Monday, 03 May 2021 00:00

ውጊያውን አሸንፎ በጦርነቱ መሸነፍ እንዳይሆን

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(2 votes)

"--ምንም እንኳን ይህንን ሁኔታ በመቀየሩ ረገድ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ግንባር ቀደም ሃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ማህበራዊ ቀስቃሾችና የፖለቲካ ተንታኞች፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፣ ለሁኔታዎች መባባስ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ መመርመር ይጠበቅባቸዋል።--"
      
             “ውጊያውን አሸንፎ በጦርነቱ መሸነፍ” (Winining the battle but losing the war) የሚለው አባባል፣ በሃያኛው ክፍለ ዘመን በተካሄዱ በርካታ ጦርነቶችና ግጭቶች ትንተና ውስጥ የሚጠቀስ አባባል ነው። በየዘመኑ የነበሩ ኃያላን መንግሥታት ይህንን ጥልቅ አባባል ባግባቡ ባለመርመራቸውና ግምት ውስጥ ባለማስገባታቸው ለከፍተኛ ሽንፈት ሲዳረጉ ኖረዋል። በቅርብ ዘመናት ውስጥ ከተመዘገቡት መሰል የኃያላን መንግሥታት ሽንፈቶች መካከል ግዙፉ የአሜሪካን ጦር በቬትናም ምድር ያጋጠመውና የሶቪዬት ህብረት ጦር በአፍጋኒስታን ምድር የደረሰበት ከባድ ሽንፈቶች ይጠቀሳሉ። ወደ ሃገራችንም ስንመጣ፣ በአፍሪካ ምድር በግዙፍነቱና በጀግንነቱ ይታወቅ የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ሽንፈት የሚያያዘው፣ በወቅቱ የነበሩት መሪዎች የዚህን አባባል ውስጠ ሚስጥር ጠንቅቆ ካለመረዳታቸው ወይንም ለመረዳት ካለመፈለጋቸው ጋር ነው። በብዙ ሃገሮች ታሪክ እንደታየው፣ አንድን ውጊያ በወቅቱ በሚኖረው የወታደራዊ አቅም የበላይነት ማሸነፍ ይቻላል። ማንኛውንም ጦርነት ባሸናፊነት ለማጠናቀቅ ግን፣ ወታደራዊው ድል በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ድሎች መታጀብ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ በቂ በሆነ ከባቢያዊ ዕውቀት ላይ የተመረኮዘና አብዛኛውን ህብረተሰብ ያሳተፈ ሰፊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ማድረግን ይጠይቃል።
ባለፈው ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ፣ የትግራይ ህዝብንም ጨምሮ፣ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያስቆጣና ያሳዘነ እንደነበር ግልጽ ነው። የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) አመራሮች ለበርካታ ዓመታት ታላቁን የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለማቃረንና ለማጋጨት በግልጽም ሆነ በስውር ሲሰሩ ቆይተዋል። በዚህ ወቅት፣ ባብዛኛው የሃገሪቱ የፖለቲካ መሪዎች፣ ምሁራንና የማህበረሰብ አንቂዎች ይራመድ የነበረው የትግራይን ህዝብ ከህወሃት ለይቶ የመመልከት አካሄድ ብስለት የታየበት ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታም፣ በህወሃት የተፈጸመውን አሳዛኝ ጥቃትና ክህደት ለመቀልበስ የተካሄደውን ውጊያ ባጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚል ዕምነት አለኝ። ምንም እንኳን የሃገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የውጊያ ብቃትና ጀግንነት በታሪክ የሚዘከር ቢሆንም፣ ያለ ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ትብብር ዋነኛው ውጊያ እንዲህ ባጭሩ የሚጠናቀቅ ሊሆን እንደማይችል መገመት ከባድ አይሆንም። ለዚህም፣ ከፍተኛ መስዋዕትነት ለከፈለው ለሃገሪቱ የመከላከያ ሠራዊትና ለሠላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ያለኝን ታላቅ አክብሮትና አድናቆት መግለጽ እወዳለሁ።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዋናው ውጊያ መጠናቀቅን ተከትሎ በነበሩ ወራቶች የተሰሙትና አሁንም ከየአቅጣጫው የሚሰሙት ሁነቶች ግን ሃገሪቱ እጅግ አሳሳቢ ወደሆነ የተራዘመ ቀውስ እየገባች ነው ወይ የሚል ስጋት ፈጥሯል። በተለይም፣ ከሶስት ሳምንቱ ውጊያ መጠናቀቅ በኋላ በትግራይ ከተከሰቱት የሰው ህይወት መጥፋትና ከሴት እህቶቻችን መደፈር ጋር ተያይዞ የሚሰማው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በማንም ይፈጸም በማን፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር የተከፈለውን ታላቅ መስዋዕትነት ጥላሸት የሚቀባ ከመሆኑም በላይ፣ ሁላችንንም እንደ ዜጋ የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ሊሆን ይገባል። ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መፈጠር በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የሚከተሉትን በአበይትነት መጥቀስ ይቻላል። ቀዳሚው፣ ወታደራዊ ግጭቱን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ የተደረገውን ዝግጅትና ጥረት ያህል፣ አጠቃላይ ከህወሃት ጋር ያለውን ጦርነት በዙሪያ መለስ አሸናፊነት ለማጠናቀቅ ሊደረግ የሚገባው ዝግጅት ባግባቡ አለመከናወኑ ነው። ለዚህም፣ ቀላሉ ማረጋገጫ ዋናው የሶስት ሳምንቱ ውጊያ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የህወሃት ደጋፊዎች በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ የተቀዳጁት ለማመን የሚከብድ የበላይነት ነው። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በመላው ዓለም የሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ ከኢትዮጵያ ወዳጆችና ዲፕሎማቶች ጋር በመቀናጀት እያደረጉ ባለው ጥረት፣ ይህ ሁኔታ በመጠኑ እየተቀየረ ቢሆንም፣ ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር ግልጽ ነው።   
ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ግን፣ ህወሃት ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ በመላው ትግራይ ክልል ሊከናወኑ የሚገባቸው አካታች የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ መረጋጋት እንቅስቃሴዎች ባግባቡ መከናወን አለመቻላቸው ነው። በዚህም የተነሳ፣ በትግራይ ህዝብ መካከልና በተለይ በወጣቱ ትውልድ ውስጥ እየጎለበተ የመጣው የተጠቂነትና የመከፋት ስሜት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በዚህ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እያለን፣ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወስጥ የሚታየው መፍረክረክና የእርስ በርስ ውንጀላ ችግሩን ይበልጥ እያወሳሰበው ይገኛል። ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ፣ ሁሉንም ውጊያዎች የመከላከያ ሠራዊቱ በአሸናፊነት ቢያጠናቅቅ እንኳን ህወሃትን ከእነ ጎጂ አስተሳሰቡ ለማስወገድ በሚደረገው ዋነኛው ጦርነት ሽንፈት እንዳያጋጥም ያሰጋል። ምንም እንኳን ይህንን ሁኔታ በመቀየሩ ረገድ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ግንባር ቀደም ሃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ማህበራዊ ቀስቃሾችና የፖለቲካ ተንታኞች፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፣ ለሁኔታዎች መባባስ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ መመርመር ይጠበቅባቸዋል። ከነዚህ ጉዳዮች አንዱ፣ ለረጅም ዓመታት ሲነሳ በቆየው የወልቃይትና ራያ ህዝቦች የመብት ጥያቄ ዙሪያ የሚሰጡ ቁንጽል አስተያየቶችና ድምዳሜዎች ናቸው። ይህንን ጥያቄ አግባብነት ባለውና አካታች በሆነ ህጋዊ አካሄድ ከመመለስ ይልቅ በውጊያው አሸናፊነት እንደተመለሰ አድርጎ መደምደም፣ በትግራይ ክልል ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ከማባባሱም በላይ ሃገሪቱን ለሌሎች መሰል ከባቢያዊ ግጭቶች ሊጋብዝ እንደሚችል ጠቋሚ ምልክቶች በመታየት ላይ ይገኛሉ።
ከላይ የተጠቀሰውን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቀየር በመንግስትና ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ ወገኖች ትብብር ሊከናወኑ ከሚገባቸው ተግባራት መካከል ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው። የመጀመሪያው አቢዩ እርምጃ፣ የትግራይን ክልል ወደ አንጻራዊ ማህበራዊ መረጋጋትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችል የሽግግር ፍኖተ ካርታ አካታች በሆነ የህዝብ ተሳትፎ በአስቸኳይ ማበልጸግ ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ፣ ሁሉም በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ ተወካዮች፣  ምሁራን፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ወገኖች ሊሳተፉበት ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ አካታች ሂደት የህብረተሰቡን የባለቤትነት ስሜት ከማጠናከሩም በላይ የአፍራሽ ኃይሎችን