Sunday, 25 April 2021 00:00

"የሁለቱ መደመሮች" መጽሐፍት ዳሰሳ

Written by  አንዳርጋቸው ጽጌ
Rate this item
(1 Vote)

   (ክፍል -3)
ያለ መደመር ያለፉት ዘመናት፣ መጪው ዘመን በመደመር እይታ
የኢትዮጵያ መንግስታት “የሃገሪቱን ችግር እናቃልላለን” በሚል ፖሊሲዎች ነድፈዋል። ተቋማት ገንብተዋል ወይም ለመገንባት ሞክረዋል። የሰው ሃይል አሰልጥነዋል። “ሃገር ለማዘመን፣ ድህነት ለመቅረፍ፣ ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ገናናነቷ ለመለስ” በሚል ብዙ ነገር ለማድረግ ሞክረዋል። ሁሉም በአንድ አይነት ሚዛን የሚለኩ ባይሆኑም።
በኢትዮጵያ ስንት አይነት የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ስርአት ነበረ። ንጉስ መር ባላባታዊ የካፒታሊስት ስርአት  የትም የማይወስደን በመሆኑ፣ በሶሻሊዝም ተተካ። ሶሻሊዝም የትም ሳይወስደን ሲቀር በብሔር ፌደራሊዝምና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተተካ። አሁን ደግሞ እድሜው አጭር ቢሆንም፣ ቃሉ በውል በተግባር ሲተረጎም ምን እንደሚመስል ባናውቅም፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርአቱ “በመደመር” እሳቤ ወደ ዴሞክራሲና ወደ ብልጽግና እንደሚያመራ እየተነገረን ነው።
በወያኔ ዘመን ብቻ “መልካም አስተዳደር ለማስፈን፣ የተሳለጠ መንግስታዊ አገልግሎት ለህዝብ ለመስጠት ብልጽግና ለማስፈን በሚል ስም ስንት አይነት ፖሊሲዎች ተቀረጹ፣ ስንት አይነት የአሰራር ፈሊጦች (Fads) ተዘረጉ፤ ታጠፉ። ለሰራተኞች የሙያ ማሻሻያ፣ የስነምግባር ማዳበሪያ እየተባለ፣ ስንት ወርክሾፖች፣ አውደ ጥናቶች፣ ስልጠናዎች ተሰጡ። ስንት ነዋይ ፈሰሰባቸው።
ዐቢይ በደንብ እንደሚያውቀው (የመደመር መንገድ ገጽ 6 እና ገጽ 101) ኢህአዴግ ውስጥ ግምገማ የሚባለው ነገር አላማው በኋላ እየተቀየረ ቢሄድም፣ የድርጅቱን መሪዎችና አባላት በማያቋርጥ የግምገማ ሂደት ህጸጾቻቸው ሳይከማቹ ማረም ነበር። ስንት ሺህ ግምገማዎች ተካሄዱ። የእነዚህ ግምገማዎች መጨረሻቸው ምን ሆነ? ሌላው ኢህአዴግ ውስጥ በትግሉ ወቅት ጎልብቶ የነበረ አሰራር ስራን በእቅድ መስራት ነው። ጥቂት የተማሩ የወያኔ አመራሮች፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ያልተማሩ አባላቶቻቸውን መስመር አስይዞ የሚፈልጉትን ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ የማያፈናፍን እቅድ በማዘጋጀትና እቅዱን በቁጥጥር ማስፈጸም ብቻ መሆኑን የተረዱት ገና በማለዳው ነበር። ከቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርት የተወሰዱ ፈሊጦችን በመጠቀም በጣም ጥቂቶች አንድን በቂ እውቀት የሌለውን ሰፊ ሃይል ባሻቸው መንገድ መምራትና የፈለጉትን አጀንዳ ማስፈጸም እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።
