Wednesday, 24 March 2021 00:00

የአለም የጤና ድርጅት በኮሮና ክትባት ምክንያት አንድም ሰው አልሞተም አለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

       8 አዳዲስ የኮሮና ክትባቶች በመጪው አመት አገልግሎት ላይ ይውላሉ

          አስትራዜኒካ የተባለው የኮሮና ቫይረስ ክትባት የደም መርጋትን ጨምሮ የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ያስከትላል የሚለው መረጃ በመላው አለም በስፋት መሰራጨቱንና አገራት ክትባቱን ለዜጎቻቸው መስጠት ማቆማቸውን ተከትሎ፣ የአለም የጤና ድርጅት፣ በአለማችን እስካሁን ድረስ የኮሮና ክትባት በመውሰዱ ለሞት የተዳረገ አንድም ሰው አለመኖሩን አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ከፍተኛ ሳይንቲስት የሆኑት ሶምያ ስዋሚናታን ባለፈው ሰኞ በጄኔቫ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ እስካሁን በመላው አለም የኮሮና ክትባቶች ባስከተሉት የጎንዮሽ ጉዳት ወይም በቀጥታ በክትባቶቹ ሳቢያ ለሞት የተዳረገ ሰው እንደሌለ በመጥቀስ፣ ህዝቡ በመሰል ስጋትና ጭንቀት ውስጥ እንዳይገባ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ሳይንቲስቷ በአሁኑ ወቅት ውጤታማነታቸው ተረጋግጦ በጥቅም ላይ ከዋሉት 10 የኮሮና ክትባቶች በተጨማሪ 8 ያህል አዳዲስ ክትባቶች በቤተሙከራ ምርምር ሂደት ላይ እንደሚገኙና እስከ አመቱ መጨረሻ ወይም እስከ መጪው የፈረንጆች አመት 2022 መጀመሪያ አገልግሎት ላይ ይውላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውንም ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ከ6 እስከ 8 ከሚደርሱት በምርምር ላይ የሚገኙ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መካከል ከመርፌ ውጭ በአፍ ወይም በአፍንጫ የሚሰጡ እንዲሁም ማቀዝቀዣ የማያስፈልጋቸው እንደሚገኙበት የጠቆሙት ሳይንቲስቷ፣ የምርምር ሂደታቸውና ህጋዊ እውቅና የመስጠት ሂደታቸው እስከ አመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለው ገልጸዋል፡፡
በመላው አለም በድምሩ ከ80 በላይ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ምርምሮች እየተካሄዱና በሰዎች ላይ እየተሞከሩ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፤ የተወሰኑት ግን ገና በክትባት ሙከራ የጅማሬ ምዕራፍ ላይ የሚገኙና ውጤታማ ላይሆኑ የሚችሉ ናቸው መባሉንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ክትባት ዜና ደግሞ፣ ከአንድ አመት በኋላ ክትባት ለወሰዱ 20 የውጭ አገራት ጎብኝዎች በሯን ክፍት እንደምታደርግ ያስታወቀቺው ቻይና፤ ያም ሆኖ ግን ወደ ግዛቷ መግባት የሚችለው “ቻይና ሰራሽ” የኮሮና ክትባት የተከተበ ሰው ብቻ መሆኑን እንዳስታወቀች ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ቻይናን ለመጎብኘት የሚፈልጉ ሰዎች በቻይና ከተመረቱ የኮሮና ክትባቶች አንዱን መውሰዳቸውን የሚያረጋገጥ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው  የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ ውሳኔው አገሪቱ የራሷን ክትባቶች በአለማቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በማሰብ የተላለፈ ነው መባሉን ገልጧል፡፡
 አሜሪካ፣ ህንድ፣ ኢራቅ፣ እስራኤልና ፊሊፒንስን ጨምሮ ለ20 አገራት ቱሪስቶች በሯን ክፍት ማድረጓን ቻይና  ያስታወቀች ሲሆን 5 የተለያዩ የኮሮና ክትባቶችን አምርታ በአገልግሎት ላይ ማዋሏ ተጠቁሟል። 34 የአለማችን አገራት ቢያንስ አንዱን የቻይና ክትባት ለዜጎቻቸው ለመስጠት መፍቀዳቸውም ተዘግቧል፡፡

Read 6426 times