ጥረት በእንጭጩ ለማምከን ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል። በዚህ ፍኖተ ካርታ  ላይ ተመርኩዞም፣ የፌደራል መንግሥቱ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መንግሥትን ቅቡልነት ባለው ሁኔታ እንደገና በማዋቀር፣ የክልሉን የሽግግር ጥረት በጠንካራ ህዝባዊ መግባባት ላይ አንዲገነባ ለማድረግ ያስችለዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ፣ ከአንድ ማዕከል በሚፈስ መመሪያ ብቻ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር መሞከር፣ ለጊዜው ውጤታማ ቢመስልም፣ ዘላቂነቱ እጅግ አጠራጣሪ ይሆናል።
ሌላው አፋጣኝ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚሻው ዓቢይ ጉዳይ፣ በወልቃይትና ራያ የማንነት ጥያቄ የተነሳ በአማራውና በትግራይ ህዝቦች መካከል እየተዘራ ያለውን የጠላትነት ስሜት መግታትና ማሰወገድ ነው። እንደሚታወቀው ይህ በሽታ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሲዘራ የቆየና በህወሃት መሪዎች የመታበይና የሴራ ባህሪ መፍትሄ ሳያገኝ የዘለቀ ነው። በጣም አስከፊው የማይካድራው የንጹሃን ዜጎች ጭፍጨፋ የዚሁ ህሊና ቢስ አካሄድ ውጤት ነው። የህወሃትን ሃገራዊ ጥቃት በማክሸፍና መክቶ በመመለስ ረገድ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ያበረከተው ድርሻ ምንጊዜም ሲታወስ የሚኖር ነው። ነገር ግን፣ የዚህ አኩሪ ድል ባለቤት የሆነው የአማራ ልዩ ኃይልና ህዝብ፣ ህወሃት ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የሄደበትን የተዓብዮ መንገድ በመድገም ለሌላ ታሪካዊ ስህተት ላለመዳረግ መጠንቀቅ ያሻል፡፡ ለዚህም፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል ውስጥ የመኖር፣ የመምረጥ፣ የመመረጥና በህጋዊ መንገድ ሃብት የማፍራት መብቱን በማክበር፣ በወልቃይት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን የማፈናቀል ተግባር ባስቸኳይ እንዲቆም ማድረግ እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት ተፈናቅለው የሄዱትን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የመጣውን የማነንትና የወሰን ጥያቄ ለመመለስ የሃገሪቱ ህገ መንግሥት በሚፈቅደው መሰረት ሁሉም የወልቃይትና ራያ ነዋሪዎች በህዝበ ውሳኔ የሚበይኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል።
እነኚህን የተጠቀሱትን ዐቢይ የመፍትሔ እርምጃዎች ተግባራዊነት ለማሳለጥም፣ የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን ወልቃይትና ራያ፣ የህዝበ ውሳኔ እስከሚደረግ ድረስ በፌደራል መንግስቱ አስተዳደር ስር እንዲሆኑ ማድረግ፣ የግጭት ሁኔታዎችን ከመቀነስ ባሻገር፣ የህዝቦችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር ይረዳል።  ከዚህ በተጨማሪ ከላይ የቀረቡትን ሃሳቦች ህዝብን ባካተተና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በሚያጠናክር መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ፣ በፌደራሉ የሠላምና ዕርቅ ኮሚሽን የሚመራና ክትግራይና ከአማራ ክልል የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች የሚወከሉበት የትግራይ የሠላምና የዕርቅ ጉባዔ መሰየምና በአስቸኳይ የህዝብ ለህዝብ ውይይቶችንና ምክክሮችን በየደረጃው እንዲካሄዱ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ምንም እንኳን ይህ ጽሁፍ በትግራይ ክልል ባለው ልዩ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ የተነሱት ሃሳቦች በአሁኑ ሰዐት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየፈነዱ ላሉ ግጭቶች ሁሉ የሚሰሩ ናቸው። በአጠቃላይ፣ ዛሬ ሃገራችን ያለችበት ሁኔታ ላንድ ፓርቲ ወይንም ለተወሰኑ ወገኖች የሚተው ሳይሆን ሁሉም ወገኖች፣ ግጭቶችና ቅራኔዎችን ከሚያባብሱ ሁኔታዎች በመቆጠብ የየራሳቸውን ገንቢ ሚና የሚጫወቱበት ወቅት ነው። ለዚህም መሳካት፣ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ፣ በዕውቀትና አስተውሎት ላይ የተመረኮዘ አካታች አመራር የመስጠት ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።                                                   
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።


Read 9427 times