ቢዮንሴ ኖውልስ በአልበሞቿ ሽያጭ፤ በማስታወቂያ እና የንግድ ገቢዎቿ ዘንድሮ 40 ሚሊዮን ዶላር በመስራት ከፍተኛ ገቢ ለቤተሰቧ ማስገባቷን የገለፀው ፎርብስ፤ ጄይዚ በበኩሉ “ዎች ዘ ትሮ”ን በተባለ አልበሙ ሽያጭ እና የኮንሰርት ስራዎች፤ ሮክ ኔሽን በተባለ የሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያው እንዲሁም የቤተሰቡ ሃብት ከሆኑ የምሽት ክለብ እና የኮስሞቲክስ ንግዶች 38 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስፍሯል፡፡
በተያያዘ ዜና ቢዮንሴ እና ጄይ ዚ በጣም ቅንጡ ህይወት የሚመሩና ለበጎ አድራጎት ግዜ የሌላቸው ሃብታም ዝነኞች መሆናቸው እያስተቻቸው ቢሆንም ጥንዶቹ ትችቱን አልተቀበሉትም፡፡ ሃሪ ቤላፎንቴ የተባለ ታዋቂ የሙዚቃ ባለሙያና ድምፃዊ የእነጄይዚ ቤተሰብ “ለበጎ አድራጎት እምብዛም ግድ የሌለው ነው” በሚል መተቸቱን ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር ገልጿል፡፡ የዴይሊ ወር በፊት የአባቶች ቀን ሲከበር ቢዮንሴ 40 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጀት ገዝታ ለ ጄይ ዚ በስጦታ ማበርከቷን የጠቆመው ዴይሊ ሜል፤ ከሳምንት በፊት በኒውዮርክ የሚገኝ ቪላ ለአንድ ወር 400ሺ ዶላር ከፍለው መከራየታቸውን አውስቷል፡፡ የቢዮንሴ ቤተሰብ ለበጎ አድራጎት እጁ አይፈታም የሚሉ ትችቶችን በመቃወም መግለጫ የሰጠችው አርቲስቷ፤ ቤተሰቡ ከሰባት አመታት በፊት ባቋቋመው “ሽዋን ካርተር ፋውንዴሽን” አማካኝነት ከፍተኛ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልፃለች፡፡ ፋውንዴሽኑ በየአመቱ 1.3 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ በመቶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 730 ወጣቶችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ቢዮንሴ ተናግራለች፡፡