቅ እንደሚጠበቅ ትዝ ይለናል፡፡ ያን ጊዜ ከሸኚዎች ወይም ተቀባዮች መኪኖች ውጪ ቦሌ ምድረ - በዳ ትሆንብናለች፡፡ ሆኖም ግን ማክሰኞ ምሽት ላይ የጠቅላይ ሚ/ሩ አስከሬን ወደ አገር ውስጥ ሲገባ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ነበር፡፡ አስከሬናቸውም በህዝብ እንደታጀበ በቦሌ መንገድ ላይ ተጉዞ ወደ ቤተመንግስት ዘልቆአል፡፡

ያልታሰበ የህዝብ ጐርፍ

በሙስሊሙ ህብረተሰብ ጉዳይ፣ በፓትሪያርኩ ሞት፤ ተደጋግመው በሚሰሙ የብሔሮች ግጭት፤ በዲያስፖራው የሽግግር መንግስት እንቅስቃሴ፤ በፍትህ ጋዜጣ መታገድና በጋዜጠኞች መታሰር ወዘተ… ግራ ተጋብቶና በጭንቀት ተወጥሮ የነበረው ኢትዮጵያዊ፤ የአቶ መለስ አስከሬን ወደ አገሩ ከገባ በኋላ ግን ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት ወደ አደባባይ በመውጣት ሀዘኑን በከባድ ሁኔታ ሲገልጽ ተስተውሎአል፡፡ መንግስት ራሱ ይህንን የህዝብ ማዕበል ያልጠበቀው መሆኑን የመንግስት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር በረከት ስምዖን በሰጡት መግለጫ ህዝቡን በማመስገን ገልፀውታል፡፡

 

የተዘጉት በሮች ተከፈቱ

የቤተመንግስት በሮች ሀዘኑን ተከትሎ መከፈታቸውና ህዝቡ የጠቅላይ ሚ/ሩን አስከሬን እንዲሰናበት መፈቀዱ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ እነዚያ ለዘመናት ለህዝብ ዝግ የነበሩ ደጆች፤ ዛሬ ሃዘኑ ምክንያት ሆኖዋቸው ወለል ብለው አንዲከፈቱ ተገድደዋል፡፡ ህዝቡም ፍፁም በሆነ ስነስርዓትና አክብሮት የ21 ዓመታት መሪውን ለመሰናበትም ታድሎአል፡፡ ኢቴቪም የጠቅላይ ሚኒስትሩን መኖሪያ ቤት እያሳየ እግረመንገዱንም የሀዘንተኞቹን አስተያየት እየተቀበለ በቀጥታ አሰራጨልን፡፡ በነገራችን ላይ የጠቅላይ ሚ/ሩ ቤትን እንዳልጠበቅኩት ነው ያገኘሁት፡፡ ቤቱ ፈጽሞ ደረጃውን ያልጠበቀና ያረጀ ሆኖ ታይቶኛል፡፡ ይህ ቤት (ቤተመንግሥት) የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያምም ነበር ሲባል ሰምቻለሁ፡፡

በ3 ደረጃ ተዋቅሮ የሚሰማው የሀዘንተኞች ቃለ - መጠይቅ

እናንተዬ የዚህ የፓርቲ አሰራር ብሎ ነገር አዕምሮን ብቻ ሳይሆን ለቅሶንም ይቆጣጠራል እንዴ? ይህንን ለመጠየቅ ያስደፈረኝ ነገር እጅግ በርካታ የሚሆኑ ሀዘንተኞች ማዘናቸውን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት መንገድ በሶስት ደረጃ የተዋቀረና ፍፁም ተመሳሳይ የሆነ መምሰሉን መታዘቤ ነው፡፡ ይህም የፓርቲ አቋም እስኪመስል ድረስ የተደጋገመ ነበረ፡፡

