Saturday, 18 August 2012 13:49

“የበዓል ዕንግዶች” ትያትር ዕይታዬ

Written by  ዳዊት ንጉሡ ረታ
Rate this item
(0 votes)

“የበዓል ዕንግዶች” ትያትር ዕይታዬ

ኢትዮጵያዊ ባህልና ዕሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረዱና እየተዋረዱ ጨዋነታችንና ኩሩነታችን ድራሻቸው እየጠፋ ስለመሆኑ ድርሰቱ ስለሚያሳስበን ከአዳራሹ ስንወጣ ራሳችንን መፈተሻችንና ስለ መፍትሄው ማሰላሰላችን አይቀሬ ነው፡፡ይህም የደራሲው ዓላማ ግቡን እንደመታ የሚያሳይ ይሆናል፡፡በጋዜጠኛና ጸሐፊ ተውኔት ዘካሪያስ ብርሃኑ ተጽፎ ለረጅም ዘመናት ከመድረክ ዕይታ በጠፋው አንጋፋው አርቲስት ዘውዱ አበጋዝ  የተዘጋጀው ‹‹የበዓል እንግዶች›› ትያትር ለማየት ወደ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ባመራሁ ጊዜ የትያትር ቤቱ ቅጥር ጊቢ በበርካታ ተመልካቾች ተሞልቶ ነበር፡፡ሀገር ፍቅር ትያትር እንደ ዘመነኞቹ ፊልም ቤቶች ዘምኖ በኮምፒውተር በመታገዝ የተመልከቹን ተራ ባያስጠብቅም፤በአንዲት ቁጥር በተጻፈባት አነስተኛ አረንጓዴ  የካርቶን ኩፖን ሥነ-ሥርዓት ለማስያዝ ይሞከር እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡አሁን ይህም በመቅረቱ ነው መሰል ተመልካቹ እዛና እዛ ተበታትኖ ግቢውን የሞላ አስመስሎታል፡፡

በአንድ ወቅት የትያትር ተመልካች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየቀነሰ በመምጣቱ የትያትር ዕድሜ ያጠረ ይመስል ነበር፡፡እየዋለ እያደረ ግን ከደረሰበት ክስረት አገግም ወደ ቀድሞ ቦታው እየተመለሰ መሆኑን በየትያትር ቤቱ እየታዩ ያሉ ትያትሮች ማሳያ ናቸው፡፡ለዚህም እንደነ ‹‹ባቢሎን በሳሎን››፣‹‹ፍሬሽማን››፣‹‹ሚስጥረኞቹ››፣‹‹ደመነፍስን›› እና  የመሳሰሉት ለረጅም ጊዜ ከመድረክ ላይ ሳይወርዱ የቆዩ ትያትሮች ያደረጉት አስተዋፆ እንደውለታ ሊጠቀስ የሚገባ ይሆናል፡፡

ዛሬም በሀገር ፍቅር ትያትር የተመለከትኩት የትያትር ተመልካቹ ቁጥር፤ተመልካቹ ለሞያውና ለሞያተኞቹ ያለው አክብሮት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ማሳያ ሆኖልኛል፡፡ ትያትር ቤቱ ግን ቢቻል ከኋላው ተነስተው ከዘመኑት ፊልም ቤቶች ተምሮ በኮምፒውተር አልያም በሌላ አንዳች ዘዴ የመግቢያ ሥነ ሥርዓቱን መላ ቢለው መልካም ይሆናል፡፡

የትያትሩ ጭብጥ

ያለፈውን የኢትዮጵያ ሚሊኒየም መቼቱ አድርጎ የተነሳው ትያትሩ የአንድ ቤተሰብን ታሪክ ያመላክታል፡፡ከቤተሰቡ አባላት ውስጥም በዓሉን በማስመልከት ከአሜሪካ ወደ ሀገሩና ቤተሰቡ ስለተመለሰ ታላቅ ወንድም፤ለሚሊኒየሙ ከውጪ ለሚመጡና ትዳር ለሚፈልጉ ወንደላጤዎች ሚስት በማቅረብ ፕሮጀክት ላይ ስለተሰማራ የቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ፤ በሚያሳየው ያልተገባ ባህሪ ለ15 ዓመታት ተፈርዶበት ወህኒ ወርዶ በሚሊኒየሙ ምክንያት ይቅርታ ተደረጎለት በ10 ዓመቱ ስለተለቀቀ ሌላ ወንድም እና ሚስት አቅራቢ ወንድሟን ተማምና ከውጪ የሚመጣ ባል ስለምትጠባበቅ እህታቸው ታሪክ የሚያሳይ ትያትር ነው፡፡

