Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 August 2012 13:02

በመልካም አስተዳደር ወርቁ ቢቀር ነሐሱ የታለ? የኢህአዴግ ፔስሜከሮች ተቃዋሚዎች ናቸው (አልተጠቀመባቸውም!) አትሌቶቻችን ወርቆች ናቸው! መንግስታችንስ?

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከዓመታት በአንዱ ዓለምአቀፍ ኦሎምፒክ ላይ ነው አሉ፡፡

ኢሕአዴግ በዲሞክራሲያዊ አሠራርና ባህል የዳበረ ልምድ አላቸው እያለ አንዳንድ ክፉ ክፉ ሕጐችን ከሚቀዳባቸው አገራት አንዷ ናት፡፡ ይቺ አገር (ህንድ ትባላለች) በዲሞክራሲ የዳበረ ባህልና ልምድ ይኑራት እንጂ በአትሌቲክስ የዳበረ ባህልና ልምድ የላትም አሉ፡፡ መንግስቷ ታዲያ በዚህ ብዙ ሲቆጭ ሲንገበገብ ቆይቷል፡፡ እናም በአንደኛው ዓለማቀፍ ኦሎምፒክ ብዙ ተዘጋጀ፡፡ ብዙ ለፋ፤ ብዙ ተጋ፡፡ ብዙ በጀትም መደበ፡፡ እናሳ … ውጤት ተገኘ? በአትሌቲክስ ውድድር የተሳተፈ አንዱ የህንድ አትሌት ጥሮ ጥሮ አራተኛ ወጣ አሉ፡፡ ወርቅ የለም፡፡ ነሐስ የለም፡፡ ብርም የለም፡፡ በቃ የልፋቱ ውጤት ያስገኘለት የአራተኛነትን ደረጃ ብቻ ነበር፡፡ የህንዱ አትሌት ኦሎምፒኩ ሲጠናቀቅ በአውሮፕላን ተሳፍሮ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡ የህንድ ሕዝብ እንደ ጉድ ወጥቶ ከኤርፖርት አንስቶ የደመቀ አጀብና አቀባበል አደረገለት፡፡ ሕዝቡ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የህንድ ጠ/ሚኒስትርም ኤርፖርት ተገኝተው ነበር - 4ኛ የወጣውን አትሌት ለመቀበል፡፡

ይሄ አትሌት ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ ግን ዕጣ ፈንታው ሌላ ይሆን ነበር፡፡ እንኳንስ አራተኛ ለወጣ አትሌት፣ ብርና ነሐስ ብቻ ላመጣም ወግና ክብር መስጠት አልተለመደም - በጦቢያ ምድር! በለንደኑ ውድድር 4ኛ የወጣው ጀግናው ቀነኒሳ በቀለ “አዋረደን እኮ!” ነው የተባለው፡፡ እናም ጀግናውን የጦቢያ ልጅ ልናዋርደው ዳድቶን ነበር (አንዳንዴ ፍሬን እንለቅ የለ!) ለነገሩ… በአትሌቲክስ እኛ የለመድነው ወርቅ ብቻ ነው፡፡ የምናጨበጭበውም ለወርቅ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል! “እንኳን ደስ ያላችሁ” የምንለውም ወርቅ ሲገኝ ብቻ ነው! (ደግነቱ አትሌቶቻችንም ወርቆች ናቸው) በነገራችሁ ላይ የኢህአዴግ ፔስሜከሮች እኮ ተቃዋሚዎች ነበሩ፡፡ ችግሩ እንጂ አልተጠቀመባቸውም፡፡ ስለዚህ ወርቅ መሆን አልቻለም - እንደ አትሌቶቻችን! (መንግስት ከአትሌቶቹ ቢማርስ?)

