Monday, 19 April 2021 00:00

አንዲት ቃል ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች! ሚስጥሩ ምንድነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

      • ከሩብ በላይ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ አንዲት ቃል ማንበብ አይችሉም። ከመንግስት በጀት ውስጥ ግን፣ ከሩብ በላይ ለትምህርት ይመደባል።
      • የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር፣ ከ2000 ዓ.ም ወዲህ በ33% ጨምሯል። ያኔ፣ 15 ሚሊዮን ተማሪዎች ነበሩ። ዓምና 20 ሚሊዮን።
      • የመምህራን ቁጥር ግን፣ በ100% (ማለትም በእጥፍ) ጨምሯል። የአንደኛ ደረጃ መምህራን 250ሺ ነበሩ። ዓምና ከ500ሺ በላይ ሆነዋል።
      • አንድ አስተማሪ ለስንት ተማሪዎች ይደርሳል? ያኔ፣ ለ60 ተማሪዎች ነበር። ዛሬ ለ38 ተማሪዎች ሆኗል። የመምህራን እጥረት ተቃሏል።
      • ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ፣ የዲፕሎማ ተመራቂ መምህራን፣ ከ10% ብዙም አይበልጥም ነበር። ዛሬ ከ90%በላይ አስተማሪዎች፣ ባለ   ዲፕሎም ናቸው።
      • የመፃህፍት ቁጥርም ጨምሯል። ጥቁርና ነጭ ህትመት ቀርቷል። የመፃሕፍት ሕትመት፣ በቀለማት ያጌጠ ሆኗል።
      • በ2000 ዓ.ም፣ የአንደኛ ደረጃ መፃሕፍት ቁጥር፣ ከ10 ሚሊዮን በታች ነበር። ለአንድ ተማሪ አንድ መፅሐፍ አይደርሰውም ነበር።
      • ዛሬ፣ የመፃሕፍት ቁጥር ወደ 80 ሚሊዮን ተጠግቷል። ለአንድ ተማሪ 4 መፅሐፍ ይደርሰዋል እንደማለት ነው።
            
               የ1ኛ ደረጃ ትምህርት የመምህራን ቁጥር
1999    225 ሺ
2000    254 ሺ
2001    271 ሺ
2002    292 ሺ
2003    308 ሺ
2004    322 ሺ
2005    335 ሺ
2006    368 ሺ
2007    396 ሺ
2008    425 ሺ
2009    461 ሺ
2010    483 ሺ
2011    530 ሺ
2012    538 ሺ

የተቀየረው ነገር?
ባለፉት 10 ዓመታት፣ ብዙ ነገር ተቀይሯል። የመምህራን የትምህርት ደረጃ፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ተቀይሯል። ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ውስጥ፣ ባለ ዲፕሎማ መምህር፣ እንደ ብርቅ መታየቱ ቀርቷል። ከአስር መምህራን አንዱ ነበር ባለዲፕሎማ። ዛሬ ከአስሩ መምህራን መካከል፣ ዘጠኙ ባለዲፕሎማ ናቸው። መፃሕፍት፣ ትምህርት ቤቶችና የመማሪያ ክፍሎች.... በቁጥርም በደረጃም በጣም ተቀይረዋል - በዝተዋል፤ ተሻሽለዋል።
ያልተቀየረው ነገር?
