Saturday, 24 April 2021 13:28

የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መባባስና የመፍትሔ አቅጣጫዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፉት ሶስት ዓመታት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም ጥሰቶቹ እየተባባሱ ሄዱ እንጂ መሻሻል አላሳዩም፡፡ ለዚህ ምክንያቶቹ ምን ይሆኑ? ለእነዚህ የመብት ጥሰቶች ዋነኛ ተጠያቂዎቹ እነማን ናቸው? የመፍትሔ አቅጣጫዎቹስ ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዳሬክተር የሆኑትን የህግ ባለሙያና የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ መስኡድ ገበየሁን አነጋግሯል፡፡ እነሆ፡-

                       ከጊዜ ወደ ጊዜ የሠብአዊ መብት ጥሰቶች መጠናቸው እየሰፋና እየተበራከቱ የመጡት ለምንድን ነው?
የሠብአዊ መብት ጥሰቶች ከሌላ የወንጀል አይነት የሚለዩበት ባህሪ፣ ተቋዋሚ የሆኑ መጠነ ሰፊና ስልታዊ መሆናቸው ነው። በሃገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ አይነት መልክ ይዞ ነው የሰብአዊ መብት  ጥሰቱ፡- ግድያው መፈናቀሉ እየቀጠለ ያለው፡፡ ግጭቶቹ ብዙ መነሻ ምክንያቶች አላቸው። ግን መልካቸውን እየቀየሩ በብዙ አይነት መንገድ እየተፈፀሙ ነው፡፡ ስለዚህ መነሻቸውን በማየት ባህሪያቸውን ማየት ጥሩ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩት ሃይማኖትን ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የሚፈፀሙት ማንነትን ወይም ብሔርን ትኩረት ያደረጉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር አብዛኞቹ መነሻቸው ፖለቲካዊ የሆኑ ናቸው። የፖለቲካው አለመረጋጋት እንዳለ ሆኖ በተለይ ከመሬት፣ ከሀብት ጋር የተያያዙ፣ "ለኔ ይገባኛል፣ የኔ መሬት ነው፣ የኔን ሀብት እየተሻማኸኝ ነው" የሚለው በተለይ የብሔር ፖለቲካው እየጦዘ ከመጣ በኋላ ያመጣቸው ችግሮች እንደሆኑ ይታወቃል። ያም ሆኖ ግን እነዚህ ጥሰቶች ሁሉ አሁን በደረሱበት ደረጃ መጠነ ሰፊ እየሆኑ፣ ውስብስብ እየሆኑ፣ ማቆሚያ የሌላቸው እየሆኑ እንዲሄዱ ግን ትልቁ ምክንያት የመንግስት የህግ የማስከበር አቅም ማነስ ነው። የአቅም ማነስ ብቻ ሳይሆን  ፍላጎት ማጣትም እየታየበት መሆኑን እየታዘብን ነው። ምክንያቱም ጥሰቶች በጣም በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ነው፡፡ ከመከሰታቸው በፊት ሰዎች “እዚህ አካባቢ ችግር ገጥሞናል ድረሱልን” እያሉ እየጠየቁ ሁሉ አዎንታዊ ምላሽ  ሳይሰጥ ጥቃቶች ተፈፅመው ሰዎች ይሞታሉ፣ ንብረት ይወድማል፤ ጉዳት ይደርሳል፡፡ እነዚህ አብዛኛዎቹ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀሙ ያሉት ደግሞ በተለያዩ ከመንግስት ወጪ ባሉ የተደራጁ  አካላት ቡድኖችና ግለሰቦች ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ራሳቸው በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ መሳተፋቸውን እንሰማለን፡፡ ስለዚህ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ማክበርና ማስከበር አለበት ስንል፣ ራሱ በዚህ ድርጊት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ  ማድረግ የለበትም ማለት ነው፡፡ የመንግስት ትልቁና ተቀዳሚው ሃላፊነት፣ የዜጎችን ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ምክንያቱም ብቸኛ የሃይል አማራጭ መጠቀም