የኢህአዴግ ተራ ታጋይ አንድ ስራ ሲባል እቅዱ የታለ ብሎ የመጠየቅ የሚያስገርም ልምድ እንደነበረው ይታወቃል። ዐቢይም በኢህአዴግ ውስጥ እሱ እራሱ ያለፈበት ሂደት ነው። ታጋዩ እቅድ ተዘጋጅቶለት፣ በእቅድ ላይ ኦረንቴሽን (ማብራሪያ) ካልተሰጠው ፈጽሞ በግል ተነሳሽነት ምንም አይነት ስራ የሚሰራ አልነበረም። ትግሉ ካበቃ በኋላ ሁሉም የኢህአዴግ መሪዎች መለስና ሌሎችም በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁትንም ጨምሮ አንዳቸውም ሳይቀሩ በኮርስፖንደንስ “የተማሩት” ትምህርት ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን (MBA) የሆነው ለዚህ ነው። ያ የቆየ ልምድ፣ የኢህአዴግን ሰዎች፣ ችግሮችን ቴክኒካዊ ብቻ በሆነ መንገድ መፍታት ይቻላል የሚሉ፣ ስፋት ያላቸውን የፖለቲካ የፍልስፍና ጥያቄዎችን ማንሳት አላስፈላጊ አድርጎ የሚያይ ስነ ልቦና ያላቸው መሪዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ዛሬ በየመስሪያ ቤቱ በመንግስት ሃላፊነት ከፍተኛና ዝቅተኛ ደረጃ የተቀመጠ የቀደሞ የኢህአዴግ ካድሬ፣ ኢህአዴግ በቃል ያስጠናውን የስራ ማከናወያ ፎርማት በቃሉ የማያውቅ የለም። አንድ ወንበር ከአንድ ጥግ ወደ ሌላው ጥግ ለማንቀሳቀስ የፕሮጀክቱ አላማ፣ ቅድመ ዝግጀት፣ ዝግጅት፣ የሚያስፈልጉ ግብአቶች፣ ስራን በየምእራፉ መቆጣጠሪያ ነጥቦች፣ የስራው ባለቤት፣ ስራ የሚፈጸምባቸው ቀናት፣ ውጤት፣ የውጤት መገምገሚያ ነጥቦች ወዘተ የሚል ነገር ሳይደረድር ስራ የሚሰራ አካል ያለ አይመስለኝም። ኢትዮጵያ ለስራ ከሚጠፋው ሃብትና ጉልበት ይልቅ ፕሮፖዛልና ፕሮጀከቶች በማሽሞንሞን የሚጠፋው ጉልበት፣ ገንዘብና ጊዜ የሚጠፋባት ሃገር ሆናለች። በየመስሪያ ቤቱ መግቢያ ላይ፣ የተቋሙ ተልእኮ፣ ራእይና መርህ የሚሉ ከመስሪያ ቤቱ የቆሸሸና ህዝብ አንገላታች አሰራር ጋር የሚጻረሩ፣ ብዙ ገንዘብ የወጣባቸው ቢል ቦርዶች፣ በኢህአዴግ ዘመን የነበሩ የአሰራር ፈሊጦች ለስራ ሳይሆን በባእድ አምልኮት ደረጃ ያደጉ ጣኦቶች ለመሆናቸው ማስረጃዎች ናቸው። ከፈረንጆቹ ተኮርጀው መጥተው ያለ ቦታቸው የሰነቀርናቸው አጸያፊ ነገሮች ሆነው ነው የሚታዩት።  
“ታማኝነት እንጂ ትምህርት ለሹመት አያስፈልግም” የሚለው የመለስ አባባል ስራን አቅደን ከሰጠነው፣ መቆጣጠሪያውን ካበጀንለት ማንም መሃይም በሚኒስትርነት ቦታ ብናስቀመጠው ስራውን መስራት ይችላል ከሚል በትግሉ ዘመን ተፈትኖ ውጤት አስገኝቷል ከሚባልለት ልምድ የፈለቀ አባባል ነው። እንዲህ አይነቱ እንደ ዶሮ በቀጭን ገመድ የታሰረ ሚኒስትር፣ ገመዱ ሲላላ ስራውን የማይበድልበት፣ የግል ጥቅም አሳዳጅ የማይሆንበት ምንም የሚያቆመው ነገር እንደሌለ በተግባር ታይቷል። እንዲህ አይነቱ ሚኒስትር በየቢሮው ተጎልቶ ስራ ተሰራ አልተሰራ፣ መንግስት በሰጠው ላፕ ቶፕና ዋይፋይ አደንዛዥ መዝናኛ ሲኒማ ሲያይ፣ የአለምን አሉባልታ በማህበራዊ ሚዲያ ሲያላምጥ ውሎ ያለምንም ሀፍረት ከቢሮው ወጥቶ እንደሚሄድ ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ነው።
ከዚህ በላይ ያስቀመጥኳቸው ነገሮች እውነት መሆናቸው በዶ/ር ዐቢይ ይታወቃሉ። በዛው ልክ ግምገማው፣ በእቅድ መስራቱም (የፈለገው ድክመት ቢኖርበትም) ችግር ፈችነታቸው እየተዳከመ፣ ችግሮች በኢህአዴግ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሃገር ደረጃም እየተበራከቱ እንደሄዱ ዐቢይ በመጽሐፎቹ ደጋግሞ የገለጸው ሃቅ ነው። ግምገማ፣ የእቅድ ፎርማቶች፣ የስራ አፈጻጸም መመሪያዎች፣ የሙያና የስነምግባር ግንባታ ስልጠናዎች፣ በኮርስፖንዳንስና በውጭ ሃገር ጉዞ ትምህርት በመከታተል የተገኙ ዲግሪዎች፣ ኢህአዴግን ይሁን ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ ሲያደርሷቸው ማየት ግን አልተቻለም። ለምን?      
