Saturday, 27 March 2021 12:43

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከወለድ ነፃ ማይክሮ ፋይናንስ ሊመሰረት ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የተባለለት “ቢላል ከወለድ ነፃ ማይክሮፋይናንስ አክስዮን ማህበር ሊመሰረት ነው። በምስረታ ላይ የሚገኘው ይሄው ማይክሮ ፋይናንስ ለመቋቋም የሚያስችለውን የአክስዮን መሸጫ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አግኝቶ ወደ ስራ ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አደራጆቹ ትላንት ከሰዓት በኋላ ግዮን ሆቴል በሚገኘው ግሮቭ ጋርደን ወክ  በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
ብዙ የፋይናንስ አቅም ላጡ ነገር ግን ትልልቅ የስራ ሀሳብ ላላቸው ስራ ፈጣሪዎች እና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር በኩል የራሱን ሚና ይጫወታል የተባለለት ይሄው ከወለድ ነፃ ማይክሮ ፋይናንስ አክስዮን ማህበር፤ የአንድ አክስዮን ዋጋ አንድ ሺህ ብር ሲሆን አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ትንሹ የአክስዮን መጠን 5  (5 ሺህ) ብር ሲሆን ትልቁ ደግሞ ሁለት ሺህ አክስዮን (ሁለት ሚሊዮን ብር) እንደሆነም አደራጆቹ ጨምረው ገልጸዋል። 100 ሚ ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የተነሳው ቢላል ከወለድ ነጻ ማይክሮ ፋይናንስ አንድ ሰው 5 ሺህ ብር አምስት አክስዮን ሲገዛ ቅድሚያ የሚከፈለው 60 በመቶውን (3 ሺህ ብር) ከ7 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ጋር ሲሆን ቀሪውን ቀስ ብሎ መክፈል እንደሚችልና 3350 ብር ከፍሎ ባለ አክስዮን መሆን እንደሚቻል ተገልጿል። በሸሪአ ህጉ መሰረት ወለድ እንደማስከፈፍል ነገር ግን ከወለድ ነፃ የሆኑ ከ42 በላይ አይነት የአገልግሎት ዘርፎችን እንደሚሰጥ እንዲሁም በአልኮል መጠጦች በቁማርና በየትኛውም አደንዛዥ ዕፅ ከተሰማሩት በስተቀር በየትኛውም የስራ ዘርፍ ለተሰማሩ ብድር በመፍቀድ ብዙዎችን ለቁም ነገር እንደሚያበቃ የተገለጸለት ማይክሮ ፋይናንሱ ቢያንስ በስድስት ወር ቢበዛ ደግሞ በ1 ዓመት ውስጥ አክስዮኑን ሸጦ በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለመግባት ማቀዱን አደራጆቹ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትጵያ ንግድ ባንክ፣ በዳሸን፣ በአዋሽ፣ በአቢሲኒያ እና በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንኮች አክስዮን መሸጥ መጀሩንም አደራጆቹ ጨምረው ገልጸዋል። አክስዮን ማህበሩ ጾታ ፣ ቀለም ፣ ዘርና ሃይማኖት ሳይመርጥ ለሁሉም አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መሆኑን የገለጹት አደራጆቹ አክስዮን በመግዛት የተቋሙ ባለቤት እንዲሆኑ ለሁሉም ጥሪ አቅርበዋል።

Read 2346 times