የሚችለው መንግስት ብቻ ነው፡፡ ይሄንን ስልጣን ተገዳዳሪ ሃይል ሊኖረው አይገባም ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሃይሎች ከአቅም በላይ ሆነው መንግስትን የሚገዳደሩት ከሆነ ለምሳሌ በትግራይ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ሰሞኑን ደግሞ ከሚሴና አጣዬ ላይ እንዳየነው ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል ይቸገራል፡፡ በተለይ ይሄ ህገ መንግስታዊ አይደለም እየተባለ ብዙ ትችት እየቀረበበት ያለው የክልል ልዩ ሃይል፣ ከፌደራል የፀጥታ ተቋማት ጋር ተናቦ አለመስራቱ አንዳንድ ጊዜም ለፌደራል የፀጥታ ተቋማት መሰናክል መሆኑ እነሱንም ሳይቀር መገዳደሩ ለምሳሌ የትግራይ ክልልን ማየት እንችላለን፤ የመንግስት አቅምን ፈተና ውስጥ እየከተተ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና አለማቀፍ ተቋማት እያሉ ያሉት፣ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅ አልቻለም፤ የደህንነት ተቋማትም ስራቸውን እየሰሩ አይደለም። በተለይ ቅድመ መከላከል ላይ መስራት አልቻለም በሚልም እየተወቀሰ  ነው፡፡  
አሁን የሚፈጸሙ የሠብአዊ መብት ጥሰቶች ምን አይነት መልክና ባህሪ ነው ያላቸው? ከቀድሞዎቹ ጥሰቶች  በምን ይለያሉ?
ከዚህ በፊት የነበሩትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ካየን፣ በዋናነት በመንግስት ተቋማት በተለይ በፖሊስ፣ በማረሚያ ቤት፣ በደህንነት ተቋማት የሚፈፀሙ አይነት ነበሩ፡፡ በአብዛኛው መንግስት ነበር በዋናነት ጥሰቶችን ይፈጽም የነበረው፡፡ አሁን ደግሞ ትንሽ የተለየ ነው፡፡ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎችና ተቋማት የሚፈፀሙ አሉ፤ ግን ከበፊቱ አንጻር ሲታይ ይሄኛው አነስ ብሎ በአብዛኛው ከመንግስት ውጪ ያሉ ቡድኖች፣ ግለሰቦች እንዲሁም የተለያየ ስም የሚሰጣቸው  ፓርቲዎች ጭምር ናቸው ተዋናዮቹ፡፡ እነዚህ ከመንግስት ውጪ ያሉ አካላት ይሔን የመብት ጥሰት በሚፈጽሙበት ጊዜ በጣም የተናበቡ እንደመሆናቸው፣ መንግስት አንዱን መልክ ለማስያዝ ወደዚያ  ሲሄድ ቦታ  እየቀያየሩ ይፈጽማሉ፡፡ ስለዚህ መንግስት እንደ መንግስት የሚጠበቅበትን ስራ መስራት እንዳይችል ከአቅም በላይ የስራ ጫና ይፈጥሩበታል፡፡ ልዩ የሚያደርጋቸው ተከታታይ መሆናቸው፣ በመጠን ማየላቸው፣ ከመንግስት መዋቅር ውጪ ባሉ አካላት መፈፀማቸው፣ መንግስት  ደግሞ ለችግሩ ህብረተሰቡን የሚያረካ አጥጋቢ ምላሽ አለመስጠቱ፣ ፍትህ አለመስፈኑ፣ በተለይ አሁን ትልቁ ችግር የመንግስት ሃላፊዎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው ነው፡፡ የመንግስት ሃላፊዎች ለዚህ ድርጊት ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ በግልጽ በመንግስት አካባቢ የሠብአዊ መብትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ የአቅም ማነስ  እየተስተዋለ ነው፡፡  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከዚህ በፊት  ከነበረው በተሻለ  ክትትልና ምርመራ እያደረገ፣ ሪፖርት እየሰነደ፣ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ እያደረገ ነበር፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ነበረ፤ ነገር ግን ይሔን ጥሩ አካሄድ ለመጠቀም የሚያስችል የፍትህ መዋቅርና የመንግስት አቅም ነው የጠፋው። ሪፖርቱን ተጠቅሞ አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ አልተቻለም፡፡
እንዴት?