ዐቢይ የኢንሳ-ኢመደኤ (በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ) ሃላፊ በነበረበት ወቅት “የመደመርን እሳቤ በተግባር ስራ ላይ  በማዋል ያገኘውን ስኬት  በሃገር ደረጃ ማዛወር ይቻላል” የሚል ጽኑ እምነት አለው።  ይህ እምነት ሃገራዊ ችግሮቻችንን አንዳንድ ቴክኒካዊ የሆኑ መፍትሄ ብንፈልግላቸውና በሚገባ ለመተግበር ብንሞክር ይቃለላሉ የሚል ኣስተሳሰብ ውጤት ነው ( የመደመር መንገድ ገጽ 20)። ይህን የምለው ዐቢይ በኢንሳ ላገኘው ስኬት ከሚሰጠው ትልቅ ትርጉም በመነሳት ነው። ግን ኢንሳ በጣም አነስተኛ በቀላሉ ሰዎች ሊቆጣጠሯቸው የሚችሏቸው ተለዋዋጮች (variables) እንቅስቃሴውን የሚገዙት ተቋም ነው።፣ የተቋሙ አለቃ በሆነው ግለሰብ ብቃትና ጽናት ሊቃለሉ የሚችሉ ችግሮች ያሉበት፣ አነስተኛ የሰራተኛ ቁጥርና እንደ አዲስ ስራ የጀመረ ተቋም ነው። ዐቢይ ይህን ተቋም  ኢትዮጵያ ከምትባል ውስብስብ ተቋም ጋር ለንጽጽር ማቅረብ የማይችል እንደሆነ በደንብ ያጤነው አይመስልም።
እንደ ዐቢይ አገላለጽ፤ ከኢንሳ ትልቁ ስኬት ተቋሙ ያፈራቸው በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤት በከፍተኛ ሃላፊነት መስራት የቻሉ ግለሰቦች መኖራቸው ነው። ከነዚህ የኢንሳ ሰዎች መሃከል ስንቶች ዐቢይ ካስቀመጣቸው ከፍተኛ የሞራልና የብቃት ማማ ላይ ዛሬ እናገናቸዋለን። ኢንሳ ካፈራቸው መሪዎች መሃል ስንቶቹ ከወያኔ ጋር ሆነው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተግተው ሲሰሩ አየናቸው። ዐቢይ ይህን ሃቅ በጥሞና መፈተሽ ችሎ ቢሆን  ችግራችን የትምህርት፣ የስልጠና፣ የተቋም ግንባታ፣ የመዋቅር ማሻሻያ ብቻ ሳይሆን ከዛም ያለፈ መሰረታዊ ችግር እንደሆነ ማየት ይችል ነበር።
ዐቢይ ለመደመር ስኬት አስፈላጊ ናቸው የሚላቸው ነጥቦች፣ የጋራ የሆኑትን መለየት፣ የጋራ ግብ ማስቀመጥ፣ ለጋራ ግብ መስራት ናቸው (መደመር ገጽ 43)። እነዚህ ሶስት መሰረታውያን በወያኔ ዘመን ከታዩ ሌሎች ተመሳሳይ እቅድ ማዘጋጃ፣ መቆጣጠሪያ፣ ማስፈጸሚያ የተለያዩ ሞዶች (Fads) መሰረታዊ ልዩነቶቻቸው እምብዛም የሚታይ አይደለም። ተግባር በጋራ የሚፈጸም እስከሆነ ድረስ ግቡም የጋራ ነው። ግብ የጋራ ቢሆንም ፈጻሚዎች ግለሰቦች ናቸው። ኢትዮጵያ ማድረግ ያልቻለችው ግለሰቦችን የጋራ ለሆነው ግብ ጥልቅ በሆነ የጋራነት ስሜት እንዲተጉ ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ፣ ብዙሃኑ በጋራ ለጋራ ግብ መስራታቸው ቀርቶ ጥቂቶች በተናጠል ሃገርና ህዝብን እያሰቡ የማይሰሩባት ሃገር እየሆነች መሄዷ የማይካድ ሃቅ ነው። ይህ ደግሞ ቀደሞ ከነበሩት ዘመናት ይበልጥ በወያኔ ዘመን እየባሰበት የሄደ ጉዳይ ነው።   
ዐቢይ በደንብ የታሰበባቸው ፖሊሲዎች አለመኖራቸው ሲነግረን በተሰበሩ ፖሊሲዎችም ቢሆን ለምን የተሰበረ እድገት ማምጣት እንዳልቻልን አይጠይቅም? የተማረ የሰለጠነ ሙያተኛ በሁሉም መንግስታዊና የግል ድርጅቶች ሃላፊነቶች ላይ የማስቀመጥን አስፈላጊነት ሲነግረን ለምን በከፍተኛ ደረጃ ትምህርትና ስልጠና የወሰዱ ሰዎች እንዳልተማረና ስልጠና እንዳልወሰደ ሰው እንዲያውም በባሰ ደረጃ ስልጠናቸውንና ትምህርታቸውን የማይመጥን ስራ ሲሰሩ ይገኛሉ ለሚለው ትዝብት መልስ አይሰጠንም።
በሌሎች ሃገሮች ስሉጥ መንግስታዊ አገልግሎት ለህዝብ መስጠት የቻሉ፣ የተዋጣላቸው የስራ ማቀጃና መተግበሪያ ክህሎቶች ወደ ሃገራችን በከፍተኛ ወጪ ስራ ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መንግስታዊ አስተዳደሩ ህዝብን ያስመረረ፣ በጉቦ በምልጃ በዘመድ አዝማድ በዘር የሚሰራ፣ እንዳውም እየባሰበት እንጂ የመሻሻል ፍንጭ የማይታይበት እየሆነ ለምን ይሄዳል ብሎ ዐቢይ አይጠይቅም። እነዚህ ስራ ማሳለጫ ዘመናዊ  መሳሪያዎች ሳይኖራቸው የአጼ ሃይለስላሴና የደርግ ዘመን ቢሮክራሲዎች ከወያኔ ዘመን ቢሮክራሲ ለምን የተሻለ እንደነበሩ ጥያቄ አያነሳም።