 

ግን አንዳንዴ ይሄ የወርቅ ባህላችን ትንሽ ለከት ያጣል መሰለኝ፡፡ እናም ያልሰጠነውን ልናፍስ ያምረናል፡፡ ወርቅ ያስለመዱን ጀግኖቹ አትሌቶቻችን ወይ አየሩ ሳይስማማቸው ወይ አቅም ይሁን ብቃት ከድቷቸው ብርና ነሐስ ያመጡ ዕለት በአራት ነጥብ ጥርቅም አድርገን እንዘጋቸዋለን (በቃ Shut down!)

በዘንድሮ የለንደን ኦሎምፒክም ያየነው ይሄንን ነው፡፡ ወርቅ ካልመጣ መንግሥትም.…ኢቴቪም.… የስፖርት ዘጋቢዎችም … የክልል መስተዳድሮችም … የ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ!›› መልዕክት እንኳን አያስተላልፉም (ለብርና ለነሐስ ሞተን ነው ቆመን ያሉ ይመስላሉ)

እኔ በበኩሌ ወኔያቸውና ሞራላቸው አስደስቶኛል (ወኔ ብቻ ሆነ እንጂ) ትልቅ ትልቁን መመኘታቸውም ክፋት የለውም (Think big ወይም Dream big እንዲሉ) የእኔ ጥያቄ ምን መሰላችሁ? ወርቅ የምንፈልገው ለምን ከአትሌቲክስ ብቻ ሆነ የሚል ነው፡፡ ከአትሌቶቻችን ወርቅ ብቻ  የሚጠብቀው መንግስታችን፤ በመልካም አስተዳደር፣ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ በሰብዓዊ መብት አከባበር፣ በነፃ ፕሬስ፣ በኢኮኖሚ ዕድገት… ወርቁ ቢቀር መቼ ነሃስ እንኳን ለእማማ ጦቢያ አመጣላት? ሁልጊዜ ውራ እየተባልን አይደለም እንዴ? (ወቀሳ አይደለም፤ ሃቅ ነው) አያችሁ … ጦቢያችን ለአትሌቶቻችን ያስቀመጠችውን መስፈርት (የወርቅ መስፈርት ማለቴ ነው) ለመንግስት አስተዳደርም፣ ለትምህርት ጥራትም፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሥርዓትም፣ ለምሁራንም፣ ለፊልም ባለሙያዎችም … ባጠቃላይ ለሁሉም ዘርፍ ማስቀመጥ ያለባት ይመስለኛል? በአንዲት አገር ሁለት መለኪያማ ተገቢ አይደለም፡፡ ያለዚያ “Fair play” አይሆንም - የእማማ ጦቢያ ጨዋታ! (ተሳሳትኩ እንዴ?)

በነገራችሁ ላይ በለንደኑ ኦሎምፒክ ጥቂት የማይባሉ አትሌቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ሰምተናል፡፡ ከጉዳት የተረፉት የአትሌቲክስ ኮሚቴው አባላት ብቻ ናቸውም ተብሏል (እንዴ ምን ሲሆኑ ጉዳት ይደርስባቸዋል?) እኔ የምለው … ባለፈው ሐሙስ አትሌቶቻችን በስቴዲየም በተደረገላቸው አቀባበል ለኮሚቴው አባላት ሁሉ የአበባ ጉንጉን ሲደረግላቸው አይቼ ግርም አለኝ (ለአጃቢነታቸው ይሆን?)

ሌላ በጣም የገረመኝ ነገር ደግሞ አለ፡፡ በ5ሺ የሴቶች ውድድር ጥሩዬና መሲ ተሟሙተው ወርቅና ነሐስ አመጡ - ለእማማ ጦቢያ፡፡ አንዳንድ ወግ አጥባቂዎች ግን የፕሮቶኮል ጥያቄ አነሱ አሉ፡፡ እንዴት ከድሉ በኋላ አልተቃቀፉም የሚል (እንዴ ባይተቃቀፉስ?) ይሄ ጥያቄ መነሳት ካለበትም በቀጥታ የሚመለከተው አትሌቶቹን ሳይሆን አንዳችም ጉዳት አልደረሰበትም የተባለውን የኦሎምፒክ ኮሚቴውን ይመስለኛል (ለንደን ድረስ የተጓዘው ለቫኬሽን ነው እንዴ?) ለማንኛውም ወርቅም ብርም ነሐስም ላመጡት፤ ከዛም በታች 4ኛም፣ 5ኛም ወዘተ ደረጃ ላስገኙት ሁሉ እንኳን ደስ ያላችሁ ብያለሁ - ኮርተንባችኋል!

