Saturday, 17 April 2021 12:21

Infertility…… ልጅ አለመውለድ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  ልጅ ለመውለድ አለመቻል ሲባል በሁለት አይነት ይገለጻል፡፡
የመጀመሪያው ወንድና ሴት ቢያንስ ለ12 ወራት የእርግዝና መከላከያ ሳይጠቀሙ ወሲባዊ ግንኙነት ፈጽመው እርግዝና አልከሰት ሲል ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ለአንድ ጊዜም ቢሆን እርግዝናው ተከስቶ በመቀጠል ሲሞክር እርግዝና እምቢ ሲል ማለት ነው፡፡
ልጅ መውለድ አለመቻል ከሴት ወይንም ከወንድ ብቻ የሚመጣ ጉድለት ሳይሆን ከሁለቱም ሊሆን እንደሚችል በሳይንስ የተረጋገጠ ነው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ8-12% የሚሆኑ ጥንዶች ልጅ የመውለድ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ከ45-50% የሚሆኑት ምንጮች እንደሚያስረዱትም ልጅ የመውለድ ችግር ምናልባትም ከወንዶች በኩል በስፋት የሚስተዋል ነው፡፡
በመቀጠል የምንመለከተው ከወንዶች ጋር በተያያዘ ልጅ ላለመውድ ምክያት ናቸው ተብለው የሚጠቀሱትን ነገሮች ነው፡፡
በእንግሊዝኛው አጠራሩ Semen እና sperm የሚባሉት ፈሳሾች በወንድ በኩል ዘር ለማፍራት መቻል እና አለመቻል ላይ የሚያስከትሉት አሉታዊ ወይንም አዎንታዊ ተጽእኖ አለ፡፡ ወንዶች የግብረስጋ ግንኙነት በሚያደርጉበት ወቅት sperm የሚባለው የዘር ፈሳሽ የሴትዋን እንቁላል ለማግኘት እና ለመስበር የሚጉዋጉዋዘው Semen በተባለው ፈሳሽ አማካኝነት ነው፡፡
በመጠኑ ወይንም በቁጥር አነስተኛ የሆነ sperm ወይም የዘር ፍሬ በግንኙነት ወቅት የሚፈስ ከሆነ እርግዝናን እውን ለማድረግ አያስችልም። sperm በቁጥር ከ15 ሚሊዮን በታች ከሆነ አነስተኛ ቁጥር ተብሎ ይገለጻል፡፡ ወደ 1/3ኛ የሚሆኑ ጥንዶች ልጅ ላለማግ ኘታቸው ምክንያት የሚሆነው የዘር ፍሬ ቁጥር ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡
በግንኙነት ጊዜ የሚለቀቀው የዘር ፍሬ ወይንም sperm ፍጥነት ዝቅተኛ መሆን የሴትዋን እንቁላል ለማግኘት ሌላው ችግር ነው፡፡
የsperm ተፈጥሮአዊ መዛባት ወይንም ተፈጥሮአዊ ቅርጽን ካልያዘ እንቁላልን ሰብሮ ለዘር ለማብቃት ስለማይችል እንደ አንድ ምክንያት ይቆጠራል፡፡  
የወንድ የዘር ፍሬ sperm በተፈጥሮው ትክክለኛ ቅርጽ የማይኖረው ከሆነ ወይም በፍጥነት መጉዋጉዋዝ ካልቻለ አለዚያም ቁጥሩ ዝቅተኛ ከሆነ እንዲሁም የዘር ፍሬውን ለማጉዋጉዋዝ የሚረዳው Semen የተባለው ፈሳሽ ጤናማ ካልሆነ ልጅ የመውለድ ችግር በወንድየው ምክ ንያት የሚከሰት መሆኑን ማረጋገጥ ያስችላል፡፡
