Saturday, 17 April 2021 00:00

የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር “የፍቅር ሳምንት” ነገ ይጀምራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  በየዓመቱ ለአንድ ሳምንት የሚቆየውና ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደው የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር “የፍቅር ሳምንት”፤ ከነገ እሁድ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ለአንድ ሳምንት እንደሚቀጥል በጎ አድራጎት ማህበሩ ከትላንት በስቲያ ረፋድ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስውቋል። ማህበረሰቡ የሚችለውን ነገር በመያዝና ኮተቤ ዩኒቨርስቲ ፊት ለፊት በሚገኘው የማህበሩ ቅጥር ግቢ በመገኘት በማህበሩ ለሚደገፉ ህፃናትና እናቶች ያለውን ፍቅር እንዲገልጽ  የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታደሰ አየለ ጥሪ አቅርበዋል።
እያንዳንዱ የፍቅር ሳምንቱ ቀናት ለአርቲስቶች፣ ለመንግስት ተቋማትና መንግስታዊ ላሆኑ ተቋማትም ተከፋፍሎ የተሰጠ ሲሆን ይህ የሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመከላከል ነው ተብሏል። እያንዳንዱ ተቋም በተመደበለት ቀን የራሱን እንግዶች ይዞ እየመጣ ተቋሙንና ተረጂዎቹን እንዲጎበኝና በቀጣይ ለሚያደርጉት ድጋፍ ቃል የሚገቡበት ሲሆን የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ከሳምንቱ አንዱን ቀን በመውሰድ አጋርነቱን ማሳየቱን የማህበሩ መሥራችና ዋና ዳሬክተር ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ተናግረዋል።
የፍቅር ሳምንቱ በተለይ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ እናቶች ያለባቸውን ጫና በመጋራት ኑሯቸው የሚሞከርበት ሁነት መዘጋጀቱም ተገልጿል። እስከ ሚያዚያ 10 በሚቆየው በዚህ የፍቅር ሳምንት፣ ቤተሰብ ልጆቹንም የሚችለውንም ድጋፍ ይዞ በመምጣት ፍቅሩን እንዲያጋራ ተጠይቋል። ሙዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ምንም ቋሚ የውጭም የአገር ውስጥም ድጋፍ ሳይደረግለት ቅን ልብ ባላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና በጎ አድራጊዎች በመደገፍ ላለፉት 21 ዓመታት በጎ አድራጎት ስራውን በከባድ ፈተና ውስጥ በፅናት እየተወጣ እንደሚገኝ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት በ3ሺህ ካ.ሜ ግቢ ውስጥ ለ650 ልጆችና ለ450 እናቶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና ከ350 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩም ተነግሯል።

Read 829 times