Saturday, 17 April 2021 11:44

“ለሰው እንተርፋለን እንኳን ለራሳችን…” -(አገራዊ መፈክር) “ሳይተርፋት አበድራ ሳትቀበል ሞተች!” - (አገራዊ ተረት)

Written by 
Rate this item
(6 votes)

     ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዋቂና አንድ አላዋቂ በመንገድ ላይ እየተጓዙ ሳለ አንድ አውራዶሮ አጥር ላይ ሆኖ ሲጮህ ያያሉ፡፡ ይሄኔ አላዋቂው፤
 “ይሄ አውራ ዶሮ እዚህ መሬት ላይ ሲጮህ‘ኮ እመንግስተ - ሰማይም ልክ ይሄንኑ የሚመስል አውራ ዶሮ በዚሁ ሰዓት ይጮሃል” ይላል፡፡
አዋቂው አዋቂ ነውና፤ “እኔ አይመስለኝም” ይላል፡፡
አላዋቂው፤ “ለምን? አስረዳኛ!”
አዋቂው፣ “አየህ እንደ ዶሮ ያለ ልክስክስና ኩሳም ነገር መንግስተ-ሰማይን ያህል ንፁህ ቦታ አይገባም” አለው፡፡
አላዋቂው አላዋቂ ነውና ለምን እሸነፋለሁ ባይ ነው፡፡
 “አይ ዶሮው ሲጮህ አፉን ወደ መንግስተ-ሰማይ፣ ቂጡን ወደ ሲዖል አድርጎ ስለሆነ ምንም ችግር አይኖርም” ይላል፡፡
 አዋቂው፤ አዋቂ ነውና አልለቀቀውም፡፡
#እንደሰማሁት ሲዖል እርጥቡን የሰው ስጋ እንኳን እንደ ጉድ ያነደዋል ነው የሚባለው፡፡ እንዲህ ያለውን የአውራ ዶሮ ላባማ እንዴት አድርጎ ይምረዋል?” ሲል ጠየቀ፡፡ ይሄኔ አላዋቂው፤ ቆጣና ፍጥጥ ብሎ፤ “ዎ!ዎ! እኔ ምን ቸገረኝ ያባቴ ዶሮ አይደለ ቢያንበገብገው?!” አለ፡፡
 * * *
በየግል መድረኩ፤ በየመሸታ ቤቱ፣ በየሻይ ቤቱ፣ በየሬስቶራንቱ ወዘተ… በዕውቀት መከራከር ከቀረ ውሎ አድሯል፡፡ የተማረ የማይከበርበት፣ ያልተማረ ዘራፍ ሲል የሚደመጥበት ሁኔታ እየበረከተ የመጣበት ዘመን ነው፡፡ በመናገርና አውቆ በመናገር መካከል ልዩነቱ ከመከነ ሰንብቷል! አገሩን፤ “እኔ ምን ቸገረኝ ያባቴ ዶሮ አደለች!” ብሎ በምንግዴ የሚያየው ዜጋ በሚያስገርም ሁኔታ እንደ ባክቴሪያ የሚራባበት አየር እየተፈጠረ ነው፡፡ አገርን መሰረት አድርጎ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን አሊያም ባህልን ማየት የተነወረበት ጊዜ እየመጣ ይመስላል፡፡ አለማወቅና ስግብግብነት ሲቀናጁ ምን ዓይነት አደጋ ላይ እየጣሉን እንደሆነ ማየት ተስኖናል፡፡ ካፒታሊዝም፤ እናት - አይምሬ ነው! የገዛ ወላጁን ሳይበላ የማይተኛ ሥርዓት ነው፡፡ ሼክስፒር እንደሚለው፤
“ያባትክን አሟሟት ሰበብ፣
 ለማወቅ ሲፈላ ደምህ
ወዳጁንም ጠላቱንም፣
 አብሮ መጥረግ ነው በቀልህ??”
