Print this page
Saturday, 18 August 2012 12:44

“የግድግዳ ጥብሶች” - በአውቶብስ ተራ

Written by  ዘካርያስ አትክልት
Rate this item
(2 votes)

ፀሐይ በማትጠልቅበት የአውቶቡስ ተራ መንደር፤ ቀን ከሌት እልፍ የሰው አይነት ይተላለፋል ወይም ይርመሰመሳል፤ ይጎለታል ወይም ይሯሯጣል፤ ይሰራል ወይም ይሰርቃል። “ያውቶቢስ ተራ” ህይወት እረፍት የለሽ ቢሆንም፤ እንደ ሰዓቱ ሁኔታ የሰዉ አይነት ይለያያል። ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በየአቅጣጫው ብቅ ብቅ ብለው፤ ጥግ ጥጉን የሚያጥለቀልቁት ሴቶች ናቸው - የአውቶቡስ ተራ እና የአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት አጥሮች፣ ግንቦችና ግድግዳዎች በሴቶች ተወርሮ ያመሻል፤ ያድራል። ጉስቁል ያሉና ነጠላ ጣል ያደረጉ፤ በጅንስ የተወጠሩና ቱታ የደረቡ፤ እንደ አየር ሁኔታውም ብጣሽ ሸሚዝና ከዳሌ አልፋ ጭን የማትሸፍን አጭር ቀሚስ.. የሴቶቹ አለባበስ ይለያያል። በዕድሜና በአቋቋምም ይለያያሉ። ዞር ዞር ብላችሁ ተመልከቱ። ጋቢ ደርበው የቆሙና ጠና ያሉ ባልቴቶችን በየቦታው ታያላችሁ። ከ13 እና ከ14 አመት ባልዘለለ እድሜ ላይ ሆነው እየተሳሳቁና ሲጋራ እየመጠጡ የሚጫወቱ ህፃናትም ሞልተዋል። ወጣቶቹ ደግሞ እጅግ ብዙ ናቸው። ህፃን፣ ወጣትና አዋቂ ሴቶች... ለዝሙት ንግድ ሚሰማሩበት የንግድ ቦታና የንግድ ሰዓት ነው - የአውቶብስ ተራ ምሽት።

የህይወትን ጣዕም በቅጡ ያላየች የ14 ዓመት ታዳጊ፣ በቻይና ጅንስ ተወጥራ፤ ዓይኗን ለገበያ ክብልል ክብልል ስታደርግ ቢያዩ ሆድዎ ይገለባበጣል - “አንዲት ፍሬ ልጅ” በሚል ስሜት። ሌላዋ ታይትና አጭር ቀሚስ አድርጋለች። አለፍ እንዳሉ በአለባበስም ሆነ በሁኔታቸው እናት ከመሰሉ ሴትዮ ጋር ይፋጠጣሉ። አንጀትዎ ይንሰፈሰፋል። “እርሶም! እንዴት ተደርጐ?...” ምናምን እያሉ ያልፋሉ።

ጌታዬ፤ ቅንዝረኛ ሁላ እንቡጥ እንቡጥ ህፃናትን እየሞጨለፈ ሲወስድ ያመሽና፤ እኩለ ሌሊት ላይ ተራው በእድሜ ጠና ወዳሉት ሴቶች ይሆናል። “እንዴት?” ማለት የማይቀር ነው። ይሄውልዎት ጌታው፤ እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት፤ ለጋ ለጋ የሆኑት የጎዳና ሴቶች የወሲብ ገበያው ይደራላቸዋል። ከሶስትና ከአራት ሰዓት በኋላ ግን፤ በመጠጥ አቅሉን የሳተ ሁላ እየመጣ ያገኘውን ሴት እየጎተተ ይሄዳል - ወጣት ትሁን አሮጊት መለየት የለም።

