Sunday, 21 March 2021 00:00

6ኛው አገራዊ ምርጫ 2013

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   "ኦነግን የማዳን ሥራ ላይ ተጠምደን ነው የቆየነው"

           • በምርጫው ሳንሳተፍ ከቀረን ችግሩ የማንም ሳይሆን የራሳችን ነው
           • ሁልጊዜ ስሞታና ውግዘት በማሰማት ብቻ መቀጠል አንፈልግም
           • ላለፉት 23 ዓመታት ኦነግን ሲረብሽ የቆየው ውስጣዊ ችግር ነው
           • ኦነግ የህዝብ ድርጅት እንጂ የግለሰብ አንጡራ ሃብት አይደለም

           ከተመሰረተ ግማሽ ክ/ዘመን ገደማ ያስቆጠረው የኦሮሚያ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ በየጊዜው በሚገጥመው ውስጣዊ የአመራር ውዝግብና የፖለቲካ ችግሮች የተነሳ በተደጋጋሚ ተከፋፍሏል፡፡ የፓርቲው መሥራቾችና ነባር አመራሮችም ጭምር ድርጅቱን ጥለው ወጥተዋል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ኦነግ ለ23 ዓመታት የድርጅቱ ሊቀ መንበር ሆነው የቆዩትን አቶ ዳውድ ኢብሳን ከስልጣን ያወረደበትን ጉባኤውን ጉለሌ በሚገኘው ዋና ፅ/ቤቱ አካሂዷል። በዚህ ጉባኤውም የቀድሞ ም/ሊቀ መንበር አራርሶ ቢቂላ በሊቀ-መንበርነት፣አቶ ቀጄላ መርዳሳ ደግሞ በምክትል ሊቀ መንበርነት የተመረጡ ሲሆን በአጠቃላይ ዘጠኝ አባላት ያሉት ስራ አስፈፃሚ መዋቀሩን አመራሮቹ አስታውቀዋል። ሰሞኑን መግለጫ የሰጠው የኦነግ አዲሱ አመራር፤ ምርጫ ቦርድ የሚፈቅድለት ከሆነ እጩዎችን አስመዝግቦ በአገራዊ ምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ጠቁሟል - ራሱን ከምርጫው የማግለል ሃሳብ እንደሌለው በመግለጽ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ አዲሱን የኦነግ ም/ሊቀመንበር አቶ ቀጀላ መርዳሳን፣ በጠቅላላ ጉባኤው ዙሪያ፣ በወደፊት የፓርቲው ዕጣ ፈንታ፣ "የብልጽግና ተለጣፊ" በሚል እየቀረበባቸው ስላለው ውንጀላና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ  አነጋግሯቸዋል፡፡    

            እስቲ  ጠቅላላ ጉባኤው ስለተካሄደበት ሁኔታ  ይንገሩን ?  
ጠቅላላ ጉባኤው የተጠራው ችግር ለመፍታት ነው፡፡ ችግር መፍታት ሲባል ደግሞ የግለሰቦችን አይደለም፤ ድርጅቱ ያለበትን ችግር ለመፍታት ነው፡፡ ድርጅቱ ተዳክሞ መዋቅሮቹ ፈራርሰው ነበር፡፡ ይሄንን መዋቅር ነው መልሰን የገነባነው። ላለፉት 8 ወራት ገደማ የኦነግ መዋቅር ሊቀ-መንበር የነበረው ግለሰብ በወሰደው እርምጃና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፣ ህዝቡም ውዥንብር ውስጥ ነበር፤ አባላቱም ውዥንብሩ ውስጥ ገብተው ሥራዎች ቆመው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሚዲያ መግለጫ ከመስጠት በስተቀር በተጨባጭ መሬት ላይ የሚሰሩ ስራዎች አልነበሩም፡፡ አሁን ጠቅላላ ጉባኤ ስናደርግ አብሮ መስራት የሚችል አመራር ተገኝቷል፡፡
የጠቅላላ ጉባኤ መስፈርትን አሟልቷል ማለት ይቻላል? የምርጫ ቦርድ ተወካዮች ተገኝተዋል?
ጉባኤው በሚገባ ህጋዊ የሚባሉ ሂደቶችን በሙሉ ያከበረና የተከተለ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ታዛቢዎቹን  ልኳል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው በህጉ መሰረት ስለመካሄዱ፣ የአመራር ምርጫውን…አጠቃላይ ሂደቱን ከኛ ጋር ሌሊቱን ሙሉ ቆይተው ተከታትለዋል፡፡ ነገር ግን የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች ስለተገኙ ብቻ ጉባኤው ትክክለኛነቱ ተረጋግጧል ማለት አይደለም። ቦርዱ የራሱን ትዝብት እንዲሁም የቀረቡ ሠነዶችን ተመልክቶ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
 የህጋዊነት ጥያቄዎችን የሚያነሱ ወገኖች አሉ--- የህጋዊነት መስፈርቶችን ያሟላ ጉባኤ ነው ትላላችሁ?
