Sunday, 18 April 2021 00:00

የኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ ፊት ማሳየት አይፈልግም - እናት ፓርቲ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

       - ሚዲያው ቢያግዘን ኖሮ ብልጽግና ፓርቲን የሚገዳደር እጩ ማቅረብ እንችል ነበር
       - ነገ ገዢው ፓርቲ ተነስቶ እኔ ነኝ ያቋቋምኳቸው ሊል ይችላል
       - አዲስ አበባ የየትኛውም ክልል አካል ነች ብንል አናምንም

           ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች 573 እጩዎችን በማቅረብ፣ ከብልጽግናና ከኢዜማ በመቀጠል ከፍተኛ እጩዎችን በማቅረብ በ3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው እናት ፓርቲ፤  በተለያዩ ተፅእኖዎች ውስጥ ሆኖም ገዢውን ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሊገዳደር በሚችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ የፓርቲው ዋና ፀሀፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ከአቶ ጌትነት ወርቁ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

              በሌሎች ፓርቲዎች የተዘናጉ  በእኛ ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ግን ተካተዋል የምትሉት ለየት ያለ ነገር ምንድ ነው?
የእኛ ፓርቲ የተለየ ነገር ያዞ መጥቷል የምንለው ሰዋዊ ፍልስፍናን ነው፡፡ ከማኦና ከስታሊን ያልተቀዳ፣ ከግራ ዘመም ሆነ ከቀኝ ዘመም ማምታታት የወጣ ፍልስፍና ነው፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል የተሰራ ውቡ ፍጡር መሆኑነን እናምናለን። እናም አዲስ ነገራችን ሰውነት ነው፡፡ ሰው መሆን ብቻውን በቂ ነው፡፡ ዋናው ጉዳያችን በጥቁርና በነጭ መካከል ያለውን ግሪን ኤሪያ ማለፍያ መስመር ማስተዋወቅ ነው። የያዝነው ጉዳይ ሰው ሰው ይሸታል ወይ ዋናው ነገራችን ነው፡፡
ስለ ኢኮኖሚ ሲወራ የፐርሰንቴጅ ጋጋታ፣ የውጭ አገር ተሞክሮ ተብሎ ይነገረናል። መሬት ላይ  ግን ድሆች ነን የኢኮኖሚ ፖሊሲው ድሃውን ፍፁም ድሃ፣ ሀብታሙም ደግሞ ፍፁም ሃብታም አደርጎ የሚያስቀጥል ነው፡፡ ድሆች ነን፤ በየዓመቱ ከ3-15 ሚሊዮን ህዝባችን ጠኔ ይመታዋል፡፡ አብዛኛውን ነገር ከውጭ እናስገባለን፣የምንልከው ነገር የለንም፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ልካ ዶላር ልታገኝ የምትችልበት  ነገር ምንድን ነው? ወጣቱን ስራ ፈጣሪ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለውን ነገር ነው ማሰብ የሚያስፈልገው፡፡ ነገሮችን ከራስ አንፃር የሚያይ እንጂ ፈረንጅ ያለው ሁሉ እውነት ነው ብሎ አየገላበጠ አገር ላይ የማይተገበር ርዕዮተ ዓለም ነው ይዘን የመጣነው፡፡ የትምህርት ፖሊሲው ምን ያህል የተራራቀ እንደሆነ ይነገረናል በተግባር ያተረፈልን ግን “የሰውን ልጅ ከእነ ነፍሱ ዘቅዝቆ የሚሰቅል ትውልድ” ነው፡፡ በርዕዮተ ዓለም፣ በአመክንዮ የሚከራከር ትውልድ ሳይሆን፣ በውሃ ቀጠና ተነሳስቶ የሚገዳደል ትውልድ ነው ያተረፍነው፡፡ ያህንን ሁሉ ችግር ሰውነት ይቀርፈዋል ብለን  እናስባለን፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያላችሁ አቋም ምንድን ነው? ችግሮቹን ለመፍታት ይዛችሁ የመጣችሁት የፖሊሲ አማራጭ አለ?
የአዲስ አበባ ጉዳይ አከራካሪ ነው፡፡ ወደ ስድስት ሚሊዮን ህዝብ የሚጠጋው የአዲስ አበባ ህዝብ፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካይ አልባ፣ የሚጮህለት የሌለው ነው፡፡ እውነት የአዲስ አበባ ባለቤት ማነው? ሁሉም የየራሱ አክቲቪስት፣ የየራሱ ጠባቂና ጠበቃ አለው፡፡ የአዲስ አበባ  ባለቤት ግን ማነው? ይህ በትክክል መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡
የአፍሪካ እምብርት፣ የዲፕሎማቲክ ከተማ እየተባለች የምትሞካሸው ከተማ፤ በተጨባጭ ተወካይ የሌላት ከተማ ሆናለች። ይህ በመሆኑ በጣም እናዝናለን፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱ በፈለገውና በመረጠው ሰው ሊተዳደር ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ አዲስ አበባ የማናቸውም ክልል አንድ አካል ነው ብለን አናምንም፡፡ አሁን ያለው የአዲስ አበባ አስተዳደር ከተማዋን አይመጥናትም፡፡ አዲስ አበባ ለአጎራባች ከተሞች ምን ጥቅም መስጠት አለባት? አጎራባች ከተሞች ለአዲስ አበባ ምን ይመግቧታል? የሚለው ጉዳይ  ውይይት ይፈልጋል፡፡