ሊባል የሚችል ጣጣ ውስጥ እየገባን እንደሆነ ማስተዋል ደግ ነው፡፡ ካፒታሊዝም፤ “ለሰላምታም ለጭብጨባም ቫት የሚከፈልበት መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን” ሊያሰኘን የሚችል ምስጥም ዐይን - አውጣም ስርዓት መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዕውቀት የሚያቀጭጭ ክፉ ባህል ጭበጨባ ነው! አደጋም ነው! ባመኑበትም ባላመኑበትም ማጨብጨብ፣ ባወቁትም ባላወቁትም ማጨብጨብ እርግማን ነው፡፡ ምክን (Reason) የማይገዛው ማህበረሰብ፣ ለገደል ቅርብ ነው ይላሉ ጸሀፍት፡፡ “እባካችሁ ክቡር እምክቡራን የተከበሩ፣ አቶ ወይም ወ/ሮ እገሌን ወደ መድረኩ ጋብዙልኝ” ይላል የመድረክ መሪው፡፡ ከዚያ ጭብጨባ ነው፡ ፡ ቸብ! ቸብ! ቸብ! ትንሽ ቆይቶ፤ “እባካችሁ የተከበሩ ክቡር እምክቡራን አቶ ወይም ወይዘሮ እገሌን ወደ ቦታቸው ሸኙልኝ!” አሁንም ቸብ!...ቸብ!...ቸብ!... ይቀጥላል፡፡ የጭብጨባ ባህል! የፓርቲ አባል ያጨበጭባል፡፡ የድርጅት አባል ያጨበጭባል፡፡ የጎሣ አባል ያጨበጭባል፡፡ ጓደኛና ቲፎዞ ያጨበጭባል፡፡ የተማረው ያጨበጭባል! ያልተማረው ያጨበጭባል! አዋቂው ያጨበጭባል! አላዋቂው ያጨበጭባል! ሃይማኖተኛው ያጨበጭባል! ሃይማኖት - አልባው ያጨበጭባል! የኪነ-ጥበቡ ሰው እያጨበጨበ ጭብጨባ ይቀላውጣል!... ከዚህ የጭብጨባ ባህል ማን ይገላግለን ይሆን? ለጭብጨባም የአየር ሰዓት የሚጠየቅበት ወቅት እየመጣ ነው፡፡ ከማቴሪያል ሙስና ወደ ህሊና ሙስና እየተሸጋገርን ይመስላል! የድንቁርና ሙስናና የዕውቅና ሙስና ምን ያህል እንደሚተጋገዙ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ አውራ - ዶሮው መጮሁን ይቀጥላል፡፡ የውሻና ግመሎቹ ነገር (The dog barks but the caravan goes) አብቅቶ፤ ግመሎቹም ውሻዎቹም አውራ - ዶሮውን እያዳመጡ መከራከር የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡ አውራ ዶሮ የጮኸውን ያህል ክርክሩም ይጮሃል፡፡ ያገራችን ነገረ በተመለደና ባልተለወጠ ነገረ - ሥራ መጯጯህ መሆኑ ያሳዝናል! ልማዳዊ አካሄዳችን አልለወጥ የሚለው ለውጥ ስለሌለ ይሆን? ሁሉ ነገር የልማድ፣ የወግ፣ የወረት (የfashion) ተገዢ የሆነ መምሰሉ ይገርማል፡፡ የእገሌ ራዕይ፣ ራዕይ፣ ራዕይ … እንደጀመርን … እንደጀመርን … (አንዴ ከገባንበት ስሜት ዓይነት ጭምር)… እንዳጋመስን … እንዳጋመስን … ስንጨርስስ? … እንደጨረስን… እንጨርሰዋለን … እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ከዘፈን ወደ መፈክር መሄድ፣ ከዘፈን ወደ ዘፈን ከመሄድ የተሻለ ነው ወይ? የሚለውን ለማረጋገጥ መሞከር ብልህነት ነው፡፡