የሴቶቹ አሰላለፍ በመላ ነው። የአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ዋና በር አለ አይደል? ከበሩ በስተግራ በኩል በእድሜ ጠና ያሉትና ባለባበስ የደከሙት ሴቶች ይደረደራሉ፤ ወይም ጥግ ጥጋቸውን ይዘው ይሰለፋሉ። ፏ ያሉትና ልጅ እግሮቹ ደግሞ በስተቀኝ ይሆናሉ። ለዘዴ ነው። በስተቀኝ በኩል፤  ጨረቃን በሚያካክሉ የመንገድ መብራቶች አካባቢው ሆጭ ብሏል - ልጅ እግሮቹና በማራኪነታቸው የሚተማመኑት ሴቶች፤ በዚሁ ብርሃን ዕንቡጥነታቸውን አድምቀው ለተመልካች ያሳያሉ። በስተግራ በኩል ያሉት መብራቶች ግን ማዶ ለማዶ የተዘረዘሩ ደብዛዛ የሰፈር አምፑሎች ናቸው። ጠና እና ደከም ላሉ ሴቶች ድንግዝግዙ ብርሃን ይስማማቸዋል።

“የፈጣሪ ያለህ” ብለው አስፓልት ሲሻገሩ፤ ሰልባጅ ጫማና ሰልባጅ ልብስ ሚሸጡ ነጋዴዎች በዜማ ገበያተኛ ሲጠሩ ይሰማሉ። “ጫማ በሰላሳ! ጫማ በሰላሳ! አልሰማንም አላየንም እንዳትሉ! ጫማ በሰላሳ!” ይላሉ በዜማ። ያስፖልቱ ጠርዝ በሙሉ በክንዴ ቡቲኮች (ክንዳቸው ላይ የሰልባጅ ልብሶች በሚይዙ ነጋዴዎችና ጫማ ነጋዴዎች)... ተሞልቷል። የእግረኛ መንገድ ልያዝ ብለው ወደ ዳር ቢወጡም ዋጋ የለውም። ግራና ቀኝ፤ ቀን ሲሰሩ ውለው ማታ በታገዙት ካፌዎች፣ ቡቲኮችና ሱቆች ተርታ አሁን ሴቶች ተደርድረዋል - አንዳንዶቹ የኤለመንታሪ ተማሪዎችን ያካክላሉ። አንጀትዎ ኩምትር ሲል ይሰማዎታል። ትንሽ አለፍ ሲሉ ደግሞ፤ በአንዲት ማዳበሪያ ውስጥ ሁለት የጐዳና ተዳዳሪ ህፃናት ተጣብቀው ተኝተዋል። ብርዱንና ነፋሱን እንዴት እንደሚችሉት እንጃ! የነፋስ መከለያ ያለበት ቦታ፤ በወጣት የጎዳና ተዳዳሪዎች ተይዟል - በማዳበሪያ ውስጥ ተሸጉጠው ተርታውን ተኝተዋል።

ለወሲብ ንግድ በተርታ ከቆሙት ሴቶች አጠገብ፤ በተርታ የተኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች፤ ከዚያው አለፍ ብለው ደግሞ ማታ ማታ የሚበቅሉ ትንንሽ የጎዳና “ዱንኳኖች” በየቦታው ይታያሉ። “ድንኳን” ሲባል፤ የምር ድንኳን እንዳይመስልዎ።

ጨዋታውን ላስታውስዎት።

የአንድ ታዋቂ ሙዚቀኛ አባት ሞተው፤ ተስፋዬ ካሣ ለቅሶ ለመድረስ ይሄዳል። ተስፍሽ በተጠቆመው መንገድ ቢፈልግ ቢፈልግ፤ ለቅሶ ቤቱን ድንኳን ያጣዋል። የሱቅ መስኮት አጠገብ ተሰብስበት ወደሚያወሩ ጐረምሶች ጠጋ ብሎ ጠየቃቸው - “የእገሌ አባት ለቅሶ የት ነው?” በማለት።

“እንዴ! ተስፋዬ አለፍከውኮ፤ ያውና!”  ብለው ሲጠቁሙት አካባቢውን ቃኘ። ምንም የለም። አንዲት ትንሽዬ ዝንጥ ያለች ድንኳን ብቻ! “ይቺ ድንኳን ናት?” ብሎ ሲጠይቅ ሁሉም በአንድ ድምጽ “አዎ” አሉ።

“አይ እኔኮ ኢትፍሩት መስሎኝ ነው” አለ ተስፍሽ። … Made in አረቄ ቤት

ጌታዬ ገና ከምሽቱ አምስት ሰዓት እኮ ነው። መሸብኝ ምናምን ይላሉ እንዴ! አውቶብስ ተራ’ኮ የፀሐይ መውጣትና መግባት አያገባትም። ሁሌም ግርግር ነች። ድንገት ሲዋከቡ እንቅፋት ቢመታዎ “እኔ ልደፋልህ!”፤ “አይዞህ ወንድሜ!” የሚልዎት አያጡም - ከምሽቱ አምስት ሰዓት!

