Monday, 08 March 2021 00:00

የአውሮፓ ሱፕር ሊግ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

• ከተጠነሰሰ 30 ዓመታት አልፈዋል፤ ኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ቀውስ ዳግም ተቆስቁሷል
   • ዋንኞቹ አስተባባሪዎች ሪያል ማድሪድ፤ ባርሴሎናና ባየር ሙኒክ ናቸው፡፡
   • በ2022/ 23 እንዲጀመር እስከ 3.4 ቢሊዮን ዩሮ እለቃለሁ JP MORGAN
   • የአህጉሪቱን እግር ኳስ የሚያዳክም ነው UEFA
   • በሱፕር ሊግ የሚጫወት ዓለም ዋንጫን አይሰለፍም FIFA
   • የአውሮፓውያን አኗኗር ዘይቤ እግር ኳስ ለሀብታሞች እና ለኃያላን ብቻ እንዲሆን አይፈቅድም European commission


              የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎችና ክለቦቻቸው የኮሮና ቫይረስ በፈጠራቸው ውስብስብ ችግሮች እስከ 8.64 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ አጥተዋል። ከ360 በላይ ክለቦች በአውሮፓ እግር ኳስ ህልውናቸውን ለማቆየት እስከ 6.8 ቢሊዮን ዩሮ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልጋቸው እየተወሳ ሲሆን፤ በትልልቅ ክለቦች ላይ የተፈጠረውን የፋይናንስ ቀውስ ለመቋቋም አማራጭ መፍትሄዎችን እየቀረቡ ናቸው፡፡ የአውሮፓ ኃያላን ክለቦች ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አስተዳደር በመውጣት  በራሳቸው ውድድር ለመስራት የነበራቸው እቅድም ዳግም ተቆስቁሷል፡፡  ይህ የስፖርት አድማስ አጭር ዘገባ የአውሮፓ ሱፕር ሊግ ምስረታ ሃሳብን እና የፈጠረውን ውዝግብ የሚዳስስ ነው፡፡
ኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ቀውስ ዳግም ተቆስቁሷል
የአውሮፓ ሱፕር ሊግ በሚል ስያሜ በትልልቅ ክለቦች ልዩ ውድድር የመመስረቱ ሃሳብ ከተጠነሰሰ 30 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በመላው አውሮፓ የሚገኙ ሃብታምና ስኬታማ ክለቦችን የሚያሰባስብ አህጉራዊ ሊግ ሲሆን በተለይ ከ1990ዎቹ ወዲህ  ባለድርሻ አካላቱን ሲያወያይና ሲያወዛግብ መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከጅምሩ ብዙ ደጋፊዎችን ያፈራ እቅድ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወዲያውኑ ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻለም። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (FIFA) እና የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (UEFA) ከመነሻው ውድቅ ሲያደርጉት ‹ተገንጣይ ሊግ› መመስረት አይቻልም በሚል አቋማቸው ነበር፡፡ በ1998 እ.ኤ.አ ላይ የጣሊያኑ ኩባንያ ሚዲያ ፓርትነር በሱፕር ሊጉ የምስረታ እቅድ ላይ ጥልቅ ምርመራ በማከናወን ለዓለም አስተዋውቆታል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ወዲያውኑ የወሰደው ርምጃ የራሱን አዲስ የሊግ መዋቅር መፍጠር ሲሆን  የአውሮፓ ክለቦች አሸናፊዎች አሸናፊ (ካፕ ዊነርስ ካፕ) ብሎ ሲያካሂድ የቆየውን ውድድር ወደ አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በመቀየር በአዲስ የውድድር ስርዓት  ሱፕርሊግን ለማቋቋም የነበረው ፍላጎት አክስሞታል፡፡
