Monday, 22 March 2021 00:00

ሃይማኖትና ፖለቲካ እንዳይቀላቀሉ ጠንቀቅ! የባሰ አደጋ ላይ እንዳንወድቅ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(5 votes)

  • ለፖለቲካም ለሃይማኖትም የሚበጀው፣ ርቀታቸውን ሲጠብቁ ነው። ሲቀራረቡ ይፈጃሉ። ወይ ይፋጃሉ።
                      
              በፖለቲካ ዲስኩር መሃል፣ ሃይማኖትን ማጣቀስ፣ በስሱ መነስነስ፣ ጣልጣል ማድረግ ጉዳት የሌለው ሊመስለን ይችላል። በጎ ማጣፈጫ መስሎ የሚታያቸውም ይኖራሉ እንጂ። እንዲያውም፣ በሃይማኖታዊ አባባሎች፣ ችክ ያለውን ፖለቲካ ለማለሳለስ፣ ሲካረርም ለማለዘብና፣ መረን እንዳይለቅ ለመግራት ይመኛሉ። ይሄ የዋህነት ወይም አላዋቂነት ነው። ከቀድሞ ታሪክ አለመማር፣ በዘመናችንም በርካታ የዓለማችን አገራት የገጠማቸውን መከራ አለማስተዋል ነው።
ሌላው ቢቀር፣ ሩቅ ሳንሄድና ሳንራቀቅ፣ እዚሁ በአገራችን፣ በየቦታውና በተደጋጋሚ የተከሰቱ፣ የቅርብ ጊዜ አስቀያሚ ጥፋቶችን እንዴት እንዘነጋለን?
ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር በሚያቀላቅሉ ጭፍን ቅስቀሳዎች ሳቢያ፣ የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ብዙ ዜጎች፣ ቤት ንብረታቸውን አጥተው፣ ከኑሮ ተፈናቅለዋል። የሃይማኖት ተቋማት ተቃጥለዋል።
ያው፣ ፖለቲካና ሃይማኖት፣ በተቀራረቡ ቁጥር፣ በየቦታውና በየሰበቡ የሚፈጠረው ጥፋትም በዚያው መጠን ነው። ታዲያ፣ የከፋ አደጋ በገዛ እጃችን ጎትተን እንዳናመጣ ብንጠነቀቅ አይበጀንም?
ፖለቲካንና ሃይማኖትን ያቀላቀሉ፤…. አንዱ የሌላው አገልጋይ፣ ወይም አንዱ የሌላው መሪ እንዲሆንላቸው የሞከሩ አገራት፣…. ጤና አላገኙም። አንድም በአፈና ሲሰቃዩ፣ አልያም በጭካኔ ሲተራመሱ ነው የምናየው። እንደ ሶሪያ ወይም እንደ ሰሜን ኮሪያ!
የአገራችን የምዕተ ዓመታት ታሪክም፣ ለዛሬና ለወደፊት፣ መማሪያ ምክር ሊሆን ይገባል። በብዙ አገራት እንደታየው፤ ኢትዮጵያም ከዳር እስከዳር ነድዳለች - “በፖለቲካዊ ሃይማኖት” እና “በሃይማኖታዊ ፖለቲካ”።
በእርግጥ፣የድሮው የጥፋትና እልቂት በግልፅ ሲተረክና ሲነገር አንሰማ፣ አናነብ ይሆናል። ነገር ግን፣ ሃይማኖትንና ፖለቲካን በማቀላቀል ሳቢያ በአገራችን የተፈጠሩ የጥፋትና የትርምስ ታሪኮች፣ ከሌሎቹ ጥፋቶችና ጦርነቶች ሁሉ፣ ቢብሱና ቢበዙ እንጂ፣ ያነሱ ወይም የቀለሉ አይደሉም። ”ሃይማኖት ነክ ፖለቲካ”፣ ወይም “ፖለቲካ ነክ ሃይማኖት” በጣም ክፉ ነው፡፡ እንዲያውም፣ የእልቂቱና የትርምሱ ታሪክ እጅግ ዘግናኝ ከመሆኑ የተነሳ፣ ከዘመን ዘመን፣ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ፣ በዘልማድ “የቁጥብነት መንፈስ” መፈጠሩ አይገርምም።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
በአገራችን፣ ፖለቲካንና ሃይማኖትን የማቀላቀል ፍላጎት ብዙም ጎልቶ አይታይም። ፍላጎት ቢኖር እንኳ፣…. በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ውስጥ፣ ያን ያህልም ችኩልነትና ጉጉት የለም። ይልቅ፣ የዘልማድ ቁጥብነት ነው ጎልቶ የሚታየው። “ጨዋነት” ልንለውም እንችላለን። ይሄ፣ ጥሩ ነው። ነገር ግን፣….
