Saturday, 06 March 2021 13:55

6ኛው አገራዊ ምርጫ 2013 ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ፤ በዘንድሮ አገራዊ ምርጫ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  (ዝግጅቱ፣ ፖሊሲዎቹ፣ ተስፋና ስጋቶቹ)

        • በመንግስት ዳተኝነት በብሔራዊ መግባባት ላይ ጠንካራ ሥራ አልተሰራም
        • አሁን አገሪቱ ውስጥ ባለው ውጥረት ምርጫው ከስጋት ነፃ አይሆንም

         በለውጡ ማግስት ከተመሰረቱ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፤ ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ፓርቲው ዝግጅቱን እያደረገ ያለው  በምን መልኩ ነው? ከሌሎች አገር አቀፍ ፓርቲዎች በምን ይለያል? በየትኞቹ አካባቢዎች ይወዳደራል? ዋነኛ የምርጫ አጀንዳው ምንድን ነው? በምርጫው ተስፋዎቹና ስጋቶቹ ምንድን ናቸው? በሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎች ዙሪያ ከፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብዱልቃድር አደም ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡


              እስቲ ፓርቲያችሁ ለምርጫው የሚያደርገው ዝግጅት ምን እንደሚመስል ይንገሩኝ?
ምርጫው በ2012 ይካሄዳል በሚል ዝግጅት ማድረግ የጀመርነው ባለፈው ዓመት ነው፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ የበለጠ አጠናክረን ቀጥለናል፡፡ አዲስ መሆናችንና ልምድ አለመኖር የሚፈጥረው ጫና አለ፡፡ ነገር ግን በጣም ጥሩ በሚባል ደረጃ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ዕቅድ አውጥተን በሚገባ ስንዘጋጅ ነው የቆየነው፡፡  
በዚህ ዕቅድ እስካሁን  ምን ሰራችሁ?
አንዱ እቅዳችን የነበረው እጩዎች መመልመል ነው፡፡ በትምህርት ብቃትና በህዝብ ተቀባይነት መስፈርቶችና ህዝብን የማገልገል ፍላጎትን ከግምት ውስጥ አስገብተን፣ እጩዎችን ስንመርጥ ነው የቆየነው፡፡ ሁለተኛው በጣም የተጠና ማኒፌስቶ ማዘጋጀት ነበር፡፡ በአምስት አመት ውስጥ ቁልፍ የሚባሉትን የሃገሪቱን ችግሮች ሊፈታ የሚችል ማኒፌስቶ አዘጋጅተናል። ለአባሎቻችንና ለእጩዎቻችን ስልጠና ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሁሉም ክልል  በሚባል ደረጃ እጩዎቻችንን እያስመዘገብን ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዚህ ጉዳይ ስራ በዝቶብን ነበር የቆየነው፡፡ በቀጣይ ቀናት ደግሞ ማኒፌስቶአችንን በይፋ እናስመርቃለን፤ እናስተዋውቃለን፡፡ በተረፈ በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ፣ ጠንካራ ራስን የማስተዋወቅ ስራ ለመስራት ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡
የምትመሩበት  ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው?
ብዙ ጊዜ በኛ ሃገር የሚቀነቀኑ ርዕዮተ-ዓለሞች ለኛ ማህበራዊ ኩነቶች የሚመቹ አይደሉም፡፡ ሊበራልም በለው ሶሻል ዲሞክራሲ ብዙም የተጣጣሙ አይደሉም፤ ከሃገሪቱ ማህበራዊ ኩነት ጋር። እኛ ርዕዮተ አለም ብለን የምናስበው የማህበረሰቡን ባህል፣ አኗኗር፣ ሃይማኖትና ማህበራዊ መስተጋብር የሚቃኝ የአዕምሮ ውቅር ውጤት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እኛ የምንከተለው ሚዛናዊ ሊበራሊዝምን ነው፡፡
ሚዛናዊ ሊበራሊዝም ሲባል ምን ማለት ነው፤ ቢያብራሩት?