ያለፈው የኢትዮጵያ ሚሊኒየም በርካታ የጥበብ ሥራዎችን ሊያሠራና ሊያሳየን ሲችል በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ቅያሜ ሳቢያ ያን ያህል ዐይን የገባ ነገር ሳናይበት በስንት ዘመን አንዴ የሚከሰተው ታሪካዊ በዓል እንደዋዛ አልፎብናል፡፡ጋዜጠኛና ጸሐፊ ተውኔት ዘካሪያስ ታዲያ ይህንን ጊዜ ለመቼትነት በመጠቀሙ እነዚያን ጊዜያት ከአምስት ዓመት በኋላ እንደገና እንድናስታውስ ዕድሉን ሰጥቶናል፡፡

አይ ጊዜ! የሚሊኒየሙ መምጣት  መከራውን ያላሳው ኢትዮጵያዊ ማን ነበር? የኢሕአዴግና የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንካሰላንቲያ፣የቅንጅት ፓርቲ አመራሮች ይፈታሉ/አይፈቱም ጉምጉምታ፣ዲያስፖራው ነቅሎ ወዳ ሀገሩ ይገባል ተብሎም ነበር፣በዛ ላይ ተያይዞ የመጣው የቤት ኪራይ ውድነት፣የትዳር ፈላጊ ሴቶች ጉጉት፤ የሆቴሎች መጎምጀት፣አጠቃላይ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት እንዴት ሊረሳ ይችላል? ቢያንስ ትዝታው እንኳን በትያትር ይድረሰን እንጂ፡፡ ‹‹የበዓል እንግዶች››ም እነዚሁኑ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዛ ባለው አቀራረብ ያሳየ ትያትር ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

ዲያስፖራና ፖለቲካ

በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው ያላቸው መረጃና ስለ ፖለቲካ ያላቸው ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ሚዛናዊ እንዳልሆነ  በተለያዩ መጽሐፍት የምናነባቸውና በመገናኛ ብዙሀን የምንሰማቸው ዘገባዎች ይጠቁሙናል፡፡ በዚህ ትያትር ላይም ከአሜሪካ የመጣው የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ በጭፍን የመንግሥት ጥላቻ ታውሮ የሴት ጓደኛውን እንኳን ሲነጠቅ ጣቱን በመንግሥት ላይ ሲቀስር እንመለከታለን፡፡

የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ እንደሆነ የሚነገርለት ትያትር ደግሞ ይህንን ዕውነታ በማሳየቱ ዲያስፖራ የተባለ ሁሉ አዋቂና የበሰለ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ እንደሆነ ያሳውቀናል፡፡

ዐይን ያወጣ ስግብግብነት

ደራሲው በገፀ-ባህሪዎቹ አማካኝነት ለገንዘብ ሲባል ስለሚከፈል ዋጋ፤ ራስን ለማያውቁት ሰው በትዳር አሳልፎ ስለመስጠት፤ ቤተሰብ ስለሚፈልገው አግባብ ያልሆነ ብልፅግና፤ ወዘተ እያዋዛ ያሳየናል፡፡

ኢትዮጵያዊ ባህልና ዕሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረዱና እየተዋረዱ ጨዋነታችንና ኩሩነታችን ድራሻቸው እየጠፋ ስለመሆኑ ድርሰቱ ስለሚያሳስበን ከአዳራሹ ስንወጣ ራሳችንን መፈተሻችንና ስለ መፍትሄው ማሰላሰላችን አይቀሬ ነው፡፡ይህም የደራሲው ዓላማ ግቡን እንደመታ የሚያሳይ ይሆናል፡፡