የነሐሴ ንፋስና ዝናብ ሀይለኛ ነው። ብርዱ ካንገበገብዎት፤ ችግር የለም ከፈለጉ ሻይና ቡና፣ ትኩስ ድንችና ሾርባ መውሰድ ይችላሉ። በእኛ ሰፈር... 24 ሰዓት የሚሰሩ ካሬዎች አሉ።

የእርስዎ ነገር... 24 ሰዓት ሚሰሩት የቦሌ፣ የሃያሁለት፣ የፒያሳ ካፌዎች ብቻ ይመስልዎታል። እኛ ጋም ሞልቷል። ያውም ካፌ ቢሉ ካፌ መሰልዎት? ካፌዎቻችን በStyle ከሌሎች ይለያሉ። ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት እነ ኮከብ ካፌ፣ አብርሃም ካፌ፣ ናርዲ ካፌ፣ Oldies ካፎ፣ ፋሲካ ኬክ ቤት …በታላቅ ትጋት ያገለግላሉ። ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ግን እነዚህ ካፌዎች ዝግ ናቸው።

ሌሎች ተተኪ ካፌዎች በጨለማ ይወለዳሉ - አሌክስ ካፌ ..(ፋሲካ ብስኩት ቤት ጐን)፤ አዩ ካፎ (ሚጣ ሆቴል ጐን) እና ሌሎች ስም የለሽ ካፌዎች። የምሽት ካፌዎች ሙድና አሰራር የተለየ ነው። ካፌዎቹ የሚሰናዱት ማዳበሪያና ላስቲክ በመወጠር፣ ከግድግዳ ጋር አስታክኮ እጥር ምጥን ያለች የሸራ ቤት በመስራት ነው። በውስጧ ሦስት አግዳሚዎች የ“በ” ቅርፅ ሰርተው ይሰደራሉ። በመሃላቸው አንድ አግዳሚ ይገባል - ጠረንጴዛ መሆኑ ነው።

መቼም እዚህ ካፌ ገብተው ብላክፎረስት ወይም ካፑቺኖ ምናምን ለማለት አያስቡም። በሀገርኛ ስሞች የሚጠሩ ነባር የአገር ምርቶች ብቻ ናቸው ለመስተንግዶ የሚቀርቡት። አምባሻ፣ ድፎ፣ ብስኩት፣ ዳቦ፣ እንቁላል …

በመዳፍዎ ቸብ ቸብ አድርገው፤ እንቁላል ፍርፍር ወይም እንቁላል ስልስ እንዳይሉ። እንቁላል ያልክዎትኮ ቅቅሉን ነው (ይሄ ዶሮ ወጥ ውስጥ ደረቱን ገፍቶ ሚታየው)። እንቁላሉ ይቀርብልዎታል፤ ቅርፊቱን ላጥላጥ አርገው ሚጥሚጣ ጨምረው ዋጥ ማድረግ ነው።

ጌታዬ አሁንም ብርዱን አልቻሉትም? አይዞን! ከካፌው እንደወጡ መንገድዎን ሲቀጥሉ፤ በአዲስ ከተማ ት/ቤትና በዳንኤል ሆቴል መካከል ትኩስ ትኩስ ነገሮችን ያገኛሉ።

በትልቅ ማንደጃ ላይ የተጣደ ትልቅ ድስት ውስጥ የበቆሎ እሸት ሲፍለቀለቅ ያያሉ - በላስቲክ ታሽጎ። በሁለት ብር ገዝተው እንፋሎቱን እፍ እፍ እያሉ መግመጥ መጋጥ ነው። “ኧረ ወዲያ! እኔ ጥሬ መጠርጠር አልወድም” ካሉም ትኩስ ድንች በሁለት ብር እዛው አስከትፈው በሚጥሚጣ መመገብ ይችላሉ። ይሄም ካልተመችዎት እየተቆላ ካለው ሽንብራ እፍታውን በሽልንግ መግዛት ነው። እንደፍላጎትዎ እንዲያማርጡ ቀርብዎለታል - የተቆላ ሽንብራ፤ የተቀቀለ ድንች፤ የተጠበሰ በቆሎ...

