Saturday, 06 March 2021 14:00

የመጣ ሳይመጣ የውሃ ቦይ ጥረግ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

  ከክርስቶስ ልደት በፊት በሶስተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ ኩንግ ሲ የተባለ አንድ ንጉስ በቻይና ይኖር ነበር፡፡ ንጉስ አሳ በጣም ይወድ የነበረ መሪ ነበር ይባላል፡፡ የአገሩ ህዝብ በሞላ አሳ ይገዛና እጅ መንሻ ያቀርብለታል፡፡
ንጉሱ ኩንግ ሲዩ ግን ስጦታውን አልቀበልም፤ ይላል፡፡
ይህንን ያየው ታናሽ ወንድሙ ወደ ንጉሱ ይመጣና፤ “ያለጥርጥር አሳ በጣም እንደምትወድአውቃለሁ፡፡ ስለምን ነው የአሳ ስጦታቸውን አልቀበልም ያልከው?” ሲል ጠየቀው፡፡
ንጉሱም፤ “ወንድሜ ሆይ  የአሳ ስጦታ የማልቀበልበት ምክንያት፤ እያንዳንዱ ስጦታ በውለታ እንድትታሰር ያደርግሃልና ነው፡፡ በውለታ ከታሰርኩኝ የሃገራችንን ህግ እስከ መጠምዘዝ ድረስ እሄዳለሁ፡፡”
“ለምን ትጠመዝዛለህ?”
“ውለታ የዋልክለት ህዝብ በፋንታው ይሄን አድርግ ብሎ ስለሚጠብቅህ ነዋ!”
“ለምን እምቢ አትልም ታዲያ?”
“አሳ የምወድደው ጭንቅላቴን ረቂቅ ስለሚያደርግልኝ ነው፡፡ ይሄንን እንዳደርግ ያደረገኝም አሳ ነው!”
“አልገባኝም”
“አሳ አትበላማ! አሳ ሳትበላ እንዴት ይግባህ?”
“ህጉ ቢጣመም ምን ቸገረህ? ስልጣኑ ያንተ?”
“ህጉን ካጣመምኩ ራሴ ተጣምሜ ከስልጣኔ እወርዳለሁ”
“ከስልጣንህ ብትወርድ ምን ቸገረህ?”
“ከስልጣኔ ከወረድኩ በኋላ ራሴን አሳ ለመመገብ አልችል ይሆናል! በተቃራኒው ካየኸው ግን፤ ከህዝብ የአሳ ስጦታ ባልቀበል፣ ከመንበሬ ባልወርድ፣ መቼም ቢሆን አሳ ገዝቼ መብላት አያቅተኝም!!”
* * *
ስጦታና እጅ መንሻ ስርዓትን እስከ መናድ እንደሚደርስ በሀገራችን አይተናል፡፡ ከፈረንሳይ ድረስ የ70,000 (ሰባ ሺ) ብር ሽቶ (ብራችን በዶላር 2.05 ብር ይመነዘር በነበረ ጊዜ) ለልደታቸው ስጦታ ይመጣላቸው የነበሩ ልዕልቶች እንደነበሩ ታዝበናል፡፡ የሀገር መሪዎች በስዊስ ባንክ አያሌ ሚሊዮን ብርና ወርቅ አስቀምጠው የነበረበት ወቅት እንደነበር አንረሳም፡፡ ይህን ዓይነቱ ነገር የዛሬ ስሙ ሙስና ነው፡፡ መታያ፣ እጅ - መንሻ፣ ስጦታ፣ የደስ ደስ፣ ቤት ማሞቂያ፣ ህንፃ ማድመቂያ፣ እጅ ማበሻ… ሁሉም የሙስና ተለዋጭ ስሞች ናቸው፡፡
“ሙሳዊ ጫና የክፉ ስራዎች ሁሉ የዓመት ከዓመት ፀደይ ነው፡፡ የስርዓቱ ብልሽት መጠንሰሻ ነው፡፡ የአገር ዕዳ ክምር - ክንብንብ ነው፡፡ ክንዳችንን ያልማል፡፡ ከሸንጎ ውስጥ የጥበብን ብልት ቆርጦ ስልጣንን ለግል ጥቅም ለማዋልና ስምና ዝናን ማትረፊያ ለማድረግ እንድናውለው ያመቻችልናል!” ይለናል በርክ የተባለው ፀሐፊ፡፡
ይህ ሁነት በዲሞክራሲ ማነቆነት፣ በልማት እንቅፋትነት፣ በሃይማኖት ግጭት መንስዔነት፣ በጦርነት ሰበብነት ትልቅ ተፅዕኖ ቢፈጠር ዞሮ ዞሮ ጦሱ ለሀገር ነው የሚተርፈው፡፡
ጀርመኖች ደግሞ ስለ ታላላቅ ጦርነቶች የሚከተለውን ይላሉ፡-
