Tuesday, 13 April 2021 00:00

አይኤምኤፍ የአለማችን ኢኮኖሚ ያገግማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ኬንያውያን አይኤምኤፍ ገንዘብ እንዳያበድራቸው እየጠየቁ ነው

             አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ፣ በኮሮና ሳቢያ ክፉኛ ተጎድቶ የነበረው የአለማችን ኢኮኖሚ በተያዘው የፈረንጆች አመት 2021 በተሻለ ሁኔታ ያገግማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት ያስታወቀ ሲሆን፣ የአለም ኢኮኖሚ በአመቱ በአማካይ የ6 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ አመልክቷል፡፡
ባለፈው አመት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የኔጌቲቭ 3.5 በመቶ ማሽቆልቆል አሳይቶ የነበረው የአለማችን ኢኮኖሚ፤ በቀጣዩ የፈረንጆች አመት በማካይ የ4.4 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
ያደጉት የአለማችን አገራት በዘንድሮው አመት የ5.1 በመቶ አማካይ እድገት ያስመዘግባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተነበየው ተቋሙ፤ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በአንጻሩ የ6.7 በመቶ እድገት ያስመዘግባሉ ተብሎ እንደሚገመት አክሎ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በብድር የምናገኘው ገንዘብ ለድሃው ህዝብ የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም፤ ለባለስልጣናት ኪስ መሙያና ለሙስና ሲሳይ መሆን የለበትም ያሉ ኬንያውያን፤አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ለአገራቸው የገንዘብ ብድር እንዳይሰጥ አቤቱታ ለማቅረብ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ መጀመራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኬንያውያኑ በድረገጽ አማካይነት #ለኬንያ ማበደር ይቁም; በሚል መርህ በጀመሩት ዘመቻ ፊርማ እያሰባሰቡ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ ዘመቻው የተጀመረው ተቋሙ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለኢኮኖሚ ማነቃቂያ የሚውል 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለኬንያ ለማበደር መወሰኑን ማስታወቁን ተከትሎ እንደሆነ ገልጧል፡፡

Read 7059 times