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተመስርቶ ለ10 ዓመታት ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ግን አሁንም  የሱፕር ሊግ ምስረታ ሃሳብ በድጋሚ ተቆሰቆሰ። የሪያል ማድሪዱ ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ትልልቅ የአውሮፓ ክለቦች ራሳቸው የሚያስተዳድሩት ሱፕር ሊግ ያስፈልጋቸዋል የሚል አቋማቸውን በማንፀባረቃቸው ነበር፡፡ ከሻምፒዮንስ ሊግ ይልቅ የምርጦች ምርጥ የሆኑ የአውሮፓ ክለቦች  የአውሮፓ ሱፕር ሊግ በሚል ስያሜ እንዲወዳደሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡  የፍሎረንቲኖ ፔሬዝ አቋም ይፋ ከሆነ በኋላ  አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን ሲሰጡ የአውሮፓ ትልልቅ ክለቦች በገቢ ክፍፍል ዙርያ ያሉባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ  በአስር ዓመታት ውስጥ (እስከ 2019) ሱፕር ሊግን እንደሚመሰርቱ ተነበዩ፡፡ ከቬንገር በኋላ በ2012 እኤአ ላይ ሆላንዳዊው ክላረንስ ሲዶርፍ የአውሮፓ ሱፕር ሊግ መመስረትን እደግፋለሁ በሚል የተናገረ ሲሆን፤ ስኮትላንዳዊው ጎርደን ስታራቸን አንጋፋዎቹ ክለቦች ሴልቲክና ሬንጀርስ ከማይመጥናቸው የአገራቸው ሊግ ተላቅቀው ከ38 በላይ የአውሮፓ ክለቦች የሚመኙትን ሱፕር ሊግ እንደሚቀላቀሉ እምነታቸው መሆኑን  ገልፀዋል፡፡ በ2016 እኤአ ላይ ደግሞ 4ቱ የእንግሊዝ ታላላቅ ክለቦች ቼልሲ፤ አርሰናል፤ ሊቨርፑልና ማንችስተር ዩናይትድ  ሱፕር ሊግን በሚቀላቀሉበት እቅድ ላይ በይፋ ምክክር ጀምረዋል፡፡
ሱፕር ሊግን የመመስረት አጀንዳ በድጋሚ ማገርሸቱ ያሳሰበው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር UEFA በስሩ ከሚያስተዳድራቸው የአባል አገራት ሊጎች እና ክለቦቻቸው ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል  16 ትልልቅና ስኬታማ ክለቦችን በሁለት ምድብ በመክፈል በልዩ ሊግ እንዲጫወቱ አደርጋለሁ የሚል መግለጫ እስከመስጠት ደርሷል፡፡ በ2018 እኤአ ላይ ፉትቦል ሊክስ Football Leaks አዲስ አህጉራዊ የክለብ ውድድር የአውሮፓ ሱፐር ሊግ በሚል ስያሜ  ከ2021 እ.ኤ.አ. ጀምሮ  ለማካሄድ በድብቅ ምምክሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን የሚጠቁም ልዩ ዘገባ በድህረ ገፁ ሲያሰራጭ፤ እንደ ማንችስተር ሲቲና  ፓሪስ ሴንትዠርሜን አይነት ክለቦች የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የፋይናንስ ህጎችን ባለማክበር  የሚንቀሳቀሱት ወደ ራሳቸው የሱፕር ሊግ አስተዳደር በማተኮራቸው ነው የሚል ትንታኔ ሰጠ፡፡ የአውሮፓ ሱፕር ሊግ የመመስረት እቅድን በልዩ ክትትል እየዘገበ የሚገኘው ታዋቂው የጀርመን ሚዲያ ዴስፒግል ከ3 ዓመታት ይፋ ባደረገው የመጀመርያ ዘገባው  16 የአውሮፓ ክለቦች በአጀንዳው መስማማታቸውን በመጠቆም እቅዳቸውን እስከ 2021 እኤአ ተግባራዊ ያደርጉታል ብሎ ነበር፡፡ የአውሮፓ ሱፕር ሊግን የመመስረት እቅድ ላለፉት 30 ዓመታት እንዲህ ሲያነጋግር ቆይቶ ኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ቀውስ ዳግም ተቆስቁሷል፡፡  
ዋንኞቹ አስተባባሪዎች ሪያል ማድሪድ፤ ባርሴሎናና ባየር ሙኒክ ናቸው
የአውሮፓ ሱፕር ሊግን ለመመስረት ፍላጎት ያላቸው በአውሮፓ እግር ኳስ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ ሃብታም  ክለቦች ናቸው፡፡ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በመውጣት በልዩ ሁኔታ የአውሮፓ ሱፕር ሊግን ለማስተዳደር የተነሱት በገቢ ክፍፍል የሚገባቸውን ድርሻ ለመውሰድ በማሰባቸው ነው፡፡ በራሳቸው የሚያስተዳድሩትን የሊግ ውድድር በከፍተኛ ደረጃ በማንቀሳቀስ የሚኖራቸውን ገቢ ማሳደግ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡ በፋይናንስ አቅምና ተወዳዳሪነት ከሚመጥኗቸው ክለቦች ጋር በመስራት  ትርፋቸውን እንደሚጨምሩም አምነዋል። ታላላቆቹ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውስጥ ሲሳተፉ በተለይ  ከብሮድካስት፤ ከስፖንሰርሺፕ እና የተለያዩ ንግዶች የሚገኙትን ገቢዎች ለሁሉም አባል አገራት ክለቦች ሲያካፍሉ መቆየታቸውን ለማስቀረትም ይፈልጋሉ፡፡
