Saturday, 03 April 2021 18:24

አዲስ የ15 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ በኬሮይድ ተመሰረተ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

‹ስፖርት ጤናማ ንቁ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ፤የሰው ልጅ በሚኖርበት፤ በሚሰራበት እና በሚማርበት አካባቢ     እንደፍላጎቱ እና ዝንባሌው በተለያዩስፖርታዊ ጨዋታዎች ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል

         ኬሮይድ የልማትና ስፖርትና  ማህበር በ15 ኪሜ አዲስ የጎዳና ላይ ሩጫ የመሰረተ ሲሆን ግንቦት 8  ላይ በወልቂጤ ከተማ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
‹‹ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ህዝብ›› በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ  በሁለቱም ፆታዎች ከ20 በላይ ክለቦችን የወከሉ ከ300 በላይ አትሌቶች የሚወዳደሩ ሲሆን በተጨማሪ 10ሺ ስፖርተኞችን የሚያሳትፍ ይሆናል፡፡
የኬሮይድ የልማትና ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት የቀድሞ አትሌት እና አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ሰሞኑን በግራንድ ኤሊያና ሆቴል በተሰጠው መግለጫ ላይ ‹‹ስፖርት ጤናማ ንቁ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ፤ የሰው ልጅ በሚኖርበት፤ በሚሰራበት እና በሚማርበት አካባቢ እንደፍላጎቱ እና ዝንባሌው በተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል›› የሚለውን መልዕክት በማስተላለፍ የ15 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫውን በወልቂጤ ከተማ የተዘጋጀው ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ፤ ከጉራጌ ልማት ማህበር እና ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር በመተባበር ሲሆን፤ ስፖርት ሰላምና አንድነትን ስለሚገልፅ ውድድራችንም ይህን የሚያስተዋውቅ ነው ብሏል፡፡ ንብ ባንክ፤ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ስንቅ፤ ደሳለኝ ሆቴልና ፍቅር ውሀ የስፖንሰርሺፕ ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን በውድድሩ ምስረታ ላይ ታዋቂ አትሌቶች ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
በወልቂጤ ከተማ የጎዳና ላይ ሩጫውን ለማዘጋጀት ከጉራጌ ልማት ማህበር ጋር  ባለፉት ዓመታት ‹‹አረንጓዴ ልማት›› በሚል የተካሄዱ እንቅስቃሴዎች መነሻ እንደሆኑ የገለፀው የቀድሞው አትሌትና አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ  የኬሮይድ  እቅድ ተመሳሳይ ውድድሮችን በወልቂጤ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ማዘጋጀትና ውድድሮችንም ማብዛት ስለሚያስፈልግ፤  ከሌሎች የልማት ማህበሮች እና ከአዲስ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር ተባብረው መስራታችን የሚቀጥል ነው፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ተወካይ የነበሩት አብዱልአዚዝ ሙስጠፋ ሃሰን ሲናገሩ ዩኒቨርስቲው በዞኑ የሚገኝ ግዙፍ ተቋም እንደመሆኑ በአካባቢው የሚካሄዱ ትልልቅ ዝግጅቶችን ያበረታታል ብለው ስፖርት ለማህበረሰቡ ትልቅ ሚና ስለሚኖረው በውድድሮች ዝግጅት እና በሌሎች መሰል ድጋፎች በሙሉ ፍቃደኝነት እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ኬሮይድ የልማትና ስፖርት ማህበር ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ እጩ ኦሎምፒያኖች፤ ታላላቅ አትሌቶች፤ ታዋቂ አሰልጣኞች እና የቀድሞ ኦሎምፒያኖች ተገኝተዋል፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት በዓለም አትሌቲክስ በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘግቡ አትሌቶች ከጉረራጌ ዞንና ከአጎራባች ከተሞች እየወጡ ናቸው፡፡ ፈርቀዳጁ አትሌት ተሰማ አብሽሮ ቢሆንም በግማሽ ማራቶንና ማራቶን ውድድሮች የሚታወቀው ወንድሙ አየለ አብሽሮ፤ በዳይመንድ ሊግ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ያሉት አትሌቶች ሰለሞን ባረጋ፤ ጥላሁን ሃይሌ፤ በህንድ የጎዳና ውድድሮች የታወቀው አንዱአምላክ በልሁ፤ አትሌት ኮከብ ተስፋዬ እና በዓለም ሻምፒዮና በኦሎምፒክ የረጅም ርቀት ውድድሮች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ሙክታር እድሪስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