በት/ቤቱና በአውቶብስ ተራ አጥር አካባቢ ግድግዳ ተደግፈው የሚቆሙትን ሴቶች፤ “የግድግዳ ጥብስ” ይሏቸዋል። ህፃን፣ ወጣት፣ ወደ አርባዎቹ እድሜም የገፉ ብዙ ሴቶች … አይነታቸው ቢለያይም፤ ብዙዎቹ የክፍለ ሀገር ሰዎች ናቸው። የ”ሀገርኛ” ሁኔታ ይታይባቸዋል። በህይወት ምሬት፣ በሞራል ውድቀት፣ በተስፋ እጦት የጨፈገገ “ሀገርኛ” ሁኔታ፤ በሴቶቹ ፊት ላይ በግልፅ ይታያችኋል - ማየት ከፈለጋችሁ። ለአንዳንዶቻችን፤ በየጎዳናው የምናያቸው የምሽት ሴቶች ከሌላ አለም የመጡ ሴቶች ሊመስሉን ይችላሉ። ግን የኛው ናቸው።

አብረውኝ ከሚሰሩ ሁለት መምህራን ጋር ስራ አምሽተን በታክሲ ልሸኛቸው ወደ አውቶብስ ተራ ስናዘግም ያጋጠመኝን ልንገራችሁ። አንደኛው የፈረንሳይ ሰፈር ልጅ ነው፤ ሌላኛው የአስኮ። የአስኮውን ባልደረባችን ታክሲ እንዳስያዝን፤ በአውቶብስ ተራው አጥር ጥግ “ቲቸር ቲቸር” የሚል ድምጽ ሰማን፤ ሁለታችንም ዞርን። ልጅቷ በፈገግታ እየሮጠች መጣች። ግን፤ ድንገት አይታን በደመነፍስ “ቲቸር፣ ቲቸር” ብላ መጣራቷ ሳይቆጫት አልቀረም። ፈገግታዋ ጠፍቷል። ሁለታችንም እናውቃታለን፤ ተማሪያችን ነበረች። ሁለታችንም ታውቀናለች፤ አስተማሪዎቿ ነበርን። ስናያት ግራ ተጋብተናል... በዚህ ሰአት ምን ታደርጊያለሽ? እዚህ ምን ልታደርጊ መጣሽ? ... ጥያቄዎቹን መጠየቅ አላስፈለገንም። እንባ እየተናነቃት ነው። ስለትምህርቷ ጠየቅናት።

“ትምህርትሽን ለምን አቋረጥሽ? በዚህ እድሜሽ ያልተማርሽ መቼ ልትማሪ ነው?” አልናት ተራ በተራ። እንባዋ ተዘረገፈ።

“አክስቴ አባረረችኝ። ሌላ ዘመድ የለኝም፤ የሚያስተምረኝ ... ምን ላድርግ? ምን ልሁን?”

ቤተልሄም፤ እናትና አባቷ የሞቱባት ገና በልጅነቷ ነው። አክስቷ እኔ ላሳድጋት ብላ አመጣቻት። ከሰባት ዓመቷ ጀምራ፤ አክስቷ ቤት አደገች። የአክስቷ ባል ግን በዚህ ደስተኛ አልነበረም። በሰበብ ባስባቡ በነገር ይኮረኩማታል። አክስቷም ቀስ በቀስ ተለወጠች። አንድ ቀን ላይብረሪ አምሽታ ወደ ቤት ስትገባ “አንቺ ዱርዬ ውጪልኝ ከቤቴ” ብላ ፈረደችባት - የአስራ አምስት ዓመቷ ቤተልሄም ላይ። ቤተልሄም በትምህርቷ ጥሩ ተማሪ እንደነበረች እኛ መምህራኗ እንመሰክራለን።

በአውቶቡስ ተራ አካባቢ ያነጋገርኳት ሌላዋ የጎዳና ሴት … ሸዋዬ ትባለላች። ከጐጃም ስራ ፍለጋ ነው ወደ ሸገር የመጣችው። በጓደኞቿ ግፊት የወሲብ ንግድን ተቀላቅላለች። ስታወራ ፈገግታ በፈገግታ ነች። ጥርሷ ብቻ ሳይሆን ዓይኗም ጉንጯም ይስቃል። ትንሽ ካወራች በኋላ ግን ሁለመናዋ ይጨፈግጋል። “ድንግልናዬን ራሱ ጓደኞቼ ተደራድረው ነው ያሻሻጡኝ። የማደርገውን ሳጣ ገባሁበት። አሁን ግን ሰልችቶኛል። የማንም መጫወቻ ሆኜ እንጀራ ከመብላት ሞት ይሻላል። ስራ ለማግኘት ዘመድ ያስፈልጋል። እኔ ብቸኛ… (ድምጿ መቆራረጥ ጀመረ.. ሳግ ተናነቃት) ...ማንም የለኝም ... ሁለት ዓመት ሙሉ የማንም መጫወቻ ሆንኩ...”

