Sunday, 18 April 2021 18:04

ትኩረት የተነፈጉት የፓርኪንሰን ህሙማን

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

• ህሙማኑ በመድኃኒት እጦት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ናቸው
                   
              በአገራችን በፓርኪንስን ህመም የሚሰቃዩ ወገኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ቢሆንም በሽታው በመንግስትም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ ተገቢው ትኩረት ያልተሰጠውና የተዘነጋ እንደሆነ ተገለጸ።
በሽታው እጅግ አደገኛና ህሙማኑን ለከፍተኛ ስቃይ የሚዳርግ  ቢሆንም፣ ህሙማኑ ተገቢውን ህክምና ለማግኘት ባለመቻልና  በመድኃኒት እጦት ሳቢያ ለከፍተኛ ችግር  እንደሚዳረጉም ተገልጿል።
እነዚህን ወገኖች የሚታደግና ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚሰራ “ፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሣፖርት ኦርጋናይዜሽን” የተባለ ተቋም ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ተቋቁሞ በበሽታው የተጠቁ ወገኖችን በመታደግና ህሙማኑ በመድሃኒት እጦት ሳቢያ ለስቃይ እንዳይዳረጉ በመስራት ላይ ይገኛል።
እ.እ.አ በየአመቱ ኤፕሪል 11 ቀን የሚከበረውን አለም አቀፉን የፓርኪንሰን ቀን አስመልክቶ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ግቢ ውስጥ ከህሙማኑ ከቤተሰቦቻቸውና ከህክምና ባለሙያዎች ጋር የጋራ ውይይት ተካሂዶ ነበር። በፕሮግራሙ ላይ ከነበሩት ህሙማን መካከል አብዛኛዎቹ ራሳቸወን ችለው ለመንቀሳቀስ የሚቸገሩ፣ በሽታው በተለያየ መንገድ ጉዳት ያደረሰባቸውና ከፍተኛ የስነ-ልቦና ስቃይ ላይ የሚገኙ ህሙማንን አግኝተናቸው ነበር። ከእነዚህም መካከልም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለስልጣን ውስጥ ለዓመታት ሲሰሩ የቆዩትና ባጋጠማቸው የፓኪርኪንስን ሕመም ሳቢያ ከስራቸው የተፈናቀሉት አቶ መሰለ ማታ እንደሚናገሩት፤ በሽታው ከሚያስከትለው አካላዊና አእምሮአዊ ህመምና ስቃይ በተጨማሪ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር ይዳርጋል።
በህመማቸው ሳቢያ ተንቀሳቅሰው ስራ ለመስራት ባለመቻላቸው ከስራቸው መሰናበታቸውን የነገሩን አቶ መሰለ፤ ያለ ምንም ገቢ በዚህ የኑሮ ውድነትና ጫና ለመድሃኒት መግዣ ከፍተኛ ወጪን በሚጠይቅ ህመም መያዝ እጅግ ከባድ ነው ብለዋል። በሽታቸው ምን እንደሆነ እንኳን ለማወቅ ተቸግረው ለወራት ሲንገላቱ መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ መለሰ፣ ከወራት አድካሚ ልፋትና ክትትል በኋላ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሽታቸው ፓርኪንሰን እንደሆነ እንደታወቀላቸው ይገልጻሉ። በሽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ በሂደትም የአልጋ ቁራኛ የሚያደርግ በሽታ መሆኑ እየታወቀ፣ ታማሚው ህይወቱ እስካለ ጊዜ ድረስ እንኳን ስቃዩን እያስታገሰ ሊቆይ የሚችልበትን መድኃኒት እንዲገኝ  አለመደረጉ ስቃዩን አባብሶታል ብለዋል። “ፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሣፖርት ኦርጋናይዜሽን” የተባለው ድርጅት በተለያዩ መንገዶች እርዳታና ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውና በተለይም ደግሞ ለመድሃኒት መግዣ የሚያደርግላቸው ድጋፍ ህይወታቸውን ለማቆየት እንደረዳቸው ነግረውናል።
የድርጅቱ ፕሮጀክት ኮኦርዲኔተር ወ/ሪት ትንሳኤ ደነቀ እንደሚናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት የህሙማኑ ከፍተኛው ችግር የመድሃኒት እጦት ሲሆን መድሃኒቱ በአገሪቱ እንደ ልብ የማይገኝ በመሆኑ ህሙማኑ ለከፍተኛ ችግርና ስቃይ ተዳርገዋል ብለዋል።