የመደመር መንገድ ገጽ 65 ላይ ችግሮቻችንን “ትክክለኛ መሪዎች በመፍጠር፣ የለወጥ አስፈንጣሪዎች በመፍጠር፣ የለወጥ ባለቤት ብዙሃኑን ህዝብ በማድረግ” መፍታት እንደምንችል የቀረቡ ሃሳቦች አለው። ተራ የቢሮክራት የስነ ምግባርና ህዝብ አገልጋይነት መስፈርቶች ከንጉሱ ዘመንና ከደርግ ዘመን እየባሰበት እየሄደ ባለበት፣ ማንኛውም ወጣት የሃገሩን ጉዳይ እንደራሱ ጉዳይ እንዳያይ በከፋ ግለሰበኛነትና ጎጠኛነት የተመረዘ ሃገር ውስጥ እየኖረ እንዴት ትክክለኛ፣ አስፈንጣሪ መሪና የለውጥ ባለቤት ነኝ የሚል ህዝብ መፍጠር እንደሚቻል ዐቢይ አይነግረንም።
ድህነት ያጠፋል፣ የብዙኃኑን መብት ያስከብራል የተባለው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስት የዜጎችን መብት አሰቃቂ በሆነ መንገድ ያፈነ፣ በገዛ ሃገራቸው ዜጎች በድህነትና በኑሮ ወድነት ከሚጠበሱ ከገዛ ሃገራቸው ይልቅ መከራና ሞት የበዛበትን የስደት ህይወት ሚሊዮኖች እንዲመርጡ አድርጎ ማረፉን እያየን ነው።
“የአገር ህልውናን በተሻለ መሰረት ላይ ለማጽናት” በሚል የተሞከረ የመንግስትና የአስተዳደር አወቃቀር መቀመቅ ውስጥ ጨምሮናል። የቋንቋ ፌደራሊዝም በፍጥነት ወደ ዘር ፌደራሊዝም እንዴት እንደተንሸራተተ፣ ሁሉም በየዘሩ ዝግ እስር ቤት ተቆልፎ፣ ነገ አንዱ በሌላው ዘር ለሚለኩስበት የዘር ጦርነት በተጠንቀቅ የቆመበትን አስፈሪ ሁኔታ ፈጥሯል። የሰው ልጅ በገዛ ሃገሩ፣ በገዛ የሃገሩ ሰው በዘሩ እየተለየ እንደ ከብት የሚታረድበትን አሳዛኝና አሰቃቂ አገር አስረክቦናል። ወያኔ የዘረጋው የመንግስትና የአስተዳደር አወቃቀር የሃገርን ህልውና ማስከበር ሳይሆን የሃገር ክስመትን የሚያፋጥን ሂደት አስጀምሮ አርፎታል።
እውነት ነው፤ ኢህአዴግ በጣም አጥብቦ ሜካኒካዊ አድርጎ ያያቸውን ጉዳዮች ዐቢይ አስፍቶ አይቷቸዋል። ቴክኒካዊ ከሆኑ ጉዳዮች በመሻገር ከመደመር ጋር የተያያዙ በጎና ጎጂ ሥነልቦናዊ ቅላጼዎች ምን እንደሆኑ ዘርዝሮልናል። የቴክኒክ ብቻ ሳይሆን የባህል፣ የሥነልቦና ተሃድሶም አስፈላጊ እንደሆነ ደግሞ ደጋግሞ ነግሮናል። የመደመር እንቅፋቶች፣ የመደመር የተግባር ሳንካዎች ምን እንደሆኑ ገልጾልናል። የመደመር አምዶች በማለት (የመደመር መንገድ ገጽ 36) ህዝቦች ኪሳራ ሳያስተናግዱ አትራፊ የሚሆኑበትን ግንኙነት መመስረት የሚችሉባቸውን ዘዴዎች ነግሮናል። እነዚህ ሁሉ ከመደመር ጋር የተሳሰሩ በተለያዩ ቃላቶችና ከተለያዩ እይታዎች የቀረቡ ሃሳቦች እንደ ሃሳብ ውብ ሃሳቦች ናቸው። ሃሳቦቹ ችግር ላይ የሚወድቁት ከወረቀት ወርደው ተግባራዊ በሚያደርጋቸው ሰው እጅ ሲገቡ ነው።
ሰዎች በመመሪያ በትእዛዝ በስልጠና በተማጽእኖ ከሚፈጽሙት የጋራ ግብ በላይ ቀጣይነት  ላለው ትልቅ ክንውን እንዲነሱ የሚያደርጋቸውና የሚያጸናቸው በጋራ ማንነት በጋራ እጣ ሲተሳሰሩ ነው። ኢትዮጵያ ይህ መሰረታዊ የጋራ ነገር የጠፋባት ሃገር በመሆኗ ለሃምሳ አመታት ፖለቲካውም ኢኮኖሚውም ባለበት ከመርገጥ ግን ነቅነቅ ማለት አልቻለም። እንዳውም እየባሰበት ነው።
በጥቅሉ ዐቢይ ከግል ፍላጎታችን ሃገራችንን ብናስቀድም፣ በጥላቻ ቦታ ፍቅርን ብናነግስ፣ ከምንጠላለፍ ብንተባበር፣ በህዝብ ከመገልገል ህዝብን ብናገለግል፣ በግል ከመትጋት በጋራ በመትጋት ችግሮቻችን እንዴት በቀላሉ መቅረፍ እንደምንችል በተማጽኖ ደረጃ የሚያቀርባቸው ነጥቦች እሱ ሲያቀርባቸው አድማጭ እንደሚያገኙ ሌሎች ሲያቀርቧቸው ግን ለምን ተደማጭነት እንዳላገኙ ተጨንቆ ያሰበ አይመስልም።
ያለፉትን መቶ አመታት ብቻ ብንወስድ ተመሳሳይ ማሳሰቢያዎች ተማጽእኖዎች ከበርካታ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ቀርበዋል። ነገስታቱ፤ ነገስታቱን ያስወገዱ አምባገነኖች ሳይቀሩ የቀደሞ የሃገሪቱን ገናናነት እያጣቀሱ በአንድነት መትጋትን እየሰበኩ ብዙ ብለዋል። የሃገር ወዳድ ምሁራን የእድሜ ልክ ውትወታ ይሄው ነበር። ከመቶ አመት በፊት ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ “መንግስትና ህዝብ” በሚለው መጽሐፋቸው፤ ኢትዮጵያውያን ከሌላው የአለም ህዝብ የሚለያቸውን ገናና ታሪክ፣ ጀግንነት ከዛም አልፎ የብሩህ አይምሮ ባለቤትነትን በምሳሌነት  እየጠቀሱ እንዴት በስልጣኔ፣ በዘመናዊነትና በብልጽግና ከአለም ጭራ እንሆናለን፣ ማስተካከያዎች ካደረግን ከሰለጠኑት ሃገሮች በላይ መሆን እንደምንችል ቁጭት በተሞላው መንገድ ጽፈዋል።
