Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 August 2012 12:08

የቡሄ ጭፈራ ድሮና..... ዘንድሮ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

የክረምቱን መውጣት የመስከረምን መባት የሚያበስሩ ልጆች ከልጥና ከቃጫ እየተገመደ የተሰራውን ጅራፋቸውን እያጮሁ ከመስክ መስክ እየዘለሉና እየቦረቁ የሚጫወቱበት ደግ ዘመን አክትሞ ቻይና - ሠራሹን ርችት በየአውራ ጐዳናውና በየመኪናው ላይ እየወረወሩ በማፈንዳት የሰውን ቀልብ የሚገፉ ልጆች የተፈጠሩበት ክፉ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ባህል አክባሪ ታዳጊዎች ልጣጩ ተልጦ በቡና ዘነዘና እየተቀጠቀጠ በተጠፈጠፈ ቆርኪ የሰሩትን ክሽክሽ እያንከሻከሹና ተድበልብሎ በወፈረው የቡሄ ዱላቸው የአባወራውን ደጃፍ እየቀጠቀጡ

“መጣና በዓመቱ ኧረ እንደምንሰነበቱ፣

መጣና መጣና ግቡ በሉና፡፡”

ሲሉ መስማት እንደናፈቀን ቀርቷል፡፡

“እዚህ ቤቶች እንደምን ናችሁ፣

በዓመት አንድ ቀን መጣንላችሁ፡፡

በዓመት አንድ ቀን የመጣ እንግዳ፣

እራቱ ዳቦ ቁርሱ ፍሪዳ፡፡”

የሚለውና የቡሄ ጨፋሪ ልጆችን መምጣት ያበስር የነበረው ዜማ ዛሬ ዛሬ ጨርሶውኑ እየተረሳ መጥቷል፡፡ የቀድሞ ቡሄ ጨፋሪ ልጆች የአባወራውንና የእማወራዋን ስም እያነሱ ያሞግሱበት የነበረው ዜማ ዛሬ ተረት ተረት ሆኖ ቀርቷል፡፡

“የእኔማ ጌታ የሰጠኝ ሙክት፣

ባለዶቃ ነው ባለምልክት፣

መስከረም ጠባ እሱን ሣነክት፡፡

የእኔማ እመቤት የፈተለችው፣

የሸረሪት ድር አስመሰለችው፡፡

ሸማኔ ጠፍቶ ማርያም ሰራችው፡፡”

እየተባለ የአባወራው ቸርነትና ለጋስነት፣ የእማወራዋ ባለሙያነት ይሞገስበት የነበረው የቡሄ ግጥም እንኳንስ በከተማ በገጠሩም እየተረሣ መጥቷል፡፡ ባህሉን ለውጠው፣ ግጥሞቹን ቀይረው፣ ትውፊቱን ቀልብሰው አራምባና ቆቦ የሆኑ ግጥሞቻቸውን ለዛ ባጣ ዜማ አጅበው ከሚጮኹት ዘመነኛዎቹ የቡሄ ልጆች አፍ የሚንቆረቆሩት የቡሄ ግጥሞች እጅግ አሣፋሪ ናቸው “መጣና በዓመቱ ኧረ እንደምን ሰነበቱ” የሚለው ጥንታዊ የቡሄ “ጭፈራ መነሻ ስንኝ ተሽሮ፣

የወንዜው ነብር፣

ሊሰጠኝ ነው ብር ሳይመነዘር፣

ያውም በዶላር፡፡

የወንዜው ሳቢሣ፣

ሊሰጠኝ ነው አምሳ፡፡”

በሚል ዘመን አመጣሽ ስንኝ ተተክቶና ቅጥ - አንባሩ ጠፍቶ ታዝበናል፡፡ የቀድሞዎቹ ቡሄ ጨፋሪዎች ከትውልድ መንደራቸውና አካባቢያቸው ሳይርቁ በርከትከት ብለውና እንደ የእድሜያቸው ተቧድነው የበዓሉን ማብሰሪያ ዜማ ሲያዜሙ መስማቱ ምንኛ ደስ ያሰኝ ነበር፡፡

“እዛ ማዶ ጭስ ይጨሳል፣

አጋፋሪ ይደግሣል፡፡

ያቺን ድግስ ውጬ ውጬ፣

በድንክ አልጋ ተገልብጬ፡፡

ያቺ ድንክ አልጋ አመለኛ፣

ያለ አንድ ሰው አታስተኛ፡፡

ሆይሽ ሆዬ ጉዴ፣

ጨዋታ ነው ልማዴ፡፡”