በመሰረቱ ሊበራሊዝም ነፃነትን የሚያቀነቅን ነው፡፡ መሰረቱ የግለሰብ መብት ነው፡፡ ነጻ ሚዲያ፣ ነፃ ማህበረሰብና ነፃነት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በኛ አረዳድ፣ ይህ የኛን ማህበረሰብ ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከኛ ባህል፣ ማህበራዊ ሁኔታ፣ ኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ደረጃ አንጻር ሚዛናዊ ሊበራሊዝምን ነው ለመጠቀም የወሰንነው፡፡ ፍፁም ሊበራሊዝም አይደለም ማለት ነው፡፡ ይሄን በዝርዝር ከፖለቲካ ፕሮግራማችን ማየትና መረዳት ይቻላል። ፕሮግራማችን ማዕቀፉ፣ ትምህርት-መር አገር አቀፍ የልማት ስትራቴጂ ነው፡፡ ይሄ ማለት የፖሊሲዎቹ ማጠንጠኛ በሙሉ የሰው ሃይል ልማት ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ፓርቲዎች ግብርናን ማዕከል ያደረገ ወይም ግብርና መር የልማት ስትራቴጂ አላቸው፡፡ የኛ ደግሞ ትምህርት መር ነው፤ ይሄ ማለት የሰው ሃይል ልማት ላይ እናተኩራለን። ይሄ ማለት የሰለጠነ ሰው መፍጠር ላይ እናተኩራለን፡፡ የሰለጠነ ሰው መፍጠር መቻል ልዩነትን መቀበልና በልዩነት ውስጥ አንድነትን ገንብቶ የሚኖር፣ እውቀትን መርሁ ያደረገ ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል፡፡ የሰለጠነ ሰው ዕውቀቱን ተጠቅሞ ራሱንም ቤተሰቡንም ሃገሩንም ከድህነት ማውጣት ይችላል፤ ዋነኛው የፖሊሲያችን ማጠንጠኛ ይሄ ነው፡፡ በዚህ መሰረት እስከ አሁን ድረስ 24 ፖሊሲዎችን እየሰራን ቆይተናል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ይሄን ስንሰራ ነበር፡፡  ሁሉም አልተጠናቀቀም፤ በተለያየ ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን ሁሉም የፖሊሲ ሰነዶች ምናልባትም ከምርጫው በፊት ተጠናቀው ለህዝብ ይፋ ይሆናሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡
የናንተን ፓርቲ ከሌላው የሚለየውና  ተመራጭ የሚያደርጋችሁ ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን 51 የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው ያሉት፡፡ ከዚያ ውስጥ 20ዎቹ  ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ  ክልላዊ ናቸው፡፡ ነእፓ፤ ከ20 ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች  አንዱ ነው፡፡ በተመሰረትን በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ብዙ አዳዲስ ነገሮች ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አስተዋውቀናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ነእፓን  ሲፈጠር ጀምሮም ሆነ ለወደፊት ከሌላው የሚለየን ሚዛናዊነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሚዛናዊነት ቀላል ይመስላል፤ ነገር  ግን ተግባር ላይ ሲውል ከባድ ነው፡፡
ሚዛናዊነታችሁ እንዴት ይገለጻል? በምንድን ነው ሚዛናዊ የምትሆኑት?