በአፍሪካ ውስጥ ብዙ አነቃቂ ተናጋሪዎችና አልፎ አልፎም አንዳንድ የሃገር መሪዎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ንግግሮች ያደርጋሉ። መሬት ላይ ግን ጠብ የሚል ለውጥ የለም።
የሚገርመው እንቆቅልሽ ችግሮቻችን እየተወሳሰቡና እየከፋባቸው እየሄዱ እንደሆነ ዐቢይ በመጽሐፎቹ የሚክደው ነገር አለመሆኑ ነው። ይህን ብሎንም እሱ ተስፋ እንደማይቆርጥ፣ እኛም ተስፋ እንዳንቆርጥ አጥብቆ ይማጸነናል። ሃገሩን የሚወድ አንባቢ በተማጽእኖው ልቡ መነካቱ አይቀርም። ዐቢይ በመደመር የማናሸንፈው ችግር የለም ብሎ ያስባል።
ዐቢይ ሃገሪቱ እንደ አንድ የፖለቲካዊና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ከመቆም ይልቅ ወደ ተሰነጣጠረ ማህበረሰቦች እየተቀየረች እንደሆነ ደጋግሞ ነግሮናል። ቴክኒካዊ ከሆኑ የችሎታና የብቃት ችግሮች ይበልጥ ሃገሪቱን ወደፊት እንዳትራመድ ሰንጎ የያዛት ልሂቃኑ መግባባት የታሳኑባቸው ጉዳዮች በመብዛታቸው መሆኑን ዐቢይ ተረድቶታል።
ይህ የተለያየ አመለካከት ከታሪክ አንስቶ፣ ዴሞክራሲን፣ ፌደራላዊ አወቃቀርና አስተዳደርን፣ የመንግስትን ቅርጽ፣ ሰንደቅ አላማን፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲንና ሌሎችንም አካቶ በተቃራኒ ጫፍ የቆመ መሆኑን ዐቢይ በግልጽ አስፍሮታል (መደመር ገጽ 119)። ዋልታ ረገጥ  አተያዮች አቋሞች ሃገሪቱን ሰንገው በመያዝ አበሳዋን እያሳይዋት እንደሆነ ጽፏል። ሁለተኛው መጽሐፍ የተሞላው እነዚህን ችግሮች ማስረዳት በሚችሉ ምሳሌዎች ነው። ዐቢይ ይህን ሁሉ ተገንዝቦ በመፍትሄነት የሚያቀርባቸው ሃሳቦች ከዚህ በፊት የተለያዩ መንግስታትና የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚያቀርቧቸው የተለዩ አለመሆናቸው ድካሙን መና አስቀርቶታል የሚል እምነት አለኝ።
“መደመርን” ወደ ትልቅ ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ ፋይዳ ወዳለው ፍልስፍና ማሳደግ የሚቻልባቸው የዶ/ር ዐቢይ ምልከታዎች
በኔ እምነት ዐቢይ ለችግሮቻቸን ሁሉ መፍቻ ወደሚሆኑ መደመርን ትልቅ ሃገራዊና አህጉራዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ማድረግ የሚችልባቸው የሃሳብ ክሮች በራሱ መጽሐፍ ውስጥ ነበሩት። እነዚህ ክሮች እየተረተረ ወደሚወስዱት ስፍራ ለመሄድ አልቻለም። ለምን አልቻለም?
 የፖለቲካ መሪ እንጂ ፈላስፋ ስላልሆነ አንዱ ምክንያት ነው። በፖለቲካ ፕራግማቲክ  መሆን የግድ ስለሆነ። በፍልስፍና መልኩ የሚያቀርባቸው ሃሳቦች ከወቅቱ የፖለቲካ እውነታ ጋር የማይሄዱ ከሆነ ሺህ ጊዜ ሃቅ ቢኖራቸውም ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያይላል ተብሎ ታስቦ ሊሆን ይችላል።
ሌላው ዐቢይን ስር ነቀል የእይታ ለውጥ እንዳያደርግ ምክንያት የሆነው ቀደም ብዬ የገለጽኩት፣ መሰረታዊ ለሆኑት የሃገሪቱ ችግሮች መፍትሄ የሚሻው በጠንካራ ኢህአዴጋዊ እይታ ነገሮችን እያየ በመሆኑ ሊሆን ይችላል።  ዐቢይ፣ የትም የማያደርሱ በንድፈ ሃሳብ ይሁን በተግባር በርካታ ችግሮች ያስከተሉ የኢህአዴግ ዘመን የፖለቲካ ቲዎሪዎችንና ፖሊሲዎችን፣ ችግሩ ከቲዎሪው/ፖሊሲው ሳይሆን ከአተገባበሩ ነው በማለት የተግባር ማሻሻያ በማቅረብ ለመሄድ ያደረገው ሙከራ የሚያሳየው ስር ነቀል የአተያይ ለውጥ (Paradigm shift) ማድረግ እንዳልቻለ ነው። በሳይንስም ሆነ በሌላው የእውቀት ዘርፍ ስር ነቀል የአተያይ ለውጥ እንቅፋት፣ ነባሩን አተያይ ችግር ፈጣሪ ነው ብሎ ከመጠራጠር አተያዩ ተግባራዊ እየሆነባቸው ያሉ ስልቶችን፣ የመተግበሪያ መሳሪያዎችን፣ ሁኔታዎችን መጠርጠር ነውና።