እንግዲህ የዛሬ “ፖለቲካ በፈገግታ” ከወትሮው ለየት ብሏል፡፡ እናም አሁን ወደ ሌላ ለየት ያለ አጀንዳ ደግሞ እንግባ፡፡ ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ቤት እግር ጥሎኝ ሄጄላችሁ በዓለም ሲኒማ የምትታተም ወርሃዊ ሚጢጢዬ መጽሔት አገኘሁና ገልበጥ ገልበጥ አደረኳት፡፡ በአማርኛ ፊልሞች ማስታወቂያ የታጀበችው መጽሔቷ፤ የዛሬው ከፊል ወጌ በፊልሞቻችን ዙሪያ ያጠነጥን ዘንድ ሰበብ ሆነኝ፡፡ እስቲ ማስታወቂያዎቹ ላይ ካገኘኋቸው አስገራሚ ጉዳዮች አንዷን ሰበዝ መዝዤ ላጫውታችሁ - መማርያም መዝናኛም መገረምያም ሊሆናችሁ ይችላል በሚል እምነትም ግምትም፡፡ በነገራችሁ ላይ “የኢትዮጵያን የሲኒማ ኢንዱስትሪ ወደላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ምርጥ ፊልም” የሚል ዓይነት በጉራ የታጀበ ማስታወቂያ ባለማየቴ ደስ ብሎኛል - በሚጢጢዬ መፅሄቷ ላይ፡፡ በምትኩ ግን ምን አስተዋልኩ መሰላችሁ …የሚገርሙ የሚገርሙ የፊልም ጥቅሶች፤ አባባሎች ወይም መሪ ቃሎች … (መፈክሮችም ቢባሉ ያስኬዳል) በእርግጥ ትኩረት እንደሚስቡ ግን አልክዳችሁም (ፉከራው ሲያልቅበት ቀረርቶ አከበለት አሉ) ለማንኛውም ግን ከመሪ ቃሎቹ ጥቂቶቹን እንደው ዝም ብለን እንመልከታቸው (ልብ አድርጉ መመመልከት ብቻ ነው!)

‹‹ሠርግ ከአሜሪካ›› የሚለው ፊልም ላይ ምን የሚል መሪ ቃል ሰፍሯል መሰላችሁ? “ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ”፣ ‹‹የፍቅር ABCD›› የተሰኘው ፊልም ደግሞ “የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል” የሚል ጥቅስ ይዟል (ያልታገሰስ?) ይሄን የሚያውቁት ፊልም ሰሪዎቹ ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹ትውልድ›› ወይም Generation የተባለው ፊልም “ሁሉም ሰው የራሱ ዕውቀት እስረኛ ነው” ይላል (እንግሊዝኛ እንደ መድሃኒት ጠብ የሚያደርጉት ሊያስፈራሩን ፈልገው ይሆን?) ወይስ ወደ ሆሊዉድ መንደር ጠጋ ለማለት አስበው? (የልጅ ስም በአማርኛ፤ የአባት በእንግሊዝኛ እኮ ነው የሚመስሉት!)

ከሳምንት በፊት በኢቴቪ “አሪሂቡ” ፕሮግራም ላይ በእንግድነት ተጋብዞ የቀረበው ዕውቁ ሲኒማቶግራፈር አብርሃም …ስለፊልሞቻችን የሰጠውን ሙያዊ አስተያየት ሰምታችሁልኛል፡፡

የተናገረው ጠቅለል ሲደረግ “ሁሌም ለመማርና ለማወቅ አዕምሮአችንን ክፍት እናድርገው!” የሚል ነው፡፡ እውነቱን እኮ ነው…ከኛ በላይ ላሳር የሚለው አባባል እንደማያዋጣ በፊልም ሠሪዎቻችን እያየነው ነው (እንዴ ባለንበት መርገጥ ሆንን እኮ!) አያችሁ እንደ ጥሩዬ ድምፅን አጥፍቶ ወርቋን ማፈስ እንጂ ባዶ ፉከራና ሽለላ ምን ይሰራል (ለትዝብት ከመዳረግ ውጪ!)