እኛ ሚዛናዊ መሆን አለብን ስንል ለምሳሌ በታሪክ ጉዳይ ፅንፍና ፅንፍ ተይዞ ነው እየተሄደ ያለው፡፡ እኛ በዚህ መሃል  አረዳዳችን የሚሆነው ለምሳሌ በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ውስጥ ችግሮች ነበሩ፤ በዚያው ልክ በጎ ስራዎች ነበሩ ብለን እናምናለን፡፡ ታሪክና ትርክት ላይ ያሉ የማይታረቁ የሚመስሉ ፅንፎችን ማስታረቅ ላይ እናተኩራለን፡፡ ይሄ በፖሊሲዎቻችንና በፕሮግራሞቻችን በግልፅ ይንፀባረቃል። ሌላው ለየት የሚያደርገን ትምህርት ላይ ማተኮራችን ነው፡፡ ይሄ ለሃገሪቱም አዲስ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ከተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች ጋርም ተነጋግረናል፡፡ ይሄ የሰው ልማት ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ ከተሳካ ለሌላውም ሞዴል ሊሆን ስለሚችል፣ በፋይናንሱም በቴክኒኩም አግዙንና አብረን እንስራ ብለናቸዋል፡፡ በእነሱም በኩል ሃሳቡ ይሁንታ አግኝቷል፡፡ ትምህርት የሰለጠነ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ዛሬ መቻቻል ጠፍቶ በየቦታው መናቆር የበዛው የእውቀት ችግር በመኖሩ  ነው፡፡ ዜጋውን ወጣቱን በመልካም አስተሳሰብና እውቀት አልቀረፅነውም፤ ስለዚህ ነእፓ በአስተሳሰብም በፖሊሲም  ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉት፡፡ በቀጣይ በሚኖሩ ክርክሮች ላይ ብዙ ነገሮች ጎልተው ይወጣሉ  ብለን አናስባለን፡፡
ፓርቲያችሁ ኢትዮጵያና ኢትየጵያዊነትን እንዴት ነው የሚበይነው?
እኛ ሃገር አቀፍ ፓርቲ ነን፡፡ ፓርቲያችን ልዩነትን ያከብራል፤ መሪ ቃላችንም አንድነት በልዩነት ውስጥ የሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ሃገር ነች፡፡ እንደ ሃገር መቀጠል አለባት፡፡ የጋራ ታሪክም አለን፡፡ በዚህ ላይ ተጨማሪ አክለን ትልቅ ሃገር መገንባት እንችላለን ብለን እናስባለን፡፡ ልዩነታችን ለኛ ውበት ነው ብለን ነው የምናምነው። ነገር ግን ኢትዮጵያን እንከን የለሽ፣ ውብ  አድርጎ የሚስል አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ጨለማ አድርጎ ለማሳየት የሚጥር አለ፡፡ እኛ መሃሉን አቻችለን መሄድ እንመርጣለን፡፡ በታሪክ ሂደት፣ ሌሎች ሃገሮችም ሲፈጠሩ የነበረበት ሁኔታ አልጋ በአልጋ ወይም በስምምነት ብቻ አይደለም። ሁሉም የተሻለ ሃገር እየገነቡ ያሉት ታሪካቸውን ለመቻቻያነት ስለተጠቀሙበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር ብዙ መልክ ያላት ናት፤ ነገር ግን በአንድነት የፀናች መሆን የምትችል ሃገር አድርገን ነው የምናስባት፡፡
ለምርጫው ምን ያህል እጩዎች ታቀርባላችሁ? የበለጠ በጥንካሬ የምትወዳደሩትስ በየትኞቹ አካባቢዎች ነው?
እኛ በትንሹ እጩ እናቀርባለን ብለን አሁንም እየሰራንበት ያለነው በአማካይ 250 ነው፡፡ በዚህ በኩል አሁንም ጠንካራ ውጤት አግኝተንበታል፡፡ ገና ደግሞ እየሰራንባቸው ያሉም አሉ፡፡ ለዚህ ነው ይሄን ያህል ነው ብዬ አሁን ቁርጥ አድርጌ መናገር የምቸገረው፡፡ እኛ ከፍ ሲል 3 መቶ፣ ዝቅ ካለ 2 መቶ እጩዎች  እናቀርባለን፤ አማካይ እቅዳችን 250 ነው፡፡ ለክልል ም/ቤት በተመሳሳይ እጩዎች እየመለመልን ነው፡፡ በቀጣይ ሳምንት የደረስንበትን ሁኔታ መግለፅ ይቻለናል፡፡ አሁን ገና እየሰራንበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የምርጫ አካባቢን በተመለከተ በሁሉም ክልሎች በተለያየ መጠን እንሳተፋለን፡፡ በትግራይ አሁን ምርጫ ስለማይካሄድ አንሳተፍም። ጋምቤላ ደግሞ እጩ የለንም፤ ነገር ግን እዚያ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች  ጋር በጋራ ለመስራት ወይም የእነሱን እንቅስቃሴ በአጋርነት ለመደገፍ እየተነጋገርን ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በሁሉም ክልል ላይ ቁጥሩ ከፍ ዝቅ ቢልም ይኖረናል፡፡
በምርጫው ጉዳዬ ብላችሁ የምትሟገቱለት ዋነኛ አጀንዳ ምንድን ነው?