የመጨረሻው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ችግሮቹን በደንብ ተገንዝቦ፣ ከችግሮቹ መውጫ መንገዶቹንም ከምሩ ፈልጎ፣ በመጽሐፉ ካስቀመጠው የችግር መውጫ መፍትሄ ሌላ አማራጭ አልታይህ ብሎት ሊሆን ይችላል።
ቀጥሎ፣ በኔ አስተያየት ዐቢይ በሁለቱ መደመሮች መጽሐፎቹ ውስጥ እያነሳ የተዋቸው፣ ነገር ግን ለስር ነቀል የአመለካከት ለውጥ መነሻ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ጉዳዮችን ወደ ማሳየት እሄዳለሁ፡፡    
“መደመር” ገጽ 34 ላይ
“ከኢትዮጵያውያን መሰረታዊ ስሪት የሚነሳ ችግሮቻችን ሊፈታ የሚችል፣ እኛው እያቃናነውና እያሟላነው የምንሄደው፣ ከአለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ፣ ሁላችንንም ሊያግባባና ሊያስተባብር የሚችል  አንዳች ሉአላዊና ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ያስፈልገናል” ይላል።  
ዐቢይ ይህን ብሎም ሃሳቡን አይገፋበትም። እንዲያውም ይህን ንኡስ ምእራፍ የሚዘጋው ኢትዮጵያዊ የሆነውን ፍልስፍና የምናገኘው “በአለም ላይ የሚቀነቀኑ ፍልስፍናዎች በመዳሰስ” ነው በሚል በሌሎች ቦታዎች ያስጠነቀንን የውጭ ፍልስፍና ቃራሚነት የሚያመጣውን አደጋ በሚያቃልል መልኩ ነው።
በሌሎች የመጽሐፉ ክፍሎች ለምሳሌ “መደመር” ከገጽ 103 እስከ ገጽ 125 በሚደርሱት ገጾች፣ እንዲሁም በ “የመደመር መንገድ; ገጽ 43 ላይ  ዐቢይ ምን አይነት ዴሞክራሲ ያስፈልገናል? በሲቪክ ብሔረተኛነትና በማህበረሰባዊ ብሔረተኛነት መካከል ስላለው መሳሳብ፣ የሀገረ መንግስት ቅቡልነት የማረጋገጥ ፈተና በሚሉ ርእሶች ስር መሰረታዊ ወደ ሆነው የሀገሪቱ ችግሮች የሚጠጋበት እድል አግኝቶ ነበር።
እነዚህን ችግሮች የሚመለከትበት አይን ከኢህአዴግ በወረሰው በተለመዱት የፖለቲካና የታሪክ መነጽሮች አይን ስለሆነ ያው ሌሎች ደግመው  ደጋግመው ሲያቀርቧቸው ከነበሩት መፍትሄዎች የተለየ መፍትሄ ማቅረብ እንዳይችል አድርጎታል። “ኢህአዴግ ለሃገራዊ አንድነት” ትኩረት ባለማድረጉ ችግር ላይ እንደወደቅን እንጂ ኢህአዴግ ሃገራዊ አንድነት እንዳይኖር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሆን ብሎ ይሰራ የነበረ ድርጅት መሆኑ ዐቢይ አይታየውም። የብሔር ማንነትም ሆነ ሃገራዊ ማንነት በሚዛን መሆን ይኖርባቸዋል የሚል አስተሳሰብ እንጂ የሃገራዊ አንድነት ከሁሉም ነገራችን በላይ ወሳኝነት ያለው አለመሆኑ ያስከተለውን መዘዝ ማየት የቻለ አይመስልም።
በአንድ ሃገር ሁለት አይነት በእኩልነት የሚታዩ ብሔረተኛነቶች ሊኖሩ አይችሉም። ይህ የስሜት ተፈጥሯዊ ባህርይ ነው። ብሔረተኛነት ደግሞ ስሜት ነው። አንዱ ስሜት የግድ ከሌላው በላይ መሆኑ የግድ ነው። እያየነው ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው ችግር ከዚህ የመነጨ ነው። የማይታረቁ ነገሮች እንደሚታረቁ አድርጎ በማቅረብ ነው ሃገር ችግር ውስጥ የወደቀችው። ችግሩ የሚፈታው በጥገና ሳይሆን ስር ነቀል የአመለካከት ለውጥ በማድረግ ነው።
#ኩሩ ትግሬ ሆኖ ኩሩ ኢትዮጵያዊ የማይኮንበት ምክንያት የለም; የሚለው የመለስ ዜናዊ አባባል በራሱ በመለስ ዜናዊ ጭንቅላት ውስጥ እንጂ በእውን አለሙ የማይገኝ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልግ ነበር። ዛሬ የመረጃ እጥረት ያለብን አይመስለኝም። ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች ኢትዮጵያን በመሰለ ሃገር ውስጥ በጋራና በሰላም ለመኖር ሁሉም ብሔሮች በመግባባት የተቀበሏቸው አይነኬ የሃገር አንድነት እሴቶች የግድ መኖር እንዳለባቸው በአመክኖዋዊ ትንተና ማሳየት ይቻላል።  እንደ ነጋዴ ሁለቱን የብሔረተኛነቶች አይነት ሚዛን ላይ በማስቀመጥ እያቻቻሉ የሚፈታ ችግር እንዳልሆነ መታወቅ ነበረበት። እነዚህን በመሰሉ ችግሮች ላይ ዐቢይ ብዙ ትኩረት ቢያደርግም፣  የአመለካከት ሽግግር  በማድረግ ወደ እውነተኛው መፍትሄ መጠጋት አልቻለም።