ታላቅ ጦርነት ሃገሪቱን የሶስት ዓይነት ሰራዊት ባለቤት ያደርጋታል፡-
የጦር- ጉዳተኞች ሰራዊት፣ የሐዘንተኞች ሰራዊት እና የሌቦች ሰራዊት!
ሃይማኖቶች የቅዱሳት፣የቀና መንፈስ፣የመልካም ስራ መመሪያ የሚሰጡ፣የበጎ ምግባር አቅጣጫ መሪ እንጂ የግጭት መንስኤና ሰበብ መሆን የለባቸውም፡፡ ለዚህ ነው:-
“ሃይማኖት ታረደ ደሙን ኩቲ ላሰው
እንግዲህ ሆድ ለሆድ አልተገናኘም ሰው”
እያለ የሀገራችን ሰው የሚገጥመው፡፡
ሁሌ የምንሰራው ስራና የእንቅስቃሴያችን ሂደት “በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ተገለፀ”፣ “የስራ ግምገማው እንደሚያሳየው የዕድገት አቅጣጫ ጠቋሚ ነው”፤ “በይሄን ያህል ፐርሰንት ያደግን መሆኑ ተገለፀ” ወዘተ እየተባባልን ችግሮቻችንን እንዳናይ ዐይናችንን መጨፈን ትልቅ አባዜ ነው፡፡
“ሞኝ፤የሚያደንቀው ሞኝ አያጣም”፤ እንዲሉ እርስ በርስ በመደናነቅና “አበጀህ”፣ “አበጀህ!” በመባባል ብዙ የተራመድን በመሰለን ጊዜ መስጋትና መጠንቀቅ ብልህነት ነው፡፡
ፍትህ፤ ዕውነታችን በየትኛው አቅጣጫ እንዲበራ እንደምናደርግ ራሳችንን የምንፈትሽበት ድንቅ መሳሪያ ነው፡፡
“ስለ አገርህ፣ስለ አምላክህ፣ስለ ዕውነትህ፤ ይሁን እንጂ ቅን ዓላማህ፣
ፍትሐዊነት ቅን ፀጋ ነው፣ ፈፅሞ ፍርሃት አይግባህ”
(ይላል ሼክስፒር)
ዲሞክራሲያችንን እንፈትሽ፡፡ “ዲሞክራሲን ማፍቀር እኩልነትን ማፍቀር ነው፡፡” ይለናል ሞንቴስኩ፡፡ ይህ የእኩልነት ፍቅር አለን ወይ?
“ዲሞክራሲ ምርጥና ለመተግበር እጅግ አዳጋች የፖለቲካ አደረጃጀት ነው” ይለናል ራልፍ ባርተን፡፡ ይህንንስ ተገንዝበናል?(dynamic democracy) ተንቀሳቃሽ እና አንቀሳቃሽ ዲሞክራሲ ካልሆነ ዲሞክራሲ የለም ብንል ይሻላል፡፡ ህዝባችን መሳተፍ ሲያቆም፣ፀሀይ ውስጥ ቦታ ሲያጣ -ያኔ ሁላችንም በመበስበስ (በንትበት) ጨለማ (darkness of decadence) ውስጥ በነን እናልቃለን፡፡
ሁላችንም ዲዳ ፣ሞራለ - ቢስ እና የቀለጡ ነብሶች እንሆናለን” (ሳውል ደ-አሊንስኪ)
ዲሞክራሲ ስንል እንደ ፕሉታርክ “ሂድ፡፡ በራስህ ቤት የራስህ ዓይነት ዲሞክራሲ ሞክር” ማለታችን ቢሆንም ይመረጣል፡፡
የሙስናን፣ የጎረቤትን የጦርነትን፣ የሃይማኖትን ነገር፣ የዲሞክራሲንና የዕድገትን ነገር፣ በወጉ ለማየት ችግራችንንና መፍትሄዎቻችንን በተያያዘ ጥምረት ማገናዘብ አለብን፡፡ የሃገራችንን ችግር ስንቃኝ አንዱን ካንዱ አስተሳስረን መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ የአንድ ሰሞን ግርግር ዘመቻ ብቻ ይሆናል፡፡ ተከታታይ ጥረትና ቀጣይነት አይኖረውም፡፡ አንዱን ዘመቻ ሌላው እያስረሳውና እየሻረው ስለሚሄድ ዕድገታችን ደብዛዛ ይሆናል፡፡ የተሳሰረ ጥረት የማይረሳሳ ትግል ነው ሊኖረን የሚገባው፡ ፡ በተበታተነ ሁኔታ ውስጥ እንዳንበታተን፤ አረሙን፣ እንቅፋቱን፣ ዳተኝነቱንና ግብዝነቱን ትተን፣ ለመጓዝ፤ ”የመጣ ሳይመጣ የውሃ ቦይ ጥረግ” የሚለውን ተረት ማሰብ አለብን!!


Read 13007 times