ደረጃ 1 መግቢያ

የጠቅላይ ሚ/ሩን ሞት ስሰማ ሰማይ የተደፋብኝ መሰለኝ፤ ከቤተሰቤ አንድ ሰው ያጣሁ መሰለኝ፤ አባቴን ያጣሁ ያህል አዝኛለሁ፤ ከመጠን በላይ ነው የደነገጥኩት ወዘተ…

ደረጃ 2 ማጠናከሪያ፤ - ጠቅላይ ሚ/ሩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የአፍሪካም መሪ ናቸው፡፡ በእሳቸው መሞት እኛ ብቻ ሳይሆን አፍሪካና መላው ዓለምም አዝኖአል፡፡ ይሉና በመጨረሻም

ደረጃ 3 ማጠቃለያ ፤ - እሳቸው የጀመሩትን ፕሮጀክቶች በመጨረስ ስማቸውን ህያው ማድረግ ይጠበቅብናል ይላሉ፡፡

ስራ ፈጣሪ/ ኢንተርፕሩነር ወጣቶች፤ - የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ወረታው ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ የሚፈጥሩ (ኢንተርፕሩነር) የሆኑ ወጣቶች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ ነው ቢሉም በተለያዩ ወቅቶች ልዩ ልዩ ፈጠራ በመፍጠር ቢዝነስ የሚያካሂዱ ወጣቶች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ (የታክሲ ላይ ጥቅሶች፤ ለሙስሊሞች የመስገጃ ምንጣፍና የሲሚንቶ መያዣ ወረቀት የሚያቀርቡ ወዘተ) ታዲያ እነኚሁ ከተፎ ወጣቶች በአራት ኪሎ አደባባይ የጠቅላይ ሚ/ሩን ፎቶዎች አባዝተው በመያዝ የጋሽዬን፤ የታላቁ መሪያችንን፤ የጀግናውን ፎቶዎች 2-2 ብር እያሉ ሲቸበችቡና ህዝቡም እንደጉድ እየተጋፋ ሲገዛቸው ተመልክቼ በእጅጉ ተደንቄአለሁ፡፡ እኔም ማስታወሻ ይሆነኝ ዘንድ እግረ መንገዴን እነዚሁኑ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ለማበረታታት የድርሻዬን ገዝቻቸዋለሁ፡፡ ጥቁር ቲ-ሸርቶችን፣ የመለስን ፎቶን በማተም የቸበቸቡ፤ መፈክር የፃፉና በዲጂታል ህትመት አትመው የሸጡና ገቢያቸው የትየለሌ የሆነላቸው፤ ጥቁር ሻርፕና ጥቁር ሹራብ፤ ታይት፤ ስካርፍ ወዘተ… የሸጡ ቡቲኮች፤ ጧፍና ሻማ የቸበቸቡት ሁሉ የህዝብ ፍላጐትን በማየት አቅርቦቱን ከፍ ያደረጉ በመሆናቸው ሊደነቁ ይገባቸዋል፡፡

የፌስ ቡኩ ዓለም

ለወትሮውም ቢሆን ለመንግስት ጥሩ አመለካከት የለሌለውና መለስንና ፓርቲያቸውን ኢህአዴግን በአምባገነንነት ሲኮንን የሚስተዋለው የፌስቡኩ ዓለም፤ በጠቅላይ ሚ/ሩ ሞት ግን እጅግ መደናገጡን ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ መርዶውን ተከትሎ በወጡት (ፖስት በተደረጉት) ምስሎችና ጽሑፎች አብዛኞቹ የመለስ ሞት እንዳሳዘናቸው ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ያም ሆኖ ግን አልፎ አልፎ “አምባገነኑ መሪ በሞት ተነጠቀ” የሚሉ ዓይነት መልዕክቶች መተላለፋቸው አልቀረም፡፡ ሰሞኑን ግን ጭራሽ ሁኔታው ተለውጦ በርካታ መንግስትን የሚቃወሙ ጽሑፎችና ምስሎች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡

 

