Saturday, 24 April 2021 12:59

አልሳካ ብሎ ኑሮና ብላቱ...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እመኛለሁ ዘወትር በየእለቱ
ላሳካ ኑሮን ከብላቱ
የምትለው ዘፈን... በየቴሌቪዥን ጣቢያዎች በየሰዓቱ እንደ ሰዓት ማሳወቂያ ትዘፈንልንማ! ልክ ነዋ...ግራ ሲገባን ምን እናድርግ ... አሁን ነገርዬው ሁሉ ተደነጋግሮ ‘ሰርቫይቫል’ እንደ ኑሮ የሚወሰድበት፣ ‘ብላት’ የሚባል እንኳን ሊኖር መዝገበ ቃላት ላይ ቶሎ ለማግኘት አስቸጋሪ የሚሆንበት፣ ማሰብ ማሰላሰል በ‘ድፍረት’ ስፍራውን የተነጠቀበት ዘመን፡፡ ‘ድፍረት’ በሁሉም መስኮች የገባበትና ‘እውቀትን’ በበቃኝ እየዘረረ የሚመስልበት ዘመን፡፡ ‘ፈረንጅ’...አለ አይደል... “ሀው ዲደ ዊ ጌት ቱ ዚስ?” የሚላት ነገር አለችው፡፡ እኛም እንዲህ አይነት እግርና ጭንቅላት የማይለይበት ዘመን ላይ ልንደርስ እንደቻልን በድፍረት ሳይሆን በአወቀት መርምረን ማስወገዱ እንኳን በአሁን አቋማችን የማይታሰብ ቢሆንም ገና በምናችንና በምናምናችን ያልተነካካውን  አዲስ ትውልድ ለማትረፍ ካልሠራን፣ ነገሩ ሁሉ እንደተለመደው “የዘንድሮው ዘመን ከመጪው ይሻላል...” እየተባለ ሊቀጥል ነው፡፡ አንድ ሰሞን ለምደናት አልነበር...ሦስት መቶ ስድሳ ምናምነኛው ቀን ላይ...
አሮጌው ዓመት እንዴት ነው
ከሚቀጥለው ይሻላል
እውነት ለመናገር... ይህች አባባል ዘንድሮ ያገኘችውን ያህል ጥንካሬ ያገኘችበትን ጊዜ ማስታወሱ አስቸጋሪ ነው... በታሪክ ወደ ኋላ ተሂዶም ቢሆን፡፡  
እኔ የምለው... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... የበቀደሙ የሜዳሊያ ምናምን ሽልማት፣ የ“ኬሬዳሽ” የ‘ፈረንጅ አፍ’ ለመጠቀም ያህል፣ ነገርዬው “ኖ ፕሬዘንት፣ ኖ ሜዳሊያ” ነው እንዴ? (በ“ኬሬዳሽ” መዝገበ ቃለት መሰረት “ኖ ፕሬዘንት፣” ማለት “አብሰንት” ማለት ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...) እናማ... ጥያቄ የምትመስለው ነገር የቀረበችው … ጠቅላላ እውቀትን ጨመር ለማድረግ ያህል ነው፡፡
ስሙኝማ... ምን ሆነ መሰላችሁ...አንድ ወዳጃችን በቅርቡ በአንድ የሳምንት መጨረሻ ቀን ‘በል፣ በል’ ይለውና ሁለት ጓደኞቹን  አሪፍ ምሳ ይጋብዛል፡፡ የተለየ ነገር ገጥሞት ወይም ቀድሞ ኪሱ ከሚገባው በላይ ፈረንካ አግኝቶ ሳይሆን “በቃ ሰው ጋብዝ፣ ጋብዝ” አለኝ ነው የሚለው፡፡ ምሳው ደግሞ ደረቁን አልነበረም፡፡ 
ታዲያላችሁ… ከጥቂት ቀናት በኋላ ሰበር ዜናዎች ይደርሱት ጀመር… ስለ ራሱ የማያውቃቸው ሰበር ዜናዎች፡፡ እናላችሁ ምን ተባለ መሰላችሁ... “ገንዘብ ከየት እንዳገኘ አይታወቅም ግን እነ እነትናን ቁንጣን እሰኪይዛቸው ነው አሉ ጥሬ ስጋ፣ ከክትፎ ወይን ከቢራ እያማረጠ ነው የጋበዛቸው፣” አይነት ነገር ተባለ፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም ልከ ሁለቱን እያዟዟረ ሲጋበዝ የፕሪሚር ሊግ ክለቦችን ተጫዋቾች በሙሉ አስከትሎ፣ እየተከተሉ ሲያዩት የዋሉ ይምስል ሁለት ሰው ጋበዘ ተብሎ የተወራበት ታሪክ መአት እኛን ቢጨምር ኖሮ ምን ሊባል ነበር፡፡ ኮሚክ አኮ ነው....ሰዎቹን በሽ የማድረጉ ብቻ ሳይሆን “ብሩን ሲመዠርጠው አደረ...” ይባል እንደነበረው እንዴት ብሩን ይመዝዘው እንደነበረ ሳይቀር ነው ያወሩት፡፡ ‘ሲመዠርጠው’ የሚለውን ቢያውቁት ኖሮና ቢጠቀሙበት አይጧን ዝሆን ለማሳከል ያግዛቸው ነበር፡፡ (የውስጥ አዋቂ መረጃ ሹክ ለማለት ያሀል...ያን ቀን በል፣ በል ብሎት ያወጣው ገንዘብ፤ በቤቱ በጀት ላይ ጫና ቢጤ ፈጥሮበታል... ‘ሁለተኛ አይለምደኝም፣’ የሚያሰኝ ጫና፡፡ እናማ...በል፣ በል የሚል ስሜት ስላደረ ብቻ የሆነ ነገር ማድረግ አሪፍ አይደለም ለማለት ነው፡፡ የ‘በል፣ በል ቦተሊካ’ የበዛ ስለመሰለን ነው!)