ከዛችው የዓለም ሲኒማ ሚጢጢዬ መጽሔት ላይ “የሆሊዉድ ክሊሼ” በሚል ርዕስ የቀረበ መጣጥፍ ሳነብ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የኢሕአዴግ ሰፈር ክሊሼ!! እናም ክሊሼዎቹን በንፅፅር እንመለከታለን - የኢህአዴግንና የሆሊዉድን፡፡ ምናልባት (ድንገት ምናልባት) ንፅፅሩ መሰረተቢስ ነው ወይም ፍፁም ፈጠራ ነው የሚሉ የኢሕአዴግ ሰፈር አባላት ወይም ቀንደኛ ካድሬዎች ካሉ ማስተባበያ ለማውጣት ዝግጁ ነኝ (ማስተባበያቸው መሰረተቢስ ቢሆንም) ያለዚያ እኮ ሳንግባባ መቅረታችን ነው (ማን ነበር በምን እንግባባ ያለው?) አሁን በቀጥታ ወደ ክሊሼ ንፅፅሩ፡፡ (ተነፃፃሪዎቹ ኢሕአዴግና ሆሊዉድ ናቸው ብያለሁ)

የሆሊዉድ ክሊሼ -

በትምህርት ክፍለ ጊዜ ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን የሚያሳይ የትኛውም የሆሊዉድ ፊልም ክፍሉ ውስጥ ከአምስት ደቂቃ የበለጠ አይቆይም፡ የፈለገውን ያህል የጋለ ጉዳይ ቢከናወንበትም ወዲያው በደውሉ ድምጽ ክፍሉ መበተኑ አይቀሬ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ክሊሼ -

ኢሕአዴግ በአንዳንድ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ስጋት ሲያድርበት ምን ያደርጋል መሰላችሁ? ቶሎ ብሎ “ሕጋዊ” ለመሆን ይሯሯጣል፡፡

እንዴት አትሉም… ሕጋዊ ነኝ የሚያስብል አዳዲስ ሕጐችና ዐዋጆች በማርቀቅና በማጽደቅ፡፡ በዚህ መልኩ የረቀቁና የፀደቁ ሕጐችና ዐዋጆች ደግሞ ፈርዶባቸው ከየአቅጣጫው ትችትና ነቀፋ፤ተቃውሞና ውግዘት ማስተናገዳቸው አይቀርም (የፀረ - ሽብር ሕጉና የሚዲያ ሕጉ ተጠቃሽ ናቸው!) ይሄኔ ኢሕአዴግ ይጠየቃል - “ምን ትላለህ?” ተብሎ፡፡ ኢሕአዴግ እንዲህ ሲል ይመልሳል “ሕጉ በዲሞክራሲያዊ አሠራርና ባህል የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት የተቀዳ ነው?” ይሄ ነው የኢሕአዴግ ክሊሼ!

የሆሊውድ ክሊሼ -

የተወሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች ቆመው/ተደርድረው በሚታዩበት የሆሊዉድ ፊልም ላይ ዋናውን ሚና የሚጫወተው አክተር ከፊት ለፊት ቆሞ መታየቱ አይቀሬ ነው፡፡ስፖርትም ቢሆን የውትድርና ልምምድ ወይም ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ ግንባር ቀደሙ እሱ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ክሊሼ-