ነገር ግን፣ የቁጥብነት ልማድ፣ ለብቻው፣ አስተማማኝ አለኝታ አይደለም። የስልጡን መርህ ያህል አቅም የለውም - የቁጥብነት ወይም የጨዋነት ልማድ። ጨዋነት፣ ክፋትን መቀነስና አደጋን ማዘግየት እንጂ፣ ክፋትን መከላከልና አደጋን ማስቀረት አይችልም። ይህንም በተግባር አይተነዋል። በምን? በምን?
ከአገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደሚመሰክረው፣ ቁጥብነት ልማድ፣ “ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ” አላዳነንም። አዎ፣ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የጨዋነት ወይም የቁጥብነት ዝንባሌ ረድቶናል። “ብሔር ብሔረሰብን” እና “ፖለቲካን” የማቀላቀል ጉጉት ሳይሆን በተቃራኒው የቁርጥብነት ልማድ ማመዘኑም፣ ለተወሰኑ አመታት አግዞናል። አደጋውን ለማዘግየት ጠቅሞናል።
 ነገር ግን፣ “የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ” በአገራችን እንዳይስፋፋ ለመግታትና አደጋውን ለማስቀረት፣ የቁጥብነት ልማድ በቂ አይደለም። በተግባርም በቂ እንዳልሆነ አይተነዋል። ከጥፋት አላዳነንም፡፡ ብዙ አስቀያሚ ጥፋቶች ተፈፅመዋል። ብዙ ሕይወት ጠፍቷል። አሁንም፤ ከአደጋው ገና ምንም አልለቀቀንም። ገና አልተቃለለም። ገና ምኑ ተነካና! ይልቅስ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ በቀላሉ የማይሽሩ ጥቁር ጠባሳዎችን ያሸከመን ነው። በአጭሩ፣ገና ብዙ ፈተና፣ ገና ብዙ ስራ አለብን። ሌላ ተጨማሪ ጣጣ አንጨምርበት።
መንግስትንና ኢኮኖሚን የሚያቀላቅል ሌላ በሽታ እንዳለብንም አትርሱ።
ስልጣንንና ኑሮን፣ መንግስትንና ኢኮኖሚን የሚያቀላቅል የጥፋት ማእበል የመጣ ጊዜ፣ “የቁጥብነት ልማድ” ለአገራችን አስተማማኝ መከታ መች ሆነላት? በእርግጥ፣ ኢትዮጵያ፣ የያኔውን የጥፋት ማዕበል፣ ለጥቂት አመታት ለማዘግየት ችላለች። ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት፣ ከኢትዮጵያ በፊት፣ አስር ዓመት ቀድመው ነው፣ በሶሻሊዝም ማዕበል የተመቱት። የቁጥብነት ልማድ፣ ለጥቂት ዓመታት ጠቅሞናል ማለት ይቻላል።
ታሪክ እንደሚነግረን፣ የያኔው የዜጎች ኑሮ፣ ያን ያህል የሚወላዳ ባይሆንም፣ “የሰውን ማሳ መድፈርና ድንበር መግፋት”፣ “የግል መኖሪያ ቤትን ወይም የእንጨት አጥርን መጣስ”፣ በአመዛኙ ነውር ነበር። ቢያንስ ቢያንስ፣ የሰውን ኑሮ መበዝበዝ፣ እንደ ጀግንነት በአዋጅ የሚያስፎክር ጉዳይ አልነበረም - ከ1966 ዓም በፊት፣ ከሶሻሊዝም ማዕበል በፊት።
እንደ ሃራም እንጂ፣ እንደ ሀላል አይቆጠርም ነበር።