በፈገግታ የጀመረችውን ወሬ፤ በለቅሶና በእንባ አቋረጠችው።

ሌላዋ የአውቶቡስ ተራ የጎዳና ሴት … ዕድሜያቸው ከአርባ በላይ ይሆናል። ወ/ሮ የትምወርቅ ይባላሉ። ሦስት ልጆችና አንድ የልጅ ልጅ አላቸው።

“የባሌ ድብደባ ሰለቸኝ - ሁሌ ጭቅጭቅ፣ ሁሌ ንትርክ። ሀገሬን ጥዬ ወጣሁ። አዲሳባ የስራ ሀገር ነች ይላሉ። ግን ለደካማ አትሆንም። አስም አለብኝ፤ የማድቤት ስራ አልችልም። ይሄው እንዲህ ሆንኩልህ”

ፈራ ተባ እያልኩ፤ “እንደው ወደ እርስዎ የሚመጡት ምን ዓይነቶቹ ናቸው?” ስል ጠየኳቸው።

“ከዕኩለ ሌሊት በኋላ በመጠጥ ራሳቸውን የሳቱ ሰካራሞችን ብቻ ነው የምጠብቀው። አሁን ግን ወጣቱም ያሮጊቶች ምንምን ይላል ብሎ ነው መሰል መምጣት ጀምሯል” አሉ እያፈሩ እያላገጡ።  ባውቶቢስ ተራና በአካባቢው መንደሮች (ኳስ ሜዳ፣ አብነት፣ መርካቶ፣ ሰባተኛ፣ ጐጃም በረንዳ) ተወልዳችሁ ለትልቅ ቁም ነገር የበቃችሁ በርካታ ሰዎች አላችሁ። እናንተ የሀገር ተምሣሌት የሆናችሁ መመኪያዎቻችን... ምነው ቸል ማለታችሁ?

መቼም እዚያ አካባቢ ተወልዶ ሲያድግ፤ ያውቶቢስተራን የህይወት ትሩፋት ያላየ፣ ያልኖረና ያልቀመሰ ልጅ ይኖራል ማለት ዘበት ነው። ታዲያ ምነው... ከፍ ከፍ ብላችሁ ትልቅ ደረጃ ላይ ስትወጡ ዝም ማለታችሁ? መናገርማ ትናገራላችሁ፤ “ሀገሬ፣ ሀገሬ...” ስትሉ እንሰማለን። ምነው በተግባር ዝም ማለታችሁ?

ሀገር ማለትኮ አንተ ነህ፤ አንቺ ነሽ። ሀገር ማለትኮ እኔ ነኝ፤ እሷ ነች። የሀገር ፍቅር ማለትኮ የእኔ፣ የአንተ፣ ያንቺ፣ የሷ መዋደድ ነው። በ13 ዓመት ህፃንነታቸው... የህይወትን ውበትና ጣዕም መለየት በማይችሉበት ጨቅላ ዘመናቸው፣ በችግር አለንጋ ተገርፈው በመከራ ጦር የሚደሙ ወገኖቻችን፤ ዞሮ የሚያያቸው ሲያጡ ምን ይባላል? ሰውን አስተባብሮ ራሱ ተባብሮ ለወገኖቹ ተስፋ የሚያሳይ አምሳለ ሙሴ ከወዴት ይገኛል? ባንዱ ችግር አንዱ እየተጽናና፣ ያንዱ የመከራ ክምር ለሌላው መከረኛ መጽናናት ሲሆን ውድቀት እንጂ እድገት እንዴት ይመጣል? አቅሙ ያላችሁ፤ በሰዎች ተስፋና ለውጥ የምትደሰቱ... አውቶብስ ተራ ሁሌ ምሽት ላይ “የግድግዳ ጥብሶቿን” አቅፋ ትጠብቅዎታለች። አድኗት ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!

 

 

Read 9036 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 12:47