ማኅበረሰባችን አንድን ነገር ቶሎ ለመልመድ የሚያዳግተውን ያህል የለመድውን ነገር ለመልቀቅም ደግሞ የዚያኑ ያህል ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ በአደገኛ ቦዘኔነት ተወንጅሎ ለ15 ዓመታት ተፈርዶበት የነበረው የቤተሰቡ አካል በድንገት በተደረገለት ምህረት ከእስር ቀነ-ገደቡ ቀድሞ ሲለቀቅ ምንም እንኳን ፍፁም የሆነ የባህሪ ለውጥ ቢያመጣም ከእናቱ በስተቀር ወንድሞቹና እህቱን ጨምሮ አጠቃላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያደርስበትን ማግለል በትያትሩ ስንመለከት ራሳችንን በድጋሚ እንድፈትሽ ያነሳሳናል፡፡

የትያትሩ ደካማ ጎኖች

በትያትሩ ላይ የሴት ደላላውን ገጸ ባሕሪ ወክሎ የሚጫወተው ተስፉ ብርሃኔ በዚሁ ትያትር ቤት ዘወትር ቅዳሜ ምሽት በሚታየው ሰማያዊ ዐይን ቴያትር ላይ ከሚጫወተው ገፀ-ባህሪ ጋር ፍፁም ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ያኛው የመሬት ይሄኛው ደግሞ የሴት ደላሎች ከመሆናቸው ውጪ! ለምሳሌ ተስፉ በዚህ ቴአትር ላይ ዮናስ ወይም አብዱልከሪም የተጫወቱትን ገጸ-ባህሪ ወክሎ ቢተውን በአዲስ ፊት መጣ ብዬ ከልቤ እደሰት ነበር፡፡

ሌላው ትያትሩ ከሚያነሳቸው ርዕሶች መካከል ስለግብረሰዶማውያንና የተለየ ወሲባዊ ባህሪ ስላለቸው ግለሰቦች የሚያነሳው ርዕስ ሰፊ ጊዜን የወሰደ ነው፡፡ይህ ደግሞ የሚወራው ኢትዮጵያዊት እናት ፊት ነው ይህ በባህልም በኃይማኖትም ለእኛ ማኅበረሰብ የቀረበ አይደለም፡፡

ርዕሱ መነሳቱ ግንዛቤን እንደ መፍጠሪያ መልካም ቢሆንም ረዘም ያለ ደቂቃ ሊሰጠው ግን አይገባም፡፡

ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ዲያስፖራ ሁሉ የተለየ ወሲባዊ ባህሪ ያለው አስመስሎ ማቅረቡ ነው፡፡

በትያትሩ ላይ በተስፉ ብርሀኔ ገጸ ባህሪ አማካኝነት ሚስት የቀረበላቸው ዲያስፖራዎች በሙሉ ወሲባዊ ችግር ያለባቸው ሆኖ መታየቱ ወገኖቻችንን ከመጠን ባለፈ ጥርጣሬ እንድናያቸው ሊያደርገን ይችላል፡፡

የመድረክ ገፅና የቴክኒክ ብቃት

እንዳብዛኞቹ ያሀገራችን ትያትሮች ሁሉ በሳሎን ቤት ውስጥ የማይጠፋው ሦስት ሶፋ በዚህም ትያትር ዝግጅት ላይ በመድረኩ ፊት-ለፊት ይታያል፡፡ ይህ አሰልቺነትን ከመፍጠሩም በላይ የአዘጋጆችን የፈጠራ ብቃት ማነስ ያመላክታል፡፡

ሌላ ዐይነት የመድረክ ገፅ፤ ሌላ ዐይነት የሶፋ አደራደር የምናየው መቼ ነው? ትያትሩ ከመድረክ ጀርባ የሚሠሩ የድምፅና የቴክኒክ ባለሞያዎችን ለፈጠራ የሚያነሳሳ መልካም አጋጣሚን ቢፈጥርም ባለሞያዎቹ ግን እንደሚፈለገው አልተጠቀሙበትም፡፡ ይህ አጋጣሚ የሚሊኒየሙን መግባት ለማብሰር ርችት የሚተኮስበት ቦታ ነው፡፡ ይህንን እነዚሁ ጥበበኞች በተሻለ ቴክኒክ ሊያሳዩንና ሊያስደንቁን በተገባ ነበር፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Read 2142 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 14:04