‹‹የሩጫ ውድድር ለማዘጋጀት የቆየ እቅድ ነበረን፡፡ በኮቪድ 19 ምክንያት ተሸጋሽጎ ነው የቆየው፡፡ አሁን የጎዳና ላይ ሩጫው ሊጀመር ጫፍ መድረሱ ያስደስታል፡፡›› በማለት አስተያየት የሰጠው ማራቶኒስቱ አየለ አብሽሮ ታዋቂ አትሌቶች ስፖርቱን ለማስተዋወቅ ፍላጎት እንዳላቸው በተለያዩ ክልለሎች ተመሳሳይ ውድድሮችን ለማስፋፋት እንደሚፈልጉ ሲጠቁም
‹‹በእኛ ጊዜ ስለስፖርት ብዙ እውቀት አልነበረም፡፡ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬት ያገኙ ስፖርተኞች በብዛት እየወጡ ናቸው፡፡ እቅዳችን በምናዘጋጃቸው ውድድሮች ሌሎችም አትሌቶች መውጣት እንዲችሉ ነው››  ብሏል፡፡
‹‹የውድድሩ ሚና ስፖርቱን ማስተዋወቅና በየክልሉ ለሚገኙ ታዳጊና ወጣት አትሌቶች የውድድር እድል መፍጠር ነው፤ በየውድድሮቹ ላይ ማናጀሮች እየተገኙ ብቁ ታዳጊዎችና ወጣቶችን እንዲመለከቱ  እንፈልጋለን። ይህም ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ይጠቅማል፡፡›› ሲል የተናገረው ደግመ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ሲሆን፤ አትሌት ጥላሁን ሃይሌ በበኩሉ ‹‹ውድድሩ በወልቂጤ ከተማ ቢጀመርም በሩጫ የሚታወቅ አገር ላይ ብዙ ውድድሮች ያስፈልጋሉ። አትሌቶች በየውድድሮቹ የምናይባቸው አጋጣሚዎች መፈጠር አለባቸው፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡
በጉራጌ ዞን ዘቢደር የተባለ አንድ ክለብ ብቻ በክልል ደረጃ እየሰራ መቆየቱን የጠቀሰው አትሌት ሰለሞን ባረጋ  የኦሎምፒክ እጩ  አትሌቶች ከዚሁ ክለብ መገኘታቸው የአካባቢውን አቅም  ስለሚያመለክት ከውድድሮች ባሻገር በርካታ  ክለቦችም እንዲቋቋሙ መስራት ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ታዋቂው ኦሎምፒያን አሰፋ መዝገቡ በመላው ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ውድድሮች መዘጋጀት እንዳለባቸው አስተያየቱን ሲሰጥ ታዋቂው አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሸቦ ደግሞ በሌሎች አገራት ታዋቂ የቀድሞ አትሌቶች ከ20 በላይ ውድድሮች በየዓመቱ እንደሚዘጋጁ ገልፀው ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በፌደሬሽኑ እና በታላቁ ሩጫ ከሚካሄዱት  3 እና 4 ውድድሮች በላይ እንዲኖሩን መሰራት አለበት ብለዋል፡፡ እነ ተሰማ አብሽሮ የጎዳና ላይ ሩጫ የማካሄድን ሃሳብ አመንጭተው የመጀመርያውን ውድድር ወልቂጤ ላይ በማዘጋጀታውም የተሰማቸውን ኩራት ገልፀዋል፡፡   
 ‹‹በርካታ አትሌቶች ከአርሲ ጭላሎ መውጣታቸው ይታወቃል፡፡ በዚያ ከተማ በአንድ ቤተሰብ ሁለ አትሌቶች ይገኘሉ፡፡  ይህንንም በወልቂጤ  ማስፋፋት ይቻላል፡፡ ከ10 እና 20 ዓመታት በኋላ በከተማዋ  ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚያስጠሩ አትሌቶችን ማፍራት ይቻላል፡፡›› በማለትም ዋና አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሽቦ ተናግረዋል።
ኬሮይድ ማለት ትርጉሙ ሰላም ለአገር ይሁን፤ ስለ ሰላም እናብስር መሆኑ በተብራራበት መግለጫ ላይ የልማትና የስፖርት ማህበሩ አትሌቶችን ለመርዳት፤ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ታስቦ እንደተቋቋመ ህጋዊ ፈቃድ እና እውቅና አግኝቶ የሚንቀሳቀስ መሆኑንም ተገልጿል፡፡
ግንቦት ስምንት ላይ የሚካሄደው የ15 ኪሜትር የሚካሄደውን የጎዳና ላይ ሩጫው ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፊት ለፊት በሚገኝ ሰፊ ሜዳማ ስፍራ ላይ  እንደሚካሄድ ያስታወቁት አዘጋጆቹ አስፈላጊውን የኮቪድ 19 ጥንቃቄ እና ፕሮቶኮል በመጠበቅ እንደሚሰሩ፤ በዋናው ውድድር ለሚሳተፉ አትሌቶች አስፈላጊው ምርመራ በአዲስ አበባ እንደሚያከናውኑና እስከ ውድድሩ መካሄጃ ቀን በተለያዩ እቅዶች እንደሚንቀሳቀሱም አብራርተዋል፡፡
ኬሮይድ ኢትዮጵያ የልማትና ስፖርትና ማህበርን ካቋቋሙት 20 መስራቾች  መካከል ብዙዎቹ ታዋቂ አትሌቶች መሆናቸው በአገራችን የተለያዩ የክልል ከተሞች ውድድሮች መፈጠር እንዳለባቸው የሚያመለክት ነው፡፡ ኬሮይድ ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ፤ ከጉራጌ ልማት ማህበር፤ ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር ተባብሮ በመስራት በወልቂጤ ከሚያደርገው የመጀመርያው የጎዳና ሩጫ  በኋላ በአዳብና በስልጤና በቡታጅራ ሌሎች ውድድሮችን እንደሚያዘጋጅም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1249 times