Saturday, 06 March 2021 13:17

በ6 ወር ውስጥ በትራፊክ አደጋ 1ሺህ 849 ሰዎች ሞተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  ባለፉት 6 ወራት በመላ ሃገሪቱ 20 ሺህ 672 የትራፊክ አደጋዎች አጋጥመው የ1ሺ 849 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ ከ5 ሺህ በላይ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የፌደራል ፖሊስ በድረ ገጹ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከትግራይ በስተቀር በሃገሪቱ ከሚገኙ ሁሉም ክልሎች የተሰባሰቡ መረጃዎችን ማጠናቀሩን የጠቆመው   ፌደራል ፖሊስ፤ አብዛኞቹ አደጋዎች በአሽከርካሪዎች ጥፋት የተከሰቱ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ ካጋጠሙት የአካል ጉዳቶች 2ሺ 646 ያህል አካልን ማጣት ጨምሮ የተለያዩ ከባድ ጉዳቶች መድረሳቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ 2ሺ 565 ያህሉ ቀላል የሚባሉ ጉዳቶች ናቸው ብሏል፡፡ በንብረት ረገድ 495 ሚሊዮን 240 ሺ 473  ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል ተብሏል፡፡
ከሁሉም አካባቢዎች ይልቅ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አደጋ መድረሱን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ 15 ሺ 849 አደጋዎች ሲመዘገቡ፣ በዚህም 192 ሰዎች መሞታቸውን፣ 846 ያህሉ በፅኑ መቁሰላቸውንና 512 የሚሆኑት ደግሞ  ቀላል ጉዳት እንዳጋጠማቸው ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
ለአደጋዎቹ በዋነኛ መንስኤነት ከተጠቀሱት የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነትና የብቃት ማነስ በተጨማሪ የተሽከርካሪዎች ቴክኒካዊ ብቃት ደካማ መሆን፣ የመንገድ ላይ ምልክቶች በስርአቱ አለመቀመጥና የእግረኛ ተገቢውን ጥንቃቄ ያለማድረግ ተጠቁመዋል፡፡  

Read 10813 times