በሚገባ! እኛ ሁሉንም የህግ ሂደቶች ማሟላቱን አረጋግጠን ነው ጉባኤውን ያካሄድነው፡፡ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎችም አንዱ ስራቸው፤ ምልአተ ጉባኤ ስለመሟላቱ ማረጋገጥ ነው፤ ያንን አረጋግጠዋል፡፡ ጉባኤው የተደረገው በትልቅ ተፅዕኖና ውጥረት መሃል ነው፡፡ በሃገሪቱ ሰላም በጠፋበት፣በድርጅት ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች በጎሉበት፣ አባላት ወደ ጉባኤው እንዳይሄዱ ጠንካራ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው ባሉበት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የተካሄደ ጉባኤ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ከ500 በላይ ሰው ነው በጉባኤው የተገኘው፡፡ በዚህም ምልአተ ጉባኤ ተሟልቷል ማለት ነው፡፡
በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን ግን “ጉባኤው ህጋዊ አይደለም፤ መንግስት የሚፈልገውን ተለጣፊ ኦነግ የፈጠረበት ነው” የሚል ውንጀላ እያቀረበ ነው……..
አዎ እኛም ሰምተናል፡፡ እንግዲህ የችግሩ ምንጭ፣ ይሄው የግለሰብ አድራጊ ፈጣሪ ልሁን ባይነት ነው። ገና የኦነግን አመራር ሆን ብሎ ለመበተን ሲፈለግ ነገር የተጀመረው በዚህ መሰሉ ስም ማጥፋትና የፍረጃ ፕሮፓጋንዳ ነበር። “የብልፅግና ሰዎች ናቸው፣ የመንግስት እጅ አለበት” እየተባለ፣ እኛን እንደ ከሃዲ በመፈረጅ፣ ከህብረተሰቡ ዘንድ ድጋፍ ለማግኘት ተሞክሯል፡፡ ይሄ ችግር በተፈጠረበት ወቅት  ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ብዙ ቀውሶች የተፈጠሩበትና ህዝቡ በንዴትና ብስጭት ውስጥ የነበረበት ወቅት ነው። እነሱም አውቀው ችግሩን በማባባስና በማጉላት፣ አንዱን አካል በውንጀላ የማጥፋት ስትራቴጂ ነበር የተከተሉት። ይሄ የሸር አካሄድ ደግሞ የተለመደ ነው። በእርግጥ በወቅቱ የነዙት ፕሮፓጋንዳ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ብዥታ ፈጥሯል። ልክ እኛ በገንዘብ እንደተገዛንና ኦነግን ለብልፅግና አሳልፈን እንደሰጠን ተደርጎ ነው የቀረበው። “40 ሚሊዮን ብር፣ 30 ሚሊዮን ብር ተሰጥቷቸዋል” እያሉ ስማችንን ሲያጠፉ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ለኛ የሚያሳየን ከስሜት ባለፈ የሚያሸንፉበት መከራከሪያ እውነትና ምክንያት እንደሌላቸው ነው። ያለመርሆ ዝም ብሎ በፍረጃ ስም ማጥፋት ብዙኃንን ከጎን በማሰለፍ ለማሸነፍ የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡ ይሄ ግን ለጊዜው እንጂ አያዛልቅም። ለአጭር ጊዜ ሰዎችን ማደናገር ይቻል ይሆናል። ለረጅም ጊዜ ግን አይቻልም። ምክንያቱም እውነቱ እያደር ይጠራል፡፡
ኦነግ በየጊዜው በሚፈጠሩ ውስጣዊ ችግሮች በተደጋጋሚ ተከፋፍሏል፡፡ ዛሬም ይኸው ችግር ቀጥሏል። የዚህ ችግር መንስኤው  ምንድን ነው ትላላችሁ?