አይነት ቀደምት የቡሄ ጭፈራዎች ዛሬ ቅርፃቸውም ይዘታቸውም መልዕክታቸውም ተለውጧል፡፡

“እዛ ማዶ አንድ በረኪና፣

እዚህ ማዶ አንድ በረኪና፣

የኔማ አባብዬ ባለመኪና፡፡

እዛ ማዶ አሮጌ ትሪ፣

እዚህ ማዶ አሮጌ ትሪ፣

የእኔማ እማምዬ ማሪያ ኬሪ፡፡

ሆያ ሆዬ ጉዴ፣

ብሯን ብሯን ይላል ሆዴ፡፡”

በሚል ዘመን አመጣሽ ስንኝ ተተክቷል፡፡ የ”ቡሄ ጨፋሪ” ቡድን አባላት ቁጥር መብዛቱ በጭፈራው ማጠናቀቂያ ላይ በሚደረገው የትርፍ ክፍፍል ወቅት ጠቀም ያለ ድርሻ እንዳይኖራቸው እንደሚያደርጋቸው የገባቸው የዘመኑ ልጆች፤ ለሁለትና ለሶስት እየተቧደኑ በቡሔ ጭፈራ ሰበብ፤ በማይታወቁበት ሰፈርና መንደር ሁሉ ከበዓሉ መድረስ አንድ ሣምንት ቀደም ብለው ጀምረው በየቤቱና በየመንገዱ እየዞሩ “ሲለምኑ”  ማየቱ የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከዘመኑ ጋር እየዘመኑ የሚሄዱት የዘመኑ ልጆች ከባህሉና ከወጉ ጋር የማይሄዱና ፈጽሞ ኢትዮጵያዊ ለዛ የሌላቸውን ግጥሞች እየገጣጠሙ በመጨፈር ሳንቲም መሰብሰቡን እንደ ቢዝነስ ቆጥረውታል፡፡ የስንዴ ዋጋ እንዲህ በናረበት ዘመን በድሮው ባህልና ልማድ መሰረት ሙልሙል ዳቦ ጋግሮ ለቡሔ ጨፋሪዎች ሁሉ የሚያድል የዚህ ዘመን ሰው ይኖራል የሚል ግምት ባይኖረኝም፤ ቡሄ ጨፋሪ የዘመኑ ህፃናትም እንደቀድሞዎቹ ሙልሙል ይቀበላሉ ብሎ ማሰቡ ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ ድሮ ድሮ ከስጦታ በኋላ የነበረውን፤

“አውደ አመት አመት-ድገምና፣

የአባብዬን ቤት-ድገምና፣

የእማምዬን ቤት-ድገምና፣

ወርቅ ይፍስስበት፡፡

ይሉ ምርቃት ለመስማት በርካታ ቡሔዎች ላይ ብንመኝም አልቀናንም፡፡ ይልቁንም አይኖቻቸውን ሰጪው እጅ ላይ ያለው ገንዘብ ላይ ሰክተው የግጥሙ ቅደም-ተከተል ጠፍቷቸው ግራ የሚጋቡ የዘመኑን ልጆች ማየትና የተሰጣቸውን ገንዘብ ተቀብለው በብርሃን ፍጥነት ከአካባቢው ሲሰወሩ ማየት ለዚህ ዘመን ሰው ብርቅ አይደለም፡፡ ከቡሔ ጭፈራ በኋላ ያገኙትን የሙልሙል እና የገንዘብ ስጦታ በሰላምና በፍቅር ተከፋፍለው፤ ለከርሞ እንዲያደርሳቸው ቸሩን ተመኛኝተውና ለምሽቱ የችቦ ማብሪያ ፕሮግራም ቀጠሮ ይዘው፤ የሚሰነባበቱትን የድሮ ቡሔ ጨፋሪዎች እያሰብን በሚከፋፈሏት ገንዘብ መነሻነት ፀብ ፈጥረው ተፈነካክተውና ተጣልተው የሚለያዩትን የዘመኑን “ቡሔ ጨፋሪ” ልጆች ማየት ልማድ አድርገነዋል፡፡ የደጉ ዘመን ቡሔ ጨፋሪ ልጆች እንደ ባህሉና ወጉ እየጨፈሩ ባህሉን ጠብቀው የሰጡንን የቡሔ በዓል በእንዲህ አይነት መልኩ ከባህልና ከሥርዓቱ አውጥተን ስናበላሸው ዝም ልንባል አይገባንምና ለዛ ወደነበረውና ወደ ቀደመው የቡሔ ጭፈራችን እንመለስ፡፡ ቀጣዩ ትውልድም ቀደምት የባህል አከባበር ሥርዓትና ወጋችንን ከነእውነተኛ ለዛው ሊያገኝ ይገባዋልና፡፡

 

 

 

Read 57501 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 12:15