እናላችሁ... ከጀርባ እየተወራበት ያለውን በሰማ ጊዜ መጀመሪያ አልጠበቀም ነበርና ብስጬ ምናምን ሞካክሮት ነበር፡፡ በዛ ቢቆም ጥሩ፣ አሁን ደግሞ ነገሮች ተለወጡና ደስ የማይሉ ፖለቲካዊ ነገሮች ይነካካቸው ጀምሯል... ከባለ ጊዜዎች፣ መሞዳሞድ ምናምን ከሚባሉ ነገሮች ጋር የተያያዙ ቀሺም ነገሮች!
የምር ግን... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ለምንድነው ዘንድሮ በትንሹም፣ በትልቁም ‘ቦተሊካ’ የሚሉት የሚሰነቀርብን! ሚዛን የሚደፉ ቁም ነገሮችም ለመነጋገር አስቸጋሪ፣ እንደው አልፎ፣ አለፎ ውጥረታችንን ለማርገብ ላላ ያሉ…. ብዙም የማይከብዱ ነገሮችን ለመነጋገርም መከራ! ስለ ግለሰብ ሰውም ሆነ  አቋም  ተገቢ የሆነ በጎ አስተያየት መስጠትም፣ ወይም በተገቢው ሁኔታ ገንቢ የሆነ አስተያየት ቢጤ ማቅረብም ፈተና!  
ደግሞላችሁ... ሁሉም ነገር አሉታዊ ሆነሳ! እዚህ ሀገር ማርስ ላይ መቶ ሰው አድርሶ የሚመልስ መንኮራኩር የሚፈለስፍ ሰው ቢኖር እመኑኝ...መንኮራኩሯ ከመነሳቷ በፊት እሱን በሞራልም፣ በአቅምም፣ በምናምንም እንዳይነሳ አደርገን እናስተኛዋለን፡፡
“አንድ የሀገራች ሰው እንዲህ የመጠቀ ሳይንሳዊ ግኝት ላይ ሲደርስ ደስ አይልም?”
“እባክህ ይሄኔ ከናሳ ሳይንቲስቶች ወይ ሰርቆ፣ ወይ አሰርቆ ነው!”
“ከእስራኤሎቹ ጋር ግንኙነት አለው ይባላል!”