ለምሳሌ “የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ የተፈጸመው በጣም መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መንግስት ያለ አይመስልም ነበር” የሚል ሰፊ ሪፖርት አውጥቶ ነበር፤ ኮሚሽኑ፡፡ ይሄ ማለት ከላይ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ሰዎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ አልነበረም ማለት ነው። በዚያ ሪፖርት መሰረት፤ የክልሉ ሃላፊዎች ከላይ ጀምሮ እንደ ተሳትፎአቸው መጠን ተጠያቂ መደረግ  ነበረባቸው፤ ግን እስካሁን የሰማነው ነገር የለም፡፡
የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በአግባቡ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ማለት ይቻላል?
ኮሚሽኑን ጨምሮ ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ትልቁ ፈተና የሆነው የጥሰቶቹ በጣም በተከታታይ መፈጸም  ነው፡፡ አንድ ቦታ የተፈፀመውን መርምሮ ሰንዶ ሳይጨርስ ሌላው ጋ ይጀመራል። እዚያ ባለሙያ ሲልክ  ሌላ ቦታ ደግሞ ተመሳሳይ  ነገር ይፈጠራል፡፡ ከኮሚሽኑ ውጪ ያሉት ደግሞ የአቅም ውስንነት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ የአቅማቸውን ያህል ግን እየሰሩ ነው፡፡  
አሁን እየተፈፀሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች  “የዘር ማጥፋት” ናቸው የሚል ክርክር ይቀርባል። እርስዎ እንደ ባለሙያ ምን ይላሉ?
የዘር ማጥፋት ተባሉ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ተባሉ አይደለም ጉዳዩ። በእርግጥ መጠናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ እነዚህን ጥሰቶች ብያኔ ከመስጠት ይልቅ ድርጊቶቹ የሚቆሙበትን መንገድ ማሰብ ነው የሚሻለው፡፡ በእርግጥ አሁን ለምሳሌ ኮሚሽኑ የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በተፈፀሙ ድርጊቶች ላይ ባወጣው ሪፖርት፤ “በሠብአዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች” ነው ያላቸው፡፡ አንድ ኢ-ሰብአዊ ድርጊትን ለመበየን ብዙ ሂደትና መስፈርቶች አሉት። ነገር ግን እነዚህን ተግባራት ከቀረቡለት ማስረጃዎች መርምሮ መበየን የሚችለው ፍ/ቤት ነው፡፡ ኮሚሽኑም ሆነ ሌሎች ተቋማት ተግባራቸው መሆን ያለበት ወንጀሎቹን መመርመር ነው፡፡ የምርመራው ውጤት ምን ፍሬ ነገር ነው የሚኖረው የሚለውን መበየን የፍ/ቤት ሃላፊነት ነው፡፡ የዘር ማጥፋት ነው? የጦር ወንጀል ነው? የሚለውን ማስረጃ አይቶ ሊበይን የሚችለው ፍ/ቤት ነው፡፡ ነገር ግን ይሄን አካሄድ በጣሰ መልኩ በእንዲህ ያለ ፍረጃ ላይ የተሰማሩ አካላት ቢታቀቡ ምክሬ ነው፡፡ አካሄዱም ትክክል አይሆንም፡፡
እየተፈፀሙ ላሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ዋነኛ ተጠያቂው ማን ነው?