እኛንም ያልገባን ጉዳይ ይሄው ነው። በተለይ ባለፉት 23 ዓመታት የተፈጠረው  ችግር ነው፣ ኦነግን ለብዙ ውጣ ውረድ የዳረገው። ከዚያ በፊት የነበረው የውስጥ ሳይሆን ከውጭ የሚመጣ ችግር ነበር። ካለፉት 23 ዓመታት ወዲህ ግን ኦነግን ሲረብሽ የነበረው የውስጥ ችግር ነው። በተለይ አሁን ከስልጣን የወረደውና ሊቀ መንበር የነበረው ግለሰብ፣ የርዕዮተ ዓለም አረዳድ ችግር ያለበት ሰው ነው። የጸና አቋም የሌለው፣ ራሱን ብቻ ማዕከል አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሰው ነው። የኦሮሞ ድምፅ የሆኑና በሰፊው ተቀባይነት ያላቸው ሰዎችን ካጠገቡ ለማስወገድ ከማንም ጋር የሚቆም፣ መርህ አልባ አካሄድ የነበረው ነው። ላለፉት 23 ዓመታት ለኦነግ አለመግባባት ምንጩ ይሄ ግለሰብ ነበር። እሱ ወንበር ከያዘ በኋላ ለድርጅቱ ሳይሆን ለወንበሩ ብቻ ስለሚጨነቅ፣ በኦነግ ውስጥ የመሪነት ልምድ ያላቸው ግለሰቦች ድርጅቱን እየለቀቁ፣ እንደገና አዳዲስ ሰዎች እየመጡ፣ እነሱም እንደገና ግጭት እየተፈጠረ አስቀያሚ አዙሪት ውስጥ የቆየ ድርጅት ነው። አሁን ይሄ አዙሪት እንዲያበቃ ነው እየጣርን ያለነው።
ችግሩ የስልጣን ጥም፣ የግል ፍላጎት፣ ራስን ብቻ ማዕከል አድርጎ የራስን ሰብዕና ለመገንባት የመንቀሳቀስ ሁኔታ የፈጠረው ነው፡፡ ሊቀ መንበሩ ያለው ሁሉ የፈጣሪ ቃል ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታ ነው የነበረው። አሁን ግን ያ ጊዜ አክትሟል። ኦነግ የህዝብ ድርጅት እንጂ የግለሰብ አንጡራ ሃብት አይደለም፤ስለዚህም አሁን ባለቤቱ ተመልሷል፤ ወደ ህዝቡ ማለት ነው፡፡
በጉባኤያችሁ ምን ያሻሻላችሁት ነገር አለ? ለምሳሌ በፖለቲካ ፕሮግራም ወይም በህገ-ደንብ ዙሪያ --
ጉባኤውን እንደ መሸጋገሪያ ነው የተጠቀምንበት። የፖለቲካ ፕሮግራሙ ከሁለት ዓመት በፊት ተሻሽሏል። ስለዚህ በዚህኛው ጉባኤ አልነካካነውም። በሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ ልንወያይበት እንችላለን፡፡ በህገ ደንባችን ላይ ማሻሻያ ያደረግንበት ጉዳይ አለ። የዛሬ 17 ዓመት በ1996 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ተደርጎ፣ ሊቀ መንበሩና ም/ሊቀ መንበሩ ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ እንዳይችሉ፣ የስልጣን ጊዜ ገደብ አስቀምጠን ነበር። ያ ተጥሶ በ2000 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ መደረግ ሲገባው ሳይደረግ ቀረ። በዚህ ሳቢያም በወቅቱ ድርጅቱ ለሁለት ተከፈለ። ከዚያም ያ የስልጣን ጊዜ ገደብ ስራ ላይ ከዋለ ከ13 ዓመታት በኋላ በ2009 ዓ.ም ኤርትራ አፋቤት ላይ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገን ነበር። በወቅቱ በሊቀ መንበሩ አምባገነንነትና ጫና፣  የስልጣን ጊዜ ገደብን የሚደነግገው አንቀፅ፣ ከህገ-ደንቡ እንዲሰረዝ ተደረገ። ላለፉት 23 ዓመታት በሊቀ መንበርነት የመራው በዚህ መልኩ ነው፡፡ አሁን ያንን ህገ-ደንብ ወደ ቦታው መልሰናል።
የድርጅቱ ሊቀ መንበርና ምክትሉ ከሁለት ጊዜ በላይ ሊመረጡ አይችሉም ማለት ነው። በሌላ በኩል፤ የመዋቅር ጉዳይንም ትንሽ ለውጠናል። ለምሳሌ የስራ አስፈጻሚ  ኮሚቴ በፊት ስምንት ነበር። አሁን ዘጠኝ እንዲሆን ወስነናል። ተቀዳሚ ም/ሊቀ መንበር እንዲኖረውም አድርገናል። እነዚህን ነው ያሻሻልነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የስም ወይም የአርማ ለውጥ አላደረግንም፡፡
በምርጫው የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላችሁ እየገለጻችሁ ነው--?