በአውሮፓ ሱፕር ሊግ ምስረታ ላይ ዋንኞቹ አስተባባሪዎች የሚባሉት የስፔኖቹ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና እንዲሁም የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ናቸው፡፡ የባየር ሙኒኩ ካርል ሄንዝ ሩሚኒገ ሃብታም ክለቦች ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አስተዳደር ተላቅቀው ራሳቸውን ማስተዳደር አለባቸው የሚል ጠንካራ አቋም ሲያራምድ ቆይቷል፡፡ በ2021 እኤአ መግቢያ ላይ የስፔኖቹ ክለቦች ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና በዝውውር ገበያው አዲስ ተጨዋች ለማስፈረም የሚያውሉት ገንዘብ ማጣታቸውም የሱፕር ሊግ ምስረታውን እንደመፍትሄ ለማሰብ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ሁለቱ የስፔን ክለቦች ገቢያቸው እየወረደና እዳቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሄደው በአገር ውስጥ እና በአህጉራዊ ውድድር የሚገባቸውን ድርሻ አለማግኘታቸው እንደሆነ ይገለፃል፡፡ የሪያል ማድሪድ ፕሬዝዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ከባድ ጊዜ እያሳለፉ መሆናቸው ሲናገሩ  በቀጣይ የውድድር ዘመናት የሚያጋጥሙ ፈተናዎች እንደሚያሰጓቸውም ገልፀው ‹‹እግር ኳስ የበለጠ ተወዳዳሪ፣ አስደሳች እና ጠንካራ እንዲሆን አዳዲስ ሀሳቦችን ይፈልጋል ፡፡›› ብለዋል፡፡ ተሰናባቹ የባርሴሎና ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ማሪያ ባርቶሜው በበኩላቸው  የክለባቸውን የወደፊት እጣፈንታ የሚወስነው በሱፕር ሊግ በመወዳደር የሚገኘው ዘላቂነት ያለው የገቢ ምንጭ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡  በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ሁለቱ የስፔን ሃያል ክለቦች በከፍተኛ ሁኔታ የተመቱ ሲሆን፤ በዚህ የውድድር ዘመን መጨረሻ ላይ ባርሴሎና  እስከ 400 ሚሊዮን ዩሮ   ሪያል ማድሪድም  ወደ 500 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ገቢን ያጣሉ፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚወዳደሩ ክለቦች ባሏቸው ግዙፍ የብሮድካስት ገቢዎች እና ባለቤቶቻቸው ቢሊየነሮች በመሆናቸው በተወሰነ ደረጃ የፋይናንስ ቀውሱን እየተቋቋሙ ቢሆንም እንደማንችስተር ዩናይትድ አይነት ክለቦች ያለባቸው የእዳ ክብር ከ540 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ሆኗል፡፡ በጣሊያን ኤሲ ሚላን፤ ጁቬንትስ እና ኤኤስ ሮማ በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ የውድድር ዘመኑን እያሳለፉ ናቸው፡፡
ከአውሮፓ ሱፕር ሊግ ምስረታ ጋር በተያያዘ በሚሰራጩ  ዘገባዎች መስራቾቹ ተብለው በተደጋጋሚ የሚነሱት ክለቦች ባርሴሎና፤ ሪያል ማድሪድ፤ ባየር ሙኒክ፤ ቼልሲ፤ ሊቨርፑል፤ ማንችስተር ዩናይትድ፤ ጁቬንትስ፤ ፓሪስ ሴንትዠርመንና አርሰናል ናቸው፡፡  እነ አትሌቲኮ ማድሪድ፤ ቦርሱያ ዶርትመንድ፤ ኢንተር ሚላን፤ ሮማና ማርሴይ በሊጉ ተሳታፊነት ተጠቅሰዋል።  በ2021 እኤአ ላይ የአውሮፓ ሱፕር ሊግን ለመመስረት ፍላጎት ያላቸው የአውሮፓ ክለቦች ብዛት 32 መድረሱን የተለያዩ ዘገባዎች አውስተዋል፡፡
በ2022/ 23 እንዲጀመር እስከ 3.4 ቢሊዮን ዩሮ እለቃለሁ JP MORGAN