ተጠያቂነት ከሃላፊነት ነው የሚመጣው። ስለዚህ ግዴታን ካለመወጣት ነው ተጠያቂነትን እምናስበው፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰትን በሚመለከት በዋናነት ተጠያቂ የሚሆኑት የመንግስት አካላት ናቸው። መንግስት የሰብአዊ መብት ባለማክበሩ ባለማሟላቱ ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ይሄ ማለት ግን ሌሎች አካላት አይጠየቁም ማለት አይደለም፡፡ በዚህ የተሳተፉ ቡድኖች ግለሰቦች፣የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንደ የደረጃቸው በማስረጃ ተጠያቂ ይሆናሉ። በማንኛውም ሁኔታ ተሳታፊ የሆነ ሰው ተጠያቂ መሆን አለበት። መንግስት ደግሞ የሰዎችን ደህንነትን ማስጠበቅ ባለመቻሉ በዋናነት ተጠያቂ ይሆናል። ጥፋተኞችን ለፍትህ አለማቅረብ ራሱ በመንግስት ላይ ተጠያቂነትን ያስከትላል። አሁን በመንግስት በኩል እያየሁት ያለው ትልቁ ችግር፣ ወይ የመብት ጥሰቶቹን አያስቆምም ወይ የመብት ጥሰቶቹ ከተፈፀሙ በኋላ ፈፃሚዎቹን በአስቸኳይ ለፍርድ አቅርቦ ማህበረሰቡን የሚያረካ ፍትህ አያሰጥም፡፡ ስለዚህ ፍትህ አለመሰጠቱ ወንጀሎቹን ካላስቆሙት ጋር እኩል ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ መንግስት ስንል በየደረጃው ያሉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ማለት ነው፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙና የዜጎች ሠቆቃ እንዲያበቃ ምንድን ነው መደረግ ያለበት?
ሃገራዊ  መግባባት ሊፈጥሩ የሚችሉ የውይይት መድረኮች ማካሄድን ነው አንዱ መፍትሔ፡፡ በዳይና ተበዳይ ተብለው የተፈጠሩ ትርክቶች አሉ። እነዚህ ትርክቶች በደንብ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ማቃናት ያስፈልጋል፡፡ በማህበረሰቡ መካከል መተማመን እንዲፈጠር ማድረግ። ለእነዚህ ችግሮች መባባስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ድህነትና ስራ አጥነት የመሳሰሉት ስለሆኑ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ መንግስት ምቹ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ወጣቶችን ወደ ስራ ማስገባት  የሚዲያና የፖለቲካ አውዶችን ማሻሻል የመሳሰሉት የመፍትሄ እርምጃዎች ሁኔታውን እያሻሻለው ይሔዳል። በተለይ ምርጫው ከተደረገ በኋላ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ የብሔራዊ ውይይቶችና መግባባቶች መድረክ መፈጠር አለባቸው፡፡ ሁሉም በየፈርጁ ብዙ ስራ ይጠበቅበታል፡፡ በዚሁ ሂደት መሃል ግን የመጀመሪያው መፍትሔ መንግስት የመንግስትነት ሃላፊነቱን መወጣት መቻል ነው። ፖለቲካዊ ችግር ያለባቸውንና እሱን ታከው ለሚፈጸሙት ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት አለበት፡፡ በፖለቲከኞች መካከል መደራደር መጀመር አለበት። ሲቪክ ማህበረሰቦች እነዚህን በማሳለጥ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።  የድንበርና ማንነት ኮሚሽን ወደ ስራ በመግባት ውዝግቦችን መፍታት አለበት። የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች በሃላፊነት ለሰብአዊነት መስራት አለባቸው፡፡ የደህንነት ስራ መስራት ያስፈልጋል። ከዚህ  ባለፈ ኮማንድ ፖስትን በማፈን ችግሩን መቅረፍ አይቻልም ጉዳዩን ለማዳፈን አጥፊው አካል የተለየ ዝግጅት እንዲያደርግ ይረዳዋል፡፡


Read 1623 times