 እኛ አስቀድመን የገጠመንን ችግር አስረድተናል። በወቅቱም ምርጫ ቦርድ ያሳየን ምላሽ ቀና ነበር ብለን እናምናለን። ጠቅላላ ጉባኤ አድርገን፣ አመራር መርጠን እቅድ ስናዘጋጅ “በልዩ ሁኔታ እንድትፈቅዱልን” ብለን ጠይቀን ነበር። አሁን ጉባኤውን ጨርሰናል፤ ዶክመንቶች እያስገባን ነው። እነዚህን አይቶ ቦርዱ ጉባኤያችንን አፅድቆልን ጊዜ ከሰጠን ወደ ምርጫው እንገባለን። የሚፈለገውን ያህል ባይሆን እንኳን እጩዎች እናስመዘግባለን። ህዝብም ድምፅ አልባ ሆኖ ከምርጫው እንዳይገለል ግፊት እያሳደረብን ነው። አሁን ባለንበት ሁኔታ እጩዎችን ማቅረብ አስቸጋሪ ነው። ችግሩ ቀላል አይደለም። አንዳንዶች እስር ቤት ናቸው፤ ሌሎች የተለያዩ ጫና ውስጥ ናቸው። እና ቀላል አይሆንም ችግሩ። ነገር ግን  ተሳትፎአችንን በሚያረጋግጥ ሁኔታ ወደ ምርጫው እንገባለን ብለን እናስባለን። ከምርጫ ራስን የማግለል ሃሳብ የለንም፤ ገብተን ለመወዳደር ነው ፍላጎታችን፡፡ በምርጫው ሳንሳተፍ ከቀረን ግን ያው በራሳችን ችግር ነው ማለት ነው። በውስጥ ጉዳይ ተይዘን ለምርጫ ሳንዘጋጅ በመቆየታችን የተፈጠረ ነው። ይህ ሁሉ ጣጣ የመጣብን በማንም ሳይሆን በራሳችን የውስጥ ችግር ነው።
ከወዲሁ “የብልፅግና ተለጣፊዎች” የሚል ውንጀላ እየተሰነዘረባችሁ ነው። እናንተ ተለጣፊ አለመሆናችሁን እንዴት ነው የምታረጋግጡት?
አሸናፊ ያልሆነ ሃሳብ ያለው ሰው ሁሌም ጉልበቱ፣ ፍረጃና ስም ማጥፋት ላይ ነው። ማደናገሪያዎችን በማሰራጨት ብዥታን መፍጠርና ማወናበድ አላማው አድርጎ ይንቀሳቀሳል። በቀጣይ ሊገጥመን የሚችለው ይኸው ችግር ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ዘመዶቻችን እንዳይቀርቡን ቅስቀሳ ሊደረግብን ሁሉ ይችላል። ግን እውነታው እኛ ዘንድ ስላለ ሁሉም እያደር ይረዳዋል። በነገራችን ላይ ትናንት ኦፌኮን ለመበተን ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችን ተጠቅመው ነው፣ እኛ ላይ ዘመቻ የተከፈተው። የእነ ዶ/ር መረራ ቢሮን ሰብረው የፓርቲያቸውን ስም ከነጠቁ ሰዎች ጋር ነው፤ ዛሬ በኦነግ ስም በእኛ ላይ ዘመቻ የተከፈተው። ይህ እንግዲህ የፖለቲካ አሻጥርና የተንኮል አዙሪት አካል ነው። ዝምታን መምረጣችንና ለሁሉም ምላሽ አለመስጠታችን ተለጣፊ ሊያስመስለን ይችላል። ነገር ግን ተለጣፊዎች ልንሆን አንችልም።
ለተለጣፊነት ባህሪያችንም አይፈቅድም። በኦሮሞ ጉዳይ፣ በዲሞክራሲ ጥያቄ ፣ በህዝቦች ነፃነት ላይ ከማንም ጋር አንደራደርም። ይሄን በምንልበት ጊዜ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር የሌሎች ህዝቦችን ነጻነትና እኩልነት ለማረጋገጥ ከሚታገሉና በፖሊሲ ከሚቀራረቡን አካላት ጋር አንሰራም ማለት አይደለም፤ ከግለሰቦችም ጋር ጭምር እንሰራለን፡፡ የዚህ ድርጅት አመራር የነበሩ፣ አሁን በግል የሚንቀሳቀሱ አሉ። ከመንግስት አካልም ጥሩ አስተሳሰብ ያላቸው ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነሱም ጋር ቢሆን መልካም ግንኙነት እንዲኖረን እንፈልጋለን። ከማንም ጋር ፀበኛ መሆን አንፈልግም።
በሰላም አብሮ መኖርን፣ ዲሞክራሲን ማጎልበትን መርህ አድርገን ነው የምንቀሳቀሰው። ከኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር አብረን እንሰራለን፤ የኦሮሞን መብት ለማስከበር ከሚሰሩና ካመንባቸው የመንግስት ሰዎችም ጋር እንሰራለን። ከሁሉ ጋር እየተጋጨን መኖር አንፈልግም። ሁልጊዜ ስሞታና ቅሬታ እያሰማን ብቻ መቀጠልም አንሻም፡፡ ከእንግዲህ ህዝባችን ከዚህ ወጥቶ ወደ ከፍታ እንዲሸጋገር ነው በትጋት የምንሰራው፡፡

Read 2648 times