ቪኦኤና ሌሎች ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን

አብዛኞቹ የመገናኛ ብዙሃን ለጠቅላይ ሚ/ሩ ሞት ሰፊ ሽፋን የሰጡ ሲሆን እንደነ ቢቢሲና አልጄዚራ ዓይነቶቹ ደግሞ የመለስን ጥንካሬ አጉልተው ካሳዩ በኋላ ምርጫ 97 ላይ ስለተከሰተው የወጣቶች ሞት መለስንና ፓርቲያቸውን ተወቃሽ ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡ ቪኦኤም በጠቅላይ ሚ/ሩ ሞት ላይ ያተኮሩ ሰፋፊ ዘገባዎችን አስተናግዶአል፡፡ በስልክ በሚሰጡ ነፃ የህዝብ አስተያየቶች ላይ ደግሞ አብዛኞቹ ደዋዮች በሞቱ አዝነናል ሲሉ አንዳንዶች ደግሞ ሞቱን በመደገፍ ይገባዋል ማለታቸውን ታዝቤአለሁ፡፡

ኢትዮጵያውያን ጋዜጦችና መጽሔቶች

ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ኢትዮጵያውያን ጋዜጦችና መጽሔቶች የጠቅላይ ሚ/ሩን ምስል በፊት ገፆቻቸው ላይ በማውጣት ሰፊ ዘገባ ሰርተዋል፡፡ አብዛኞቹ የመለስን የኋላ ታሪክ በማስታወስ፤ ሌሎቹም ሞቱን ተከትሎ በቀጣይ ስለሚኖረው ሁናቴ ፖለቲካዊ ትንተናቸውን አቅርበውልናል፡፡ ከዚህ በፊት ያላየናቸውም የመለስ ፎቶዎች በገፆቻቸው ላይ ለመመልከትም ችለናል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጣ ልዩ ዕትም አውጥቶ ነበር፡፡ ጋዜጣው የፓርቲውን የኃዘን መግለጫ ካስነበበን በኋላ በተለያዩ አምደኞቹ ግን በመለስ ላይ ትችቶችን አቅርቦአል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችም ሀዘናቸውን በጋዜጣው በመግለጽ ጠቅላይ ሚ/ሩ የሚደነቅ ችሎታ ቢኖራቸውም ስልጣናቸውን በሞት   ሳይሆን በፈቃደኝነት ለመልቀቅ ባለመፈለጋቸው ኮንነዋቸዋል፡፡ አገሪቱም በቀጣይ ህዝባዊ መንግስት እንድትመሰርት የሚያስችላትን ህዝባዊ ውይይት በመጥራት ኢህአዴግ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ያሳሰቡም አልጠፉም፡፡

ጊዜያዊ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማርያም ደሳለኝ

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከመለስ በኋላ ስልጣኑን የሚተካው ሰው ከህውሃት ወይንም ከብአዴን እንጂ ከሌላ አይሆንም የሚል የጥቅል ድምዳሜ ነበረው፡፡ ሆኖም ግን አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ይዘው እንደሚቀጥሉ በአቶ በረከት ሲገለፅ፤ የፓርቲውን ውሳኔ በግሌ በጣም ነው ያደነቅሁት፡፡ ይህም በትክክል ከቀጠለ፤ ሰውዬውም የፖለቲካም ጭምር አመራርነቱ ከተሰጣቸው (ጦሩንም ጭምር የዕውነት የሚያዙ ከሆነ ማለቴ ነው) እንዲሁም የፓርላማው ብቸኛው የተቃዋሚዎች ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ እንደተናገሩት፤ አቶ ኃ/ማርያም በራሳቸው የአመራር ዘይቤ አገሪቱን እንዲመሩ ሁኔታዎች ከተመቻቸላቸው በእርግጥም ወደ ተረጋጋ ፖለቲካ የሚያደርሰን ምርጥ የመተካካት ሂደት ውስጥ እንዳለን የሚጠቁም ክስተት ይሆናል፡፡