እኛ ነገ መንግስት ብንሆን በምንፈጥረው አወቃቀር፤ አዲስ አበባ ከተማ ራሱን የቻለ የፌደራል ክልል ሆኖ መዋቀር እንዳለበት ሰለምናምን የምናደርገው ይህንኑ ነው፡፡
ፓርቲያችሁ “የሃይማኖት አወቃቀርና አደረጃጀት ያለው ፓርቲ ነው” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህ መልሳችሁ ምንድን ነው?
በፓርቲው ውስጥ ሃይማኖተኛ ሰዎች አሉበት ወይ ከሆነ አዎ አሉበት፡፡ እኛ አባላትን በምንመለምልበት ወቅት የት ተወለድክና ሃይማኖትህ ምንድን ነው የሚሉ ጥያቄዎችን አንጠይቅም፤ ግን የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች በፓርቲው ውስጥ በአባልነት እንዳሉበት ይታወቃል፤ ደግሞም ሀይማኖተኛ ሰዎች የፓርቲው አባል መሆናቸው የሚደግፍ እንጂ የሚወገዝ ጉዳት አይደለም፡፡ ባለፉት ስርዓቶች ያየናቸው ስህተቶች የሚጀመሩት ከዚህ ነው፡፡ ሃይማኖትን በካልቾ ብሎ ከመነሳት፡፡ በተለይም በውጭ አገር ተምረው የሚመጡ ፖለቲከኞች፣ የሚያደርጉት ይህንን ነው፡፡ የአብነት ት/ቤቶች፣ የመድረሳ ት/ቤቶች ሁሉ ጉዳያችን አይደለም ብለው ነው የሚነሱት፡፡ ይህ ሲጎዳ እንጂ ሲጠቅም የታየበት አጋጣሚ ግን የለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ 98 በመቶው ሃይማኖተኛ ነው፡፡ ለፈጣሪው ይገዛል፤ እናም ቅንነትና ሰውነት በሃይማኖተኛ ሰዎች ውስጥ መኖሩ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ከዚህም በተረፈ ግን ፓርቲው ውስጥ የሁሉም እምነት ተከታዮች በእኩልነት የየራሳቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ የሚገኙበት ፓርቲ ነው እንጂ ሃይማኖታዊ አቋምና አደረጃጀት ይዞ የተነሳ ፓርቲ አይደለም፡፡ የኛ ጉዳይ ማንም ሰው በፍትህ ፊት እኩል መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ እናት አባቶቻችን ያስተማሩንም ይህንኑ ነው፡፡ የእኛ ሃገር ፖለቲካ ምክንያት ፈልጎ የሚጠልፍ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ብዙ ነገር ተብለናል፡፡ ግለሰብ ነው ያቋቋመው፣ብልፅግና ነው ያቋቋመው፣ የሆነ አካላትን ድምጽ ለመክፈል ታስቦ ነው የተቋቋመው” ሁሉ ተብለናል። ስለዚህ በዚህ ወገባችን አይሰበርም፡፡ ከዚህ የበለጠም ነገር ሊመጣ ይችላል፡፡ ነገ ገዢው መንግስት ተነስቶ እኔ ራሴ ነኝ ያቋቋምኳቸው ሊለን ሁሉ ይችላል፡፡ ግለሰቦችንም ከመሃል አስነስቶ እንደዚህ ሊያስብል ይችላል። በትክክል የምናገረው ነገር ግን ይህ የመጠላለፍ አባዜአችን አንዱ ክፍል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ ፊት ማሳየት አይፈልግም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሆኑ ሰዎች ሁሉንም ነገር በሞኖፖል ይዘውታል፤ እንዲነካ አይፈልጉም፡፡ የግብርና ፖሊሲ አዋቂ እነሱ ናቸው፣የኢኮኖሚ፣የትምህርት ፖሊሲ አዋቂዎች እነሱ ብቻ ናቸው ፖሊሲው ያለ እነሱ አይነካም፡፡ ያ እንዲነካባቸው አይፈልጉም፡፡ ከእነሱ በላይ አዋቂና ተናጋሪ እንዲመጣባቸው አይፈልጉም፤ ሚዲያው የእነሱ ድምጽ ሆኖ ነው የሚሰራው፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ለአገራቸው ዋጋ የከፈሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሚዲያው ግን ይህንን ማሳየት አይፈልግም፡፡ ብዙ ሚዲያዎች የእኛን መግለጫ ይወስዳሉ፤ የእኛ መሆኑን ግን አይናገሩም፡፡ ሚዲያው ዕድል ሰጥቶን ቢሆን ኖሮ ብልጽግናን ሊገዳደር የሚችል የእጩዎች ቁጥር ማቅረብ እንችል ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡
አመጣጣችሁ ድንገት መሆኑ ይሆን ይህን ያመጣው?
አመጣጣችን ድንገት አይድለም፡፡ ድንገት የሆነው ለሚዲያው ነው፡፡ እኛ ዝም ብለን ስራችንን ስንሰራ ነው የቆየነው፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ዓመት ኮቪድ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የላክነው መልዕክት አለን፤ መግለጫዎቻችንን ማየት ይቻላል፡፡ ሚዲያው እኛን ማሳየት ስለማይፈልግ ነው ድንገት የመጣን የመሰለው፡፡  



Read 10663 times