ፓርኪንሰን የሚፈውሰው መድሃኒት ባይገኝለትም በሽታው የሚያስከትለውን ስቃይ ለማስታገስ  የሚረዱ መድሃኒቶች መኖራቸውን ያመለከቱት ወ/ሪት ትንሳኤ፤ በአገራችን ግን መድሃኒቱ በበቂ ሁኔታ የማይገኝ በመሆኑ ህሙማኑ ለከፍተኛ ችግር እንደሚጋለጡና የሚያገኙትን አነስተኛ መጠን ያለውን መድኃኒት ለብዙ ጊዜ ለመጠቀም እንዲቻሉ፣ በአንድ ጊዜ መወሰድ የሚገባቸውን መድሃኒት እየሰበሩ ለሁለት ጊዜ ለማድረግ እንደሚገደዱም ገልጸዋል። ድርጅቱ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት በተቻለ መጠን አነስተኛ መጠን ያላቸውን መድሃኒቶች በእርዳታ እያገኘ ቢሆንም ይህ በበሽታው እየተሰቃዩ ካሉት ከ700 በላይ የድርጅቱ አባላት ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡ ስለዚህም መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ህሙማኑን ከስቃይና እጅግ ከከፋ ህይወት ለመታደግ እንዲቻል የመድሃኒት አቅርቦቱ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና ህብረተሰቡም ስለ በሽታው ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረጉ ተግባር ላይ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የፓርኪንስን በሽታ ለታማሚው ብቻ ሳይሆን ለአስታማሚውም ከፍተኛ ስቃይ ያለው  በሽታ ነው ያሉት ወ/ሪት ትንሳኤ፤ አስታማሚዎች ስለ በሽታው ምንነትና ባህርይ በማወቅ ለህሙማኑ ማድረግ ስለሚኖርባቸው እንክብካቤ በየጊዜው ስልጠና የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። ድርጅቱ በየጊዜው የተለያዩ ስልጠናዎችን ከመስጠቱ ባሻገር ለሃይማኖት ተቋማት ፣ ለጋዜጠኞችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ስለ በሽታው ምንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን የሚሰራ መሆኑና ለህሙማኑ የመድሃኒት መግዣ የገንዘብ ድጋፍ፣  የአልጋ ቁራኛ የሆኑትን ደግሞ በጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት የህክምናና ልዩ ልዩ ድጋፎችን የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል። የፓርኪንሰን ህመም ችግር በአንድ ግለሰብ ማለትም በታማሚው ላይ ብቻ የሚያበቃ አይደለም ያሉት ወ/ሪት ትንሳኤ፤ ተጽዕኖው በቤተሰብ፣ በማህበራዊ ኑሮና በኢኮኖሚ ላይ በከፍተኛ መጠን የሚታይ ነው ብለዋል።
ህመምተኛው ራሱ ስራ ባለመስራቱ ከሚገጥመው የገቢ ማጣት ውጪ እሱን ቤተሰቦቹ በማስታመምና በመንከባከብ ተግባር ላይ በማተኮራቸው ሳቢያ ስራ ለመስራትና ገቢ ለማግኘት እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል። ይህም እጅግ ከባድ የኑሮ ጫና እንዲደርስበት ያደርገዋል ብለዋል።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከጥቁር አንበሳ፣ ከዘውዲቱና፣ ከጳውሎስ ሆስፒታሎች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነ የሚገልጹት ወ/ሪት ትንሳኤ፤ ከዚህ በበለጠ ህሙማኑ ሊረዱና ሊደገፉ የሚችሉበት  ሁኔታ ላይ ሊሰራ ስለሚገባ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ትብብር ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። “ፓርኪንሰን ፔሸንስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን” ከ10 ዓመታት በፊት በወጣትነቷ ለበሽታው በተዳረገችው ወ/ሮ ክብራ ከበደ የተቋቋመና ለህሙማኑ የተለያዩ ድጋፎችና እንክብካቤዎችን የሚያደርግ ድርጅት ነው።
የፓርኪንሰን ህመም በአንጎላችን ውስጥ የሚገኙና እንቅስቃሴን የሚቆጣጠረውን ኬሚካል የሚሰሩ ዶፓሚን የሚባሉ ሴሎች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሲሞቱ የሚከሰት በሽታ ሲሆን በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ በስፋት ይታያል።

Read 2756 times