የአውሮፓ ሱፕር ሊግን የመመስረት እቅድ በአዲስ መልክ ሲቆሰቆስ ከአሜሪካው ግዙፍ የባንክ ተቋም ጄፒ ሞርጋን ጋር በልዩ ፕሮጀክት ለመስራት በድብቅ ስምምነት ተደርጓል የሚሉ ዘገባዎች በስፋት ተሰራጭተዋል፡፡ በ2022/23 የውድድር ዘመን ላይ 20 ክለቦችን በማሳተፍ ሱፕር ሊጉ እንደሚጀመር ያወሱት ዘገባዎች 15 የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች እስከ 3.4 ቢሊዮን ዩሮ በሚያወጣ ፕሮጀክት ለመስራት መወሰናቸውን አመልክተዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋሙና ክለቦች ስምምነት አድገውበታል ተባለው  ባለ18 ገፅ ሰነድ ላይ እንደተጠቀሰው በሱፕር ሊጉ መስራች ሆነው ለሚሳተፉ ክለቦች እያንዳንዳቸው እስከ 357 ሚሊዮን ዩሮ የሚከፈላቸው ሲሆን፤  በእያንዳንዱ የውድድር ዘመን ላይ የሚሳተፉ ክለቦች በነፍስ ወከፍ እስከ 201 ሚሊዮን ዩሮ ሊያገኙ እንደሚችሉ ቃል ተገብቷል፡፡ ክለቦች በአንድ የውድድር ዘመን ከ15 እስከ 23 ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ፤ ከቲቪ መብት እና ስፖንሰርሺፕ የሚገኘውን ገቢ  መስራች ክለቦች 32.5 በመቶውን ሲካፈሉ ሌሎች ደግሞ ሌላ 32.5 በመቶውን ድርሻ የሚጋሩ ይሆናል፡፡በአውሮፓ ሱፕር ሊግ ምስረታ አዲስ  እቅድ መሰረት ብዙዎቹ የአውሮፓ ክለቦች ከገጠማቸው የፋይናንስ ችግር እንዲላቀቁ ጄፒ ሞርጋን ኢንቨስት የሚያደርግ ሲሆን ፈሰስ ያደረገውን መዋዕለንዋይ በጥቂት የውድድር ዘመናት ከብሮድካስት ብቻ በሚገኝ ገቢ መመለስ እንደሚችል እምነት አሳድሯል፡፡
ስጋት እና ተቃውሞ እግር ኳስ በሚያስተዳድሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት
የአውሮፓ ሱፕር ሊግን የመመስረቱ ሃሳብ ገቢያቸው በቀነሰባቸው፤ በብድር ቁልል አደጋ ውስጥ የገቡ እና በከፍተኛ ስኬት የመኒገባቸውን ድርሻ ለማግኘት ባልቻሉ የአውሮፓ ክለቦች ዘንድ ከፍተኛ ጉጉት ቢፈጥርም፤ እግር ኳስን በሚያስተዳድሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን  ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡ የሊጉን ምስረታ በመቃወም  የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ግንባር  ቀደሙ  ሲሆን በስሩ የሚያካሂደውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን የሚያጠፋ ሂደት መሆኑን በመግለፅ ተቃውሞውን እያሰማ ቆይቷል፡፡  በአውሮፓ እግር ኳስ እንቅስቃሴ ላይ ስኬታማና ሃብታም ክለቦች የሚኖራቸውን ሚና እንደሚቀንሰው፤ የብዙ አገራት የውስጥ ሊግ ውድድሮችን እንደሚያዳክም፤ ትንንሽ ክለቦችን ወደ መፍረስ አደጋ ውስጥ እንደሚከት በዝርዝር በመግለፅም ተቃውሞውን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡  የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ከፍተኛ አመራሮች ፤ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎችን የሚያስተዳድሩ ባለድርሻ አካላት፤ የደጋፊ ማህበራትና ሌሎች አህጉራዊ ተቋማትም የሱፕር ሊጉን ምስረታ አይደግፉትም። የአህጉሪቱን እግር ኳስ ያዳክመዋል ሲሉ ትችቶችንም አቅርበዋል፡፡
ጄፒ ሞርጋን ከአውሮፓ ክለቦች ጋር ስምምነት አድርጎበታል የተባለው የአውሮፓ ሱፕር ሊግ የምስረታ ሰነድ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች መሰራጨቱን ተከትሎ  ፊፋ እና በስሩ የሚገኙ ስድስቱም የእግር ኳስ አህጉራዊ ኮንፌደሬሽኖች ይህን የመሰለ እርምጃ በፍፁም እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና የአውሮፓ ኮሚሽንም በአደባባይ ውድቅ አድርገውታል፡፡ ሁሉም አካላት በመግለጫቸው የአውሮፓ ሱፐር ሊግ የሚባል ውድድር ከዩኤኤፍኤ ወይም ከፊፋ ኦፊሴላዊ ማረጋገጫ እንደማይኖረው፤በሚመለከታቸው ኮንፌዴሬሽኖች እውቅና እንደማይሰጠውና በውድድሩ  የሚሳተፉ ማናቸውም ተጫዋቾች እና ክለቦች  የእግር ኳስ ሕገወጦች ይሆናሉ ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ማርጋሪቲስ ሺናስ “የአውሮፓውያን የአኗኗር ዘይቤ እግር ኳስ ለሀብታሞች እና ለኃያላን ብቻ እንዲሆን አይፈቅድም” ብለዋል፡፡


Read 872 times