ዋናው ቁልፉ ነገር አልተቀየረም። ከ10 ዓመት በፊትም፣ ዛሬም፣ የማንበብ ነገር፣ ለተማሪዎች፣ ከባድ አቀበት እንደሆነ ዘልቋል። የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች፣ ፅሁፍ ማንበብ ቢከብዳቸው፣ ቢፈታተናቸው ላይገርም ይችላል። የሁለተኛ፣ ከዚያም የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ ማንበብ ሲሳናቸው ግን፣ ያስደነግጣል፤ ግራ ያጋባል።
አሳዛኙ ነገር፣ ማንበብ አለመቻል የእድሜ ልክ ልምሻ መሆኑ ነው። የክፍል ደረጃ እያደገ ሲሄድ፣ ዋነኛው የማወቂያ ዘዴ፣ ንባብ ይሆናልና።
ከሩብ በላይ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ አንዲት ቃል ማንበብ አይችሉም። ጨርሶ አንዲትም ቃል ማንበብ አለመቻል! ዓረፍተ ነገር አንብቦ መረዳትማ፤ ለአብዛኞቹ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ የማይታሰብ ነገር ነው። አያስደነግጥም? አዎ፣ “አዲስ ነገር አይደለም” ማለት ይቻላል። ግን፣ ይሄስ አያሳዝንም? መፍትሄ መጥፋቱ?
ከ2002 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም፣ ምን ተለወጠ?
በአስር ዓመት ልዩነት የተካሄዱት ሁለት ጥናቶች፣ የተማሪዎችን የማንበብ ችሎታ በዝርዝርና በጥንቃቄ ለመመዘን የሚያገለግሉ ጥናቶች ናቸው።
ከአዲሱ የጥናት ውጤት ጋር ሲነፃፀር፣ የዛሬ 10 ዓመት የወጣው የመጀመሪያው የጥናት ውጤት፣ ብዙም ልዩነት የለውም።
አብዛኞቹ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ አንድ ዓረፍተ ነገር አንብበው የመገንዘብ አቅም የላቸውም ይላል - የአምናው አዲስ ሪፖርት።
ከ10 ዓመት በፊት፣ በ2002 ዓ.ም የወጣው የጥናት ሪፖርትም፣ ተመሳሳይ መረጃዎችን የያዘ ነበር። ልዩነቱ ምንድን ነው?
አንደኛው ልዩነት፤ የያኔው የመጀመሪያ ሪፖርት፣ በርካታ ሰዎችን አስደንግጧል። “ከፈሩትም በላይ “ትልቅ መርዶ ሆኖባቸው ነበር።
የአምናው ሪፖርት ግን፣ ብዙም ሰሚ አላገኘንም። እንደ ቁምነገርም አልተቆጠረም።
ሁለተኛው ልዩነት፤ ያኔ በ2002 ዓ.ም፣ ያን የመሰለ “ግዙፍ የትምህርት ብልሽትና ውድቀት” በይፋ ሲገለፅ፣ በቁጥር ተዘርዝሮ ሲታይ፣ ከድንጋጤ ጎን ለጎን፣ ብዙ ማመከኛዎችንና ሰበቦችን የመደርደር ሩጫም እንደ ጉድ ተፈጥሮ ነበር።
“የመማሪያ መፃህፍት ጥቂት ናቸው፣... ሕትመታቸውም ውበት የለውም”... የሚሉ ምክንያቶች ቀርበው ነበር። “ከመምህራን እጥረት በተጨማሪ፣ የትምህርት ደረጃቸውም ዝቅተኛ ነው” የሚል ሰበብም ተነግሮን ነበር። የመማሪያ ክፍል መጣበብም፣ እንደማመካኛ ቀርቧል።
በአጠቃላይ፣ “ትምህርትን ለማስፋትና ለማዳረስ እንጂ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ በቂ ትኩረት ስላልተሰጠ ነው፤ ችግር የተፈጠረው” ተባለ። ሌላ ሌላም ብዙ ተባለ።
ያው፣ እንደምታውቁት፣ ሰበብና ማምከኛ፣ ሁሌም ይኖራል። እውነታው ግን ሌላ ነው። በ2002 ዓ.ም የነበረው የመፃሀፍት፣ የመምህራንና የመማሪያ ክፍል ሁኔታ፣ ድሮ ከነበረው የሚብስ ሆኖ ነው? ከ20 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር፣ የመማሪያ መፃህፍት ወይም የመምህራን እጥረት ተባብሶ ነው? አይደለም። ቢሆንም እንኳ፣ ከዚያ ወዲህስ? ከ2002 ዓ.ም ወዲህስ?
በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ባለዲፕሎማና ባለድግሪ መምህራን ተጨምረዋል። በቁጥርም በትምህርት ደረጃም፣ “የመምህራን ችግር፣ ከሞላ ጎደል መፍትሄ አግኝቷል” ማለት ይቻላል - ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል። ብዙ ትምህርት ቤቶችና በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል። “የክፍል መጣበብ”፣ ባለፉት 10 ዓመታት እጅግ በጣም ቀንሷል። የመፃህፍት ህትመትም፣ በብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላሮች ብድርና እርዳታ አማካኝነት፣ በእጥፍ ጨምሯል። መፃህፍት፣ በቀለማት አጊጠዋል።
ገንዘብ እየፈሰሰ ነው። ንባብ ግን ደርቋል።
እንደ ሰበብ እየተደረደሩ የነበሩ በርካታ ችግሮች፣ በአብዛኛው ተቃልለዋል። እቅድ ተዘጋጅቶ፣ ገንዘብ ተመድቦ፣ በተግባር “ውጤቱ” ታይቷል። ከአገሪቱ መደበኛ ሰራተኞች መካከል፣ አብዛኛዎቹ´ኮ መምህራን ናቸው።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር፣ ከ37 ሺ በላይ ሆኗል። ከ350ሺ የሚበልጡ የመማሪያ ክፍሎችም አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ “ከመኖሪያ ቤቶች ይልቅ፣ ለትምህርት ቤቶች ቅድሚያ ተሰጥቷል” ማለት ይቻላል።
ይሄ ሁሉ አይገርምም። ከመንግስት በጀት ውስጥ፤ ሩብ ያህሉ፣ ለትምህርት የሚመደብ ነው። ተወዳዳሪ የለውም።
ይሄ ሁሉ ሆኖም፤ ዛሬም የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ በአብዛኛው፣ አንዲት አጭር ዓረፍተ ነገር አንብበው መረዳት አይችሉም። በአብዛኛው ማለት፣ ከመቶ ተማሪዎች መካከል፣ 90% ያህሉ፣ አንብበው  የመገንዘብ አቅም የላቸውም ለማለት ነው።
በዚህ መደንገጥ የለብንም? እንላመደው ካልተባለ በስተቀር፣ ከባድ ውድቀትና ትልቅ ኪሳራ፣ የቱንም ያህል ቢደጋገም፣ ሁሌም ሊያስደነግጠን ሊያሳስበን ይገባል።
“የትምህርት ጥራት ጉድለት” ብለን ውድቀቱን ልናድበሰብሰው ብንሞክር፣ እሺ አይለንም። እንዲያውም፣ “የጥራት ጉድለት” ብሎ መናገር፣ በባዶ የመቀናጣት ሙከራ ነው የሚሆንብን። ልጆች፣ “አበበ በሶ በላ” የሚለውን ፅሁፍ ማንበብ የመቻልና ያለመቻል ችግር ላይ ነው የወደቁት። 1ኛ ክፍልና 2ኛ ክፍል አልፈው፣ አንዲት ቃል ማንበብ መቻል ነው፣ እንደ ሰማይ የራቀባቸው።
ከሩብ በላይ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ አንዲት ቃል ማንበብ እንደማይችሉ እየተነገረን? በእርግጥ፣ ችግሩ፣ ከዚህም የከፋ ነው።
ከአዲስ አበባና ከሀረር ከተሞች ውጭ፣ ግማሽ ያህል የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፤ አንድም ቃል ማንበብ የማይችሉት። ዓረፍተ ነገር አንብበው መረዳት የሚችሉትማ አስር ከመቶ አይሆኑም።
ምንድነው ሚስጥሩ? ምንድነው ችግሩ?