ዐቢይ በሃገራችን ውስጥ የትብብር የአንድነት ውጤት የሆኑ ብዙ ክንውኖችን በምሳሌነት ያነሳል። የጋራ ሊሆኑ የሚችሉ እሴቶቻችንን በስፋት ያቀርባል። “ወደ ኋላ ዞር ብላችሁ እዩት ስንተባባር ምን መስራት እንደምንችል። ያለፈው በትብብር ላይ የተገኘ የድል ታሪካችን የወደፊቱ ታላቅነታችን የመሰረት ድንጋይ መሆን ይችላል” እያለ ይወተውተናል።  “ጣሊያንን አሸንፋለሁ ብሎ በተስፋ ከቤቱ የወጣ ያ የአድዋ የድል ባለቤት እንዴት ለጥቃቅን ነገሮች ተሸንፎ እጅ ሰጥቶ ምኞትና ህልሙን በመቀስ ቆረጠ (ገጽ 360 የመደመር መንገድ)።” ይለናል።
ዐቢይ ደግሞ ደጋግሞ #ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን እንዳንለያይ ሆነን የተጋመድን… እጣችን … በአብሮነታችን ድርና ማግ ውብ ሆኖ የተሸመነ ጥበብ” መሆኑ ይነግረናል (የመደመር መንገድ ገጽ 352)። ደግሞ ደጋግሞ በኩራት የሚያነሳቸው የኢትዮጵያ የታሪክ ቅርሶች፣ በጋራ ጠላትን በመመከት የተገኙ ድሎች በመደመር ምን ማከናወን እንደሚቻል ከመጠቆም አልፈው ራሱ የመደመር ሃሳብ የሚፈተልባቸው ድርና ማግ እንዴት መሆን እንደሚችሉ ማሳየት አልቻለም።   
ድርና ማግ መሆን የሚችሉት እነዚህ የታሪክ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ድሎች በሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች መንፈስ፣ ነፍስ፣ ስነልቦና ውስጥ በተመሳሳይ የኔነት ስሜት ሲኖሩ ብቻ ነው። ይህ እንዳይሆን የልሂቁን ዋልታ ረገጥ ሰነጣጣቂ አመለካከት ስህተተኛነት ቀጥሎም ጎጂነት መጀመሪያ እራሱ ልሂቁ አምኖ እንዲቀበለው ማድረግ ያስፈልጋል።  ዐቢይ ይህን አላጣውም። ይህ ችግር ይፈታል ብሎ የሚያስበው አሁንም በነባሩ የችግር መፍቻ ሞዴል ነው።
የልሂቁ ችግር ካለፈና ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን የሚመዘዝ በደል፣ ቂም፣ በቀል፣ ጥላቻ ነው ብሎ በማመኑ የዚህ ችግር መፍቻ ይቅርታና ፍቅር ነው ብሎ ያምናል። ለዚህ ነው ዶ/ር ዐቢይ በይቅርታ ብሔራዊ መግባባት የተደረሰባቸውን የሌሎች ሃገሮች ተመክሮዎች እንድናጤን የተጋው።
በ “የመደመር መንገድ” መጽሃፉ ገጽ 64 እና ገጽ 195 “ቁስላቸውን ያደረቁ ሀገራት” ምእራፍ 6 ሙሉ በሙሉ፣ እንዲሁም “የኢትዮጵያን እርቅ ፍለጋ”  የሚለው ምእራፍ 7 በከፊል የተመደበው እንዴት እኛም በይቅርታና በፍቅር በመደመር ከገባንበት ሃገራዊ ችግር መውጣት እንደምንችል ለማሳየት ነው።
ዶ/ር ዐቢይ በእርቅና መግባባት ሞዴልነት ያቀረባቸው ሃገሮች (ካናዳ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ) ከኛ ሃገር ጋር የሚመሳሰል ችግራቸው በጣም ጥቂት ነው። እሱም ይህን አልካደም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ለተፈጠሩ ቁርሾዎች ማስወገጃነት ያገለግሉ ካልሆነ በስተቀር ከታሪክ ጋር ተያይዞ ለሚነሳ መካሰስ መፍትሄ መስጠት የሚችሉ አይደሉም። ትልቁ ችግራችን የደርግ ወይም የወያኔ ዘመን በደል ያመጣው ቁርሾ ሳይሆን በመቶዎች አመታት ወደ ኋላ እየተመለስን የምናቀርባቸው የመበዳደል፣ የቂምና የበቀል ትርክቶች ናቸው። የደርግና የወያኔ ዘመን ቁርሾዎችም በእርቅ መንገድ ይፈቱ የሚለውን ሃሳብ እየተቃወምኩ አይደለም። ለነዚህ ዘመናት ግፍና በደል ወግ ባለው የእርቅ ሂደት ውስጥ ሃገሪቱ ብታልፍ መልካም ነው።
በተለያዩ ልሂቃን መካከል ያሉ ችግሮች በይቅርታ፣ ወይም የተለያዩ ሃገራት ተመሳሳይ በሆነ የሃገር ግንባታ ማለፋቸውና  እኛ የተለየን አለመሆናችንን በማመላከት የሚቃለሉ አይደሉም። ዐቢይ ግን በሁለቱ መንገዶች ከመሄድ ውጭ ሌላ አማራጭ አይታየውም።
