Sunday, 11 April 2021 00:00

በቢሊየነሮች ብዛት አሜሪካና ቤጂንግ ቀዳሚነቱን ይዘዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     ጄፍ ቤዞስ ለ4ኛ ተከታታይ አመት ቁጥር 1 ቢሊየነር ሆነዋል


            ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የ2021 የአለማችን ቢሊየነሮችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ላለፉት ሶስት አመታት የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ሆነው የዘለቁት የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ ዘንድሮም በ177 ቢሊዮን ዶላር ሃብት በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸው ተነግሯል፡፡
በርካታ ቢሊየነሮች የሚኖሩባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር አሜሪካ ናት ያለው ፎርብስ፤በአገሪቱ 724 ቢሊየነሮች እንደሚገኙ የገለጸ ሲሆን ቻይና በ698 ቢሊየነሮች የሁለተኛነትን ደረጃ መያዟን፣ ህንድ ደግሞ በ140 ቢሊየነሮች ሶስተኛነትን መያዟን አብራርቷል፡፡
ከአለማችን ከተሞች በአንጻሩ የ100 ቢሊየነሮች መገኛ የሆነቺው የቻይናዋ ቤጂንግ በአንደኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ባለፉት ሰባት አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረቺው የአሜሪካዋ ኒው ዮርክ በ99 ቢሊየነሮች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ብላለች፡፡
በአመቱ ከፍተኛውን የ126.4 ቢሊዮን ዶላር የሃብት ጭማሬ ያስመዘገቡትና አጠቃላይ ሃብታቸው 151 ቢሊዮን ዶላር የደረሰው ሌላኛው አሜሪካዊ ኤለን መስክ፣ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፤ ፈረንሳዊው ቢሊየነር በርናንድ አርኖልት በ150 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ሶስተኛ ደረጃን መያዛቸው ታውቋል፡፡
የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ በ124 ቢሊዮን ዶላር፣ የፌስቡኩ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዘከርበርግ በ97 ቢሊዮን ዶላር፣ ዋረን ቡፌት በ96 ቢሊዮን ዶላር፣ ላሪ ኤሊሰን በ93 ቢሊዮን ዶላር፣ ላሪ ፔጅ በ91.5 ቢሊዮን ዶላር፣ ሰርጌይ ብሪን በ89 ቢሊዮን ዶላር እና ሙኬሽ አምባኒ በ84.5 ቢሊዮን ዶላር ሃብት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውም ተነግሯል፡፡
የአለማችን ባለጸጎች በአመቱ በታሪክ ከፍተኛውን የ5 ትሪሊዮን ዶላር የሃብት ጭማሬ ማስመዝገባቸውን የጠቆመው የፎርብስ መጽሄት ሪፖርት፣ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ያፈሩ የአለማችን ቢሊየነሮች ቁጥርም አምና ከነበረበት 1 ዘንድሮ ወደ 4 ከፍ ማለቱን አመልክቷል፡፡
ፎርብስ ለ35ኛ ጊዜ ባወጣው አመታዊ የቢሊየነሮች ሪፖርት እንዳለው፣ የአለማችን ቢሊየነሮች ቁጥር አምና ከነበረበት በ660 በመጨመር ዘንድሮ 2ሺህ 755 የደረሰ ሲሆን፣ እነዚህ ቢሊየነሮች በድምሩ 13.1 ትሪሊዮን ዶላር ሃብት እንዳላቸው ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በአመቱ በአለማችን 493 አዳዲስ ቢሊየነሮች መፈጠራቸውንና ይህን ያህል ብዛት ያለው ቢሊየነር በአንድ አመት ውስጥ ተፈጥሮ እንደማያውቅ የጠቆመው ፎርብስ፣ አምና በዝርዝሩ ውስጥ ተካትተው የነበሩ 250 ባለጸጎች በአንጻሩ ሃብታቸው በመቀነሱ ከዝርዝሩ መውጣታቸውን አመልክቷል፡፡

Read 4220 times