ሆኖም ግን ጊዜያዊ ጠ/ሚ/ሩ ኃይለማርያም በዚህ ወሳኝ የፖለቲካ ወቅት ራሳቸውን የበለጠ ወደ ህዝቡ ብቅ በማድረግ ራሳቸውን የበለጠ ማስተዋወቅና ህዝቡንም ማረጋጋት ይጠበቅባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን ማናቸውም የመንግስት መግለጫዎች በኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚ/ር አቶ በረከት ስም ብቻ መውጣታቸው ከስራ አንፃር ቅቡል ቢሆንም ጊዜያዊ ጠ/ሚ/ሩ ኃይለማርያም ደሳለኝን እንዳያደበዝዛቸው እሰጋለሁ፡፡

ሁለቱ የመንፈስ አባቶች የት ገቡ?

በአንድ ወቅት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የመንፈስ አባት ተብለው ይጠሩ የነበሩትና “ፍትህ” ጋዜጣ ከመዘጋትዋ በፊት ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ፅሁፎችን ያስነበቡ የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምና የህውኃት/ኢህአዴግ መስራችና ቀደምት መሪ የሆኑት እስከቅርብ ጊዜም ድረስ ከፓርቲው መደበኛ የስልጣን ተዋረድ በተለየ መልኩ በራሳቸው መንገድ ልዩ ልዩ መግለጫዎችን ሲሰጡ የቆዩት አቦይ ስብሀት፤ ከጠቅላይ ሚ/ሩ ህልፈት በኋላ የት እንደደረሱ ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ እነዚህ ሁለት የመንፈስ አባቶች ሀዘናቸውንም ኃሳባቸውንም እስካሁን አልገለፁም የት ገቡብን?

የተዘጋው የመዝናኛ ኢንዱስትሪው

የጠቅላይ ሚ/ሩን ሞት ተከትሎ ብሄራዊ የሀዘን ቀን በመታወጁ ምክንያት የመዝናኛው ኢንዱስትሪም አንቀላፍቶአል፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከማስታወቂያ ያገኝ የነበረው፤ ቴአትር ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች ከመዝናኛ ዘርፉ የሚያገኙት፤ ቡና ቤቶችና የምሽት ጭፈራ ቤቶችም እንደዚሁ በልዩ-ልዩ መንገዶች ሊያገኙዋቸው የሚችሉዋቸው ገቢዎች ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጠዋል፡፡

ለቅሶውና ድንኳኖቹ የማናቸው?

ከመርዶው በኋላ በየቀበሌው ድንኳን መጣል ሲጀመር አንዳንድ የፓርቲው ቅርብ ሰዎች ለቅሶውን የራሳቸው ብቻ ለማስመሰል ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ የታሪክ አጋጣሚና በአገር ጉዳይ ሁልጊዜም አንድ በመሆን የሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ግን ይህንን እንዲያደርጉ አልፈቀደላቸውም፡፡ ወደ የድንኳኖቹ በሰላም በመሄድ ሃዘኑን ተወጥቶአል፡፡ ያም ቢሆን ግን እነዚሁ ለመንግስት ቅርብ ነን የሚሉት ግለሰቦች፤ ፎቶ በመያዝና በተለየ ሁናቴ ለማልቀስ በመሞከር ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለፓርቲያቸው ያላቸውን ታማኝነት ለመግለፅ ሲታትሩ ተስተውለዋል፡፡

ዜናቸው የተዳፈነባቸው ፓትሪያርኩ

ከጠቅላይ ሚ/ሩ አስቀድመው ህልፈተ ህይወት ያጋጠማቸው ፓትሪያርኩ አቡነ ጳውሎስ እንዳለመታደል ሆኖ ከእርሳቸው በኋላም ጠ/ሚ/ሩ በማረፋቸው ሳቢያ ዜናቸው በሚፈለገው መጠን ሳይነገርላቸው አልፎአል፡፡ የአቡኑ ህልፈት ከጠቅላይ ሚ/ሩ በኋላ ቢሆን ኖሮ ካሁኑ የተሻለ ትኩረት ያገኙ እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡

የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ነገር

ቁጥራቸው ቀላል የማይባል እድሜያቸው ከ20 በታች የሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች ምንም እንኳን በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ወደ ጎዳና ህይወት የወጡ ቢሆንም (ኢህአዴግ 21 ዓመቱ ነውና) ጠቅላይ ሚ/ሩ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ህይወታቸውን እንደሚለውጡላቸው ተስፋ ያደርጉ እንደነበር በመግለፅ፤ ይህ ሳይሆን ሞት ስለቀደማቸው ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው ሲገልፁ በኢቴቪ ተመልክተናል፡፡

 

የተምታታበት መፈክር

አብዛኛውን ሃዘንተኛ በንግግሩም ሆነ በመፈክሩ “ጀግናው አይሞትም!” የሚል መፈክር ቢያሰማም ያንኑ ያህል ቁጥር ያለው ሌላው ሃዘነተኛ ደግሞ “ጀግናው ቢሞትም ራዕዩ አይሞትም!” የሚል ለቀደመው መፈክር ማስተባበያ የሚመስል ሌላ መፈክር ይዞ ታይቶአል፡፡

ያልታሰበችው ቀዳማዊት እመቤት ማን ትሆን?

የጠ/ሚኒስትሩ ድንገተኛ ህልፈት የእመቤት አዜብ መስፍንን ቀዳማዊት እመቤትነት ለክቡር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ባለቤት ማስተላለፉ የግድ ይሆናል፡፡ ይህ የታሪክ አጋጣሚ አዲሲቷን እመቤት ወደ አደባባይ ሊያወጣቸውና ከህዝብ ጋርም ሊያስተዋውቃቸው ይችላል፡፡ መኖሪያቸውም ወደ ቤተመንግስት ይዛወራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የአገሬ የሁለት ሳምንት የሃዘን አክራሞት ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ጊዜው ቢኖር ብዙ ትዝብቶችን ባወሳን ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ክስተት የታየው አገሬ እንዲህ ግልፅ/ኦፊሴላዊ በሆነ መልኩ መሪ ሲሞትባት የመጀመሪያዋ በመሆኑ ነው፡፡ በሁሉም ወገኖች ዘንድ የልምድ ማነስ ስለሚኖር ይህ ሁሉ እንዲከሰት ግድ ሆኖአል፡፡

ነገሩን ስናጠቃልለው አውራው ፓርቲ ኢህአዴግ አውራነቱን ረስቶ በአንድ ጠ/ሚኒስትር ላይ ተጣብቆ እንደነበረ በሚያሳብቅ መልኩ ብሔራዊ የሃዘን ቀኑን እያሳለፈ ነው፡፡ አዲሡ ጠ/ሚ/ር በቀጣይ ስላሰቡት ነገር የተባለም የታወቀም ነገር የለም፡፡ ከህዝቡና ከአንዳንድ ባለስልጣናት አንደበት እንደሚሰማው ግን መለስ የጀመሩት አጠቃላይ የልማት ስትራቴጂዎች በቀጣይም ከአገሪቱና ከአዲሱ ጠ/ሚ/ር ጋር አብረው እንደሚዘልቁ ነው፡፡

በእርግጥ በርካታ ዓመታትን ያለ ዕረፍት ስራ ላይ ብቻ በማተኮር ሲተጉ የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ በህልፈታቸው ህዝቡ ከዳር እስከዳር ነቅሎ በመውጣት እንዳዘነላቸው አሳይቶአል፡፡ ይህ ኢህአዴግን የመደገፍ የፖለቲካ ትርፍ ተደርጎ ሊታይ አይገባውም፡፡ ቢሆንም ግን በክፉ ጊዜ እጅ-ለእጅ የሚያያዘውን ይህንን ታላቅ ህዝብ ማድነቅ ግድ ይላል፡፡ በነገው ዕለት ስርዓተ-ቀብራቸው ለሚከናወነው ለጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በገነት ያኖርላቸው ዘንድ ምኞቴን እገልፃለሁ፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

 

 

 

 

 

Read 25268 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:24