Wednesday, 10 March 2021 00:00

ባለፈው አመት በ29 አገራት፣ 155 ጊዜ ኢንተርኔት ተቋርጧል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በመላው አለም በሚገኙ 29 አገራት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ከ155 ጊዜያት በላይ ሆነ ተብሎ እንዲቋረጥ ወይም ፍጥነቱ አዝጋሚ እንዲሆን መደረጉን አክሰስ ናው የተባለ ተቋም ያወጣውን አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
በአመቱ በብዛት የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠባትና ፍጥነቱ አዝጋሚ እንዲሆን የተደረገባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ህንድ መሆኗን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአገሪቱ በአጠቃላይ ለ109 ጊዜያት ያህል ክስተቱ መፈጸሙንና 96ቱ ህንድ በምታስተዳድረው የካሽሚር ግዛት ውስጥ መደረጉን ያብራራል።
በአመቱ የኢንተርኔት አገልግሎት በየመን 6 ጊዜ፣ በኢትዮጵያ 4 ጊዜ፣ በዮርዳኖስ 3 ጊዜ ያህል መቋረጡን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ በቤላሩስ፣ ቻድ፣ ጊኒ፣ ኬንያ፣ ፓኪስታን፣ ሱዳን፣ ቶጎና ቬንዙዌላ ደግሞ በተመሳሳይ ለ2 ጊዜያት መቋረጡንም አክሎ ገልጧል፡፡
ከአለማችን አገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የኢንተርኔት አገልግሎትን በመዝጋት ቀዳሚነቱን የያዘችው ማይንማር መሆኗን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአገሪቱ በተለያዩ ግዛቶች ግጭቶች መቀሰቀሳቸውን ተከትሎ አገልግሎቱ ለ19 ወራት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ እንደነበርም ገልጧል፡፡
በአለማችን አገራት በአመቱ ከተፈጸሙት 109 የኢንተርኔት አገልግሎት ማቋረጦች መካከል 85 ያህሉ የተፈጸሙት ለጥንቃቄ ሲባል እንደሆነ የአገራቱ መንግስታት እንደሚናገሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ተቋሙ ባደረገው ጥናት ግን 80 ያህሉ ከፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ 17 የሚሆኑት ከምርጫ፣ 14 ያህሉ ደግሞ ከተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን አመልክቷል፡፡
በአመቱ በተለያዩ አገራት የተከሰቱት የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጦች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከስራቸው፣ ከትምህርት፣ ከመረጃና ከግንኙነት እንዲስተጓጎሉ ማድረጋቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በተለይም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴ በተገደበበትና መረጃ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወሳኝ በሆነበት ወቅት የተፈጸሙ መሰል ድርጊቶች አግባብነት የሌላቸውና ከፍተኛ ጉዳት ያስከተሉ መሆናቸውን ገልጧል፡፡

Read 2499 times