አንዳንዴ ሳይሆን በአብዛኛው ለስኬት ያበቃሉ ወይም ውጤታማ ያደርጋሉ ተብለው የተቀረፁ ፖሊሲዎች ግባቸውን ሳይመቱ ይቀሩና በይፋ ኢላማቸውን አልመቱም ይባላሉ (እንደ BPR ዓይነት) ኢሕአዴግ ይሄን ጊዜ ምን ይላል መሰላችሁ? “ኢሕአዴግ የፖሊሲ ችግር የለበትም፤ የአፈፃፀም እንጂ!” ይልላችኋል፡፡ እቺም የኢህአዴግ ሠፈር ክሊሼ እንደሆነች እወቁልኝ፡፡

የሆሊዉድ ክሊሼ -

አክተሮች ሻንጣ ተሸክመው በሚታዩባቸው ትዕይንቶች ሁሉ ሻንጣዎቹ ባዶ ናቸው፡፡ አክተሮቹ ሻንጣውን ሲያነሱና ሲሸከሙ ሻንጣው በኮተት የተሞላና ከባድ እንደሆነ ለማስመሰል ፊታቸውን ያኮማትሩታል፡፡ሆኖም ጥቂት ቆይተው እንደላባ በቀላሉ ሲያንቀሳቅሱት መያዛቸው አይቀሬ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ክሊሼ -

ሁልጊዜም መንግሥት በዜጐቹ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን የሚጠቁም ዜና፣ ሪፖርት ወይም መረጃ ያሰራጨ ዓለምአቀፍ ሚዲያ ወይም ተቋም የእርግማንና የውግዘት ውርጅብኝ እንደሚወርድበት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ (በኢህአዴግ ባህል)

የተለያዩ ታፔላዎች እየተለጠፉለትም ጉደኛ ዘመቻዎች ሲካሄድበት ይሰነብታል…በኢቴቪ፣ በአዲስ ዘመንና በሌሎች የኢሕአዴግ ልሳኖች፡፡

(አንድ ወዳጄ “ይሄ መንግስት እኮ አይታመንም፤ እኔ አዲስ ዘመንንም ቢዘጋቸውስ? ብሎኛል ማን ያውቃል? ከተነሳበት ይዘጋቸዋል”) ከጥቂት  ጊዜያት በኋላ ይኸው ተቋም ወይም ሚዲያ የአገሪቱ ኢኮኖሚ 11 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን የሚጠቁም ሪፖርት ወይም መረጃ ሊለቅ ይችላል (በአጋጣሚ በቀኝ ጐኑ ይነሳና) ይሄኔ ኢቴቪ የዜና ምንጭ አድርጐ በመጥቀስ መረጃውን እስኪታክተን ይግተናል፡፡ ይሄም ዝነኛ የኢህአዴግ ክሊሼ ነው፡፡

ሌላ ክሊሼ እነሆ፡- ኢህአዴግ ኢኮኖሚው ተመንድጓል፤ የእህል ምርቱ በእጥፍ አድጓል፤ በምግብ ራሳችንን ችለናል ሲል ከሰማችሁት … ችግር አለ፡፡

የዋጋ ግሽበት ይጨምራል፤ የኑሮ ውድነቱ ይንራል፤ ከዓለማቀፍ ማህበረሰብ የእህል እርዳታ ይጠየቃል (እንደሰሞኑ) ይሄንንም የኢህአዴግ ክሊሼ ብላችሁ ልታልፉት ትችላላችሁ፡፡

በነገራችሁ ላይ የኢሕአዴግ ክሊሼዎች ስል የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ክሊሼዎች እያልኩ እንደሆነ ይታወቅልኝ! (ኢሕአዴግና አብዮታዊ ዲሞክራሲ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ስለሆኑ!)

እንግዲህ በቦታ ውስንነት ተገደብን እንጂ የኢሕአዴግ ክሊሼዎች ማብቂያ ወይም ማለቂያ የላቸውም ለዛሬ ግን ኢሕአዴግንም፣ እኛንም፣ ፊልሞቻችንንም፤  ሆሊዉድንም ከክሊሼ ያውጣን ብለን እንሰነባበት፡፡ አሜን!!

 

 

 

Read 3510 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 13:07