Saturday, 10 April 2021 13:32

"የሚመጣው አልፏል"

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   “--ይቅርታ ንጉሥ ሆይ፤የንጉሥ ግድያ እኮ ህይወት ነው፡፡ በንጉስ እጅ መሞት ታላቅ ዕድል ነው፡፡ የሕዝቡም ጥያቄ “ሞታችን በንጉሥ እጅ መኾን ሲገባው ለምን ዐማፂያኑ ይገድሉናል? እኛ፣ ንጉሥ መቼ መጥተው እንደ በግ ይባርኩናል? በጉጉት የምንጠብቀው ጥይታቸው መች ይገድለናል? በንጉሥ እጅ የመሞት ዕጣ መች ይደርሰናል? እያልን በተስፋ ስንጠብቅ እንዴት በተረገሙ ዐማፂያን ጥይት ሕይወታችን ይጠፋል?--"


             -- ንጉሡ  በቤተ መንግስቱ የአትክልት ስፍራ ውስጥ ከአማካሪው ጋር እየተንሸራሸረ እጁን የአማካሪው ትከሻ ላይ አድርጎ፡-…. “ሕዝብ ኹሌም ተስፈኛ ነው፤ ለዚኽም ነው ተስፋ የሚቆርጠው፡፡ ተስፋ ላለመቁረጥ ተስፋ አለማድረግ ነው፡፡”
“ንጉሥ ሆይ፤ ሕዝባችን እኮ አማኝ ነው። አማኝ ደግሞ ተስፋ አይቆርጥም” ፈገግ ብሏል፤ አማካሪው፡፡
“የሚገርመኝም እሱ ነው፡፡ ሰው እንዴት በሚያጠፋውና በሚገድለው አምላክ ተስፋ ያደርጋል? ይደንቃል! ተስፋቸውን እየነጠቃቸው እያዩ ተስፋ ያደርጉታል፡፡”
“ሕዝቡማ፣ የፈጠረን ቢገድለን ትክክል ነው ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡” በአማካሪው ምላሽ ንጉሡ ሳቀ፡፡
“እንዲያውም የፈጠራቸው ሲገድላቸው ነበር ተስፋ መቁረጥ የነበረባቸው፡፡ ይገርማል! የፈጠራቸው ያልራራላቸውን እኔ እንድራራላቸው ይሻሉ፡፡ ጨካኝ እንደኾንኹም አድርገው ያምናሉ፡፡ በእውኑ እኔ ከአምላክ ይልቅ እጨክናለኹኝ? እስቲ ክቡር አማካሪዬ ሆይ፣ ምክርኽን ወዲህ በለኝ፡፡”
“ታላቁ ንጉሥ ሆይ፤ ከሕዝብ ይልቅ ንጉሥ ለፈጣሪ ቅርብ መኾኑን ፈጣሪም ያውቃል። ንጉሥን የሚያነግሰው ፈጣሪ  በመኾኑ የልቡን አሳብ ያጫውተዋል፡፡ ንጉሥ ተጠሪነቱም ለፈጣሪ በመኾኑ ሕዝብ የንጉሥ ባሪያ ነው፡፡ ንጉሥ…” ንጉሡ ያቋርጠዋል፡፡
“አማካሪ ሆይ፤እኔው አንተኑ መምከር ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ እኔ ራሴን በራሴ የቀባኹ ንጉስ ነኝ እንጂ በፈጣሪ የተቀባኁ አይደለኹም፡፡ በአምላክ የተቀባኹ እንደኾንኹ ሕዝቡ የሚያምን ከሆነ ግን ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛት አለበት፡፡”
#ዐማፂያኑ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየጋቱት እንጂ ሕዝቡማ ንጉሡን እንደ ፈጣሪ የሚያይ ነው፡፡;
“ይህን ሕዝብ እኔ አልፈጠርኹትም፤ እንደ ፈጣሪ እንዲያየኝ አልሻም። እኔ የፈጠርኹትን አልገድልም፡፡ የምገድላቸውም ስላልፈጠርኋቸው ነው፡፡”
“ንጉሥ ሆይ፤ በአንተ ተጠቅሞ የሚገድላቸው ፈጣሪ እንጂ አንተ እኮ አይደለኽም፡፡”
“ስማ ሥራዬን ከንቱ እያደረግኽብኝ እንደኾነ ታውቃለኽ? በኃይሌና በጥበቤ የማደርገውን ኹሉ ለፈጣሪ እየሰጠኽብኝ ነው፡፡”
“ይቅርታ ንጉሥ ሆይ፤የንጉሥ ግድያ እኮ ህይወት ነው፡፡ በንጉስ እጅ መሞት ታላቅ ዕድል ነው፡፡ የሕዝቡም ጥያቄ “ሞታችን በንጉሥ እጅ መኾን ሲገባው ለምን ዐማፂያኑ ይገድሉናል? እኛ፣ ንጉሥ መቼ መጥተው እንደ በግ ይባርኩናል? በጉጉት የምንጠብቀው ጥይታቸው መች ይገድለናል?
በንጉሥ እጅ የመሞት ዕጣ መች ይደርሰናል? እያልን በተስፋ ስንጠብቅ እንዴት በተረገሙ ዐማፂያን ጥይት ሕይወታችን ይጠፋል? እንዴት በሰይጣን ቁራጮች እንሞታለን? ልጆቻችን የንጉሥ ሰይፍ ሊበላን በደጅ ነው ብለው በደስታ እየቦረቁ፣ በተስፋ እየጠበቁ ሳለ፣ እንዴት በአረመኔዎች እጅ እንወድቃለን?  ንጉሡ ይድረሱልንና ህይወታችንን ይረከቡን” እያለ ነው፡፡”
"አየኽ፣ ሕዝብ እንዲኽ ተስፋ ሲያደርግ ደስ ይላል፡፡ እመነኝ ተስፋቸው ይፈፀማል፤ እየተፈፀመም ነው፡፡” ንጉሡ እጆቹን ትከሻው ላይ እንደ ማኅተም አኖረ፡፡---
(ከደራሲ ዳዊት ጸጋዬ "የሚመጣው አልፏል" የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ልቦለድ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 2566 times