ሁሉም የተበደለበትን የክስ ፋይል ማውጣት በሚችልበት ሃገር፣ ይቅርታ ሰጪ ይቅርታ ተቀባይ ሊኖር አይችልም። ሁላችንም ይቅር እንባባል ከተባለም ለአንድ ምሽት ለይቅርታ በተሰባሰበው፣ ለዚህም ሲባል የተዘጋጀው የሞቀ ድግስ በስሜት ለወሰወሰው ተሰብሳቢ ይሰራ እንደሆነ እንጂ ችግራችንን ከመሰረቱ የሚፈታው አይሆንም። ምክንያቱም፣ ልሂቃኑ የዋልታ ረገጥ ትርክታቸውን ማስቀጠል የሚፈልጉት ይቅርታ እንዲጠየቁ ሳይሆን ይህ ዋልታ ረገጥ ትርክትና የሚቀሰቅሰው የቂምና የበቀል ስሜት ትርፍ ያስገኝልናል ብለው በማሰባቸው ነው። ትርፉ ከጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች የስሜትና የቁስ እርካታ የማይሻገር ነው።  ይህ ደግሞ የደሃ ሃገር እርግማን ነው።
የችግሩ መፍትሄ ሁሉም ቂምና በቀሉን በማራገብ የሚያደርገው መካረርና መከፋፈል ትርፍ የማያስገኝ መሆኑን በማያሻማ ትንታኔና መረጃ ለአብዛኛው ልሂቅና ህዝብ ከማሳየት ውጭ ሊሆን አይችልም። ይህ አካሄድ በጣም ከባድ ነው። ተከታታይ ስራ፣ ብዙ ድካምና ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ነው። ግን ሌላ መንገድ የለም። የዛሬ ሶስት አመት ይህን ተገንዝበን ቢሆን ኖሮ፣ ከሌሎች ዐቢይ ከሰራቸው ስራዎች ጎን ለጎን ይህን ስራ ማስጀመር አያቅተንም ነበር። ከዚህ ቀደም የተሄደበት መንገድ ባለመሆኑ ዶ/ር ዐቢይ በሃሳብ ደረጃ ጀመር ቢያደረግውም ሊገፋበት የሞከረው አልሆነም።  
ሌላው ዐቢይ የዋልታ ረገጥ  እይታ ያመጣቸውን ችግሮች መፍቻ በሁለቱም መደመሮች ደጋግሞ ብዙ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ለማሳየት የሞከረው የሌሎችን ሃገራት ብሄራዊና  ሃገራዊ መንግስት ግንባታ ከኛ ሃገር ጋር ያለውን ተመሳሳይነት ዋልታ ረገጦቹ እንዲያዩት በማድረግ ነው። ይህም ሙከራ የትም  የሚያደርሰው አይደለም። ምክንያቱም  ሁሉም ልሂቅ ጥላቻውን ቂምና በቀሉን በልቡ ይዞ የሚዞረው ይህን የአለም ሃገረ መንግስታት የአመሰራረት ታሪክ አጥቶት አይደለም። በእሳት በብረት በመገበርና በማስገበር ሂደት ሃገሮች እንደተገነቡ የማያውቅ ልሂቅ ዛሬ በሃገራችን አይገኝም።  
ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዘመናትን ከተሻገሩ የታሪክ ኩነቶች ጋር የተያያዙ ቁርሾዎችን የሚያረግብ እርቅ አይደለም። ወይም ሌሎች ሃገሮች እንዴት እንደተመሰረቱ የሚያሳይ ለልሂቃኑ የሚሰጥ ሴሚናር አይደለም። ከሌሎች ነገሮች የጸዳ በጋራ በተሰሩ የታሪክ ክንዋኔዎች ዙሪያ መፈጠር የሚገባው ብሄራዊ መግባባት ላይ ሃገር መገንባት ካልቻልን መጨረሻችን አሰቃቂ እንደሚሆን ማሳየት ብቻ ነው።
ዐቢይ ለብሄራዊ መግባባት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦችንም ከማሳየት አልቦዘነም። የመደመር መንገድ ገጽ 30 በአፍሪካና በአሜሪካ የሚገኙ ጥቁር ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚጋሩት የኢትዮጵያዊነት ትርጓሜ ምን እንደሆነ ይነግረናል። “የነጻነትና የአሸናፊነት በሌሎች አልገዛም” የሚል “አስተሳሰብ ድምር ነው” ይለናል። ሆኖም ግን ይህ ግንዛቤ በራሱ በኢትዮጵያውያን አይን አንድ ወጥ በሆነ መንገድ የማያታይ መሆኑ ችግር እንደፈጠረ ይነግረናል።
ዐቢይ “መደመር” ገጽ 119 ላይ የብሄራዊ መግባባት የሚጠይቁትን ጉዳዮች ዘርዘር አድርጎ ቢያነሳም፣ የሚያጠቃልለው “ብሄራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ አስቀድመን ያለፉ ቁስሎቻችንን ማከምና መዳን ይገባናል፣ እርቀ ሰላም ማውረድ ያሻናል” በማለት ነው። ለብሄራዊ መግባባት አስፈላጊ ነው የሚለው እርቀ ሰላም በመቶዎች ለሚቆጠሩ አመታት ወደ ኋላ እየተመለስን የሚደረግ እርቀ ሰላም በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ቦታ ሊኖረው የማይችል መሆኑን ግን ዐቢይ ማየት የቻለ አይመስለኝም።  ከዛም አልፎ ይህን ችግር እያባባሰው የመጣውን የወያኔ ዘመን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል አተያይና ይህን ተከትሎ የመጣው በተግባር የተተረጎመ መዋቅራዊና ተቋማዊ ጉልበት የተሰጠው በማህበረሰባዊና ግለሰባዊ አመለካከቶች ላይ ያደረሰውን ትልቅ ጉዳት በተመለከተ ዐቢይ  የሚሰጠን ምልከታና መፍትሄው ላይ ውስኑነት አለው።   


Read 2674 times