“እሱ ደግሞ አይደለም ማርስ ድረስ የሚሄድ መንኮራኩር የሦስተኛ ክፍል የመንኮራኩር ስዕል መሥራት ይችላል?” ግዴላችሁም...አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ነው ያለነው፡፡
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...በሰርግ ላይ “ይቺ ናት ወይ ሚዜሽ፣ አየንልሽ፣” የሚባል ነገር አለ። ነገርዬው ዝም ብሎ ከሰማይ ዱብ ያለ አይደለም፡፡ የሆነ ታሪካዊ  የሆነ መነሻ ይኖረዋል፡፡ ግን የቀድሞውን አምጥቶ በዘንድሮ በአብዛኛው ‘የተንጋደደ’ እይታ  እንየውማ፡፡ (ልክ በምናምነኛ ዘመን የነበሩና በዛው ክፍለ ዘመን ነባራዊ ሁኔታዎች በተፈጠሩ አስተሳሰቦች ተመርኩዘው የነበሩ የፖለቲካ አመላካከቶችን በዚህ ክፍለ ዘመን ሚዛን ላይ አስቀምጦ፣ ጥምብርኩስ እንደ ማውጣት አይነት ያወቅነውም፣ ያላወቅነውም፣ ‘ኮንፊዩዝድ’ የሆንነውም “ማን አለኝ ከልካይ...” እያልን  እየተካንበት ያለ ልማድ ማለት ነው፡፡ ልምዱ ‘የጋራ’ ይመስላል ለማለት ያህል ነው፡፡)
እናላችሁ...ሰርግ፣ ሰርግ እንጂ የሆነ ለተመልካች የሚቀርብ ብቻ ‘ስቴጅ ፐርፎርማንስ’ የሚሉት አይነት ባልነበረበት በዛ ዘመን በምክንያት የተጻፈን ስንኝ ፣በዛሬው ምክንያተ ቢስ አተረጓጎም ‘ስንበልተው’...አለ አይደል... “እሺ ብላ የጓደኛዋን ሰርግ ለማሳመር ሚዜ በሆነች ስደብ አለባት እንዴ!” እንላለን፡፡ (ስሙኝማ... አንግዲህ ጨዋታም አይደል... ምን ይመስለኛል መሰላችሁ... አሁን ያለንበት ዘመን ወደፊት በምናምነኛው ክፍለ ዘመን፣ ወይም ዓመተ ምህረት ከሚባል ይልቅ “ሰዉ ሁሉ ስድብ አጠጪና ስደብ ጠጪ በነበረበት በዛ የስደብ ዘመን ሊባል ይችል ይመስለኛል፡፡”“  
ታዲያላችሁ...ምናልባት የአብዬን ወደ እምዬ እንደሚሉት፣ ከደሙ ንጹህ ለመሆን በርካታ አስርትና መቶዎች ዓመታትን ወደ ኋላ ሄደን ”ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊው ነገር ላይ ማተኮር በእኛ ዘመን የመጣ ሳይሆንም ድሮም የነበረ ነው፣” አይነት ነገር ማለት የተለመደ ነው፡፡ እናማ...“ሚዜሽ ስታምር፣ ጽገሬዳ አበባ አይደለም እንዴ የምትመሰለው!” ይባላል እንጂ... “አሁን ይቺን ሰው ብለሽ ሚዜ አደረግሻት አይነት ነገር ይባላል!” የሚመስል ነገር እንላለን፡፡ እናም ይቀጥልና...
“ኧረ ሚዜው ደሀ ነው ሽቶው ውሀ ነው፣” የሚለውን ወስደን “መጀመሪያ ድሀ አሉት፣ ቀጥሎም ሽቶው ውሀ ነው አሉት፡፡ ምን የማይረባው ነው....ይሄን ሁሉ እየሠማ፣ ልብሱን ሙሽራው አፍንጫ ላይ ወርውሮ አይሄድላቸውም እንዴ!” ልንል እንችላለን፡፡
እናማ...ትናንትም ተጀመረ፣ ከትናንት ወዲያም ተጀመረ ‘ስቶሪው’ ምን መሰላችሁ... በአሁኑ ጊዜ ሁሉነም ነገርና ሁሉንም ሰው በአሉታዊ መነጽር ማየት የብዙዎቻችን ባህሪይ የሆነ ይመስላል፡፡”
“ምሳ ስጋብዝህ እምቢ ያልከኝ መኮራቱ ነው!” የሚባልበት ዘመን አልፏል፡፡ እናም...ምን መሰላችሁ? በዛን ጊዜ “ምሳ ልጋብዝህ...” ጣጣ፣ ፈንጣጣ የሌለው የግብዣ ጥያቄ ነው.... አንጃ ግራንጃ የሌለበት። (እግረ መንገድ... ‘አንጃ ግራንጃ’ ግን ምንኛ ቋንቋ ነው?) የእኔ ቢጤው... አለ አይደል... ያልተጠበቀ ካፊያ ሲጥል “ይሄ እኔ አምሮብኝ እንዳልወጣ ሆነ ተብሎ የሚደረግ ነው...” ለማለት የሚዳዳው ካልሆነ በስተቀር፣ እንደ ዘንድሮ አይነት ‘የተደበቀ ትርጉም ቁፋሮ’ ብሎ ነገር የለም፡፡  
“እሱ ሰውዬ ግን እንዴት፣ እንዴት ነው የሚያደርገው፡፡ እሱ ማን ሆነና ነው ትከሻውን አሳይቶኝ የሚያልፈው!”
“በእሱ ቤት መናቁ ይሆናላ!”
“እኔን! እሱ ነው እኔን የሚንቀው!”
“ምን መሰለሀ የሆነች አምስት፣ ሰባት ሰው ያለባት ክፍል ሀላፊ ሆኗል፡፡ ወደ እነሱ ተጠግቷል እየተባለ ይወራል፡፡”
“ታዲያ እንደዛ አትለኝም!”
ዌል እንግዲህ... “አልሳካ ብሎ ኑሮና ብላቱ” ከሚል እንጉርጉሮ ያውጣንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1441 times