Saturday, 10 April 2021 12:31

የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ከትላንት በስቲያ ተጀምሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

                 7 ጋዜጦች፣ 21 ሬዲዮና 29 ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተመድበዋል
                       

 

   ከሁለት ወራት በኋላ ለሚካሄደው ሃገራዊ ምርጫ 57 የመገናኛ  ብዙኃን የ46 የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምረጡኝ ቅስቀሳ ያስተናግዳሉ።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ተወዳዳሪ  ፓርቲዎችና ብሮድካስት ባለስልጣን በጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመገናኛ ብዙሀን አጠቃቀም ድልድልን በእጣ የለዩ ሲሆን የፓርቲዎችን መልዕክት እንዲያደርሱም ሰባት ጋዜጦችን ጨምሮ 57 መገናኛ ብዙሃን ተመርጠዋል፡፡
ከመጋት 30 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነውና ግንቦት 23 ቀን 2013 በሚቋጨው የፓርቲዎች የሚዲያ  የምረጡኝ ዘመቻ፤ መገናኛ ብዙኃን ባቋቋሙት የምርጫ ጉዳዮች ዴስክ በኩል ከፓርቲዎች የሚመጡላቸውን መልዕክቶች ገምግመው እንዲተላለፉ ወይም እንዲታተሙ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች መልዕክቶቹን ሲያቀርቡ ብሔርን ከብሔር፣ሃይማኖትን ከሃይማኖት ከሚያጋጩ ቃላትና ንግግሮች እንዲሁም የአመፅና ቀውስ ዲስኩርና መልዕክቶችን እንዳያቀርቡ ሃላፊነት ያለባቸው ሲሆን መገናኛ ብዙሀንም እነዚህን መልዕክቶች በጥንቃቄ መርምረው የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ ችግሮች ካጋጠሙ ፓርቲዎች ከቦርዱ ጋር እየመከሩ መፍትሔ የሚያፈላልጉ ሲሆን መገናኛ ብዙሀኑን ደግሞ ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር እየመከሩ መፍትሔ ያበጃሉ ተብሏል፡፡
በዘንድሮ ምርጫ 46 የፖለቲካ ድርጅቶች የሚፎካከሩ ሲሆን 57 መገናኛ ብዙኃን ማለትም 7 ጋዜጦች፣ 21 ሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲሁም 29 ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የፖርቲዎች የቅስቀሳ ፕሮግራም ያሳልጣሉ ተብሏል፡፡ በዚሁ መሰረት ከትላንት በስቲያ ሃሙስ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን በመገናኛ ብዙኃ ማስተላለፍ ጀምረዋል፡፡

Read 10181 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 11:17