Print this page
Sunday, 25 April 2021 00:00

በአለም ዙሪያ ዓምና ብቻ ከ483 በላይ ሰዎች በሞት ቅጣት ተገድለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በአለም ዙሪያ ባለፈው የፈረንጆች አመት ብቻ ከ483 በላይ ሰዎች የሞት ቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸው እንደተገደሉና ከእነዚህም ውስጥ 88 በመቶ የሚሆኑት በአምስት አገራት ውስጥ ብቻ የተፈጸሙ እንደሆኑ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰሞኑ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በአመቱ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በሞት ከቀጡ ቀዳሚዎቹ አምስት አገራት ውስጥ አራቱ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ኢራን 246፣ ግብጽ 107፣ ኢራቅ 45 የሞት ፍርድ ቅጣቶችን በመፈጸም ከአለማችን አገራት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡
ግብጽ የሞት ቅጣት ያስተላለፈችባቸው ሰዎች ቁጥር ከአምናው በሶስት እጥፍ ማደጉን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በሳኡዲ አረቢያ በአንጻሩ ቁጥሩ በ85 በመቶ ያህል ከአምናው መቀነስ ማሳየቱንና ይህም ሊሆን የቻለው አገሪቱ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ጥፋተኛ የሆኑትን በሞት ፍርድ መቅጣት በማቋረጧ ሰበብ ነው መባሉንም አክሎ ገልጧል፡፡
በአመቱ በመላው አለም የተመዘገበው የሞት ቅጣት ባለፉት አስር አመታት እጅግ ዝቅተኛው ነው ቢባልም፣ ሪፖርቱ ግን በሞት በመቅጣት የሚታወቁትንና መረጃዎቻቸውን አሳልፈው የማይሰጡትን ቻይና፣ ሰሜን ኮርያ፣ ሶርያና ቬትናምን አለማካተቱ ቁጥሩን በእጅጉ ዝቅ እንደሚያደርገውም ተነግሯል፡፡ በአለማችን 108 ያህል አገራት የሞት ፍርድ ቅጣትን ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውንም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡


Read 3901 times
Administrator

Latest from Administrator