Monday, 12 April 2021 00:00

የ533 ሚ. የፌስቡክ ደንበኞች መረጃ ተዘርፎ መሰራጨቱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

          የድረገጽ መረጃ መንታፊዎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የ106 አገራት ዜግነት ያላቸው የ533 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚ ደንበኞችን የግል ሚስጥራዊ መረጃዎች በመዝረፍ በይፋ ማሰራጨታቸውንና ይህም ተጠቃሚዎችን ለባሰ ጥቃት ይዳርጋል ተብሎ መሰጋቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
በድረገጾች በኩል ባለፈው ቅዳሜ በነጻ የተሰራጩት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃዎች የተጠቃሚዎቹን ስሞች፣ የስልክ ቁጥሮች፣ የኢሜይል አድራሻዎችና ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን ያካተቱ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ የስልክ እንዲሁም የኢ-ሜይል አድራሻዎችን ጨምሮ ሌሎች ግለሰባዊ ሚስጥሮችንም ያካተቱ ናቸው ተብሏል፡፡
መረጃዎቻቸው በድረገጽ መንታፊዎች ተዘርፈው ይፋ ከተደረጉባቸው የፌስቡክ ደንበኞች መካከል 32 ሚሊዮን ያህሉ በአሜሪካ፣ 11 ሚሊዮን የሚሆኑት በብሪታኒያ፣ 6 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በህንድ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፤ ፌስቡክ በበኩሉ መረጃው ተዘርፎ ወጣ መባሉን እንዳስተባበለ አመልክቷል፡፡


Read 10149 times