የሰውን ንብረት የመውረስ ዝርፊ፣ በወንጀለኞች የሚፈጸም ግፍና በደል እንጂ፣ እንደ መልካም አላማ፣ በመንግስት የሚታወጅ ህግ ይሆናል ብሎ ማን ገመተ? ቤትና ንብረት እንደዘበት የመውረስ ሃሳብ፣ የሚጨበጨብለት ዲስኩር ይሆናል ብሎ ማን ጠበቀ? ጨርሶ የብዙ ሰው ሃሳብ አልነበረም። የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዝንባሌ፣ በእንደዚያ አይነት ሞገደኛ ሃሳብ የተቃኘ አልነበረም። የመንግስት ስልጣንና የግል ኑሮን የማቀላቀል ጉጉት ሳይሆን፣ የቁጥብነት ልማድ ነበር የሚያመዝነው።
ነገር ግን፣ “የቁጥብነት ልማድ”፣ “የመንግስት ስልጣንና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ” እንዳይቀላቀሉ ለማዘግየት እንጂ ለመከላከልና ለመግታት፣ ወይም በሩቁ ለማስቀረት፣ በቂ አልሆነም።
እውነት ለመናገር፣ ኢትዮጵያ፣ ከሶሻሊዝም የጥፋት ማዕበል ለመዳንና ለማምለጥ፤ ጥቂት ዓመታት ነበር የቀሯት። ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ጋር ስትነፃፀር፣ በቀላሉና በፍጥነት ለሶሻሊዝም፤ እጇን አልሰጠችም። ለአስር ዓመታት ተገዳድራለች። ለተጨማሪ 10 አመታት፣ ሶሻሊዝምን የመቋቋም አቅም ቢኖራት ኖሮ፣ የማምለጥ እድሏ ሰፊ ይሆንላት ነበር። ንብረት የመውረስ አባዜና የሶሻሊዝም ሞገድ፣ አጥፊነቱ በመላው ዓለም ገሃድ እየወጣ ነበራ፡፡ በመላው ዓለም መፍረክረክ  የጀመረውም፣ ከ1980 ዓ.ም በፊት ነዋ!
ምን ዋጋ አለው? ኢትዮጵያ አላመለጠችም። የሰዎች ኑሮና መኖሪያ ቤት፣ የሰዎች ስራና ንብረት፣ በመንግስት እጅ ገባ። ቤት ንብረት፣ በፖለቲካ ውሳኔ ተወረሰ። ከአንድ ሰው ነጥቆ ለሌላ መስጠት፣ የዝርፊያ ወንጀል ወይም የግፈኛ በደል መሆኑ ቀረና፤ እንደ “ፍትህ” ተቆጠረ። ከዚህ የከፋም አለ።
ሃብትና ንብረት አላቂ ነው። በየቀኑ መዝረፍና መውረስ አይቻልምና። ስራ እና ኑሮ ሁሉ፣ በመንግስት ትዕዛዝና ፈቃድ ብቻ እየሆነ መጣ፡፡ የእለት ተእለት በደልና ግፍ ይሉሃል እንዲህ ነው፡፡መንግስትና ኢኮኖሚ ሲቀላቀሉ፣አገር ተመሳቀለ፡፡ ሆነ። የዜጎች ኑሮ ይባስኑ ተጎሳቆለ፤ የአገሪቱ ድህነት ከፋ፡፡
አዎ፣ ዛሬ እንደያኔውም አይደለም። ይሄን ስራ፣ ይሔን አትስራ፤ያን ግዛ ያንን አትግዛ የሚሉ ትዕዛዞችና ቁጥጥሮች ቀንሰዋል። የግል ኑሮና ፖለቲካ በትንሹም ቢሆን ተራርቀዋል። መንግስት በሁሉም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ከመግባት ቆጠብ ብሏል።
እንዲያም ሆነ፣ ዛሬም ፖለቲካና ኑሮ፣ ፣መንግስት ቢዝነስ በቅጡ እንዲራራቁ አላደረግንም።