 የእኛው ፀሐፌ ተውኔት፣ ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን የሚለንን መስማት ደግ ነው፡- “አንድ የፍየል ሙክት ቆዳ እያለፋ ስልቻ የሚያወጣና የሚያዜም ሰራተኛ ነበር፡፡ ደግሞ ጆሮ ደግፍ ይዞታል፡፡ እና ቆዳ ሲያለፋ በረገጠ ቁጥር ያመው ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ዘፈኑ ይበላሽበትና ወደ ለቅሶ ይለወጥበታል። ወደ ህመም ይለወጥበታል፡፡ ግን ህመሙን በዘፈኑ ማስታመም እንጂ ከእዚያ እቤት የሚሰማውን ቻቻታ መስማት አይፈልግም፡፡ እዚያማ የሙክቱ ሥጋ ይበላል፡፡ ሰዎች በደስታ ያሳልፋሉ፡፡ እሱ ግን እዚህ ቆዳ እያለፋ ይሰቃያል” ያው ያንዱ ደስታ ላንዱ ዋይታ ነው፡፡ “ህመምን በዘፈን ማስታመም” አንዱ በሽታችን ነው፡፡ ፖለቲካችን የዚህ በሽታ ልክፍት እንዳለበት ልብ ካላልን አንድንም! የሀገራችን ኢኮኖሚ፤ እሱን ተከትሎም የኑሮ ደረጃውን፤ ማመዛዘን ግራ አጋቢ ነው፡፡ በዚህ ፋሲካ ወይም በሌላ ማናቸውም ክብረ በዓል የሰውን አኗኗር ለማሰብ ብንሞክር፤ …ከዓመታት በፊት ዶሮ እንዴትና በምን ዋጋ ይበላ እንደነበር የሚተርክ ሰው ይገኛል፡፡ ዛሬ አይበላም፤ “አይ ኑሮ” ይላል፡፡ ሌላው ዶሮ አርዷል። በግም አርዷል፡፡ “የቅርጫውን ዋጋ አልቻልነውም‘ኮ፤ ይሄ የኑሮ ውድነት ተጫወተብን! አይ ኑሮ!” ይላል፡፡ የመጨረሻው ዶሮም አለው፡፡ በግም አርዷል፡፡ “በሬው ግን ከቄራ ይገዛ ወይስ ተነድቶ ከገጠር ይምጣ? ቀረጡ፣ ማስነጃው ሰማይ ወጣ እኮ!” “አይ ኑሮ!” እያለ ያማርራል፡፡ በዚህ ኢኮኖሚ ጥላ ሥር ፖለቲከኛው የራሱ ቋንቋ ነው ያለው፡፡ የሕግ የበላይነት ተከብሮ ቢሆን  ኖሮ… የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ቢሆን ኖሮ … በቂ ተቋማት ተዋቅረው ቢሆን  ኖሮ… ሰብዓዊ መብት ቢከበር ኖሮ… ዲሞክራሲ ዕውነት ቢሆን ኖሮ… በቂ ኮንዶምኒየም ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ… የፕሬስ ችግር ቢፈታ ኖሮ…”
አይ ኑሮ! አገራችን ከምትችለው በላይ ኑሮና ኗሪ ተሸክማ የምትጓዝ ናት፡፡ ይሄን ሁሉ ኑሮ፣ ድህነትና ሃሳዊ ጥጋብ መፍቻ ቁልፉ፣ የህዳሴው ግድብ ከነዙሪያ ገባ ዲፕሎማሲው ነው… ለማለት ለጤናማ ኢኮኖሚስትም ለጤናማ ሀገራዊ ፖለቲከኛም ያስቸግራል፡፡ አንድ ያላት ጥርስ በዘነዘና ትነቀስ አይሆንም፡፡ ዶሮ ብታልም ጥሬዋንም አይሠራም፡፡ ዘርፈ - ብዙና መረበ - ብዙ መፍትሔ እናገኝ ዘንድ ዘርፈ - ብዙ ልብ ይስጠን፡፡
“ለሰው እንተርፋለን እንኳን ለራሳችን” የሚለው የዱሮ መፈክር፣ ትዝ ይለናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን እርስ በርስ በመተሳሰቡ፣ ለወገን ፈጥኖ በመድረሱ፣ወዘተ-- የማንታማ ልንሆን ይገባል፡፡ ሁሌ እንግዳ ተቀባይ ነን እንደምንል ሁሉ፣ ሁሌ ለጋሥ ነን ማለትን እንፈልጋለን፤ ቅንነታችን የተባረከ ይሁን! በተጨባጭና ከልብ እንግዳ ተቀባይ፣ በተጨባጭና ከልብ ያለን የተረፈንና ለሌላ የምንለግስ ልንሆን ይገባል፡ ፡ በመብራቱም፣ በውሃውም፣ በቡናውም፣ በጤፉም፣ በበጉም በከብቱም፣ በዲሞክራሲውም፣በሰለጠነ የፖለቲካ ባህሉም፣በነጻና ፍትሃዊ ምርጫውም ወዘተ-- የዚህ ዕውነታ ዕሙን ሊሆን ይገባል፡፡ አለበለዚያ “ሳይተርፋት አበድራ ሳትቀበል ሞተች” የሚለው ተረት ዕሙን ይሆናል!!



Read 13149 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 11:57