የድሮዎቹን ሰበቦች እንደገና ዛሬ ለመደርደር መሞከር፣ ቀሽም ሞኝነት ነው። ወይም ቀሽም የማሞኘት ሙከራ ከመሆን አያልፍም። የመምህራንን የትምህርት ደረጃ ብናሻሽል፣... የመምህራንን ቁጥር ብናሻሽል... እያሉ እንደያኔው መዝፈን ትርጉም የለውም። የክፍል መጣበብ፣ የመፃህፍት እጥረት እያሉ ማምታታት፣... ዋጋ የለውም።... እነዚህን የመሳሰሉ እንጉርጉሮዎች ሁሉ አያስኬዱም።
እና ታዲያ ምንድነው ችግሩ?
የትምህርቱ ይዘት፣ የማስተማሪያው ዘዴ፣ የተማሪዎች የግል ጥረት፣ የመልመጃ አይነትና ብዛት፣... እነዚህ ሁሉ ባለፉት 20 ዓመታት ተቀይረዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሩና እየተበላሹ መጥተዋል።
የትምህርቱ ይዘትና መማሪያ መጻህፍት፣... እንዲራቆቱ እንዲዝረከረኩ ተደርገዋል። ለምን ተብሎ ሲጠየቅ፣ “መፃህፍት፣ በመረጃና በእውቀት የታጨቁ ናቸው” በሚል ግራ የገባው ይመልሱላችኋል።
የትምህርት ዓላማ፣ “እውቀትና መረጃን ማንቆርቆር አይደለም በሚል” የጥላቻ አባባልም አላቸው። ፍኖተካርታ ተብሎ የተዘጋጀውን ሰነድ ማየት ትችላላች። እናስ? “የአስተማሪ ስራ ማስተማር አይደለም።  የአስተማሪ ስራ ለተማሪዎች የውይይት መድረክ ማመቻቸት ነው” ተባለና፤ የመማሪያ ጊዜ ለዘፈቀደ ወሬ እንዲውል ተመቻቸ። የመማሪያ ክፍል ወንበርና ጠረጴዛ፣ በክብ ቅርጽ፣ የስብሰባና የድግስ መልክ መያዝ እንዳለባቸው ታወጀ። ለምን? “ትምህርት፣ ነፃ የውይይት መድረክ መሆን አለበት” ይላሉ የትምህርት ሚኒስቴር ሰዎች።
መሰረታዊ መረጃዎችን የማስተዋልና የማገናዘብ፣ እውቀትን የመጨበጥና በቅጡ ከራስ ጋር የማዋሃድ ጊዜስ? “ትምህርት ቤት የእውቀት ጎተራ አይደለም” በማለት ይሳለቁባችኋል - የትምህርት ቢሮ ሰዎች።
“መረጃና እውቀት በየቦታው ሞልቷል። ኢንተርኔት አለ። ጉጉል አለ። ዊኪፒዲያን አለ። ማንኛውም መረጃና እውቀት፣ ባስፈለገህ ጊዜ ከኢንተርኔት ማግኘት ትችላለህ። ትምህርት ቤት ግን፣ ነጻ የውይይት መድረክ መሆን አለበት፤ ተማሪዎች፣ ሞጋች አስተሳሰብንና የፈጠራ ችሎታን ያዳብራሉ” በማለት ያነበንባሉ የትምህርት ሚኒስቴር ሰዎች። ለመሆኑ ስለምን እያወሩ እንደሆነ ያውቃሉ?
እስቲ ያሳዩን! የፈጠራ ችሎታ ጠብታ ከወጣቸው እንይ።
ካልኩለስ እና ከዚያ በላይ የረቀቁ የሂሳብ ዘዴዎችና እውቀቶች ኢንተርኔት ውስጥ ስለሚገኙ... በቃ፣ ያለትምህርት፣ ማንም ሰው ባስፈለገው ቀን ይጠቀምባቸዋል? በቅድሚያ መሰረታዊዎቹን ነገሮች እውቆና  በልምምድ ከራሱ ጋር አዋህዶ ካልቆየ፣ ምኑ ይገባዋል?