ዛሬም፣ መንግስት በብዙ የቢዝነስ ፕሮጀክቶች አማካይት ሃብት ያባክናል።
ይሔንም ያንም እደጉማለሁ እያለ፤ገንዘብ ይመድባል።
ወጪው ሲበዛ፣ ይበደራል። እዳው ይከማቻል።
ዞሮ ዞሮ እዳውን ለማቃለልም ወጪውንም ለማቃለል፤ በገፍ ገንዘብ እያሳተመ ያመጣል።
ብር ይረክሳል፤ ዋጋ ይንራል፤ ኑሮ ይወደዳል። ከዚያስ? የዋጋ ንረቱ በቢዝነስ ተቋማትና በነጋዴዎች ላይ የማላከክ ሩጫ፣ የዋጋ ተመንና ቁጥጥር፣ የመጋዘን ብርበራና ፍተሻ፣ ከፌደራልና ከክልል፣ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ፣ የአገርን ገበያ ያመሰቃቅላል።
የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ “የገበያ ዋጋ ከጨመራችሁ እርምጃ እወስዳለሁ” መግለጫ ይሁን ዛቻ የሰማነው በዚህ ሳምንት አይደል? እና ደግሞ ይህን እየሰሙና እያዩ፣ ኢንቨስሮች ሃብታቸውን አፍስሰው ፋብሪካዎችን እንዲከፍቱ እንጠብቃለን? መንግስት ከቢዝነስ ስራዎች ውስጥ አለቦታው ከመግባትና ለመታቀብ፣ ከመፈትፈት ተቆጥቦ፣ ርቀቱን ለመጠበቅ፣ አስቦ የወጠነው እቅድ ላይ ቢበረታና ቢገፋበት ነው የሚሻለው፤ የሚሻለን።
መንግሰትና ቢዝነስ ሲቀላቀሉ፣ ብዙ ኪሳራ እንደሚያስከትል፣ ፖለቲካና “ብሔር ብሔረሰብ” ሲደበላለቅ፣ አገርን እንደሚያቃውስና እንደሚተረማመስ፣ በተግባር ደጋግመን አይተነዋል፡፡ መራራነቱንም እያየነው ነው።
ሃይማኖትንና ፖለቲካን በማጠጋጋት ወይም በመቀየጥ፣ ሌላ ተጨማሪ አደጋና መከራ አንጥራ።
“ፈጣሪ አትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ! ፈጣሪ ይባርካችሁ” የሚል የመልካም ምኞት አባባል በቂ ነው ከዚያ ባሻገር አልፎ፤ የፖለቲካ ስብሰባና የፖለቲካ ዲስኩር ውስጥ፣ የሃይማኖት ስብከትም ሆነ ቅስቀሳ፣ በስሱ መነስነስም ሆነ፣ በይሉኝታቢስነት ማዥጎድጎድ፣ መጨረሻው አያምርም። አንዱ ፖለቲከኛ በለዘብታ የጀመረው የቁልቁለት መንገድ፣ ሌላው ፖለቲከኛ ይንደረደርበታል። ያባብሰዋል።
አንዱ የሀይማኖት ሰባኪ፣ በፖለቲካና በሕግ ጉዳዮች ላይ በለዘብታ ሃይማኖታዊ ትንታኔ ለማቅረብና ተፅዕኖ ለማሳደር ዳርዳር ማለት ሲጀምርም፤ በማግስቱ ለደርዘን አምሳያዎቹ ወይም ለእልፍ ተፎካካሪ ሰባኪዎች መንገድ ይከፍታል።
ፖለቲካዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ ፖለቲካ፣ ምን ያህል አስፈሪና መዘዙም እጅግ ዘግናኝ እንደሆነ፣ አገራችንንም ከመላው አለምም በርካታ አገራትን በማየት ማረጋገጥ ትችላላችሁ። እናም፣ በገዛ እጃችን አናባብሰው፡፡ ግድ የለም። ይቅርብን። ደግሞም ለፖለቲካም ለሃይማኖትም የሚበጃቸው ርቀታቸውን ሲጠብቁ ነው።


Read 8705 times