በጣም ትኩረት የምንሰጠው እስካሁንም ስንጮህለት የቆየነው፣ ነገር ግን ያልተሳካልን የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ነው፡፡ በመንግስት ዳተኝነት በብሔራዊ መግባባት ላይ ጠንካራ ስራ አልተሰራም፡፡ እኛ በጣም በትኩረት የምንሰራው በብሔራዊ መግባባት ላይ ነው፡፡ ይሄ ነው የኛ የመጀመሪያ ትልቅ አጀንዳ፡፡ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ የሚሻለው ምንድን ነው በሚለው ላይ ነው መነጋገር ያለብን፡፡
ለምርጫው የፋይናንስ አቅማችሁ ምን ይመስላል? ገቢስ ከየት ነው የምታገኙት? የራሳችሁን ጽ/ቤት የመገንባት እቅድ እንዳላችሁም ገልጻችኋል --
ይህ የህንፃ ግንባታ ጉዳይ በጣም ትንሹ ጉዳያችን ነው፤ እንደ ትልቅ  ጉዳይ መነጋገሪያ መሆን የለበትም፡፡ ሃገር አስተዳድራለሁ ብሎ የሚያስብ ፓርቲ ህንፃ የመገንባት ሃሳቡ ጉዳይ ሲሆን የፖለቲካችንን ደካማነት ነው የሚያሳየው፤ ቢሮ ያስፈልገናል ለእዛ ህንፃ ያስፈልገናል እንገነባለን፡፡ የእኛ ፓርቲ የገቢ ምንጮች ሶስት ናቸው፡፡ አንደኛና ዋነኛው የአባላቱ መዋጮ ነው፡፡ ሁለተኛው ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ተቋማት ናቸው። ተቋማት በስፖንሰር መልክ ይደግፉናል፡፡ ሌላው በጣም ትንሽ ቢሆንም ለምርጫው ከምርጫ ቦርድ የምናገኘው ፋይናንስ ይኖራል፡፡ እስከ አሁን ምርጫ ቦርድ ምን ያህል ድጋፍ እንደሚያደርግ አልነገረንም።  ከአባላትና ደጋፊዎች ሌላ ከውጭ ሃገር ተቋማት ገንዘብ ማምጣት ወንጀል ነው፡፡ ይሄ ይታወቃል፡፡ እኛም ከውጪ የሚረዳን ወይም የምንቀበለው ድጋፍ የለም፡፡
በዚህ ምርጫ ያላችሁ ተስፋና ስጋቶች ምንድን ናቸው?  
ስጋት ሁልጊዜ ይኖራል፡፡ የእኛ ስጋቶች ተጨባጭ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ውጥረት ምርጫው ከስጋት ነፃ አይሆንም፡፡ አመራሮቻችን ታስረዋል የሚሉ ፓርቲዎች አሉ፡፡
ይሄ ሁኔታ ምርጫውን ቅቡልነት እያሳጣው ይሄዳል፡፡ ለዚያ ነው ብሔራዊ መግባባቱ መቅደም የነበረበት። ከዚህ በኋላ ያለው ስራ እነዚህን ስጋቶች መቀነስ መቻል ነው፡፡ በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ውስጥ ነእፓ በም/ሊቀ መንበርነት እየተሳተፈ ነው፡፡ በዚያ በኩል ውጥረቶች እንዲቀነሱ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ተስፋችንም ከዚሁ የመነጨ ይሆናል፡፡


Read 11007 times