በወንድ በኩል ዘር አልባነት ወይንም መካንነት የሚከሰተው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ ይኸውም አንዱ የፈሳሽ (Sperm) ሲሆን ሌላው የአፈጣጠር ችግር ነው፡፡ በእርግጥ እርግዝናን ለመፍጠር በአንድ ጊዜ አንድ እስፐርም (Sperm ) በቂ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ የወሲብ ግንኙነት ወቅት በሚሊ ሊትር ከሀያ ሚሊየን በታች እስፐርም የሚኖራቸው ወንዶች ለዘር አልባነት ምክንያት ይሆናቸዋል፡፡ የስፐርም መጠኑ ብቻም ሳይሆን የጥራቱም ጉዳይ እንዲሁ አስፈላጊ ነው፡፡ የስፐርም ጥራቱን ምሁራን በፍሰቱ ወይም በእንቅስቃሴው ፍጥነት ይለኩታል፡፡ እስፐርም (Sperm ) እንቅስቃሴው አዝጋሚ ከሆነ ረዥም እርቀት መጉዋዝ ስለማይችል ከሴቷ ብልት አልፎ እንቁላሉ ወደሚገኝበት (fallopian tube) መድረስ አይችልም። ሌላው (Sperm ) ስፐርም አፈጣጠሩ ትክክለኛ ካልሆነም የሴቷን እንቁላል ለመስበር አቅም ያንሰዋል። ወንዶች ለዘር አልባነት ከሚዳረጉበት ምክንያት አንዱ ተፈጥሮአዊ ችግር በብልት አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡ አንድ ወንድ ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ደርሶበት ከነበረ ወይንም ለኢንፌከልሽን (ለመመረዝ) የሚያበቃ ሕመም አጋጥሞት ከነበረ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት በትክክለኛው መንገድ ፈሳሹን እንዳያወጣ ያግዱታል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ወንዶች ልጅ ላለማስወለድ ምክንያት የሚሆኑዋቸው ሌሎች ነገሮችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡      
ልጅ ያለማግኘት ችግር ከአባላዘር በሽታዎች መንስኤነት ይከሰታል፡፡ እነዚህም ለልጅ እጦት እንደዋነኞቹ ምክንያቶች ከሚቆጠሩት ውስጥ ናቸው። እንደ ጎኖሪያ ወይንም ጨብጥ የመሳሰሉት በሽታዎች ሳይታከሙ ከቆዩ ለስነተዋልዶ አካላት በበሽታ መጎዳት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ይሆናሉ፡፡ከቅርብ አመታት ወዲህ በዚህ ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች እንደደረሱበት በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩት ሕመሞች በሁለቱም ማለትም በወንዱም ሆነ በሴቷ ማለት ነው፣ ከወንድየው ለሚወጣው ፈሰሽ ወይም ስፐርም (Allergic) አለመስማማትን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ይህ አለመስማማት ደግሞ የወንድ የዘር ፍሬው እንቁላሉን የመስበር አቅም እዳይኖረው ሊያደርገው ስለሚችል ልጅ የመውለድ ችግር ያጋጥማል፡፡
የወንዶች የዘር ማፍራት መቻል አለመቻልን በተለይ ስንመለከት በተለምዶ ወንዶች ወሲብን መፈጸም እስከቻሉ ድረስ ወላድ እንደሆኑ ይታሰብ ነበር፡፡ ነገር ግን በምርምር የተገኘው ውጤት ልጅ ላለመውለድ ምክንያት ከሚባሉት ውስጥ ወደ ሰላሳ በመቶ የሚሆነው በወንዶች ምክንያት እንደሚመጣ ነው፡፡ ሌላው ወንዶችን ዘርአልባ የሚያደርገው የህክምና ጉዳይ ነው፡፡ በተለያዩ ሕመሞች ምክንያት (ለደም ግፊት፣ ለአልሰር፣ ለአእምሮ መነቃቃት..ወዘተ) በተከታታይነት የሚወሰዱ መድሐኒቶች  ዘርን ሊያመክኑ ይችላሉ፡፡
ወንዶች ልጅ ለማስወለድ ከማያስችሉዋቸው ምክንያቶች መካከል የሚከተሉትም ይገኙበታል፡፡
ሰውነት ላይ የሚታዩ አንዳንድ መመረዞችን ለመከላከል ሲባል የሚወሰዱ አንዳንድ መድሀኒቶች የወንዶችን የዘር ፍሬ ቁጥር ዝቅ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በእርግጥ መድሀኒቱ በሚቋረጥበት ጊዜ ቁጥሩ ከነበረበት ሊመለስ ይችላል፡፡