አንድ፣ ሁለት እያለ ከመቁጠር ጀምሮ፣ መደመርና መቀነስን፣ ማባዛትና ማካፈልን ሳይማር? እነዚህን በተደጋጋሚ በመልመጃ ከራሱ ጋር ሳያዋህድ? ክፍልፋይና “ዴሲማል”፣ የማባዛት ድግግሞሽና የማካፈል ድግግሞሽ (ሃይል)፣ ጂኦሜትሪ፣ ትሪግኖሜትሪና፣ ሎጋሪዝምን ጠንቅቆ ሳያውቅ?
የቀመር አይነቶችን... ደረጃ በደረጃ፣ ከታች በደንብ ያላወቀ ተማሪ፣ በመልመጃ ብዛትም ከራሱ ጋር እያዋሃደ ተማሪ፣ ለቀጣዩም እውቀት አስተማማኝ መሰረት እያደራጀ ያልመጣ ተማሪ፣... ባሰኘው ጊዜ፣ ባስፈለገው ጊዜ፣ ያሰኘውን መረጃና የእውቀት አይነት ከኢንተርኔት አፍሶ መውሰድ ይችላል?
እስቲ አንድ የህግ ባለሙያ፣ ዛሬ አስፈልጎት፣ ስለቫይረስና ስለክትባት ያሻውን እውቀት ከኢንተርኔት አፍሶ ይወሰድና ይሞክረው። እስቲ፣ “ችግር ፈቺ የፈጠራ ችሎታውን” ያሳየን። ክትባትና መድሃኒት ይፈጥርልናል?
እውቀትን ለማንቋሸሽ ሲሽቀዳደሙ የምናያቸው የትምህርት ባለሙያዎች፣ እስቲ ዛሬ፣ ያሰኛቸውን “የማክሮና የማይክሮ ኢኮኖሚ፣ ፊስካልና ሞነታሪ መረጃዎችን” ከኢንተርኔት አፍሰው መውሰድ ይችሉ እንደሆነ ይሞክሩት። ምኑ ከምኑ እንደሚገናኝ፣ እጅና እግሩን ለይተው መገንዘብ ይችላሉ? ለስራ አጥነትና ለዋጋ ንረት ችግሮችም መፍትሄ ይውለዱና፣ “ችግር ፈቺ የፈጠራ ክህሎታቸውን” ያሳዩን።
“መረጃና እውቀት ማንቆርቆር አያስፈልግም” እያሉ በጥላቻ የሚያነበንቡ የትምህርት ሚኒስቴር ሰዎች፣ የያዙት ፈሊጥ፣ ማብረጃ ያጣ ስካር ነው የሚመስለው። “የብዙ ቋንቋ መዝገበ ቃላትና ብዙ የሰዋሰው መፃሕፍት ከኢንተርኔት ማግኘት ስለሚቻል፤ አስቀድሞ መማር አያስፈልግም” እንደ ማለት ነው - የሰከረው አስተሳሰብ። “ባሰኛችሁ  ጊዜ፣ በማንኛውም ቋንቋ፣ መናገርና መስማት፣ መጻፍና ማንበብ ትችላላችሁ” ከሚል ቅዠት አይተናነስም። “መረጃዉንና እውቀቱን መማር፣ በመልመጃም ከራስ ጋር ማዋሃድ አያስፈልግም” እንደ ማለት ነው።
በእንዲህ አይነት የቅዠት አስተሳሰብ ሳቢያ ነው፤ ህጻናት “የፊደል ትምህርት” የተነፈጋቸው። “የንባብ ትምህርት፣ ከፊደል ትምህርት ሳይሆን፣ ከቃላትና ከዓረፍተ ነገር መጀመር አለበት” በሚል ተሳከረ ሃሳብ ሳቢያ፣ ተማሪዎችን ወደ መሃይምነት አስገብተው አስቀሯቸው። አንዲት ቃል እንኳ ማንበብ አቃታቸው።


Read 8843 times