አንዳንድ ጊዜ በአትሌቲክስ ወይንም ክብደት በማንሳት ሰውነትን ማጎልበት በመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች ምክንያት የሚወሰዱ መድሀኒቶችም ለረጅም ጊዜ ከተጠቀሙዋቸው በተመሳሳይ የዘርፍሬን ቁጥር ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡
ኬሞቴራፒ የተባለው መድሀኒትም ሁሉም ሳይሆን የተወሰኑ አይነቶች በተመሳሳይ መንገድ የዘርፍሬን ቁጥር ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡
ሱስ አስያዥ እጾች ማለትም እንደ ማሪዋና እና ኮኬይን የመሳሰሉት የዘርፍሬን ቁጥር ለመቀነስ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡
እድሜ የወንዶችን ዘር ለማምከን አንዱ ተጠቃሽ ችግር ነው፡፡ የወንዶች ዘር ፍሬ ልጅን ለማግኘት የነበረውን እድል ወንዱ 40/አመት ሲሞላው ጀምሮ እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል፡፡
በኑሮ እና በስራ ምክንያት ሊጋለጡባቸው ከሚችሉ መመረዞች ለምሳሌም ተባይ ማጥፊያ የመሳሰሉት ኬሚካሎች በተመሳሳይ ለወንዶች የዘር ፍሬ መቀነስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡
አልኮሆልን በከፍተኛ ሁኔታ መጠጣት ወንዶችን ልጅ የማፍራት ብቃታቸውን ሊቀንስ ይችላል፡፡ በመካከለኛ ደረጃ መጠጥን መጠጣት ወንዶችን ዘር ለማፍራት አያስችላቸውም የሚል የምርምር ውጤት ያልታየ ቢሆንም ነገር ግን በተፈጥሮአቸው ዝቅተኛ የሆነ የዘር ፈሳሽ ቁጥር ያላቸውን ወንዶች ግን አይጎዳም ማለት አይቻልም፡፡  
ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ክብደት ያላቸው ወንዶች ልጅን ለማፍራት ያላቸውን እድል ሊቀንስባቸው ይችላል፡፡
የአእምሮ ጭንቀት ሌላው ዘር ለማፍራች እንደችግር የሚቆጠር ነው፡፡
ወንዶች ዘር ለማግኘት የማያስችላቸውን ችግር ለመፍታት በሚከተለው መንገድ እርዳታ ማድረግም ይቻላል፡፡  
በወሲብ ግንኙነት ወቅት የብልት መነቃቃትን ችግር ወይንም ጊዜውን ያልጠበቀ ፈሳሽን መልቀቅ የመሳሰሉትን ችግሮች ለማስወገድ በሕክምና ወይንም ምክር አገልግሎት ባህርይን መለወጥ በሚያስችሉ መንገዶች ማሻሻል ይቻላል፡፡
የዘር ፍሬ በትክክለኛው የሚያልፍበት መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች የተዘጋ ከሆነ የዘር ፈሳሹን በመውሰድ በላቦራቶሪ ከእንቁላል ጋር በማገናኘት ልጅ እንዲገኝ ማድረግ ይቻላል፡
Epididymis የተባለ የወንድ የዘር ፍሬ ሊቀመጥበት ወይንም ሊጉዋጉዋዝበት የሚችል መስመር ያለ ሲሆን በዚህ አካል ላይ የመዘጋት ሁኔታ ካለ sperm በትክክለኛው መንገድ ለመጉዋዝ አይችልም፡፡ ስለዚህ ይህንን የተዘጋ መንገድ በመክፈት ችግሩን ማስወገድ ይቻላል፡፡
ማንኛውንም መድሀኒት ሲወስዱ ስለሚኖረው የጎንዮሽ ጉዳት ማወቅ ይጠቅማል፡፡

Read 13058 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 12:30